ጥር 2 ፣ 2015

ስርቻ የተጣለው የአዳማ የካንሰር ህክምና ማዕከል

City: Adamaጤና

በአዳማ ሆፒታል የካንሰር ማዕከል የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ የሆነ የመገልገያ መሳሪያዎች፣ የአስፈላጊ ግብዓቶች እንዲሁም የመገልገያ ግንባታዎች ችግር ተመልክቷል

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ስርቻ የተጣለው የአዳማ የካንሰር ህክምና ማዕከል
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሚዲያ

በሰው ልጅ እድሜ ልክ እድሜው የሚቆጠርለት ካንሰር አሁን አሁን በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በኢትዮጵያ እየናረ ነው። የዘርፉ ባለሞያዎችም በሁለት መላምቶች ነገሩን ለመረዳት ይሞክራሉ። አንድ በውስን ደረጃ ካንሰርን የመረዳት እና መርምሮ የማወቅ አቅም እያደገ ስለመጣ ከዚህ ቀደም በምርመራ የማይደረስባቸው ህመሞች መታወቅ መጀመራቸውን፣ አልያም በተጨባጭም የካንሰር በሽታ በመጨመር ላይ ሆኖ ነው የሚል መላምታቸውን ያስቀምጣሉ።

የካንሰር ህክምና በሌሎቹ ዓለማት እድሜ ያስቆጠረ ህክምና ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን ገና የሚድህ ህጻን እድሜ ያለው ነው። ኢትዮጵያም ነገሬ ብላ የህክምና ፖሊሲ የነደፈችለት እ.ኤ.እ 2016 ነበር። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የካንሰር ህክምና የተጀመረው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በ1997 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱ አንድ ብቸኛ ባለሞያ የሆኑት ዶ/ር ቦጋለ ሰለሞን ብቻ ይህንን አገልግሎት ይሰጡ ነበር። ይህ ህክምና በ2005 ዓ.ም ሶስት ባለሙያዎችን ወደ ውጪ ሃገር ልኮ በማስተማር የባለሙያዎቹን ቁጥር ከፍ ለማድረግ ሞክሯል። በ2013 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የካንሰር ህክምና ሳይንስ (ኦንኮሎጂ) ትምህርት ተጀመረ። በአሁን ወቅት በ20 የመንግስት ሆስፒታሎች የካንሰር ህክምና እየተሰጠ ይገኛል። ኬሞቴራፒ እና የራዲዮቴራፒ ህክምናዎች እየተለመዱ ቢመጡም ዛሬም ኢሚኖቴራፒ፣ ታርጌትድ ቴራፒ ዓይነት የመፍትሔውን መንገድ የሚያሳጥሩ መላዎች ለሀገራችን የህክምና ተቋማት የብርቅ ብርቅ ናቸው።

ያልዳበረ ህክምና፣ አናሳ የባለሞያ ቁጥር፣ የመድሃኒት እጥረት፣ ከመዘንጋት ያልዘለለ የመንግስት ትኩረት ያለበት ይህ ዘርፍ ብቸኛ የካንሰር ምዝገባ የሚደረግበትን አዲስ አበባ ተንተርሶ ለድፍን ኢትዮጵያ ይሆናል በተባለለት ቁጥር በየዓመቱ 77 ሺህ አዲስ ካንሰር ተጠቂዎች እንደሚገኙ አልያም እንደሚያዙ ይገለፃል። የከፋው ደግሞ አብዛኛው ተጠቂ ካንሰሩ ደረጃ የከፋ የተባለለት ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ የጤና ማዕከል መድረሱ የችግሩን ጥልቀት ያጎላዋል።

የካንሰር ጥናት እና ምርምሩም ቢሆን “የለም ማለት ይሻላል” በማለት ትኩረት ማጣቱ እና የግንዛቤ ችግሩ ከነዋሪ እስከ መሪ ነው ሲሉ ባለሞያዎቹ ያማርራሉ።

