ታህሣሥ 26 ፣ 2015

2 ቢልየን ብር ገቢ የታቀደበት እና ለአካል ጉዳተኛ ጎብኚዎች ፈታኝ የሆነው የጎንደር ሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ

City: Gonderማህበራዊ ጉዳዮችንግድ

“በሃገራችን ኢትዮጵያ የቱሪዝም ሃብቶችን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ባለመደረጋቸው ከአካል ጉዳተኞች መገኘት ያለበትን ገቢ እንዲያገኝ የሚያስችል ደረጃ ላይ አልተደረሰም”

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

2 ቢልየን ብር ገቢ የታቀደበት እና ለአካል ጉዳተኛ ጎብኚዎች ፈታኝ የሆነው የጎንደር ሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ
Camera Icon

ፎቶ፡ ጌታሁን አስናቀ

በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ዜጎችን ታሳቢ ያደረገ የህዝብ አገልግሎት ማግኘት በትኩረት እንዳልተሰራበት የሚያመላክቱ በርካታ ማሳያዎች አሉ። ከውጭ ሀገር ባህር እና ውቅያኖስ ተሻግረው የኢትዮጵያን መዳረሻዎች ለመጎብኘት የሚመጡ አካል ጉዳተኛ ጎብኚዎችስ? 

ለጉብኝት የሚያግዟቸው መረጃዎችን በሚያስፈልጋቸው ዘዴ የሚያስጎበኛቸው ሰው ያገኛሉ? 

የሚያርፉባቸው ሆቴሎች እና እንግዳ ማረፊያዎችስ ምቹ አገልግሎት ይሰጧቸዋል? የምግብ እና መጠጥ አማራጮችስ በብሬል ይቀርባሉ? የሚሉትንና ሌሎችም ጥያቄዎችን ማገናዘብ ያስፈልጋል። 

አዲስ ዘይቤ በርካታ የውጭ ሀገራት እና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን የሚስቡ መዳረሻዎች ያሏትን እና በቅርቡ የጥምቀት በዓልን በድምቀት የምታስተናግደው ጎንደር ከተማን ቃኝታለች። በቅርቡም ከጥምቀት በዓል 2 ቢልየን ብር ለመሰብሰብ የታቀደባት ጎንደር ከተማ ከጎብኚዎች መዳረሻ አንፃር ከላይ ያነሳናቸው ጥያቄዎች በስፋት አልተመለሱም። መረጃዎችን ለአይነ ስውራን እና መስማት ለተሳናቸው ሰዎች በአግባቡ አይቀርቡም። እንደአጠቃላይ በጎብኚዎች መዳረሻዎች እንዲሁም በሆቴል ዘርፉ ውስጥ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ያልሆኑ አገልግሎቶች ይስተዋላሉ። 

አካል ጉዳተኞች ሃገራቸውን እንዲያውቁ ለማድረግ የመዳረሻ ቦታዎችን ምቹ ከማድረግ በተጨማሪ ስለመዳረሻዎቹ መረጃ ሊያገኙ የሚችሉበት እድል ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ ለአካል ጉዳተኞች የወጣው አዋጅ ይደነግጋል ሲሉ የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ፍሬሰላም ዘገየ ገልፀዋል።

“በሃገራችን ኢትዮጵያ የቱሪዝም ሃብቶችን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ባለመደረጋቸው ከአካል ጉዳተኞች መገኘት ያለበትን ገቢ እንዲያገኝ የሚያስችል ደረጃ ላይ አልተደረሰም” ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ይገልፃሉ።

ህዝብ አገልግሎት የሚያገኝባቸው ተቋማት ሲገነቡ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሆን የህግም ሆነ የሞራል ግዴታ ቢኖርባቸውም በተለይ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ የእንግዳ ማረፊያ ቦታዎች፣ የATM አገልግሎቶች፣ መፀዳጃ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች እንዲሁም ሌሎች ተቋማቶች አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ ሲያደረጉ አይታዩም። 

የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ እንኳን አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ የሚያደርጉ ሆቴሎች 47 ብቻ እንደሆኑ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ህብረት መረጃ ያሳያል። በማንኛውም የህዝብ መገልገያ ህንፃ ውስጥ በተሽከርካሪ ወንበር (ዊል ቼር) ለመንቀሳቀስ የሚገደዱ ሰዎችን እንዲሁም በድጋፍ የሚራመዱና ደረጃ ለመውጣት የሚቸገሩ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎችን ታሳቢ አድርጎ የሚመች መዳረሻ መዘጋጀት እንዳለበት የኢትዮጵያ የህንፃ አዋጅም ይደነግጋል።

