ሐምሌ 19 ፣ 2014

ሰሚ ያጣው የሹፌሮች ሞትና ጥቃት

City: Adamaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

እንደ ሹፌሮች ማህበር መረጃ በዚህ አንድ አመት ብቻ ከ40 በላይ አሽከርካሪዎች በመንገድ ላይ በወንበዴዎች በጥይት ተገድለዋል

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ሰሚ ያጣው የሹፌሮች ሞትና ጥቃት
Camera Icon

ፎቶ፡ አፍሪካ ልማት ባንክ

ለወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ የፈሳሽ እና የደረቅ ጭነትን ከወደብ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት እና በሀገር ውስጥ ከጫፍ ጫፍ ጭነትን በማመላለስ የሀገሪቱን የአቅርቦት ሰንሰለት በከፍተኛ ሁኔታ ደግፈው የሚገኙት የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ናቸው። እነዚህ የሀገር አቋራጭና ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች በተለያዩ ጊዜና ቦታዎች በሚደርሱባቸው የመብት ጥሰትና ጥቃት “በስራችን እና በህይወታችን ላይ አደጋ ተጋርጧል” ይላሉ። 

ችግራቸውን መንግስት እንዲፈታላቸው በተለያየ ጊዜ በመገናኛ ብዙሃን እና በማህበራዊ ሚዲያዎች ድምፃቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። ነገር ግን ተገቢውን ምላሽ እና ትኩረት እንዳላገኙ የተናገሩት አሽከርካሪዎች መብታቸውን ለማስከበር ተጨማሪ እርምጃዎች ለመውሰድ ማሰባቸው ተሰምቷል። “የሚደርስብን ጥቃት ትኩረት ተነፍጎታል” ያሉ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ከሐምሌ 15/2014 ዓ/ም ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ ሊያደርጉ እንደሆነ አዲስ ዘይቤ አሽከርካሪዎችን አናግራ መዘገቧ ይታወሳል።

ሆኖም  በቀን 13/11/2014 ዓ.ም “ጥብቅ ማሳሰቢያ” በሚል በተጻፈ ደብዳቤ በጅቡቲ ክልል ውስጥ የስራ ማቆም አድማ ማድረግ በጥብቅ ተከልክሏል። ክልከላውን ያሳወቀው በጅቡቲ ወደብ የሚገኘው የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ነበር።  

ለአዲስ ዘይቤ ሀሳቡን ያካፈለውና ስሙን እንዳይጠቀስ የፈለገው አሽከርካሪ “በዚህ ሁለት ወር ውስጥ ብቻ ከአስር በላይ የማውቃቸው ሹፌሮች ተገድለዋል፤ የአጋጣሚ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም የቀን ጉዳይ ነው” ሲል ስጋቱን ይገልጻል።

አዲስ ዘይቤ ካነጋገረቻቸው አሽከርካሪዎች መካከል አቶ መከተ ነጋሪ አንዱ ነው። “ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ናት ሲባል እበሳጫለሁ፤ ሹፌሮቿ ወደቦቿ ነን” የሚለው መከተ ከኬንያ፣ ከሱዳንና ከጅቡቲ የሀገሪቱን ወጪ ገቢ ጭነት በአግባቡ እያመላለሱ ቢሆንም ተገቢውን የደህነት ከለላ እያገኙ አለመሆኑን በብስጭት ይናገራል።

"እኔ በአጋጣሚ ምንም ገጥሞኝ አያውቅም፤ ነገር ግን የተዘረፉ፣ የተደበደቡ፣ መስታወታቸው በጥይት የተመታ ጓደኞች አሉኝ” ይላል አቶ መከተ። ከጅቡቲ በጋላፊ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ያለው መንገድ ላይ የታጠቀ ኃይል እንዳለና በተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰ እንደሆነም ጨምሮ ይስረዳል።

ለብቻ መንቀሳቀስ የሚያስከትለውን አደጋ በመፍራት አሽከርካሪዎች በቡድን ሆነው እንደሚጓዙ ገልጸዋል። ይህም ለተለያዩ የጉምሩክ አሠራሮች እና ቅጣቶችም እያጋለጣቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

