ጥቅምት 25 ፣ 2014

የጥንቃቄ መመሪያዎችን የዘነጉት የአዳማ የኮቪድ ህክምና ማዕከላት

City: Adamaጤናኮቪድ 19መልካም አስተዳደርወቅታዊ ጉዳዮች

የኮቪድ 19 የህክምና ፕሮቶኮሎችን ሳያሟሉ፣ ተገልጋዮችና የህክምና ባለሙያዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርጉ፣ አስታማሚና ጠያቂዎች ያለ በቂ ጥንቃቄ ከታማሚዎች ጋር እንዲገናኙ የሚፈቅዱ የህክምና ተቋማት መኖራቸውን መስማት አስደንጋጭ ነው።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የጥንቃቄ መመሪያዎችን የዘነጉት የአዳማ የኮቪድ ህክምና ማዕከላት
Camera Icon

Photo: EthiopiaSports

በአዳማ ከተማ የሚገኙ ጥቂት የግል ሆስፒታሎች የኮቪድ-19 ታማሚዎች የሚረዱባቸውን ለይቶ ማቆያዎች አዘጋጅተዋል። ለአገልግሎታቸው የሚጠይቁት ክፍያ እስከ 80 ሺህ ብር መድረሱ አነጋጋሪ ቢሆንም መንግሥት ካዘጋጃቸው ለይቶ ማከሚያዎች በተጨማሪ ለታካሚ በአማራጭነት መቅረባቸውን የሚያበረታቱ በርካታ ናቸው። የኮቪድ 19 የህክምና ፕሮቶኮሎችን ሳያሟሉ፣ ተገልጋዮች እና የህክምና ባለሙያዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርጉ፣ አስታማሚ እና ጠያቂዎች ያለ በቂ ጥንቃቄ በኮቪድ ከተያዙ ታማሚዎች ጋር እንዲገናኙ የሚፈቅዱ የህክምና ተቋማት መኖራቸውን መስማት ግን አስደንጋጭ ነው።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ በአዳማ ከተማ ከተከፈቱት ለይቶ ማቆያዎች መካከል በአዳማ ጀነራል ሆስፒታል የነበረው አንዱ ነው። ቫይረሱ የጎዳቸውን ሰዎች ለይቶ የመንከባከብ ሥራ ሲያከናውን የቆየው ማዕከሉ በአዳማ ጀነራል ሆስፒታል ስር ሲተዳደር ቆይቷል። በትንፋሽ እና በንክኪ የሚዛመተውን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሲባል ከሌሎች ታካሚዎች ርቆ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት ከሦስት ወራት ወዲህ ወደ ሆስፒታሉ ሕንጻ ተመልሷል። በአሁን ሰዓት አዳማ ጀነራል ሆስፒታል የኮቪድ ታማሚዎችን የሚረዳው ከሌሎች ታካሚዎች ጋር ቀላቅሎ በተቋሙ አራተኛ ላይ በሚገኝ ፎቅ ነው።

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው በዚህ ዘገባ ላይ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሆስፒታሉ ባልደረቦች ከአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ “ሐኪሞች ራሳቸውን ከኮቪድ 19 ጠብቀው ታማሚዎችን የሚረዱባቸው መሳሪያዎች በበቂ መጠን አይቀርቡም” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። የህክምና እርዳታ ፈልገው የተቋሙን በር የሚያንኳኩ ታማሚዎች የሚጠየቁት ክፍያ ከፍ ያለ ከሚለውም ልቆ የተጋነነ የሚባል ዐይነት መሆኑን በማንሳት “ክፍያው ምን ምን አገልግሎቶችን ያጠቃልላል?” ስንል የሆስፒታሉን ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሞቱማ በቀለን ጠይቀናል። ዶ/ር ሞቱማ “ይህንን መመለስ ያለበት አስተዳደር ቢሮ ነው” የሚል ምላሽ ቢሰጡም የአስተዳደር ኃላፊው በበኩላቸው ጉዳዩ ሜዲካል ዳይሬክተሩን እንጂ እኔን አይመለከትም ብሏል።

በተጨማሪም ዶ/ር ሞቱማ በቀለ “ከኮቪድ ታማሚዎች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሀኪሞች እና ሰራተኞች በተቋሙ ውስጥ ባቆየን ቁጥር ወጪው እጅግ ከፍተኛ ይሆናል። አሰራሩ በሆስፒታላችንም ሆነ በከተማችን እንዲሁም በሀገራችን አቅም የማይቻል ነው። በዚህ ምክንያት አሁን ጥንቃቄ እያደረግን ነው የምንሰራው።" የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ስሜን ደብቁልኝ ያለን ወጣት ሀኪም በበኩሉ “ጥንቃቄ ይደረጋል” የሚለውን የኃላፊውን ምላሽ አይቀበለውም። "ከጓንት ጀምሮ እንደ ፒፒኢ ያሉ የግል መከላከያ ግብአቶች አልተሟሉም። ይህ ሁኔታ የባለሞያውን የኮቪድ ተጋላጭነት እንደሚያሰፋው ጥርጥር የለውም። ሆስፒታሉ ከአንድ ታማሚ ከሚቀበለው ክፍያ አንጻር ሲታሰብ ደግሞ የሀኪሙን ሞራል በእጅጉ ይጎዳል። ሁሉም ስራውን ላለማጣት ነው የሚሰራው።" ብሎናል።