እንደኢትዮጵያ በርካታ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ የቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ ቦታዎች ባሏት ሀገር ውስጥ ታዲያ፤ እነዚህን የቱሪስት መዳረሻዎች በየአካባቢው እየተዟዟሩ ለመጎብኘት እንዲችሉ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የማይደረጉበት ምክንያት መኖር የለበትም። አንድ መስማት የተሳነው የውጭ ጎብኚ እንግዳ በኢትዮጵያ ውስጥ ጉብኝት በሚያደርግበት ወቅት በምልክት ቋንቋ በራሱ አስጎብኚ ገለፃ የሚደረግበት እድል እንደሌለ ማወቅ ተችሏል።

አዲስ ዘይቤ በጎንደር ከተማ እና አካባቢዋ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ናቸው ወይ ስትል የጎንደር ከተማ የግል አስጎብኚዎች ማህበር ጊዚያዊ ሊቀ መንበር አቶ ፈንታሁን ያለውን ጠይቃለች። አቶ ፈንታሁን ያለው ከተማዋ ያላት የቱሪዝም ሀብት በርካታ ከመሆናቸውም ባለፈ “በተሽከርካሪ ወንበር (በዊል ቼር) ለመንቀሳቀስ የሚገደዱና በድጋፍ የሚራመዱ ሰዎችን ታሳቢ ያደረጉ መዳረሻዎች ቢኖሩም መስማት የተሳናቸው አካል ጉዳተኛ ጎብኚዎች በምልክት ቋንቋ ባለሙያ በሆነ አስጎብኚ ገለፃ የሚደረግበት እድል እስካሁን የለም” ብሏል። 

የጎንደር ከተማ የግል አስጎብኚዎች ማህበር ተወካዩ እንደሚገልፁት ሁሉንም የጎብኚ መዳረሻዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ለማድረግ እንዲሁም እነሱን ታሳቢ ያደረገ አስጎብኚና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲኖሩ በየጊዜው ጥረት ይደረጋል። ውጤቱ ግን በሚጠበቀው ደረጃ አለመሆን ግን የአዲስ ዘይቤ ትዝብት ነው። 

በኢትዮጵያ በርካታ ሆቴሎች፣ ሎጆች እና ሬስቶራንቶች ያሉ ሲሆን በርካቶቹ ከጎብኚዎች መዳረሻ ጋር የተሳሰሩም ናቸው። የአገልግሎት ጥራታቸው የተሻለ እንደሆነ የሚገልፁ ግዙፍ ሆቴሎች እንኳን በተሽከርካሪ ወንበር (ዊል ቼር) ለሚንቀሳቀሱ አካል ጉዳተኞች የተሻሉ ቢሆኑም ለአይነ ስውራን እና ለሌሎች አካል ጉዳተኞች አስቸጋሪ ናቸው።

የጥምቀት በዓልን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች መዳረሻ የምትሆነው ጎንደር ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች ለአካል ጉዳተኞች ምን ያህል የተሟላ አገልግሎት አላቸው የሚለውንም አዲስ ዘይቤ ጠይቃለች። በጎንደር ከተማ ከ10 የሚበልጡ ባለ 5 ኮከብ ሆቴሎች፣ ከ20 በላይ ባለ አራትና ሶስት ኮከብ ሆቴሎች እንዲሁም በርካታ እንግዳ ማረፊያዎች፣ ሎጆች፣ ሬስቶራንቶችና ባህላዊ ምግብ ቤቶች የሚገኙ ሲሆን ጎሃ ሆቴል፣ ዞብል ሪዞርትና ሆቴል እንዲሁም ሃይሌ ሪዞርትና ሆቴል ይገኙበታል። 

የዞብል ሪዞርትና ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ሮቤል ታየ ሆቴላቸው አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርጎ እንድተገነባ ይናገራሉ። “በተሽከርካሪ ወንበር (ዊል ቼር) ለሚንቀሳቀሱ አመች የሆነ እና ለተሽከርካሪ ወንበራቸው የራሱ የሆነ የማቆሚያ ስፍራ የተዘጋጀለት፣ ለአካል ጉዳተኞች ብቻ ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መፀዳጃ ቤትንም ያሟላ ነው” ሲሉም ስራ አስኪያጁ ያስረዳሉ። ከዚህ ቀደም በብሬል ለአይነ ስውራን  የተዘጋጀ የምግብና መጠጥ አማራጭና ዋጋ ያለበት ሜኑ ነበረን የሚሉት አቶ ሮቤል ታየ “ነገር ግን በየጊዜው የአገልግሎቶች የዋጋ ዝርዝር ስለሚቀያየር እና ተጠቀሚ ስለሌለው በብሬል መረጃ ማዘጋጀቱን ትተነዋል” ብለዋል። 