ዛሬ ላይ አዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ተብሎ የሚጠራውና ለሚሊዮን ሩብ የጎደለውን የአዳማን ነዋሪን ጨምሮ ለስድስት ሚሊዮን ሰዎች የሪፈራል ሆስፒታል ሆኖ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ይህ ሆስፒታል በሀገሪቱ ካሉ የጤና ተቋማት ውስኑነት እና ተዳራራቢ ችግሮች አንጻር በከፍተኛ ደረጃ የህዝብ ቅሬታ የሚሰማበት ነው። ከዚህ ቀደም አዲስ ዘይቤ በሆስፒታሉ  የድንገተኛ ክፍል ላይ የሚስተዋለውን ከፍተኛ ቅሬታ መዘገቧ ይታወሳል።

የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር በሆስፒታሉ በታካሚዎች ቅሬታ መሰረት ባደረገው ዳሰሳ የካንሰር ህክምና ከፍል በመደበኛ አጠራሩ የኦንኮሎጂ ህክምና ክፍል ከፍተኛ የሆነ የመገልገያ መሳሪያዎች እጥረት እና አስፈላጊ ግብዓቶች እንዲሁም የመገልገያ ግንባታዎች ችግር ተመልክቷል። በዚህ ጽሁፍ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ እና የጥቃት አድማስ እንዲሁም በአዳማ ሆስፒታል እየተሰጠ ያለው የካንሰር ህክምናን በተመለከተ ዳሰሳ ተደርጓል። 

ፅዮን እድሜዋ ሀያዎቹ አጋማሽ ውስጥ የምትገኝ የአዳማ ነዋሪ ናት። “ካንሰር እንዳለብኝ ሲነገረኝ ራሴን ስቼ ነበር የወደቅኩት” ትላለች። ህክምናው ብዙ አካላዊ ለውጦች ያመጣል የምትለው ፅዮን የጸጉር መነቃቀል፣ የጥፍር መጥቆር፣ የቆዳ ቀለም መጥቆር ወዘተ በጉልህ የሚታዩ ምልክቶች እንደሆኑ ትናገራለች። ነገርግን ከዚህ በላይ የስነ-ልቦና ጫናው ከፍተኛ እንደሆነ የምታስረዳው ፅዮን፣ ስለበሽታው መደበኛው ህዝብ ቀርቶ የህክምና ባለሞያዎች እንኳን በቂ ግንዛቤ የላቸውም ትላለች።

ብሪጅ ዘ ጋፕ ይህንን የአመለካከት ክፍተት (በተለይም በጡት ካንሰር ላይ) ለመቅረፍ እየሰራ የሚገኝ ግብረ-ሰናይ ድርጅት  ነው። ነሐሴ 2013 ዓ.ም የተቋቋመው ይህ ድርጅት በአሁን ወቅት በሁለት ነገሮች ላይ እየሰራ ይገኛል። በዋነኝነት በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ፣ አድአ እና ሎሜ ወረዳዎች ስለጡት ካንሰር ግንዛቤ እየሰጠ ይገኛል። ከዚህ ሌላ ባሳለፍነው ጥቅምት ለመጀመሪያ ጊዜ በአዳማ የራስ ጡት ካንሰር ልየታ አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪ የስነ-ልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ (Psycho-Social Support) ቡድን በማቋቋም ከ50 እስከ 60 የሚሆኑ የካንሰር ተጠቂ  ሴቶችን በማደራጀት በየጊዜው ውይይት ያደርጋል።

በአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ስር ካሉ የህክምና ክፍሎች መካከል አንዱ የሆነው የካንሰር (ኦንኮሎጂ) ህክምና ክፍል አንዱ ነው። በዚህ ክፍል አገልግሎት ላይ በተገልጋዮች በቀረበ ቅሬታ ወደ ስፍራው ያቀናው የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ከፍተኛ የሆነ የመገልገያ መሳሪያዎች እጥረት፣ የአስፈላጊ ግብዓቶች እንዲሁም የመገልገያ ግንባታዎች ችግር ተመልክቷል።

