ሐምሌ 20 ፣ 2014

በኢትዮጵያ የደም ባንኮች ከፍተኛ የደም እጥረት ተከስቷል

ዜናማህበራዊ ጉዳዮች

ከክረምቱ በተጨማሪ ሰላምና መረጋጋት የሌለባቸው እንደ ወለጋ እና ጋምቤላ ክልል ያሉ አካባቢዎች የደም ፍላጎታቸውን አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋና ቢሮ ማሟላታቸው ፍላጎት እና ልገሳው እንዳይመጣጠን አድርጎታል

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

በኢትዮጵያ የደም ባንኮች ከፍተኛ የደም እጥረት ተከስቷል
Camera Icon

ፎቶ፡ ሚድል ኢስት ሞኒተር

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተፈጠረው የደም እጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን አዲስ ዘይቤ ከብሔራዊ ደም ባንክ እንዲሁም የክልል ቅርንጫፎች አረጋግጧል። አዲስ ዘይቤ በአዲስ አበባ ከሚገኘው የብሔራዊ ደምና ቲሹ ባንክ፣ ከአዳማ፣ ከጎንደር እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማ የደም ባንኮች በሰበሰብው መረጃ መሰረት በአሁን ወቅት ከአምስት ቀናት እስከ አንድ ሳምንት ብቻ የሚበቃ የደም ክምችት እንዳለ ማወቅ ተችሏል።

የብሔራዊ ደምና ቲሹ ባንክ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐብታሙ ታዬ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፁት በዋናው መስሪያ ቤት ያለው ክምችት ከአምስት ቀናት በላይ የሚያዘልል አይደለም። ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የእጥረቱን መንስኤዎች ሲያስረዱ “የክረምት ጊዜ መሆኑና ወቅቱ ለለጋሾች እንቅስቃሴ ምቹ አለመሆኑ፣ ወጣቶች ላይ መሰረት ተደርጎ በትምህርት ቤቶች በስፋት የሚከናወነውም የደም ስብሰባ በተማሪዎች እረፍት መቀነሱ እንዲሁም ደም የሚያስፈልጋቸው የህክምና ተቋማት ቁጥር መጨመር” ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል።

በአዲስ አበባ ብቻ ከ100 በላይ የደም ህክምና የሚሰጡ ተቋማት አሉ ያሉት አቶ ሀብታሙ እጥረቱን ለመፍታት ያለመ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል። “በቀይ መስቀል ቅጥር ግቢ፣ በብሔራዊ ደም ባንክ መስሪያ ቤት እንዲሁም በሁሉም ክፍለ ከተማዎች ድንኳን በመጣል በድምሩ በ13 ቦታዎች ላይ ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ጋር በመተባበር የጎዳና ላይ ደም ስበሰባ እየተከናወነ ነው” ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት በአማካይ በቀን 250 ዩኒት ደም እየተሰበሰበ ሲሆን በመደበኛ ጊዜ ወይም ከክረምት በፊት ይሰበሰብ ከነበረው በግማሽ የቀነሰ ሲሆን በቀን በአማካይ ከ400 እስከ 500 ዩኒት (ከረጢት) ደም ይሰበሰብ ነበር።

እንደ ኃላፊው ገለፃ ከክረምቱ በተጨማሪ ሰላምና መረጋጋት የሌለባቸው እንደ ወለጋ እና ጋምቤላ ክልል ያሉ አካባቢዎች የደም ፍላጎታቸውን አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋና ቢሮ ማሟላታቸው ፍላጎት እና ልገሳው እንዳይመጣጠን አድርጎታል። አዲስ ዘይቤ ቅኝት ያደረገበት የአዳማ ከተማ ደም ባንክም ከፍተኛ የደም እጥረት እንዳጋጠመው ገልጿል። የአዳማ ደም እና ቲሹ ባንክ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ከተማ ደቀባ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፁት "በደም ባንኩ አሰራር አነስተኛ እና የማስጠንቀቂያ ክምችት ተብሎ የሚታወቀው 200 ከረጢት ደም መጠን ሲሆን አሁን ግን በባንኩ ያለው የደም መጠን ከ70 ከረጢት ደም አይበልጥም” ብለዋል።

በአሁን ወቅት በኦሮሚያ ከሚገኙት ቅርንጫፎች ትልቁ ቅርንጫፍ ባንክ ያለው ክምችት ከመጠባበቂያ ክምችቱ አንድ አራተኛ ብቻ እንደሆነም ጠቅሰዋል። "ዛሬ የሰበሰብነውን ነገ ለሆስፒታሎች እያከፋፋልን ነው። እርሱም በሚፈለገው ደረጃ አይደለም" ያሉት ስራ አስኪያጁ አቶ ከተማ ደቀባ የአዳማ ደም እና ቲሹ ባንክ ቅርንጫፍ ከፍተኛ የደም ለጋሾች ቁጥር ያገኝ የነበረው በት/ቤቶች እንደነበር አስታውሰው ክረምት ከመሆኑ ጋር የትምህርት ቤቶች መዘጋት የለጋሾች ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጉን ይገልጻሉ። መንግስት በአሁን ወቅት ለደም የሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው የሚሉት አቶ ከተማ “የተፈጠረውን እጥረት ለመፍታት ወደ ተለያዩ የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች ብንቀሳቀስም አጥጋቢ ምላሽ አላገኘንም" ብለዋል። 