የጎሃ ሆቴል ስራ አስካሄጅ አቶ አማረ አጥናፉ በበኩላቸው “አንድ ህንፃ ወይም ሆቴል ሲገነባ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ተደርጎ በመሆኑ የተሟላ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል” ሲሉ ስለጎሃ ሆቴል ይገልፃሉ። ነገር ግን በብሬል የተዘጋጀ ሜኑ እንደሌላቸውም ተናግረዋል። የሃይሌ ሪዞርት ስራ አስኪያጅ አቶ ፍሬስብሃት መዝገቡም ለአካል ጉዳተኞች በብሬል የተዘጋጀ መረጃን ከማቅረብ አኳያ እስካሁን የተሰራ ስራ እንደሌለ ገልፀው “አዲስ ዘይቤ በጣም ጥሩ ጥቆማ ነው የሰጠችን ለወደፊቱ ለማዘጋጀት ጥረት እናደርጋለን” ብለዋል። አቶ ፍሬስብሃት ጨምረውም ከዚህ ውጭ ሀይሌ ሪዞርት መፀዳጃ ቤትንና ደረጃ መውጣት የማይችሉትን ጨምሮ ሁሉንም አካል ጉዳተኞች እንዲያሳትፍ ሆኖ መገንባቱን ገልፀዋል። 

የህንፃ ግንባታ አዋጅ ቁጥር 624/2001 አንቀፅ 36 “የመፀዳጃ ቤት ሊሠራበት በሚገባ በማናቸውም ህንፃ ውስጥ የአካል ጉዳት ላለባቸው ሰዎች የሚመቹና ሊደርሱባቸው የሚችሉ በቂ መጠን ያላቸው መፀዳጃ ቤቶች መኖር አለባቸው” በማለት ያስቀምጣል።

ዘመናዊ የባንክ ሲስተምን ለመጠቀም እና ከእጅ ንክኪ ለመላቀቅ ሁሉም ባንኮች የኤቲኤም (ATM) አገልግሎቶችን ለተጠቃሚ ክፍት ያደረጉ ቢሆንም አሰራራቸው በቁመት ልክ ታስቦ መሰራታቸው በተሽከርካሪ ወንበር ለሚንቀሳቀሱ አካል ጉዳተኞች አመቺ ካለመሆን ባለፈ ሁሉንም አካል ጉዳተኞች ታሳቢ ያደረጉ የኤቲኤም አገልግሎቶችን ማቅረብ ብዙ የሚጎድለው ነገር ነው።

ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌድሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ፍሬሰላም ዘገየ “ለአካል ጉዳተኞች ምቹና አካታች የሆኑ ተቋማቶች የሉም። አብዛኛውቹ ህንፃዎች ሲሰሩ የህንፃ አዋጁን ተግብረናል ለማለት ምልክት ያስቀምጣሉ እንጂ ተደራሽ አይደሉም” ብለዋል። 

አሁን ባነሳነው የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍም “ሆቴሎች በተሽከርካሪ ወንበር ለሚንቀሳቀሱ ሰዎች ራንክ (መወጣጫ) ይሰራሉ ነገር ግን አሰራሩ በጣም ቁልቁለትና አቀበት ከመሆኑም በላይ በጣም ለስላሳ በመሆኑ ወደታች አሽከርክሮ የሚደፋ ነው ወይም ወደላይ ለመሄድ ያለ ደጋፊ የማይወጡባቸው በመሆናቸው ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አይደሉም” ሲሉ ነግረውናል። 

መፀዳጃ ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች ሲሰሩ መደጋፊያን ጨምሮ ተሽከርካሪ ወንበሩ 360 ዲግሪ መዞር እንዲያስችለው ሆኖ መገንባት አለበት የሚሉት ፕሬዘዳንቱ መፀዳጃ ቤት ተጠቅሞ ሲጨርስ በተሽከርካሪ ወንበር (ዊልቸር) 360 ዲግሪ ተሽከርክሮ እንዲወጣ አመች ሁኔታን እንዲፈጥር መደረግ ነበረበት ብለው “ነገር ግን አብዛኞቹ ህንፃዎች ይሄን ያሟሉ አይደሉም። እንደውም መፀዳጃ ቤቶቹ በጀርባ በመገንባታቸው አካል ጉዳተኞች ካለመሪ እንዳይንቀሳቀሱ እየሆኑ ነው” ብለውናል። 

በአጠቃላይ ተቋማቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ ላይ ናቸው ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ እንደሌለ ከአዲስ ዘይቤ ቅኝትም ሆነ ካነጋገርናቸው ሰዎች የተገኘ እውነታ ነው። “በምልክት ቋንቋ የተዘጋጀ መረጃ በየትኛውም ቦታ የለም። በየትኛውም አገልግሎት መስጫ ተቋማት በብሬል፣ በምልክት ቋንቋ እንዲሁም በድምፅ ብቻ (ኦዲዮ) መረጃዎች መቀመጥ ነበረባቸው፤ ነገር ግን የተዘጋጀ መረጃ በሃገራችን በየትኛውም ቦታ እንደሌለ” አቶ ፍሬሰላም ዘገየ ለአዲስ ዘይቤ ገልፇል።

አስተያየት