እንኳን ለተወለዱባትና ለሃገሬው ለሚያውቃት ባዕድ የማይሻር ፍቅርና ትዝታ በልቦና ቀርፃ የምታስቀረው ድሬዳዋ የሚናፍቋት ሁሉ ሲገናኙ በናፍቆት የሚያነሱት አያሌ ርዕስ ይኖራቸዋል። አካባቢው፣ ከዚራ፣ ደቻቱ፣ ለገሃር፣ ጣፋጭ ምግቦቹ፣ የባቡር ጉዞው፣ ፍራፍሬው፣ የሰዉ ፍቅር፣ . . . ስንቱ ተነግሮ ያልቃል። የናፍቆት ድሬ አከባበር ሳምንት ከሃገር ውስጥና ከሃገር ውጪ ያሉ የድሬ ልጆችና ወዳጆች የተገናኙበት፣ ትዝታቸውን ያደሱበት፣ የከተማዋ ፈርጦች የተዘከበሩበትና የተሸለሙበት፣ ብቻ በአጭሩ የድሬ ናፍቆት አካል ሆኖና ገዝፎ የታየበት ክብረ በአል ነበር።
የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ወደ ድሬዳዋ የናፍቆት ጉዞ በማድረግ ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር መፍጠርና የከተማዋን መልካም ገፅታ መገንባትን ግብ አድርጎ ከሐምሌ 11 እስከ 16/2014 ዓ.ም የተከበረው ናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት የተለያዩ መርሀ-ግብሮች ደምቆ ተጠናቋል። አዲስ ዘይቤም በየእለቱ በቦታው በመገኘት ዝግጅቶቹ ምን ይመስሉ እንደነበር በዚህ መልኩ አጠናቅራለች።
ዝግጅቱ ናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንትን ለመታደም ከባህር ማዶ እና ከሀገር ቤት ለመጡ እንግዶች ይፋዊ 'እንኳን ደና መጣችሁ' አቀባበል በድሬዳዋ ቤተ መንግስት በማድረግ ነበር የተጀመረው። የድሬዳዋ ቤተ መንግስት በአረቢክ የቤት አሰራር ዲዛይን በአፄ ኃ/ስላሴ አባት በራስ መኮንን የተገነባ ሲሆን 'የሰላም አዳራሽ' የሚል ስያሜም ተሰጥቶት ነበር። ሐምሌ 10 ምሽት ላይ በዚሁ አዳራሽ በተደረገው የእራት ግብዣ፤ ከረዥም ዓመታት በኋላ የድሬዳዋ ወዳጆችና ተወላጆች በናፍቆት ተገናኝተው በአንድ ማዕድ ቆረሱ።
በእራት ግብዣው ላይ ብዙዎችን ያስደሰተው ሌላኛው ክስተት የገጣሚ የሲሳይ ዘለገሀሬ የእውቅና ሽልማት ነበር። በግጥሞቹ ስለ ድሬዳው የሚቀኘው ገጣሚ ሲሳይ ዘ ለገሀሬ 'ለፍቅራችሁ' የተሰኘ የግጥም መድብል ከአመታት በፊት አሳትሟል። በተጨማሪም አጫጭር የሬዲዮና የቴሌቪዥን ድራማዎችን ይፅፋል። ድሬዳዋ ውስጥ በሚዘጋጁ የስነ ጥበብ መድረኮች ላይ የግጥም ስራዎቹን በማቅረብ ስፊ እውቅናና ተወዳጅነትን አትርፏል።
የድሬዳዋ አስተዳደር አቶ ከድር ጁሀር በቀጣይ እጣ ከሚወጣባቸው ባለ ሁለት መኝታ ኮንደሚኒየም ቤቶች መካከል ቅድመ ክፍያው በአስተዳደሩ የሚሸፍን ሆኖ ለሲሳይ ተሰጥቷል። የድሬዳዋ ሲሚንቶ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ብዙአየሁ ሙሉ ወጪውን ለመሸፈን፤ የበዓሉ አስተባባሪዎችም ደግሞ የቤት እቃ ሊያሟሉልት ቃል ገብተዋል። ቢጂአይ ኢትዮጵያም የሲሳይ ዘ ለገሀሬን ሁለተኛ የግጥም መድብል ለማሳተም ቃል ገብቶለታል።
ሲሳይም ሽልማቱን ላበረከቱለትና ከጎኑ ሆነው ሲደግፉት ለነበሩ ሁሉ ምስጋናውን አቅርቦ “ከቃል በላይ ተግባራዊ ምላሽ ለምስጋና አቅም ያሳጣል። ከኔ በላይ በሆነልኝ ሁሉ ለተደሰታችሁ ቃሌ ምስጋና ብቻ ነው” ሲል ስሜቱን ገልጿል።
ቀን አንድ- ሰኞ- የፍቅር ቀን
ናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት የመጀመሪያው ቀን 'የፍቅር ቀን' የሚል ስያሜ ከለገሀር እስከ ለገሀሬ የእግር ጉዞ፣ የፎቶ ኤግዚቢሽንና የሙዚቃ ኮንሰርት ተካሂዶ ነበር። ሶስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የእግር ጉዞ መነሻዉን ከጥንታዊቷና ከዚራ አድርጎ መድረሻ ለገሀሬ። በተለያዩ የሰርከስ ትርኢቶችና በማርሽ ባንድ የታጀበው ጉዞ በከዚራ ጥላው ስር፣ በኮኔል ድልድይ አድርጎ፣ ብዙዎች ጣፋጭ ትዝታ ባሳለፉበት አል ሀሽም ባቅላባ መንደር አልፎ፣ በታዋቂው ጁመዓ መስኪድ ወደ ለገሀሬ ደረሰ። እንግዶቹም በየደረሱበት ቆም እያሉ ትውስታቸውን እየተጨዋወቱ እና በመንገድ ላይ ከወዳጅ ከዘመድ ጋር እየተገናኙ በሳቅና በጨዋታ የእግር ጉዞውን አጠናቀዋል።
ከሰዓት በኋላ በነበረው ዝግጅት ደግሞ በዙዎች ፈረንሳይኛ ቋንቋን በተማሩባት አልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ ግቢ ውስጥ የፎቶ እና የስዕል ኤግዚቢሽን ተሰናዳ። በካሱ ኪዳኔ የተዘጋጀው 'ዝክረ እስክንድር ፒካሶ' የተሰኘ መታሰቢያነቱ ለሰዓሊ መርዕድ ወርቁ የሆነ ይህ የፎቶ እና የስዕል ኤግዚቢሽን ለእለቱ የመጨረሻ ዝግጅት ነበር። በአልያንስ ኢትዮ-ፍራንሲስ፣ በድሬዳዋ ባህልና ቱሪዝም እና በፓቭሊዮን ህትመት ድርጅት ጋር በትብብር የተዘጋጀው የድሬዳዋን ጥንታዊ ታሪክ የሚያሳይ የስዕል ኤግዚቢሽን ነበር፡፡
ድሬዳዋ ያፈራችው ሰዓሊ መርዕድ ወርቁ (1950~1998 ዓ.ም) ግሩም የሆኑ የስዕል ስራዎችን ያበረከተ ሲሆን፤ ይህ ችሎታው መርዕድ የሚለውን ስሙን በታዋቂው ሰዓሊ ፓብሎ ፒካሶ ስም እስከመጠራት አድርሶታል። ሰዓሊ መርዕድ (ፒካሶ) በህይወት በነበረት ጊዜ የሳላችው የስዕል ስራዎች በእለቱ ቀርበው ከጎብኚዎች አድናቆትን አግኝተዋል።
ቀን ሁለት- ማክሰኞ- የስፖርትና ባህል ቀን
የናፍቆት ድሬዳዋ ሳምንት ሁለተኛው ቀን 'የባህልና ስፖርት ቀን' በመባል ተሰይሞ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ተካሄደውበታል። በእለቱ ከጠዋቱ 12 ሰዓት የስፖርት ውድድሮች መካሔድ የጀመሩ ሲሆን የመጀመሪያው ውድድር ድሬዳዋ የምትታወቅበት የብስክሌት ውድድር ነበር።
ከቀድሞዎቹ ብስክሌተኞች እስከ ታዳጊዎቹ ያሳተፈው የብስክሌት ውድድር የተመልካችን ቀልብ የሳበ ነበር። በአዝናኝ ትዕይንቶች የታጀበው የብስክሌት ውድድር ይበልጥ አጓጊነቱን የጨመረው በአጋፋዎቹ ብስክሌተኞች በጀማል ሮጎራና በዮሃንስ ቪክቶርዮ ፍጥጫ ነበር። ውድድሩን ዮሃንስ አንደኛ ሲወጣ ጀማል ተከትሏል። በወጣቶች የብስክሌት ውድድር የቀድሞው አንጋፋው ብስክሊተኛ የጀማል ሮጎራ ልጅ ኪያ አሸናፊ ሆኗል።
በስፖርቱ መርሃ ግብር ቀን ከ 10 ሰዓት ጀምሮ በድሬዳዋ ስታድየም በዙዎች በጉጉት ሲጠብቁት የነበር የእግር ኳስ ጨዋታ ተካሄዷል። በ1980ዎቹ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ስመ ገናና የነበሩት የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ እና ምድር ባቡር የእግር ኳስ ቡድኖች ዳግም በናፍቆት ድሬዳዋ ሳምንት ከዘመናት በኋላ ተጋጥመዋል።