“በጉምሩክ አሰራር መሰረት 'የጅቡቲን ድንበር አቋርጦ የገባ ሹፌር በ3 ቀን ውስጥ አዲስ አበባ መድረስ አለበት' የሚል ህግ አለ” ያለን መከተ በዝርፊያውና መንገድ ላይ በሚፈጠሩ የተለያዩ የደህንነት ስጋቶች ምክንያት አሽከርካሪዎች ከዚህ ቀን ለረዘመ ጊዜ ሲቆዩ በጉምሩክ ከ 5 ሺህ ብር ጀምሮ በየቀኑ በፐርሰንት ይቀጣሉ። 

ጥቃት ደርሶባቸው ለፖሊስ በሚያመለክቱበት ጊዜ “'ይጣራል' ከመባል ያለፈ ምላሽ አናገኝም” የሚለው መከተ አሽከርካሪውን የሚያስተባብር እና የሚሟገት ተቋም አለመኖር እጅግ ተጎጂ እንዳደረጋቸው ያስረዳል። ከዚህ በፊት የተሞከረውም የማህበር ምስረታ የታሰበውን ውጤት ሳያመጣ መበተኑ ጭምር ጠቅሷል።

የጭነት ወረፋ ደርሷቸው ወደ ጅቡቲ እየሄዱ በመንገድ ላይ በጸጥታ ሀይሎችም ሆነ በሌሎች የታጠቁ ቡድኖች በግድ ስራ ማሰራት፣ ጭነት ማስጫን በተደጋጋሚ እንደሚከሰት የሚያስረዳው መከተ፤ በግዳጅ ወደ ማይፈልጉበት ቦታ በመሳሪያ አስፈራርቶ ከሚወስዳቸው አካል ለሰጡት አገልግሎት ምንም አይነት ክፍያ እንደማይገኙና መኪናቸውም እንደሚጎዳ ይናገራል። “ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ ከ12 ሰዓት በላይ እንሄዳለን። ኢትዮጵያ ከገባን በኋላ የኬላ ሰልፍ ስንጠብቅ 5 ሰዓታት በላይ እንቆያለን” ሲል ያለውን መጉላላት ይገልጻል።

'ጣና የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር' በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀስ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎችን መብት ለማስጠበቅ በባህር ዳር ከተማ የተቋቋመ ነው። ማህበሩ በ11/06/2014 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤትን ጨምሮ ለተለያዩ ክልሎችና ቢሮዎች በአሸከርካሪዎች ላይ እየደረሰ የሚገኘውን እንግልትና ግድያን በተመለከተ በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሚከተለውን ብሏል።  

በሃገሪቱ ተዟዙሮ ዘር ቀለም ብሄር ሳይል ለሁሉም ግልጋሎት የሚሰጥው አሽከርካሪ ዛሬ ላይ በየደረሰበት እየተሳደደ፣ እየተዋረደ፣ እየተበደለ፣ እየተገደለ ይገኛል። አሽከርካሪውም ከነገ ዛሬ ይሻላል፣ ለውጥም ይታያል፣ ህግ ጉዳታችንን አይቶ ለማስከበር ይሰማራል ብሎ በተስፋ ቢንቀሳቀስም ከእለት እለት በደሉ እየበረታ መሄዱ አሳሳቢ ሆኖ እያየን ነው። ከበደላችን ባለፈ መንግስትም ሆነ ሚዲያዎች ለጉዳታችን፣ ለበደላችን፣ ለአገልግሎታችንና ለሞታችን ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠት የሚያሳዩት ቸልታ ለሙያችን ያላቸውን ክብር ዝቅ ያለ መሆኑን አመላካች ሆኖ አይተነዋል በዚህም ቅሬታ ተሰምቶናል” ሲል ቅሬታውን አስተላልፏል።

እንዲሁም በመላው ሀገሪቱ አሽከርካሪዎች ከፍተኛ ጥቃት ይደርስባቸዋል ያላቸውን ቦታዎችም አስቀምጧል። በዚህም በኦሮሚያ ክልል ከፍቼ ጎሃፅዮን አባይ ድልድይ፣ ወለጋ መስመር ሁሉም ቦታዎች፣ በአማራ ክልል ጎንደር አብረሃ ጅራ ዳሽን እንዲሁም ከጎንደር ሾህዲ ድረስ፣ ከጋይንት ደብረታቦር ገረገራ ያሉ ቦታዎች፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከካር ኬላ አባይ ግድብ መንገድ፣ በአፋር ክልል ከሚሌ አዋሽ አርባ ያሉ ቦታዎች እና በሌሎች ባልጠቀስናቸው ቦታዎች አሽከርካሪዎች ከፍተኛ በደል እየደረሰባቸው ይገኛል ብሏል ማህበሩ።

