ታህሣሥ 28 ፣ 2015

ከጣሊያን ጀነራሎች መቀመጫነት እስከ የደርግ “ጥፋተኞች” መቅጫነት ታሪክ የተፃፈበት 'ራስ ግንብ'

City: Gonderታሪክ

ግድግዳው የአፄ ሃይለስላሴ እና የባለቤታቸው የእትጌ መነን ምስል ተሰቅሎበት ይታያል። ክፍሉ ጠጅ ይጠጣበታል፣ ቁርጥ ይቆረጥበታል። የግብር አዳራሽም ሆኖ አገለግሏል። ደርግ ደግሞ ጥፋተኛ ያላቸውን አስሮ ገርፎበታል

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ከጣሊያን ጀነራሎች መቀመጫነት እስከ የደርግ “ጥፋተኞች” መቅጫነት ታሪክ የተፃፈበት 'ራስ ግንብ'
Camera Icon

ፎቶ፡ ጌታሁን አስናቀ

ራስ ግንብ፤ በጎንደር ከተማ ከሚገኙ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው። ራስ ግንብ ከፋሲል ግቢ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 300 ሜትር ርቀት ላይ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን ፊትለፊት ይገኛል። ግንቡ ከአፄ ፋሲል ቤተ-መንግስት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን የውሃ ማጠራቀሚያ ዘዴያቸው እንዲሁም የመስኮት አሰራርሩ መጠን ጠባብ መሆን በአፄ ፋሲል ዘመነ መንግስት እንደተሰራ ያመለክታል። 

የቦታው አቀማመጥ ከአፄ ፋሲል ግቢ ከፍ ያለ ሲሆን የከተማዋን ዙሪያ ለመቃኘት እንዲያስችል ተደርጎ የተሰራ ከመሆኑም ባለፈ ራስ ግንብ እንደ አፄ ፋሲል ግቢ ራሱን የቻለ ቅጥር ግቢ አለው። 

ወ/ሮ ዘነብ ጥላሁን በራስ ግንብ ውስጥ አስጎብኚ ናት። ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፀችው ራስ ግንብ የተገነባው በድንጋይና በኖራ ሲሆን ማን እንደሰራው በውል የተቀመጠ ሰነድ ባይኖርም በአፈታሪክ በአፄ ፋሲል ዘመን እንደተሰራ የሚነገር ነው ብላለች። ራስ ግንብ “በጎንደር ዘመነ መንግስት ከንጉስ ነገስቱ ቀጥሎ ያለውን ትልቁን ስልጣን የሚይዘው ራስ ቢትወደድ ተብሎ ለተሾመው ባለስልጣን ለመኖሪያ ቤት እንዲያገለግል ታስቦ በ1636 ዓ.ም የተሰራ ነው” ስትልም ወ/ሮ ዘነብ ነግራናለች። 

በዚህ ግንብ የኖረው በአፄ ፋሲለደስ ዘመን የተሾመው የመጀመሪያው ሰው ራስ ቢትወደድ ወልደ ጊዮርጊስ ሲሆን በ1664 ዓ.ም ሲሞቱ በቀጣይነት በእትጌ ምንትዋብ ዘመን አዛዥ የነበሩት ራስ ሚካኤል ስሁል እንደኖሩበት እና ልጃቸውን ልዕልት እሌኒን በማጋባት በዚህ ስፍራ እንዲቀመጡ አድርገዋቸው እንደነበር አስጎብኚዋ ነግራናለች። በራስ ግንብ ውስጥ ያሉ ታሪካዊ ቅርሶችን በባህልና ቱሪዝም መምሪያ ህግና ደንብ መሰረት ፎቶ ማንሳት ባለመፈቀዱ የግንቡን ውስጣዊ ክፍል በምስሎች መደገፍ አልቻልንም። 

ራስ ግንብ ምድር ቤቱን ጨምሮ ባለ 4 ወለል ህንፃ ሲሆን ምድር ቤቱ መመገቢያ አዳራሽ ነው። ግድግዳው ላይ የአፄ ሃይለስላሴ እና የባለቤታቸው የእትጌ መነን ምስል ተሰቅሎ ይታያል። ጠጅ ይጠጣበታል፣ ቁርጥ ይቆረጥበታል። የግብር አዳራሽም ሆኖ አገለግሏል። ወለሉ ላይ በአፄ ሃይለስላሴ ጊዜ የተሰራ ዘመናዊ ቡፌ ይገኛል። በሌላ በኩል ለወይን እና ጠጅ መጠጫ ሲያገለግሉ የነበሩ 'ሹርቤ' የሚል መጠሪያ ያላቸው ብርሌዎች ተደርድረው ይታያሉ። 