በጨዋታው ላይ በድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ በኩል የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ኮከብ ተጫዋች የነበረው ዮርዳኖስ አባይን ጨምሮ ሀብታሙ ግርማና የድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ የእግር ኳስ ክለብ መስራች ከሆኑት አንዱ ተሾመ ሀይሌ የሚገኙበት ሲሆን ግብ ጠባቂያቸው ደግሞ ዳዊት ለገሰ ነበር።
የድሬዳዋ ስፖርት አፍቃሪዎችን በትዝታ ወደ ኋላ በመለሰው በዚህ ጨዋታ በድሬዳዋ ምድር ባቡር ቡድን በኩል ደግሞ ታዋቂዎቹ እነ አህመድ ዝያድ (ጁዲ)፣ ተስፋ ግደይ፣ ዳዊት ለገሰና መስፍን ታደሰ የተሰለፉ ሲሆን አድላቸው ፍቅሩ በረኛ ነበር።
ተመልካቾቹን አዝናኝ በነበረው ጨዋታ በምድር ባቡር ቡድን 3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በቦታው የነበሩትን ታዳሚዎች በቀድሞ ጊዜ የነበረውን የድሬዳዋን የስፖርት ስኬት በማስታወስ በቁጭት ያነጋገረ ሁኔታም ፈጥሮ ነበር።
የምድር ባቡርን የመጀመሪያዋን ጎል ያስቆጠረው አህመድ ዚያድ (ጁዲ) “በፊት ከኮተኒ(ከጨርቃ ጨርቅ) ጋር ስንጫወት አብዛኛውን ጊዜ ኮተኒ ያሸንፍ ስለነበር በደንብ ተዘጋጅተን ነው የመጣነው። የበፊቱን ፉክክር አሁንም ደግመነዋል” ሲል ተናግሯል፡፡
በመቀጠል የተካሄደው የድሬዳዋ ከፍተኛ አመራሮች ከሀረር ክልል አቻዎቻቸው ጋር ብርቱ ፉክክር የታየበት አዝናኝ ግጥሚያ ነበር። ጨዋታውን የሀረሪ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ሶስት ለባዶ በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።
አቶ ንጉሴ ውቃው በምድር ባቡር ኩባንያ በጡረታ ምክንያት ስራ እስካቆሙበት ጊዜ አገልግለዋል። በወቅቱ ስለነበረው የእግር ኳስ ሁኔታ ሲገልፁ “በደጋፊ ደረጃ በጣም ተፎካካሪ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ምድር ባቡር ኩባንያ እና ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የእግር ኳስ ክለቦች ነበሩ። ከተማዋን ለሁለት ይከፍላት የነበረው ሁለቱ የእግር ኳስ ክለቦች ጨዋታ በነበራቸው ጊዜ ነው። አብዛኛው የአዲስ ከተማ እና ደቻቱ ሰፈር ሰዎች የኮተኒ ደጋፊ ሲሆኑ ከዚራ፣ ዲፖ፣ ኮኔል የመሳሰሉት የምድር ባቡር አሻራ ያረፈባቸው ሰፈሮች ደግሞ የምድር ባቡር ደጋፊ ነበሩ” ሲል ትውስታውን አጋርቷል፡፡
በጨዋታው ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በንግግራቸው ለድሬዳዋ ከነማ ተጫዋች ለመሆን ለከተማዋ ታዳጊዎች ቅድሚያ በመስጠት እግር ኳሱን ለማነቃቃት ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡
ቀን ሶስት- ዕሮብ- የባቡር ቀን
በእለተ ረቡዕ “ባህል ጥበብና ስልጣኔ በድሬዳዋ ከየት ወዴት” በሚል መሪ ቃል በካፒታል ሆቴል የፓናል ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ ከውጪ የመጡና በከተማዋ የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጀች የተገኙ ሲሆን፤ ከመካከላቸውም አምባሳደር መሀሙድ ድሪር እንዲሁም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ንግግር አድርገዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑት በአሜሪካ ሂዩስተን ቴክሳስ የሚኖሩ የከተማዋ ተወላጆችና ወዳጆች ለህፃናት ማሳደጊያ መዕከል እና ለህክምና ተቋማት የሚውል ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ አበርክተዋል።
