“ክረምቱን በናዝሬት በአዳማ ከተማ ፣
ምሽት ለእግር ጉዞ የምትወጣው ቀድማ፣
ምነው ዘንድሮ ላይ ላይኔ ተከለለች
ተጠየቂ ናዝሬት ያቺ ልጅ የታለች…”
ይህ ሙዚቃ አዳማ/ናዝሬት ተወልዶ ላደገባት፣ ለኖረባትና በተለያዩ አጋጣሚዎች ለጎበኛት በትዝታ ወደኋላ የሚወስድ ብቻ ሳይሆን በአካል ተገኝቶ ያልጎበኛትን ሁሉ በክረምት ምን ልትመስል እንደምትችል ምስል የሚከስት ነው። በአብዛኞቹ የአዳማ ልጆች ዘንድ ዘመን አይሽሬና ኮርኳሪ የሆነ የናፍቆት ስሜት የሚፈጥር፣ ክረምት በመጣ ቁጥርም ከሚታወሱ የሀገራችን ሙዚቃዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ዘልቋል።
“ዲንቢ ለዲንቢ” በሚለው የሙዚቃ ስራው በዘጠናዎቹ አጋማሽ ላይ ወደ ኢትዮጵያ ሙዚቃ መጥተው ተወዳጅነትን ካተረፉ ሙዚቀኞች አንዱ የሆነው አህመድ ተሾመ ተወልዶ ያደገው አዳማ ነው። አህመድ በሰራቸው ሙዚቃዎቹ አዳማን ደጋግሞ በማንሳት በብዙዎች ህሊና ውስጥ የከተማዋ ምስል አስቀምጧል።
“ተጠየቂ ናዝሬት” የሚለው ሙዚቃ ግን በብዙዎች ዘንድ የተለየ ስሜት ይፈጥራል፡፡ የዐይን ፍቅር ይዞት በሚንገላታው ወጣት ድምጽ ውስጥ የአዳማን የጥንት ሰፈሮችን በምናባችን እንዳስሳለን። ሙዚቃው አዳማን ለማያውቃት ያስተዋወቀ፤ እነ ደንበላ፣ ሀዲድ በላይ፣ ቦኩ፣ ገዳም ሰፈር፣ በሬቻ፣ ሚጊራ ፣ አቡስቶ ቡሉኮ የተባሉትን ሰፈሮች ያስቃኘ ነው።
ከክፍለ ዘመን ፈቅ ያለ እድሜ ያላት አዳማ ሞቃታማው የበጋ አየሯ ከፍተኛ ቢሆንም በክረምት ወቅት ግን እጅግ ተስማሚ የሆነና ለብዙዎች ምቹ የሆነ የአየር ጸባይ አላት።
ይህ ምቹ የአየር ጸባይዋ አዳማ ከጥንት ምስረታዋ ጀምሮ በክረምት የሀገራቸውን ሙቀት ሸሽተው ለሚመጡ የሶማሊያ እና የጅቡቲ እንግዶች የክረምት ማረፊያ አድርጓት ቆይቷል። ለቆለኞቹ ብቻ ሳይሆን ከደጋማው የሀገሪቱ ክፍሎችና ከአዲስ አበባ እንዲሁም ከተለያዩ የኢትዮጵያ ጥጎች ክረምትን ለማሳለፍ የሚመጡ ሰዎችም አዳማና ክረምት ሲታወሱ አብረው የሚነሱ ማስታወሻዎች ናቸው። በተለይ ደግሞ ቤተሰቦቻቸው ወይም ዘመዶቻቸው በአዳማ የሚኖሩ ወጣቶች እና ተማሪዎችም የክረምት ጊዜያት ጠብቀው ብቅ ማለታቸው ስለማይቀር የከተማይቱ የክረምት ልዩ ትዕይንቶች አካል ናቸው።
አዲስ ዘይቤም ልዩ ቅኝቷን በአዳማ እና የክረምት መልኳ ላይ አድርጋለች። በቅድሚያ ያነጋገርነው አህመድ ተሾመን (ዲንቢን) ነው። አህመድ በስራ ምክንያት ኑሮውን በአዲስ አበባ ካደረገ ሰነባብቷል።
አህመድ “ተጠየቂ ናዝሬት” የሚለውን ዜማ እንደሰራ በብዙዎች ዘንድ መወደዱን አስታውሶ የተለየ ገጠመኙንም አጫውቶናል።