አቶ ሰጡ ብርሃን የጣና ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር ፀሓፊ ነው። ፀሓፊው ከአዲስ ዘይቤ ጋር ባደረገው ቆይታ ችግሩ ስር እየሰደደ እንደመጣ ይናገራል። ለአብነትም ከ2 ዓመት በፊት ባህርዳር ላይ ለክልሉ እና ለፌደራል መንግስት ድምፃችን ይሰማ ዘንድ ሰልፍ አድርገን ነበር ሲል ይናገራል።

“በሹፌሮች ላይ የሚደርሰው በደል ብዙ ነው። ችግሩ በከተማ ውስጥ ይጀምራል” ይላል አቶ ሰጡ። “ረዳት ቀጥረን እየሰራን ባለንበት ሁኔታ በሸራ ስም የተደራጁ አጋዥ ማህበራት የተባሉ የረዳቱን ስራ በግድ ሰርተው እስከ 1500 ብር ድረስ በጉልበት ያስከፍሉናል” ይላል።

አቶ ሰጡ ብርሃን እንደሚለው “ከደህንነት ስጋቶች በተጨማሪም በኬላዎች ላይ ብዙ አይነት ቀረጥ እንከፍላለን። እኛ የምናውቀው የይለፍና ሮያሊቲ ታክስ ነው”። ሮያሊቲ ታክስ ማለት አንድ አካባቢ ላይ ያለ ምርት ከአካባቢው ተጭኖ ሲወጣ ለአካባቢው የሚከፈለው እና እርሱም ህጋዊ ደረሰኝ ያለው እንደሆን ያስረዳል። አብዛኞቹ ኬላዎች ግን እንዲሁ ገንዘብ ለመሰብሰብ በየቦታው የተቋቋሙ እንደሆኑ ይናገራል። ማህበሩ ባደረገው ጥረት በተለይም በአማራ ክልል ከ80 ከመቶ በላይ ኬላዎች መነሳታቸውን ገልጿል።

“በኬላዎች ላይ መክፈላችንን የሚያሳይ ደረሰኝ ስናሳይ የኮቴ ክፈሉ እንባላለን” የሚለው አቶ ሰጡ 'የኮቴ' የሚከፈለው ለባዕድ ሀገር መሬት እንጂ ሀገር ውስጥ መጠየቅ እንደሌለበት ይናገራል። “አብዛኞቹ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱት በፌደራል መንገዶች ላይ ነው። ለዚህ ደግሞ በየአመቱ የመንገድ ፈንድ ይከፈላል” ይላል አቶ ሰጡ። የመንገድ ፈንድ በከፈልንበት መንገድ ድጋሚ ክፍያ መጠየቃቸው እጅግ እንዳሳዘናቸውም ይናገራሉ።

'ከሹፌሮች አንደበት' በሚባል የፌስቡክ ገጽ ላይ ሹፌሮች የተለያዩ መረጃዎችን ሲያጋሩ እና ሲተጋገዙ ይታያል። በዚህ ገፅ ላይ ከሚነሱ ጉዳዮች አንዱ በየከተሞቹ መግቢያ እና መውጫ ላይ የሚደረጉ የቀረጥ እና ለከተማ ልማት የሚጠየቁ ወጪዎች አንዱ ናቸው። ለአብነትም ፍቅር የሚባል አስተያየት ሰጪ ከድሬዳዋ ከተማ ወደ አይሻ ደወሌ የክፍያ መንገድ ላይ ወደ ከተማ ሲገባ እና ሲወጣ ለከተማ ልማት ተብሎ በተደጋጋሚ ክፍያ እንደሚጠየቁ ይገልፃል።

በተጨማሪም በስፍራው የሚገኝ የትራፊክ ፖሊስ ተሽከርካሪ ባለፈ ቁጥር ጉቦ እንደሚቀበል እና 'አልሰጥም' ያለውን አሽከርካሪ እንደሚከስ ፅፏል። ይህንን ቦታ ምሳሌ ወስደን የጠየቅነው አቶ መከተ ነገሪ የተባለ አሽከርካሪ “ማንኛውም ሰው ከሰዓት በፊት ከተጓዘ የተባለው ትራፊክ ያገኘዋል” ሲል በቦታው ቆሞ ከአሽከርካሪዎች ላይ ገንዘብ ስለሚቀበለው ትራፊክ ጉዳይ ያነሳል።