የአዳማ ደም እና ቲሹ ባንክ ከ6 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ለሆኑ ሰዎሽ አገልግሎት የሚሰጠውን የአዳማ ሆስፒታልን ጨምሮ የመንግስቶቹን የአሰላ፣ የሞጆ፣ የቢሾፍቱ፣ የወለንጪቲ፣ የመተሐራ ሆስፒታሎችን እንዲሁም በአዳማ እና አካባቢዋ ለሚገኙ 36 ከፍተኛ የጤና ተቋማት ደም የሚያቀርብ ቢሆንም በደም እጥረቱ ምክንያት እንደሚፈለገው የደም አቅርቦቱን እያደረሰ አይደለም።

የጎንደር ደም ባንክ አገልግሎት ሃላፊ አቶ ደመቀ ጥላሁን በበኩላቸው ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ ለአንድ ሳምንት የሚያገለግል 460 ዩኒት ደም ብቻ እንዳላቸው ገልጸው ከሳምንት በኋላ እጥረቱ እንደሚከሰት አስረድተዋል።

አቶ ደመቀ እንደሚሉት 90 በመቶ የሚሆኑ በየተቋማቸው ደም ሲለግሱ የነበሩ ተማሪዎች አሁን ላይ ትምህርት በመዘጋቱ የደም ለጋሾች ቁጥር ቀንሷል። “ባለፉት ሁለት አመታት የደም እጥረት ተከስቶ አያውቅም ነበር” የሚሉት ሃላፊው “በዘንድሮው ዓመት በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ካሉ በጎ ፈቃደኞች ከሐምሌ 01-18 2014 ዓ.ም ድረስ 800 ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን” ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።

ለጎንደር ከተማ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች በአማካኝ 15 ሺህ ዩኒት ደም ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ደመቀ ጥላሁን በቀን 50 ዩኒት ደም ይሰበሰባል ተብሎ ቢታቀድም ከ20 ዩኒት በታች ደም እየሰበሰቡ እንዳሉ ተናግረዋል። የቅርንጫፍ ኃላፊው በጎንደር ከተማ የደም ባንክ ቅርንጫፍ ደም ለመሰብሰብ ከፍተኛ የሆነ የመመርመሪያ ማሽን ችግር እንዳለ ጠቁመው በአጠቃላይ በጎንደር ደም ባንክ አገልግሎት 460 ዩኒት ደም ብቻ መኖሩን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

ሌላው በጉዳዩ ላይ አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው በድሬዳዋ አስተዳደር የደም ባንክ አስተባባሪ አቶ ፋሲል ዘውዴ እንደሚያስረዱት በድሬዳዋ አስተማማኝ የደም ክምችት የለም። አቶ ፋሲል ዘውዴ እንደነገሩን ከዚህ ቀደም ከ250 እስከ 300 ዩኒት የደም ክምችት የነበረው የድሬዳዋ የደም ባንክ በአሁን ሰዓት ያለው ከ60 እስከ 70 ዩኒት የደም ክምችት ብቻ ነው።

እንደ አቶ ፋሲል ገለፃ በክረምት ወራት በአብዛኛው የደም እጥረት እንደሚያጋጥምና እንደምክንያትነት የሚጠቀሰው ወጣቶች በብዛት የሚገኙባቸው እንደ ዩኒቨርስቲዎችና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ዝግ መሆን እና በተጨማሪም ተቋማት በክረምት ወቅት ደም ለማሰባሰብ ያላቸው ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆኑ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የአየር ንብረቱ ቀዝቃዛና ዝናባማ በሚሆን ጊዜ ሰዎች ደም የመስጠት ፍላጎታቸው ይቀንሳል ብለዋል። አቶ ፋሲል ይህንን ችግር ለመቅረፍ በጋራ መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም እንደ ሁርሶ ኮንቲንጀንት ባሉ ወታደራዊ ተቋማት በመሄድ ደም የማሰባሰብ ስራዎችን ጀምረናል ሲሉ ገልፀዋል። 

ከባንኮቹ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው የደም ህክምና በሚሰጡ ተቋማት በአማካይ አንድ ታካሚ እስከ ሶስት ከረጢት ደም ይጠቀማል። ከወራት በፊት በነበሩት ሁለት ታላላቅ ሐይማኖታዊ አጽዋማት ምክንያት ከፍተኛ የደም እጥረት አጋጥሞ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ከአጽዋማቱ መፈታት በኋላም በአንዳንድ አካባቢዎች በመርመሪያ ቁሳቁሶች እጥረት የደም እጥረት ማጋጠሙን አዲስ ዘይቤ መዘገቧ ይታወሳል።

አዲስ ዘይቤ ያነጋገራቸው የብሔራዊ ደምና ቲሹ ባንኮችና የቅርንጫፍ ኃላፊዎች ህብረተሰቡ በደም ልገሳ ሰብዓዊ ተግባር ተረባርቦ የሰዎችን ህይወት እንዲያድን ጥሪ አቅርበዋል።

አስተያየት