“አንድ ልጅ ከጅቡቲ ድረስ መጥቶ 'ታሪኩ የእኔ ነው፣ ታሪኬን ስለምታውቅ ነው የዘፈንከው' አለኝ። ከብዙ መነጋገር በኋላ የሱ ታሪክ አለመሆኑን አሳመንኩት። ልጁ ከጅቡቲ ክረምቱን አዳማ ለማሳለፍ መቶ የተዋወቃት ልጅ ነበረች። እሷም የመጣችው የድሬዳዋን ሙቀት ሸሽታ ነበር። ለጥቂት ግዜ አዳማ ላይ የፍቅር ጊዜ አሳልፈው ወደየመጡበት ሲመለሱ ተለያይተዋል። ከዚያ በኋላ ቢያፈላልጋትም ሊያገኛት አልቻለም” በማለት ዘፈኑ የብዙዎችን የክረምት ትዝታ አስታዋሽ መሆኑን ገልጾልናል።
ይህን የመሰሉ የፍቅር ታሪኮች፣ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ቦታዎች መተው አዳማ ላይ ለክረምት የሚገናኙ ወጣቶች የሚጋሩት የፍቅር ጊዜ፣ የአዳማና ክረምቶቿ አይረሴ ገጽታዎች ናቸው። ለዚህ ምስክር የሆነው አህመድ ደግሞ ጉዳዩን በሙዚቃው ከትቦት ከባለትዝታዎቹ ጋር ዘላቂ ጓደኝነት መስርቶበታል።
የፍቅረኛሞች መንገድ
አህመድ ተሾመ በተጠየቂ ናዝሬት ካነሳቸው ቦታዎች አንዱ “የፍቅረኞች መንገድ” ነው።
"በፍቅረኞች መንገድ ነበር
የማገኛት ድሮ በክረምቱ"
የሚሉት ስንኞቹ “ይህ መንገድ አዳማ ውስጥ የትኛው ነው?” የሚል ጥያቄ ያጭራል።
በተለምዶ ከሪፍት ቫሊ ሆስፒታል ወደ 15 ቀበሌ ያለውን መስመር ይዞ ማዘጋጃን እና ፍርድ ቤትን አልፎ እስከ ሀዲድ ሰፈር ይደርሳል።
መንገዱ ቀን ከሚያሳልፈው የባለጉዳይ እና ተመላላሽ ጥድፊያ ሲያርፍ ዝግ ብለው በሚራመዱ ጥንዶች ይወረራል። ሌሎች እንደ በቀለ ሞላ ሆቴል አካባቢ እና በተለምዶ አንደኛ መንገድ የሚባለው ከቴሌ እስከ ፖስታ ቤት ያሉት ቦታዎችም በተመሳሳይ ስያሜ ይጠራሉ።
የክረምት እንግዶች
ደመላሽ አመነሸዋ ተወልዶ ያደገው በአዳማ ነው። በአዳማ ለአስርታት አመታት ሲኖር አሁን ቢቀዛቀዝም ቀድሞ ብዙ ጅቡቲያውያን እና ሱማሊያዊያን በክረምት የሃገራቸውን ሙቀት ሸሽተው ይመጡ እንደነበር ትዝታውን አጋርቶናል። ከዚያም ሲያልፍ በቀደመው ጊዜ ከንጉሳዊያኑ ቤተሰብ አባላት ጀምሮ ከፍተኛ ሀብት እስካላቸው ግለሰቦች ድረስ በከተማዋ የክረምት ማረፊያ እንደነበራቸው የሚናገረው ደመላሽ ከአዲስ አበባም ክረምቱን በአዳማ ለማሳለፍ የሚመጡ ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል እንዳልነበር ያስታውሳል።
“ከተማዋ ከሀገር ውስጥ እስከ ጎረቤት ሀገር ዜጎች ድረስ ተወዳጅ እና ተመራጭ የክረምት ማሳለፊያ ነበረች፣ አሁንም እንደድሮውም ባይሆን በክረምት ጎብኚዎቿ ይበዛሉ” ሲል አጫውቶናል።
