ለሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት የተሳተፉ እና በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ የኤርትራ ጦር አባላት እየወጡ መሆኑን አዲስ ዘይቤ ከተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎች አረጋግጣለች።
ከአዲስ ዘይቤ ጋር በስልክ ቆይታ ያደረጉ የሽሬ ከተማ ነዋሪዎች እቃዎችን ሲጭኑ እና በመኪና ሲጓዙ ማየታቸውን ገልፀዋል።የከተማው ነዋሪ የሆነች ወጣት “ከትላንት ወደ ምሽት አካባቢ ጀምሮ የኤርትራ ጦር አባላት ከሽሬ ከተማ ወደ ሽራሮ መስመር በአውቶብስ ሲጓዙ” መመልከቷን ነግራናለች።
ሌላኛው የሽሬ ከተማ ነዋሪ እንደገለፀው ደግሞ “በትላንትናው እለት የኤርትራ ጦር አባላት ምግብና ሌሎች እቃዎችን ሲጭኑ” መመልከቱንታቸውን የገለፁልን ነዋሪዎችም አሉ።
ይሁን እንጂ ነዋሪዎቹ የኤርትራ ጦር አባላት ከትግራይ ክልል ለቀው ሊወጡ ወይም ወደ ሌላ አካባቢ እየተጓዙ መሆኑን መለየት እንዳልቻሉ ገልፀውልናል። ለነዋሪዎቹ የተንቀሳቀሱት ታጣቂዎች የኤርትራ ጦር አባላት መሆናቸውን በምን አወቃችሁ ለሚለው ጥያቄ “የለበሱት የትጥቅ ልብስ እና የሚናገሩት ቋንቋ ይታወቃሉ” ብለዋል።
ሽራሮ ከተማ ከኢትዮጵያ-ኤርትራ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ አካባቢ ቢሆንም የሽሬ ነዋሪዎች “የጦር አባላቱ እየወጡ ይሁን ቦታ እየቀየሩ” ማወቅ አልቻልንም ብለዋል።
በተመሳሳይ የአድዋ ከተማ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፀው ዛሬ ከሰዓት በኋላ በነበረው ጊዜ “የኤርትራ ጦር አባላት ንብረቶቻቸውን እየጫኑ እና ለመውጣት እየተዘጋጁ እንደሚገኙ” ተመልክቷል። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ “የኤርትራ ኃይሎች ከአድዋ ከተማ በኤፍ ኤስ አር [የጭነት ተሽከርካሪ] ተጭነው እየወጡ ነው፤ ግን አሁንም የቀሩ አሉ” ሲል የከተማው ነዋሪ ገልጿል።
ሌላ ያነጋገርነው የአድዋ ከተማ ነዋሪ እንደገለፀው ደግሞ “በከተማው ውስጥ የኤርትራ ጦር አባላትን ዛሬ እንዳልተመለከታቸው” ገልፆ “በገጠር የአድዋ አካባቢዎች ግን የኤርትራ ጦር እንደሚገኙ” እየተነገረ ነው ሲል ገልፆልናል።
ሮይተርስን ጨምሮ የተለያዩ የመረጃ ምንጮች የኤርትራ ጦር አባላት ከሽሬ እና አክሱም ከተሞች እየወጡ መሆኑን የአይን እማኞችን ዋቢ አድርገው ዘግበዋል። አዲስ ዘይቤ የአክሱም ነዋሪዎችን ለማግኘት ያደረግችው ጥረት አልተሳካም።
የፌደራል መንግስት እና የህወሓት ኃይሎች በመጀመሪያ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተፈራረሙት የሰላም ስምምነት እና በመቀጠልም በኬንያ ናይሮቢ ሁለት ጊዜ በተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ማስፈፀሚያ ሰነዶች መሰረት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ውጪ በትግራይ ክልል የሚገኙ ኃይሎችን ከክልሉ ለማስወጣት መስማማታቸው ይታወሳል።
በትላንትናው እለት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በትግራይ ክልል የሚገኙ በኢፌዲሪ መንግሥት የሚተዳደሩ አየር ማረፊያዎች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቴሌኮም አገልግሎት፣ የባንክ እና ሌሎች ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ የፌዴራል ተቋማት አስተማማኝ ጥበቃ እንደሚያደርግ አስታውቆ ወደ መቀሌ ከተማ መግባቱ ተገልጿል።
በተመሳሳይ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል የአየር በረራ አገልግሎት ወደ መቀሌ እና ሽሬ ከተሞች የተጀመረ ሲሆን በተጨማሪም የቴሌኮም እና የኔትዎርክ አገልግሎት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ ነዳጅ ወደ ክልሉ የሚደርስበት መንገድ እንዲሁም የህክምናና ሌሎችም መሰረታዊ አገልግሎቶች እየተጀመሩ ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅትም የሰላም ስምምነቱ የትግበራ አፈፃፀምን የሚከታተለው እና የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት ኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ እና ሌሎች አባላትም የሚገኙበት ኮሚቴ በመቀሌ ከተማ ይገኛል።