የናፍቆት ድሬዳዋ ሳምንት ላይ ለመታደም ከቴክሳስ አሜሪካ የመጡት ወ/ሮ አዜብ እና ቤተሰቦቻቸው በድሬዳዋ እየተገነባ ለሚገኘው የኩላሊት ዕጥበት ህክምና ማዕከል ከ 10 ሺ ዶላር በላይ የሚያወጡ የህክምና ቁሳቁሶች አስረክበዋል። ከህክምና ቁሳቁሶቹ መካከል 400 ለህክምና አገልግሎት ስራ የሚያስፈልጉ የመከላከያ መነፅሮች፣ 400 የፊት መሸፈኛ የህክምና ጭንብሎች፣ 200 መስታወት መሰል የፊት መካከያ 'ፌስ ሼልድስ' እና መስል ቁሳቁሶቹ ይገኙበታል።
በዚሁ ቀን ከሰዓት በኋላ በ'ኦተራይ' ባቡር ለመንሸራሸር የከጀሉ ዲያሰፖራዎችና የድሬዳዋ ነዋሪዎች ሰበሰብ በለው ልክ 10 ሰዓት ሲል ከድሬዳዋ እስከ ሺኒሌ ጉዞ ለማድረግ ተንቀሳቀሱ። የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተርም አብራ ተጉዛለች። አብዛኞቹ ተጓዦች ወደኋላ ተመልሰው የባቡር ትዝታቸውን መጨዋወት ጀመሩ። ብዙም ሳይቆዩ “ሸፍተራን መጣ ሻግ ሻግ” በመባባል የጥንቱን የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች እና የፍተሻ ትቆጣጣሪዎችን ግብግብ አስታወሱ።
በተለይ አንዲት ተሳታፊ “ፉርጎ ስር የደበቅሽ እያንዳንድሽ፤ ኮትሮባንድ የያዝሽ ያለትኬት የገባሽ ወጣ ወጣ” እያለች ጮክ በላ ስትናገር በባቡሩ ውሰጥ የነበረው ህዝብ በሳቅና በጭብጨባ ተቀበላት። አንዳንዶች ከረዥም ጊዜ በኋላ ከናፈቁት ወዳጅ ዘመድ ጋር እዚሁ ባቡር ላይ ተገናኝተዋል።
ከ30 ዓመታት በላይ ተለይተው በዚህ ባቡር ላይ እንደተገናኙ ያጫወቱንም ነበሩ። የባቡር ላይ ነጋዴ እንደነበሩና እንደዚህ ተለያይተው የሚቆዩ የማይመስላቸው ጓደኛሞች ሲሁኑ “ኦተራይ መልሳ አገናኝታናለች” ብለዋል። ወ/ሮ አሰፉ ከመካከላቸው አንዷ ስትሆን ልባሽ ጨርቅ (ሰልባጅ) በመሸጥ ትተዳደር ነበር። ወ/ሮ አሰፉ “ለበርካታ የድሬዳዋ ነዋሪዎች የኑሮ መሰረት የነበረው የባቡር ትራንስፖርት አትክልቶች፣ ሰልባጅ፣ የታሸጉ ምግቦች፣ ዘይት በአጠቃላይ ገቢና ወጪ የሚደረጉ እቃዎች እንዳለ በባቡር ነበር የሚመላለሰው” ስትል አስታውሳለች።
እንደ ወ/ሮ አሰፉ አባባል በጊዜው ባቡር ሲያርፍ ውሀ፣ ሙጠበቅ፣ ሳንቡሳ፣ ቆሎ የመሳሰሉትን ነገሮች ትሸጥ እንደነበር ትናገራለች። የምትሸጠው ነገር ባጣች ወቅት ደግሞ “በስፋት ነጋዴዎች ይመላለሱበት የነበረው 'ሀሰን ጆግ' እና 'ኦተራይ' የሚባሉ ባቡሮች ስላሉ ልክ ነጋዴዎች እቃቸውን ሲያወርዱ እቃ ለ10 እና 15 ደቂቃ በመጠበቅ ብር እናገኝ ነበር። ለብዙ ሰው ስለምንጠብቅ ገበያው የደራ ነው። ሌላው ደግሞ ሰልባጅ ልብሶችን ደራርበን እንለብስላቸዋለን ወይንም ይዘንላቸው ሮጠን ፊላንሶች ሳይመጡ እናሳልፍላቸዋለን ለዚህ ደሞሞ 50 ብር ይከፍሉን ነበር። ይህንንም ስራ በቋሚነት እየሰሩ በዚህ ብቻ ይተዳደሩ የነበሩ ብዙዎች ነበሩ” ስትል ትውስታዋን አካፍላናለች። ዳግም በኦተራይ መንሸራሸር በመቻሏም መደሰቷን ተናግራለች።
በሳቅና በጨዋታ የደመቀው የኦተራይ ባቡር ጉዞ ከድሬዳዋ ሽኒሌ ደርሶ ተመለሰ። በባቡር የተንሸራሸሩት እንግዶችም 'ሼመንደፈር' አጠገብ ለገሀር አደባባይ የናፈቁትን የያዘው ባዛር ጠበቃቸው። ባዛሩ ላይ የተለያዩ ጣፋጭ ምግቦችን እና ባህላዊ አልባሳትን የያዘ ነበር።