በሌላኛው ክፍል የጎንደር የወቅቱ የገበያ ሁኔታ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ 'ጉልት' የተሰኘ የገበያ ምስል ተሰቅሏል። በወቅቱ ጎንደር ከተለያዩ ሃገራት ጋር የንግድ መናገሻ ከተማ ሆና ከማገልገሏ ጋር ተያይዞ ከውጭ ሃገራት ጋር የንግድ ትስስር ስለነበራት ፍቅራቸውን ለመግለፅ የአረብ፣ የህንድ፣ የፖርቹጋል እና የጃፓን ምልክቶች በግድግዳው ላይ ተቀርፀዋል። 

ሌላኛው ክፍል እነሻለቃ መላኩ ተፈራ ለስርዓቱ አደጋ ናቸው ተብለው የታሰቡትን ግለሰቦች የሚገርፉበት ክፍል ሲሆን ክፍሉ ለዚህ አገልግሎት ይውል እንደነበር የሚያሳይ ምስልም በግድግዳው ላይ ተሰቅሎ ይገኛል። የጎንደር ህዝብ በስፋት ራስ ግንብን የሚያውቀው ለመግረፊያ ብቻ እንደሚያገለግል ሲሆን ውስጡ ግን ብዙ ታሪኮችን ተሸኮሞ ይገኛል። የመረጃዎችን እውነትነት ለማረጋገጥ አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው አስጎብኚዎች “በዚህ ሰዓት በወቅቱ የተገረፉ ሰዎች በህይወት እንዳሉ እና እንደነገሯቸው” ይገልፃሉ። 

ራስ ግንብ በ1880 ዓ.ም ገደማ በተፈፀመው 'የድርቡሽ' ወረራ በቃጠሎ ተጎድቶ ነበር። እስከ 1928 ዓ.ም በዛው ሁኔታ ቆይቶ ኢትዮጵያን ጣሊያን ወርሯት በነበረበት ወቅት ግንቡ በጣሊያኖች እድሳት ተደርጎለት ለጀኔራሎች መኖሪያ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ ሲሆን የጣሊያን ጦር በኢትዮጵያ ኃይሎች ተሸንፎ ከሃገሪቱ ሲወጣ ለአፄ ሃይለስላሴ የግዛት ዘመን ለሰሜኑ ጠቅላይ ግዛት ቤተ መንግስት ሁኖ ሲያገለግል መቆየቱ በታሪክ ተገልጿል።

አንደኛው ወለል ደግሞ አፄ ሃይለስላሴ ወደ ጎንደር ሲመጡ ያርፉበት የነበር ክፍል ሲሆን የንጉስ ነገስቱ እንዲሁም የእቴጌ መነን መኝታ ክፍሎች ይገኙበታል። ከክርስትና እምነት ጋር በተያያዘ እንቅልፋቸውን ሲተኙም ከእንቅልፋቸው ሲነሱም ፀሎት የሚያደርጉበት በራስጌው በኩል የመላዕክት ስዕል አድኖዎችን አድርገው እደሚተኙም የክፍሉ ሁኔታ ያመላክታል። አልጋ ክፍላቸው አጠገብ ንጉሱ ጫማ ሲለብሱ እንዳይጎነበሱ ወደ ላይ እና ወደታች ከፍና ዝቅ የሚል የጫማ መልበሻ ሳጥን መሰል ቁስ ተቀምጦ ይገኛል። 

ከዋንዛ እንጨት የተሰራ በቀይ ቢጫ አረንጓዴ ያሸበረቀ ሞሰብ በንግስቷ አልጋ ክፍል በኩል ይገኛል። በበረንዳው በኩል ሰገነት የሚባል ክፍል ያለ ሲሆን ንጉሱ በዛ ቦታ ላይ ቆመው ህዝቡን ከታች ቅጥር ጊቢው ውስጥ በሚገኘው ሜዳ ላይ በመሰብሰብ ንግግር የሚያደርጉበት ቦታ ነው። ከጠርሙስ የተሰራ 'ደንበጃን' የሚባል የጠጅ መጣያ ገንቦም /ጋን/ በክፍሉ ይገኛል። 

