የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 13 ብሔረሰቦችን የሚወክል ምክር ቤት ለማቋቋም የመስራች ጉባዔ ሊያካሄድ እንደሆነ ተገለፀ። በኢትዮጵያ 11ኛ ክልል በመሆን ከአመት በፊት የተመሰረተው ክልሉ ነገ ታህሳስ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. የብሔረሰቦች ምክርቤት የመስራች ጉባዔዉን በቴፒ ከተማ ሊያካሄድ መሆኑ ተሰምቷል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ በተለይ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት "ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው መስራች ጉባዔ የብሔረሰቦች ምክርቤት ስልጣንና ተግባር ለመዘርዘር በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 9/2015 በክልሉ ምክርቤት የፀደቀ በመሆኑ እያንዳንዱ ብሔር 5 ተወካዮች ይኖሩታል” ብለዋል።
በምክር ቤት ዉክልና የሚያገኙት በክልሉ ካሉ ብሔረሰቦች ዉስጥ ነባር ናቸዉ የተባሉ 13 ብሔሮች ሲሆኑ እነርሱም በካፋ ዞን የሚገኙ ብሔሮች 20፣ በዳዉሮ ዞን 5፣ በቤንች ሸኮ 8 ፣ ኮንታ ዞን 5 ፣ በሸካ ዞን 12 እንዲሁም በምዕራብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ብሔሮች 20 ተወካዮች ሲኖሩት በአጠቃላይ 70 የምክር ቤት አባላት እንደሚኖሩት ተገልጿል።
በክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት መቋቋሙ ግጭቶች እና አለመግባባቶችን አንድነታቸዉን በሚያጠናክር መልኩ በዉይይት ለመፍታት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።
እንደ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ ገለፃ "የሚቋቋመው የብሔረሰቦች ምክር ቤት የክልሉ ህገመንግስት መተርጎም፣ አጣሪ ጉባኤ ማደራጀት እንዲሁም በክልሉ ዉስጥ በሚገኙ አስተዳደር እርከኖች መካከል የሚነሱ ችግሮችን መፍትሔ ማፈላለግ እንዲሁም የህዝቦችን ባህልና ታሪክ የማጠናከር ስልጣኖች ተሰጥቶታል" ብለዋል።
የብሔረሰቦች ምክር ቤት የሚመረጡበት መንገድም፣ የተወካዮች ቁጥር የሚወሰንበት እንዲሁም የስራ ተግባራቸዉ ከመደበኛው ከክልሉ ምክር ቤት የተለየ መሆኑን ማወቅ ተችሏል።
የብሔረሰቦች ምክር ቤት ተመራጭ የሚሆኑት በዞኑ ምክር ቤት አባል የሆኑና በበቂ ሁኔታ ያልተወከሉ፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባል የሆነ የየብሔረሰብ ተወካዮች የሚወከሉበት ነዉ ሲሉ የክልሉ መንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ ገልፀዋል።
ማክሰኞ ታህሳስ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በቴፒ የሚካሄደው የብሔረሰቦች ምክር ቤት መስራች ጉባዔ ላይ የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤና ምክትል አፈ ጉባኤ ሹመት የሚያፀድቅ ሲሆን መቀመጫዉ በቴፒ ከተማ ይሆናል ተብሏል።