ጥር 1 ፣ 2015

የመሬት ባለቤቶች እና ደላሎች ያስቸገሯት ባህር ዳር ከተማ

ወቅታዊ ጉዳዮችንግድ

በባህር ዳር ከተማና አካባቢዋ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያለሙ የተሰጣቸውን መሬት ወደ ሪል ስቴት ተቀይሯል በማለት የመሬት ደላሎች እና ባለቤቶች የመሬት ሽያጩን አጧጡፈውታል

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

የመሬት ባለቤቶች እና ደላሎች ያስቸገሯት ባህር ዳር ከተማ
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ድረ ገፅ

በባህር ዳር ከተማ እና አካባቢው ለባለሀብቶች የተሰጡ የአበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ማልሚያ ቦታዎች በህጋዊ መልኩ 'ሰነዳቸው ወደ ሪልስቴት ተቀይሯል' ተብሎ እየተሸጠ መሆኑን አዲስ ዘይቤ መታዘብ ችላለች።

ሰለሞን ጌታሁን ከአስር ዓመታት በላይ በአሜሪካ ኑሮውን እንዳደረግ ይገልፃል። በባህር ዳር ከተማ ቤት የመስራት ፍላጎት ስለነበረው በከተማው ለአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የተሰጠ ቦታ ወደ ሪልስቴት ተቀይሯል ተብሎ አንድ እጣ አራት መቶ ሺህ ብር ከፍሎ እንደገዛ ይናገራል። ከእሱ አልፎ ዕድሉ እንዳያልፋቸው የደወለላቸው አሜሪካ የሚገኙ ወዳጆቹ በወኪሎቻቸው በኩል ገዝተዋል ብሏል። “ግዢ ሲፈፅም ደላሎች ቦታውን ወስደው እንዳሳዩትም” ሰለሞን ይናገራል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የህዝብ ግንኘነት ኃላፊ አቶ ይህነው አለም ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ “በባህር ዳር ከተማ እና አካባቢው የአበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ቦታዎች በህጋዊ መልኩ ሰነዳቸው ወደ ሪልስቴት ተቀይሯል የሚል ወሬ በስፋት መሰራጨቱን” ነግረውናል። እንደ አቶ ይህነው ማብራሪያ በከተማው የአትክልት እና ፍራፍሬ ለማልማት መሬት የወሰዱ ባለሃብቶችን ቢሮው ጠርቶ ማናገሩን እና ይህን ማድረግ እንደማይችል ማሳወቁን ገልፀዋል። ነገር ግን ቦታ የወሰዱ ባለሀብቶች “ከእነሱ እውቅና ውጭ ደላሎች ይህን እያደረጉ መሆኑን” ነግረውናል ሲሉም የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጨምረዋል።

የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የህዝብ ግንኘነት ኃላፊ በከተማው በደላሎች ወደ ሪል ስቴት ተቀይሯል ተብሎ እየተሸጠ ከሚገኙት አንዱ ባለሀብት መሬት ጥቆማ ደርሷቸው ማጣራታቸውን ገልፀው “ባለሀብቱ መሬቱን በተቀመጠው ጊዜ ማልማት ባለመቻሉ ሊቀማ ደብዳቤ የተፃፈበት” መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል። በባለሃብቱ ስም የተሰጠ ቦታ ለሪል ስቴት ተብሎ እየተሸጠ ስለመሆኑ የተጠየቀው ባለሀብቱ ስለጉዳዩ ምንም እንደማያውቅ ተናግሯልም ተብሏል።

እንደ አቶ ይህነው ገለፃ በባህር ዳር እና አካባቢው ሀያ ባለሀብቶች ለአበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ቦታ ወስደዋል። የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው በባህር ዳር ከተማና አካባቢው “በዚህ ዘርፍ የተሰጠ አንድም ቦታ ወደ ሪል ስቴት አልተቀየረም፤ ሊቀየርም አይችልም” ብለዋል። የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮም ህብረተሰቡ በዚህ ጉዳይ እንደይጭበረበር እና ተግባሩ ህገ ወጥ መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገፁ እና በደብዳቤ አሳውቋል። ባለሀብቶቹ በዚህ ህገ ወጥ ድርጊት ላይ ከተገኙ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ሲሉም አቶ ይህነው አለም ገልፀዋል።

በክልሉ ለኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ፕሮጀከቶች የተሰጡ ቦታዎች ለታለመላቸው ዓላማ እየዋሉ መሆኑን እና አለመሆኑን ለማረጋገጥ በአማራ ክልል 6 የተመረጡ ከተሞች (ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሀን፣ ኮምቦልቻ እና ቱለፋ) የዳሰሳ ጥናት ማካሄዱን የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነግረውናል።

የጥናቱ ውጤት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በተገኙበት ውይይት የተደረገበት ሲሆን "ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት የተሰጠ ቦታን ለታለመለት አላማ ብቻ በማያውሉ አካላት ላይ ክልሉ ቆራጥ እርምጃ  ይወስዳል” ሲሉ ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ መረጃ በ2014 በጀት ዓመት ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ስራ ባልገቡ ከ254 የሚበልጡ ባለሃብቶች መሬት እንዲመልሱ መደረጉን ያሳያል። በሌላ በኩል በ2015 1ኛ ሩብ ዓመት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ብቻ ከ21 በላይ በሚሆኑ ባለሀብቶች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ተወስዷል።

በአማራ ክልል ያለው የመሬት ወሪራ አሳስቢነት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርን ጭምር "የመሬት ወረራ አስፈሪ ደረጃ ላይ ደርሷል” ማስባሉን ተከትሎ የክልሉ መንግስት የመሬት ከወረራ ይከላከላሉ ያላቸውን የተለያዪ የዕገዳ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

በክልሉ መንግስት የዕገዳ ውሳኔ የተጣለባቸው መሬት ነክ ጉዳዩች መካከል በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ከተሞች በከተማ አቅራቢያ ያለ ቦታ በክልሉ የኢንቨስትመንት ቦርድ ቀርቦ ውሳኔ ካልተሰጠ በስተቀር መስጠት እንደማይቻል፣ በክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ የገጠር የእርሻ መሬት የባለቤትነት ማስረጃ ወይም አረንጓዴ ደብተር የሚደረግ ስጦታ እንዲቆም ተደርጓል። ከዚህ ቀደም አርሶ አደሮች ወይም የመሬት ባለቤቶች ካላቸው ቦታ ቀንሰው ለሌላ ሰው ሲሰጡ በሰጡት ሰው ስም የባለቤትነት ማረጋገጫውን አረንጓዴ ደብተር ያሰሩ ነበር። 

"አሳፋሪ "ደረጃ ደርሷል በተባለው የአማራ ክልል መሬት በክልሉ መንግስት በኩል ማንኛውም የመሬት ምሪት በከተሞች አካባቢ እንዳይሰጥ በቅርቡ መመሪያ ተላልፏል።

አስተያየት