በካንሰር ህክምና ላይ ከሚሰጡ የህክምና ዓይነቶች አንዱ ኬሞቴራፒ ሲሆን ይህንን ህክምና ለመስጠት የሚያስፈልጉ መድሃኒቶች እና ማሽን አለመኖር በታካሚዎች እና በሰራተኞቹ ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ይናገራሉ።

በሆስፒታሉ የካንሰር ህክምና ክፍል ካገኘናቸው ታካሚዎች አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ሀይማኖት ታደሰ የአዳማ ነዋሪ ናቸው። የካንሰር ህክምና የሆነውን ኬሞቴራፒ ሊወስዱ ወደ ማዕከሉ የመጡት ወ/ሮ ሀይማኖት ያለፉትን ስድስት ወራት በካንሰር ህክምና ክትትል ላይ ቆይተዋል።

“ሰራተኞቹ ጥሩዎች ቢሆኑም መድሃኒት ግን የለም” የሚሉት ወ/ሮ ኃይማኖት ያለፉትን 6 ወራት በየ21 ቀኑ በእያንዳንዱ ዙር ኬሞቴራፒ ህክምና ከ7-8 ሺህ ብር ድረስ እያወጡ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህም ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ጫና እንዳደረሰባቸው ይናገራሉ።

ሌላው ባለቤታቸውን ሊያሳክሙ በሆስፒታሉ ያገኘናቸው አቶ ጀማል መካ ባለቤታቸው ህክምናውን ከጀመሩ አንድ ወር አልፏቸዋል።

“በሰራተኛ በኩል ያለው መስተንግዶ ጥሩ ነው። የአልጋ እጥረት ከመኖሩ ባለፈ በሆስፒታሉ መድሃኒት የሚባል ነገር የለም” ይላሉ አቶ ጀማል።

በሆስፒታሉ የኦንኮሎጂ (የካንሰር) ህክምና ክፍል ለኬሞቴራፒ ህክምና የሚያገለግለው ባዮሴፍቲ ካቢኔት ቢኖርም በተቋሙ ከመጣ ጀምሮ አገልግሎት ላይ አለመዋሉን የድርጅቱ ሰራተኞች ይናገራሉ። 

በሆስፒታል በኬሞቴራፒ ህክምና ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ነርሶች በግል መከላከያ በመጠቀም ብቻ እየሰሩ እንደሆነና በኬሞቴራፒ ህክምና ወቅት ለጥንቃቄ የሚያገለግለው ሴፍቲ ካቢኔት ባለመስራቱ ለከፍተኛ የኬሚካል ብክለት ተጋላጭነት መዳረጋቸውን ይገልፃሉ። በኬሞቴራፒ ህክምና ወቅት የህክምና ባለሙያዎች ለኬሚካል ተጋላጭነት ከተዳረጉ ከፍተኛ ጉዳት ሊገጥማቸው እንደሚችል ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ። 

ባዮሴፍቲ ካቢኔት ማለት በአንድ የጤና ላብራቶሪ ውስጥ ሊገኝ የሚገባ የራሱ የአየር አጠቃቀም ስርዓት ያለው መሳሪያ ነው።  መሳሪያው የራሱ መዝጊያ ያለው ሲሆን በአቅራቢያው ስራ ላይ ያለን ባለሙያና አካባቢውን ከተጓዳኝ ጉዳቶች የመታደግና የመከላከል አቅም አለው።

ነርስ ጫላ ተርፋሳ በኦንኮሎጂ ክፍል የኬሞቴራፒ ህክምና ላይ ሁለት ዓመት ኬሚስት ሆኖ አገልግሏል። ከዚህ ቀደም ከ10 እስከ12 ሰዎች እናስተናግድ ነበር የሚለው ጫላ አሁን ባለው ቦታ ጥበት እና በተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመር እያስተናገዱ የሚገኙት ከ6 እስከ 9 ታካሚዎችን እንደሆነ ይናገራል።