የአህመድ ተሾመ “ተጠየቂ ናዝሬት” ሙዚቃ በወጣበት ወቅት የነበረው ምላሽም ለዚህ ምስክር ይሆናል። ከ16 ዓመታት በፊት በወቅቱ በሀገራችን ተመልካች ብዙም እውቅና ባልነበረው አለማቀፍ የማህበራዊ ሚዲያ ድረ-ገጽ ዩቲዩብ ላይ የተጫነው ይህ ሙዚቃ ከስሩ የተቀመጡ አስተያየቶች በሀገር ውስጥ አድማጮች ብቻ ሳይሆን በወቅቱ አዳማን ደጋግመው በሚጎበኙ ሶማሊያውያን እና ጅቡቲያዊያን ጭምር ተደማጭ እና ተወዳጅ እንደነበረ ያሳያል፡፡
አሊ መድ የተባለ አስተያየት ሰጪ እንዲህ ይላል “A friend from Djibouti , this song never gets old and Nasireth was my favorite place in my summer vacation but now… - የጅቡቲ ጓደኛችሁ ነኝ፤ ይህ ዘፈን መቼም የማያረጅ ነው። ናዝሬት ደግሞ የክረምት እረፍቴ ተወዳጅ ማሳለፊያ ቦታ ነበረች … የዛሬን አያርገውና …”
አዳዲሶቹ ልጆች
ሌሎቹ የአዳማ የክረምት ትዝታ “አዳዲሶቹ ልጆች” ናቸው። በክረምት የትምህርት ጊዜ ከተዘጋ በኋላ አዳዲስ እንግዳ ልጆች በከተማው ማየት የተለመደ ነው። እንግዶቹ ልጆች ብዙውን ጊዜ የቅርብ ዘመዶቻቸው ጋር የክረምቱን የትምህርት እረፍት ሊያሳልፉ የሚመጡ ናቸው።
አቤኔዘር ወርቅዬ ቦኩ ሚካኤል አካባቢ ነው ነዋሪነቱ። ድሮ ብዙ የአጎት እና የአክስቶቹ ልጆች በክረምት ወደአዳማ ይመጡ እንደነበርና ሰፈራቸው ውስጥም እንዲሁ ዘመዶቻቸው ጋር የሚመጡ ልጆች እንደነበሩ ይናገራል።
"የሰዎቿ ማህበራዊ ህይወት እና ያላት የአየር ጸባይ ተመራጭ ያደረጋት ይመስለኛል። ማህበረሰቡ አዲስ ሰው ሲመጣ እንደእንግዳ ከማየት ይልቅ ከነባሩ ጋር አቀላቅሎ እንቅስቀሴውን ስለሚቀጥል ብዙዎች መጥቶ ለመልመድ አይቸገሩም፤ ደጋግሞ ለመምጣታቸውም ምክንያት ሆኗል” ይላል።
የክረምት ትዕይንቶች
አዳማ ላደጉባት፣ ለኖሩባት፣ ለሚያስታውሷት የክረምት ልዩ ነገሯ ምን ሲዘንብ ቢውል፣ ዝናቡ እንዳባራ ሰዎች እንቅስቃሴያቸውን ወዲያው መቀጠላቸው ነው። ጭቃ የሚባል ነገር አያውቃትም። በተለይ ደግሞ መሸት ሲል፣ ሴቶች ትኩስ ንፍሮ፣ ድንች፣ በቆሎ ይዘው ወደ መንገድ ይወጣሉ። ባለንፍሮዎቹ እንፋሎታቸው ከሩቅ የሚጣራ ትኩስ የባቄላና ሽንብራ ንፍሮ ይዘው ሲቀመጡ፣ በቆሎ ጠባሾቹ ደግሞ የከሰል ምድጃቸውን ፍም እያርገበገቡ በቆሎ እያገላበጡ ይጠብሳሉ። የእርስ በርስ ጫወታቸው ከያዙት ትኩስ መክሰስ አልፎ አላፊ አግዳሚውን፣ ታዛቢውን ያሞቃል።