ከአስር አመት በላይ በአሜሪካ ቆይታ የመጣችው ወ/ሮ እየሩስ ባቅላባ እና ሙሸበክ እየገዛች አገኘናት። ወ/ሮ እየሩስ ሰሊጥና ሙጀርጀር ስታገኝ በደስታ ፈንድቃ ለአዲስ ዘይቤ በሰጠችው አስተያየት “በጣም ደስ ብሎኛል፤ በፊት የተማርኩት 'ልዑል መኮንን' እየተባለ በሚጠራው ምስራቅ ጀግኖች ት/ቤት ነበር። እና ከትምህርት ቤት ስመለስ ሰሊጥና አላሊ ሳልበላ አልመለስም። እነዚህን ጣፋጭ ምግቦች በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ” ስትል ተናግራለች።
በባዛሩ ላይ የድሬዳዋ አንዱ ምልክት የሆነው የአል-ሀሺም ጣፋጭ ምግቦች (ሀለዋ፣ ባቅላባ፣ ሙሸበክ፣ ሙጀርጀር)፣ ልዩ የሆነው የድሬዳዋ እጣን፣ ጊሽጣ፣ ሮቃ፤ አንጎራ የመሳሰሉ ፍራፍሬዎች እንዲሁም በብዛት በድሬዳዋ የሚገኘው ደረቅ ቴምር የመሳሰሉት ይገኙበት ነበር።
ቀን አራት- ሀሙስ- የቤተሰብና የበጎ ፈቃድ ቀን
የናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት አራተኛው ቀን የቤተሰብ ቀን የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። በዚህም ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው በመምጣት ከኤሌክትሮኒስ ነፃ የሆነ ቀን የሚያሳልፉበት፤ የደም ልገሳ የሚያካሄዱበት፣ ድሬዳዋ ልጆቿን የምታመሰግንበት 'የምስጋና' ፕሮግራሞች ተካሄደዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ለከተማዋ እድገትና ልማት ከፍተኛ አስተዋፆ አድርገዋል ለተባሉ ግለሰቦች በስማቸው የመታሰቢያ ቦታ ተሰይሞላቸዋል።
በ 2000 ዓ.ም የተመረቀው ሚሊኒየም ፓርክ የድሬዳዋ ፈርጥ ለሆነው አንጋፋው ድምፃዊ አሊ መሐመድ ሙሳ (አሊ ቢራ) መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በስሙ ተሰይሞለታል። አሊ ቢራ ግንቦት 18 በ1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ልዩ ስሙ ቀንደቆሬ እየተባለ በሚጠራው ሰፈር ተወለደ። በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጎልቶ ከሚነሱ አንጋፋ ድምፃዊያን መካከል አንዱ ነው። በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ያቀነቀነ ሲሆን በኦሮምኛ፣ በአማርኛ፣ በአረብኛ፣ በአደርኛ እና ሶማለኛ ቋንቋዎች ሙዚቃን መጫወቱ ልዩ ያደርገዋል። አሊ ቢራ በአጠቃላይ ከ 260 በላይ ዘፈኖችን ተጫውቷል።
የኦሮሞን ባህል ለማስተዋወቅ የተመሰረተውን 'አፍረን ቀሎ' የተባለውን የሙዚቃ ቡድን የተቀላቀለው ገና የ14 አመት ታዳጊ እያለ ነበር። የአሊ ቢራ የሙዚቃ ህይወት የተጀመረውም እና 'አሊ ቢራ' የተሰኘውን ስሙን ያገኘውም ከዚሁ አፍረን ቀሎ ከተባለው የሙዚቃ ቡድን ጋር ባዜመው 'ብራን በሪኤ' በተሰኘው ዘፈን ነው።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር አርቲስት አሊ ቢራ ለህዝብ ነፃነት እና እኩልነት ትግል ማድረጉንና ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎችን ማበርከቱን ገልፀዋል። ይህ ፓርክ በስሙ መሰየሙም የሚያንስበት መሆኑን ተናግረዋል። በእለቱም ክቡር ዶ/ር አርቲስት አሊ ቢራና ባለቤቱ ክብርት ሚስስ ሊሊ ማርቆስ፣ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችና የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡
ከአርቲስት አሊ ቢራ በተጨማሪ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ድሬደዋ ከተማን የመሩት ከንቲባ አልፍሬድ ሻፊ በስራ ዘመናቸው ወቅት ያሰሩት ድልድይ ታድሶ በስማቸው ተሰይሟል። የድሬዳዋ ትልቁ ድልድይ ከከዚራ ወደ ኮኔል የሚያሻግረው በተለምዶ ደቻቱ ድልድይ በመባል የሚጠራ ነው። ከተማዋን ለሁለት በሚከፍለው የአሽዋ ገደል ላይ የተሰራው ድልድይ ነው። በቀድሞ ዘመን የድሬዳዋ አውራጃ አገረ ገዥና አስተዳደር በነበሩት ከንቲባ አልፍሬድ ሻፊ የተሰራ ድልድይ ስለሆነ በስማቸው እንደተሰየመ ተገልጿል፡፡
በእለቱ የናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት የቤተሰብ ቀን በመሆኑም በአሊቢራ ፓርክ ለልጆች የሚሆን 'ኑ ጭቃ እናቡካ' በሚል ስያሜ የልጆች የመዝናኛ ዝግጅት ተካሂዶ ነበር። በቦታው የተገኙ ህፃናትም በጭቃ የተለያዩ ቅርፃቅርፅ በመስራት፣ በቀለም ስዕሎችን በመሳል፣ ጥጥ በመፍተል እና የተለያዩ ጨዋታዎችን በመጫወት ከኤሌክትሮኒክስ ነፃ የሆነ ቀን ማሳለፍ ችለዋል።
በቦታው ከልጇ ጋር ጭቃ እያቦካች ጀበና ስትሰራ ያገኘናት ወ/ሮ ህይወት ዋለልኝ እንደነገረችን “እንደዚህ አይነት ፕሮግራም በመዘጋጀቱ በጣም ደስ ብሎኛል። እንደዚህ አይነት ዝግጅት ቢያንስ በወር ሁለት ጊዜ ቢኖር ልጆቻችን ከተፈጥሮ ጋር እየተገናኙ የሚጫወቱበት ቦታ እናገኝ ነበር” ስትል አስተያየቷን ገልፃለች፡፡ የደም ልገሳና የሰርከስ ትርዒት ዝግጅትም የፕሮግራሙ አካል ነበሩ።
ቀን አምስት - አርብ- የምስጋናና የሽልማት ቀን
የናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት የመጨረሻ መርሀግብር የነበረው የምስጋናና ሽልማት ቀን ነበር። ፕሮግራሙ አርብ ሐምሌ 15/2014 ዓ.ም በራስ ሆቴል መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄዷል። የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 'ለናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት' ዝግጅት መሳካት አስተዋፅዖ ላደረጉ ግለሰቦች፤ ድርጅቶች፣ ዲያስፖራዎችና የመንግስት ተቋማት ምስጋናና ሽልማት አበርክቷል።
እንደ ዝግጅቱ አስተባባሪዎች ገለጻ ናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት ዝግጅት ላይ ለመታደም ከ 450 በላይ የድሬዳዋ ተወላጆች የሆኑ ዲያስፖራዎች ከባህር ማዶ መምጣታቸውን፤ በሀገር ቤት ደግሞ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚኖሩ ከ 500 በላይ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ተገኝተዋል። ናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት በቀጣይንት በዓመቱ ለማክበር እንደታሰበ ቀደም ሲል አዲስ ዘይቤ መዘገቧ ይታወሳል።