“ካለው ፍላጎት አንጻር በቀን ከ15 እስከ 20 ለሚሆኑ ሰዎች አገልግሎት ልንሰጥ እንችላለን” የሚለው ጫላ በስታንዳርዱ መሰረት የኬሞቴራፒ ኬሚስቶች ኬሚካሉ ካለው ባህሪ የተነሳ በቀን ከአራት ሰው በላይ መስራት እንደሌለባቸው እንደሚያስገድድ ይናገራል። ስለዚህም ተጨማሪ ሰራተኛ እና ሴፍቲ ካቢኔት ሊኖር እንደሚገባ ጫላ ይጠቁማል። “በአሁኑ ወቅት በግል የጥንቃቄ መሳሪያዎች (personal protection equipment) ሰርተን ስንወጣ እንኳን ገላችንን ለመታጠብ የመታጠቢያ ቤት አናገኝም” የሚለው ጫላ በስራው ላይ የተሰማሩ ባለሞያዎች ተጠቃሚዎችን ለማገልገል ራሳቸውን አደጋ ላይ ጥለው እየሰሩ እንደሆነ ይናገራል።

እንደ ጫላ አስተያየት እስከአሁን ድረስም ለተለያዩ ኬሚካሎች ተጋላጭ ለሆኑ ባለሙያዎች የሚከፈል የተጋላጭነት (ሀዛርድ) ከፍያ እተከፈላቸው አይደለም። በሴፍቲ ካቢኔቱም ሆነ በሀዛርድ ክፍያ ጉዳይ ለሆስፒታሉ ጥያቄ ቢያቀርቡም ያለፉትን ሁለት ዓመታት መልስ አለማግኘታቸውንም ጨምሮ ይናገራል።

የካንሰር ህክምና ክፍሉ ከዚህ ቀደም የድንገተኛ ህክምና ይሰጥበት ክፍል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን አነስተኛ የተፈጥሮ ብርሃን ያለው፣ በቂ አየር የማይገባበት እንዲሁም እጅግ ጠባብ መተላለፊያ እና ጠባብ የአገልግሎት መስጫ ያለው ነው። በየቀኑ ስድስት የኬሞቴራፒ አገልግሎት ታካሚዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው የህክምና ክፍል ከ10 በላይ ሰዎችን እያስተናገደ ይገኛል። 

በማዕከሉ ያገኘናቸው መሰረት እና ወንድሟ እናታቸው ወ/ሮ አሰገደች በቀለን ለ4ኛ ጊዜ ለኬሞቴራፒ ህክምና ይዘው ነበር ወደ ማዕከሉ የመጡት። ልጃቸው መሰረት ስዩም እንደምትለው የተገልጋዮች አያያዝ ቀድሞ ከነበረው እጅግ መሻሻል ያሳየ ሲሆን በህክምናው አገልግሎት ላይ ግን የተሰማትን ቅሬታ ትገልጻለች።

ከፍተኛ ሆነ የመድሃኒቶች እጥረት አለ የምትለው መሰረት ከዚህ ቀደም በሆስፒታሉ 900 ብር የገዙትን መድሃኒት በእጥፍ ከውጪ በ1500 ብር መግዛታቸውን ትናገራለች። ከዋጋው ውድነት ባልተናነሰ በመድሃኒቶቹ አለመገኘት እንደተቸገረችና በመድሃኒት ውድነት ምክንያት ህክምናውን ጥሎ የሄደ ሰው ማስተዋሏንም ታስረዳለች።

ለወ/ሮ አሰገደች ህክምና ቤተሰባቸው በአንድ ዙር ብቻ እስከ 4ሺህ ብር ያወጣል። “በተደጋጋሚ እንዳየሁት ከታካሚዎች ቁጥር ጋር ታሳቢ ተደርጎ የካንሰር ህክምና መድሃኒቶች በሆስፒታሉ እንዲገኙ ቢደረግ መልካም ነው” ስትል መሰረት አስተያየቷን ትሰነዝራለች። በተጨማሪም የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት አለመኖሩ የካንሰር ህክምና የሚከታተሉ ሰዎች የግሉኮስ መርፌ እንደተሰካላቸው ረጅም ርቀት ሄደው እንዲጠቀሙ እንዳስገደዳቸውም ትናገራለች።