አዳማ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ከሚገኙ ከተሞች አንዷ እንደመሆኗ ሞቃታማ አየር ንብረቷ ክረምቱን እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከባድ አያደርገውም። ነገር ግን ተዳፋት ተፈጥሮዋ ለጎርፍ ተጋላጭ ያደርጋታል፤ እንደ 09 ያሉ የከተማዋ ክፍሎች ክረምት በመጣ ቁጥር የጎርፍ ስጋት እንቅልፍ ይነሳቸዋል። ጎርፉ በከተማዋ ካሉ ዳገታማ አካባቢዎች የሚመጣ ነው፤ ከተማዋን እያጠበ አልፎ አዋሽ ወንዝ ይገባል።
የክረምት ጊዜ ልዩ ትዝታዬ በአሸዋ ጎጆ እና የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾች እየሰራን የምንጫወተው ነው ትለናለች የአዳማ ከተማ እርዳታ አካባቢ ነዋሪዋ ቤተማርያም። ይህ አብዛኞቹ የአዳማ ልጆች የሚጋሩት ትዝታ ሲሆን፣ ለአሁኖቹ ህጻናት ደግሞ አሁንም የክረምት ጊዜ ማሳለፊያ ነው። በአሸዋ በተሰሩ ግድቦች ውሃ እያቆሩ “ብዙ ውሃ በያዘ” መጫወት ከድሮ ጀምሮ የተለመደ ነው።
አሁን አድጎ የፊልም ሞያ ላይ የተሰማራው በለጠ ሽመልስ በአዳማ ያሳለፈው ልጅነት ሲታሰበው ለክረምት ልዩ ቦታ አለው። ብዙ ትዝታዎች ቢኖሩትም ትምህርት ቤት ከተዘጋ በኋላ በክረምት ከሰፈሩ ልጆች ጋር ያደርጋቸው የነበሩትን የእግር ኳስ ውድድሮችን መቼም እንደማይዘነጋቸው አጫውቶናል።
በክረምት በየሰፈሩ ታዳጊዎች በቡድን ይከፋፈሉና የተወሰነ ገንዘብ በማዋጣት ያሰባስባሉ። የተዋጣውን ገንዘብ እንዲይዝ በሃላፊነት የሚሰጠው አዘጋጅ ስራው ለጨዋታዎቹ መርሃ ግብር ማውጣት ነው። እግር ኳስ ጨዋታው በምድብ በተከፋፈሉት ቡድኖች መሃል ለቀናት ይካሄዳል።
የውድድሩ ማለቂያ ላይ አሸናፊው ቡድን አዘጋጁ ጋ ተሰብስቦ በተቀመጠው ገንዘብ የሙሉ ቡድን ማልያ ይገዛና ተሸላሚ ይሆናል።
ቡድኖቹ በአሰልጣኞቹ ስም የዞላ ልጆች፣ የሳሚ ልጆች እየተባሉ ሲጠሩ ለክረምት ብቻ የሚሰባሰቡት ልጆች ደግሞ የ04 ልጆች፣ 14 ልጆች በሚል በሠፈሮቻቸው ስም ይደለደላሉ። በእነዚህ አይረሴ የክረምት ውድድሮች ላይ የታዋቂ ቡድኖች አሰልጣኞች ለምልመላ ይመጡ ስለነበር ብዙ በቋሚነት ወደ ስፖርቱ አለም የተቀላቀሉ ተጫዋቾችን አዳማ አፍርታለች ይለናል በለጠ። “እኔም ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች ቡድን ውስጥ ተካችቼ የተጫወትኩበት ጊዜ ነበረ” ሲል የክረምት ትዝታውን አጋርቶናል።
አዳማ አሁን መንገዶቿ ሰፍተው፣ የነዋሪዎቿም ቁጥር ጨምሯል። ከመሠረተ ልማት ችግሮቿ ጋር የክረምት ድምቀቷ እንደጥንቱም ባይሆን ዛሬም ግን እንግዶቿን ተቀብሏ ከማስተናገድ አልቦዘነችም።