ሌላው በተደጋጋሚ በሹፌሮች ላይ የሚደርሰውን እገታ በቂ ትኩረት እንዳላገኝ የሚናገረው የጣና ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር ፀሓፊ አቶ ሰጡ ብርሃን ነው። “አጋቾች በስልክ ተደራድረው እጅ በእጅ ገንዘብ ተቀብለው ታጋቹ የሚለቀቅበት ሁኔታን ለማስቆም አለመሞከሩ የቴክኖሎጂ እጦት ሳይሆን ቸልተኝነት ነው” ይላል። እንደ አቶ ሰጡ አስተያየት ለታገተ ሹፌር ከ400-700 ሺህ ብር ድረስ ለማስለቀቂያ ይጠየቃል። እንደ ማሳያ በቅርቡ  እንኳን ሙገር አካባቢ 5 ሹፌሮች ታግተው እንደነበር መስማቱንና እገታው በቤተሰብ እና በአሽከርካሪው ላይ የሚፈጥረው የስነ-ልቦና ጫና ከገንዘብ በላይ ከባድ እንደሆነ ይገልፃል።

“በዚህ አንድ አመት ብቻ ከ40 በላይ አሽከርካሪዎች በመንገድ ላይ በወንበዴዎች በጥይት ተገድለዋል” ይላል አቶ ሰጡ። የሟች ሹፌሮች ፎቶ በእጃቸው እንዳለ የነገረን አቶ ሰጡ “እኛ ገፍተን ካልሄድን ሹፌሩን ቀርቦ የሚያናግር ቀርቶ ችግራችንን ለመስማት ፍቃደኛ የሆነ አካል የለም” ሲል ቅሬታውን አጋርቷል።

“ከአመት በፊት አፋር ክልል እንዱፉ አካባቢ እግር ኳስ ተጫዋች ይዞ በሚጓዝ አውቶብስ ላይ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት አንድ ተጫዋች ተገደለ። በወቅቱ በሚዲያዎች ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ ነበር” በማለት ትዝብቱን በመግለፅ፣ በተመሳሳይ ቦታ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ10 በላይ ሹፌሮች ተገድለው ነበር ግን ሚዲያዎች ስለሹፌሮች ሞት አለመዘገባቸውን አቶ ሰጡ ወቅሷል።

አቶ ሰጡ ባካፈለን መረጃ መሰረት በአንድ ቀን 5 ሹፌሮች ተገድለው ንብረትም ተቃጥሎ ያውቃል፤ ከዚህ ሌላ በአባይ በረሃ ውስጥ አንድ ሹፌር በ30 ጥይት ተደብድቦ ሞቷል። ከዚህ ባለፈም በአፋር ክልል ከአዋሽ አርባና ሰሜን ጎንደር አካባቢም እገታ እና ግድያው አሁንም እንደቀጠለ ይናገራል። 

እንደ መፍትሄም የፀጥታ ስጋት ያለባቸው ቦታዎች ተለይተው ቋሚ የፀጥታ ሀይል ሊመደብ እንደሚገባ የሚገልጸው የማህበሩ ፀሐፊ ከ14 ዓመት በፊት አፋር ገዋኔ ላይ የተፈጠረውን ተመሳሳይ የሹፌር ጥቃትና ዝርፊያ በዚህ መንገድ መፍትሔ እንደተገኘለት ያስታውሳል። “እገታውም ቢሆን ያለውን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ አጋቾችን በቁጥጥር ስር አውሎ አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ ለህዝብ መግለፅ ያስፈልጋል” ብሏል።

በመጨረሻም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበ የሎጂስቲክ ሪፓርት ላይ የተጓጓዘው ጭነት መጠን ሲገለፅ፤ በሹፌሮች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ጭራሽ አለመገለፁ በሹፌሮቹ ዘንድ ትልቅ ቅሬታ እንደፈጠረ በመግልጽ ሀሳቡን ቋጭቷል።

በጉዳዩ ላይ ያላቸው አስተያየት ለማግኘት አዲስ ዘይቤ ለፌዴራል የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር እንዲሁም ለስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ህዝብ ግንኙነቶች በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው በመደወል፣ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት እና በኢሜል ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም። ይሁንና መ/ቤቶቹ ያላቸውን ሀሳብና አስተያየታቸውን ለማስተናገድ በራችን ክፍት ነው።

አስተያየት