ከፍተኛ የአልጋ እጥረት በመኖሩ ለሊት መጥተን ነው አልጋ የምንይዘው የሚለው የወ/ሮ አሰገደች ልጅ፣ በአልጋ እጥረት ምክንያት ህክምናውን ሳያገኙ የሚቀሩ ሰዎች አሉም ሲል ይናገራል። የመድሃኒት እጥረትን በተመለከተ አዳማ ላይ እጅግ ውስን የመድሃኒት አቅርቦት ስላለ አዲስ አበባ ሄደው ለመግዛት በመገደዳቸው ለተጨማሪ ወጪ እና እንግልት እንደዳረጋቸው ይናገራል።

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከካንሰር ታካሚዎች ከ80 በመቶ በላይ እድሜያቸው ከ50 በላይ ነው። ከዓለማቀፉ ተሞክሮ በተቃራኒ በኢትዮጵያ የካንሰር ታካሚዎች ላይ የሚስተዋለው ግን 80 በመቶ ታካሚዎች በወጣትነት እድሜ ክልል የሚገኙ እንደሆኑ በባለሙያዎች ዘንድ በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ይሰማል።

ይህ በምን ምክንያት ሆነ ያልናቸው በአዳማ ሆስፒታል የኦንኮሎጂ የህክምና ክፍል ኃላፊ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ቢኒያም ተፈራ “ጥናት ባለመሰራቱ እርግጠኛ ሆኖ መደምደም ከባድ ነው” በማለት ሁለት ሃሳቦችን ያነሳሉ።

“ኢትዮጵያ የወጣቶች ሀገር ናት ይህ ደግሞ ከታካሚዎች ቁጥር ውስጥ ወጣቶች የአንበሳውን ድርሻ እንዲወስዱ አድርጎት ሊሆን ይችላል ወይንም ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለየ የዘረ-መል አጋላጭነት ኖሮ ይሆናል” ሲሉ በመግለፅ፣ ከመላምት በዘለለ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ መረጃ አለመኖሩን ይናገራሉ።

ዶ/ር ቢኒያም በተጨማሪ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ካንሰርን በተመለከተ “ሃገር ውስጥ እየተከናወነ ያለው ጥናት በቂ ነው ብዬ አላምንም” ይላሉ። በሀገር አቀፍ ደረጃ የካንሰር ምዝገባ ያለው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ሆስፒታል ላይ የሚደረግ ምዝገባ የሚደረገው አዳማ ሆስፒታል ብቻ ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገ ምዝገባ የተገኘ መረጃ እንደሚያሳው የጡት፣ የማህጸን በር እና የአንጀት ካንሰር በሰፊው በመከሰት በቅደም ተከተል የሚታዩ መሆናቸውን ዶ/ር ቢኒያም ያስረዳሉ። በአዳማ ያለው ግኝት ግን የጡት ካንሰርን አስቀድሞ የጉሮሮ እና የጉበት ካንሰር በተከታይነት፣ በአርሲ እና ባሌ አካባቢ ደግሞ የጉሮሮ፣ የአንጀት፣ የጉበት ካንሰር በስፋት ይታያሉ። ከዚህም በመነሳት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ሁኔታ ለመረዳት እና ተገቢውን ህክምና ለመስጠት የካንሰር ምዝገባ ወሳኝ መሆኑን አፅዕኖት ይሰጣሉ። 

ለበሽታው በቂ ትኩረት ያለመሰጠቱ አንዱ ማሳያ 70 በመቶ በላይ ካንሰር ወደ ጤና ተቋማት ሲደርስ ከፍተኛ አሳሳቢነት ላይ ደርሶ ነው የሚሉት ዶ/ር ቢኒያም ይህም ከበሽታው የመዳን እድልን እጅግ አነስተኛ እንደሚያደርገው ይናገራሉ።