ሌላኛው በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኘው ታሪካዊ ቅርስ ደግሞ በክብር ተቀምጦ የሚገኘው ነጋሪት ጋዜጣ ነው። በ15ኛው ክፍለ ዘመን ግራኝ መሃመድ ከተመታባቸው መሳሪያዎች ውስጥ 'ሹልኪት' የምትባል መሳሪያ ትገኛለች። በ17ኛው ክፍለ ዘመን ከመዳብ የተሰራ እንደወርቅ የሚያበራ የ እትጌ ምንትዋብ የክብር መመገቢያ ትሪ ይገኛል። 

(አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን የሰውበት መሳሪያ ጋር ተመሳስሎ የተሰራ)

በተጨማሪም በዘመኑ ጠላትን ለመከላከል ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ ከጎሽ ቆዳ የተሰራ ጋሻ፣ ሰይፍ፣ ጎራዴ እንዲሁም በአፄ ሚኒልክ ዘመን የተሰራ ሽጉጥ እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች ይገኛሉ። አፄ ቴዎድሮስ ህይወታቸውን የሰውበት ሽጉጥም ትክክለኛው ሳይሆን ለታሪክ ማሳያ ተመሳስሎ የተሰራ መሳሪያም ተቀምጧል። ሴቶች በሰርግ በበዓላት ይጠቀሙባቸው የነበሩ ጌጣጌጦችን ጨምሮ የዝሆን ጥርስ፣ የጎሽ ቀንድ፣ የአጋዘን እና የዋሊያ ቀንድም በራስ ግንብ ውስጥ ይገኛሉ። 

ሁለተኛው ፎቅ ሰገነት ያለው ሰፊ ወለል ሁኖ በበዓላት ጊዜ ካህናት ዝማሬ የሚያቀርቡበት፣ የከበሮ ቅርፅ ያለው ግንብና በእንቁላል ቅርፅ የተሰሩ ለፀሎትት የሚያገለግሉ ክፍሎች አሉት። ሶስተኛው ወለል ደግሞ በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዘመን የተሰሩ አንድ ትንሽ ክፍል እና ሁለት በእንቁላል ቅርፅ የተሰሩ ግንቦች የሚገኙ ሲሆን የንጉሰ ነገስቱ ገንዘብ ያዥ ቢሮ እና የጥበቃ ቢሮ ሆና እንዳገለገለች ይወሳል። የግንቡ የመጨረሻው ሰገነት የከተማዋን ዙሪያ ለመቃኘት ይጠቀሙበት እንደነበረ ታሪክ ያስረዳል።

ራስ ግንብ ከነዚህ ሁሉ አገልግሎቶቹ ባለፈ ሌላ ገፅ አለው፤ በራስ ግንብ ውስጥ አሳዛኝ ድርጊቶች ሲካሄዱበት እንደነበር የሚያመላክቱ የስዕል ስራዎች ተሰቅለው ይታያሉ። ደርግ ለስርዓቱ አስጊ ናቸው ያላቸውን ግለሰቦች በራስ ግንብ ውስጥ እያስገባ ይገርፍበት እንደነበር የታሪካዊ ስፍራው አስጎብኚዎች ይናገራሉ። በሻለቃ መላኩ ተፈራ አማካኝነት በደርግ ስርዓት ሲሰርቁ የተያዙ፣ ጥፋት አጥፍተዋል የተባሉ ሁሉ ስቃይ ሲያዩበት የነበር መሆኑ የሚነገርለት ጠባብ ክፍልም በዚሁ የራስ ግንብ ውስጥ ይገኛል። 

በአሁኑ ሰዓት በዚህ ጠባብ ክፍል ውስጥ እንዴት ይገረፉ እንደነበር የሚያሳይ ምስል ለታሪክ ተቀምጦ ይገኛል። ምስሉ ጥፋተኛ የተባለ ሰው አግዳሚ እንጨት ላይ ተንጠልጥሎ በአለንጋ ሲገረፍ፣ ጥይት ተደኖባቸው እንዲሁም እግር እና እጃቸውን አጣምረው በተንጠለጠለ አግዳሚ አንጨት ላይ በማሰር ወለሉ ደም እስኪለብስ ሲገረፉበት እንደነበርም የሚያሳይ ምስል አለ። 

ከደርግ መውደቅ በኋላ ራስ ግንብ ለምንም አይነት አገልግሎት ሳይውል ተዘግቶ የቆየ ቢሆንም የጎንደር ከተማ በ2002 ዓ.ም በፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አነሳሽነት ከፈረንሳይ ቬንስን ከተማ ጋር በተደረገ ስምምነት ለጥገና የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎለት ተጠግኖ የጎንደር የታሪክና የባህል ሙዚየም ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

አስተያየት