በሚመሩት ተቋም ላይ የተነሳውን ቅሬታ አስመልክተን የጠየቅናቸው ዶ/ር ሞቱማ ሲመልሱ በስብሰባም ሆነ በቢሮ ደረጃ የተባለው ዓይነት ቅሬታ ቀርቦ እንደማያውቅ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። 

በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ አራተኛ ፎቅ ላይ የሚሰጠው የኮቪድ ታማሚዎች ህክምና ለቫይረሱ የመዛመት እድል የሚፈጥርለት እንደሆነ መታዘብ ይቻላል። በሊፍት፣ በደረጃ፣ በድንገተኛ ክፍል፣ በመጸዳጃ ቤት፣ በላቦራቶሪ እና የመሳሰሉት የጋራ መገልገያዎች የቫይረሱን መዛመት የሚጨመሩ ጥንቃቄ የጎደላቸው እንቅስቃሴዎች ይበዙባቸዋል።

አስታማሚዎች ወይም ጠያቂዎች እንደልብ መንቀሳቀሳቸው ሌላው የኮቪድ ህክምና መስጫ ተቋሙ ላይ የተነሳ ቅሬታ ነው። ዶ/ር ሞቱማ ይህንን ከህክምና ባለሙያዎች እና ከታካሚዎች የቀረበ ጥያቄ ሲመልሱ “እኛ ሊፍት መውጫ እና መውረጃ ላይ ጥበቃ መድበናል” ይላሉ። “መዘናጋቱ የታየው በተቋሙ ቸልታ ሳይሆን ሕብረተሰቡ በሽታውን አቅልሎ በመመልከቱ ነው” እንደ ዶ/ር ሞቱማ ማብራሪያ የጥንቃቄ መመሪያዎችን የማይተገብሩ፣ ሊፍቱ በአንድ ጊዜ እንዲያጓጉዝ ከተፈቀደለት ቁጥር በላይ መጓዝ የሚፈልጉ ተገልጋዮች አምባጓሮ እስከመፍጠር የደረሱበት አጋጣሚ ብዙ ነው።

በአዳማ ከተማ ለኮቪድ 19 ታማሚዎች ህክምና ከሚሰጡ የግል ሆስፒታሎች መካከል “የመድህን ቤዛ ሆስፒታል” አንዱ ነው። የሆስፒታሉ ቴክኒካል ዳይሬክተር ሲስተር መቅደስ መርከቡ ያነሳነውን ርዕሰ ጉዳይ አስመልክቶ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ “በሆስፒታላችን የሚረዱ የኮቪድ ታማሚዎች የሚጠየቁት ክፍያ ከፍተኛ የሆነበት ምክንያት ለጤና ባለሞያዎች የሚቀርቡ መከላከያ መሳሪያዎች፣ የመድኃኒት፣ የህክምና ቁሳቁስ እንዲሁም የኦክስጅን ዋጋ መወደድን ጨምሮ እያንዳንዱ ባለሙያ በተሳትፎው እና በተጋላጭነቱ መጠን የሚታሰብለ ክፍያ ተደምሮ ነው” ብለዋል። በሕብረተሰቡ በኩል ያለው የግንዛቤ ማነስ የጥበቃ ሰራተኞችን ደብድበው ታማሚዎችን የመጎብኘት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እየበዙ መምጣታቸውን ታዝበዋል።

በሰራተኞች ደህንነት፣ ክፍያ እና የሕብረተሰብ ተጋላጭነት ጉዳይ ላይ ያነጋገርነው የመድህን ቤዛ ሆስፒታል ክሊኒካል ነርስ ናትናኤል ጥላሁን “ተጋላጭነትን ለመቀነስ አንድ ባለሙያ የኮቪድ ህክምና ክፍል የሚገባው በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ነው። አንድ ታካሚ ሲገባ የሚያስፈልገው የመከላከያ ማቴሪያል እና መድኃኒት ቀድሞ ስለሚወጣ በዚህ በኩል በጥሩ ሁኔታ እየሰራን ነው።” ብለዋል፡፡ 

በአዳማ ከተማ ጤና ቢሮ የቁጥጥር ክፍል ኃላፊ አቶ ሁሴን ሮባ በበኩላቸው ያነሳነውን ርዕሰ ጉዳይ አስመልክቶ ከአዲስ ዘይቤ የቀረበላቸውን ጥያቄ ሲመልሱ “የኮቪድ ታማሚዎችን ለይቶ የማከም አገልግሎት መሰጠት የሚገባው በመንግሥት ተቋማት ብቻ ነው። የግል ተቋማቱ አገልግሎቱን ለመስጠት ፈቃድ የላቸውም። ለግል ሆስፒታሎች ፈቃድ የመስጠት እና የቁጥጥር ስራው የሚሰራው በክልል ጤና ቢሮ ደረጃ ነው። እንደ ከተማው ጤና ጽ/ቤት ግን ጥቆማ ሲደርሰን ተከታትሎ ሪፖርት ማድረግ ግዴታ አለብን። እስካሁን ግን ምንም መሰል ጥቅማ አልደረሰንም።” ያሉ ሲሆን ለኮቪድ ታማሚ ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ተኝቶ ታካሚ የበሰለ ምግብ ማቅረብ ሆስፒታሎች ማሟላት ከሚገባቸው መስፈርቶች  መካከል እንደሆነ ተናግረዋል። ለሐኪሞችም ሆነ በሆስፒታሉ ውስጥ ለሚሰሩ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች መሟላት የሚገባቸውን ቁሳቁሶች የማሟላት ጉዳይ ግን ቅድሚያ የሚሰጠው ግዴታ መሆኑን በመንገር ሐሳባቸውን ደምድመዋል።

አስተያየት