ዶ/ር ቢኒያም በተሳተፉበት እና በ እ.አ.አ 2021 ይፋ በተደረገውና በጥቁር አንባሳ ሆስፒታል የካንሰር የራዲዮቴራፒ  ህክምና መስጫ ላይ በተደረገው Contemporary treatment patterns and survival of cervical cancer patients in Ethiopia በሚል ርእስ ይፋ በሆነው ጥናት የማህጸን ጫፍ ካንሰር የመዳን ምጣኔ በአማካኝ ከ28 በመቶ እንደማይበልጥ ይገልጻል።  የከፋ ደረጃ ላይ በሚገኙ ታካሚዎች ላይ ደግሞ የመዳን ምጣኔው ከዚህም እንደሚያንስ ጥናቱ ያሳያል። 

በአዳማ ሆስፒታል በሚገኘው ኦንኮሎጂ ማዕከል ላይ በተገልጋዮች የቀረበው ቅሬታ በተመለከተ ያነጋገርናቸው ህክምና ክፍሉ ኃላፊ ዶ/ር ቢኒያም እንደሚሉት የተነሱትን ችግሮች እንደሚያውቁና ለሆስፒታሉ ማኔጅመንት ቢያቀርቡም መፍትኄ አለማግኘቱን ይናገራሉ።

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የሆስፒታሉ የሜዲካል አገልግሎት ምክትል ፕሮቮስት ዶ/ር በሽር አብደላ “ከህክምና መስጫ ቦታው ለህክምናው ተገቢ አይደለም። አሮጌ ህንጻ ነው። ችግሩ በሆስፒታሉ አመራር ብቻ ሳይሆን በኦሮሚያ ጤና ቢሮም ደረጃ ይታወቃል” ይላሉ። የካንሰር ህክምና ክፍሉ በ2014 ዓ.ም የተጀመረ ህንፃ ላይ ይዛወራል ተብሎ እንደሚጠበቅና ግንባታው ለመጠናቀቅም ሶስት ዓመታት እንደሚፈጅበት ኃላፊው ጠቁመዋል።

የማይሰራውን የጥንቃቄ ባዮሴፍቲ ካቢኔትን በተመለከተም መሳሪያውን ለመግዛት ጨረታ መውጣቱን ገልፀዋል

በኬሞቴራፒ ነርሶች የተነሳውን የአደጋ ተጋላጭነት ክፍያ አለመከፈል ጋር ለቀረበው ቅሬታ ምላሽ የሰጡት ዶ/ር በሽር ይህን ክፍያ የማይከፈላቸው እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች እንደቀዶ ጥገና ላይ ያሉ ነርሶችም ጭምር እንደሆኑና  ውሳኔው የጤና ቢሮ መሆኑን ይናገራሉ።

ከተገልጋዮች ቅሬታ “የመድሃኒት እና ላብራቶሪ ማስመርመሪያ ወጪ በግል እንድንሸፍን በመደረጉ ኪሳችን ተራቆተ” ስለሚሉት ታካሚዎች የጠየቅናቸው ኃላፊው ቅሬታውን ሙሉ በሙሉ መቀበል እንደሚከብዳቸው ይናገራሉ። ካለው ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ አንጻር የመድሃኒት እና የሌሎች ግብዓቶች እጥረት በተደጋጋሚ እንደሚገጥም የሚያስረዱት ኃላፊው በሚባለው ደረጃ በወራት እድሜ ግን እንደማይቆይ ይናገራሉ። በተጨማሪም አዳማ ሆስፒታል አዳማን ጨምሮ ለአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጥ ብቸኛው ተቋም በመሆኑ ከፍተኛ ጫና እንዳለበት ይገልጻሉ።

በነዚህ ሁኔታዎች መካከል ዛሬም ታዛቢ ሊመለከተው የሚችለው የአዳማ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ማዕከል በተፋፈገና ምቾት በሚነሳ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አገልግሎት መስጠቱን ቀጥሏል።

አስተያየት