ሐምሌ 19 ፣ 2014

ጥንታዊው የ 'ጪጩ' ገብርኤል ገዳም

City: Hawassaባህል ቱሪዝም

በደቡብ ኢትዮጲያ ጌዲኦ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ጥንታዊ ገዳማት መካከል አንዱ የ 'ጪጩ' ገብርኤል ገዳም ነው። በተራራ አናት ላይ የተመሰረተው ገዳም ከ 80 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ጥንታዊው የ 'ጪጩ' ገብርኤል ገዳም
Camera Icon

ፎቶ፤ ከማህበራዊ ሚዲያ

ከጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ በ 4 ኬ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘዉ እና በደን የተከበበዉ  የ 'ጪጩ' ገብርኤል ገዳም በአካባቢው የመጀመሪያው የእምነት ተቋም እንደሆነ ይነገራል። በ1933 ዓ.ም የተቋቋመው 'ጪጩ ገብርኤል ገዳም' በሺዎች በሚቆጠሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ይጎበኛል። በተለይ ታህሳስ 19 እና ሐምሌ 19 በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረውን አመታዊውን የንግስ በዓል ለማክበር ከተለያዩ ቦታዎች ምዕመናኑ ወደ 'ጪጩ' ገብርኤል ገዳም ኃይማኖታዊ ጉዞ ያደርጋሉ። 

ገዳሙ 'ጪጩ' የሚለውን ስያሜ ያገኘዉ በአካባቢው በሚኖሩት ከጌዴኦ ብሔረሰብ ዘንድ ነው። 'ጪጩ' ለወተት መያዣነት የሚያገለግል አነስተኛ እንስራ ሲሆን፤ ቀደም ሲል በአካባቢው ይመረት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዚህም መነሻነት የገብርኤል ገዳም በአካባቢው መሰራቱን ተከትሎ ስያሜዉ በዚያው ሊፀና መቻሉን የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መመሪያ የመረጃና ፕሮሞሽን ባለሞያ የሆኑት አቶ ዳንኤል ከተማ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። ባለሙያው አቶ ዳንኤል እንደሚሉት ለቤተክርስቲያኑ መመስረት እና  የኦርቶዶክስ እምነት በአካባቢው እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ ከነበራቸዉ መካከል ማሩ አባ (አባ ማሩ) አንዱ ነበሩ። 

ከሐዋሳ ከተማ 90 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘዉ የዲላ ከተማ በተፈጥሮ ሀብቶቿ በተለይም በቡና፣ እንሰትና ፍራፍሬ የታደለች ናት። ዲላ የጌዲኦ ዞን አስተዳደር ዋና መቀመጫ ስትሆን፤ ስፊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት ከተማ ነች። ታዲያ በየአመቱ ታህሳስና ሐምሌ 19 የገብርኤል ክብረ በዓልን በጪጩ ገብርኤል ገዳም ለማክበር በዙዎች ወደ ከተማዋ ከዋዜማው ጀምሮ ይገባሉ። 

የጌዲኦ ዞን አጎራባች ከሆኑት ከሲዳማ ክልል፣ ከኦሮሚያ ከጉጂና ቦረና ዞኖች በዓሉን ለመታደም ምዕመናን ይመጣሉ። በተለይም ከይርጋጨፌ፣ ከያቤሎ፣ ከአለታ ወንዶ፣ ከተፈሪ ኬላ፣ ከሻኪሶ፣ ከቡሌሆራ እና መሰል በቅርብ ርቀት ካሉ ከተሞች ወደ ጪጩ የገብርኤል ገዳም ይጓዛሉ። አካባቢዉ ካለዉ መልክአ ምዕድራዊ አቀማመጥ አንፃር የጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን ከጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የተገኘዉ መረጃ ያሳያል። 

ከሲዳማ ክልል በንሳ ዳዬ ወረዳ የገብርኤል ክብረ በዓልን ለመታደም መምጣቷን የነገረችን ወ/ሪት መንበረ አስራት ዘንድሮ በዲላ በዓሉን ስታከበር ለአራተኛ ጊዜ እንደሆነም ታስታውሳለች። “ከዲላ ከተማ ወጣ ብላ ወደ ምትገኘዉ ጪጩ የገብርኤል ቤተክርስቲያን መምጣት ከጀምርኩ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜዬ ነው። በዕለቱ ከሚደረገዉ የሐይማኖታዊ ስርዓት በተጨማሪ ቤተክርስቲያኑ የተሰራዉ ጥቅጥቅ ባለ አረንጓዴ ስፍራ መሆኑ መንፈስን ያድሳል” ትላለች።

ይህ ክብረበዓል ለቱሪዝም ዘርፍ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መመሪያ የመረጃና ፕሮሞሽን ባለሞያ አቶ ዳንኤል ከተማ ናቸው። ለጎብኚዎች መጠለያዎችን በመስራት፣ የአካባቢው ምርት የሆነዉን ቡና በማፍላት እና በጥሬዉ አሽጎ በማዘጋጀት፣ ሐይማኖታዊ መፅሐፍትን እና ሌሎችንም ለዕለቱ በማቅረብ የአከባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላም በኩል ከተለያዩ አከባቢዎች በዓሉን ለማክበር ወደ ዲላ የሚመጡ ታዳሚዎች በአካባቢው ነዋሪዎች በዕለቱ የሚከወነዉን ትዕይንት ለማየት እንደሚጓጉ ሰምተናል። ይህም በጌዴኦ ብሔረሰብ ዘንድ 'ሲርባ' ተብሎ የሚጠራዉ ሀይማኖታዊ መገለጫ ያለዉ ጭፈራ ሲሆን ከበሮ በያዝ በመሽከርከር እና በመዝለል ትዕይንቱን ያደምቁታል። ጎብኚዎችም ብር በመስጠት አብሯቸዉ ይደሰታሉ።

አስተያየት