ሐምሌ 17 ፣ 2014

መከረኛዋ መተከልና ምንዱባኑ ነዋሪዎቿ

City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

ተገፋን የሚሉ ማሕበረሰቦችን (በዋናነት የጉሙዝ ማሕበረሰብን) ያኮረፉ የጉሙዝ ፖለቲከኞች ‘አክራሪነትን’ ከጠብ-መንጃ ጋር አስታጥቀዋል የሚሉ ወገኖች አያሌዎች ናቸው

Avatar: Kassaye Dametie
ካሳዬ ዳምጤ

ካሳዬ ዳምጤ በወቅታዊ ጉዳዮችና ስርዓት ጾታ ላይ የምታተኩር በተለያዩ የብዙኃን መገናኛ አውታሮች የመስራት ልምድ ያላት የአዲስ ዘይቤ ጽሁፍ አቅራቢ ነች።

መከረኛዋ መተከልና ምንዱባኑ ነዋሪዎቿ
Camera Icon

ፎቶ፡ ካሳዬ ዳምጤ (ከመተከል ግጭት ተፈናቃዮች አንዷ በለጤ ተሾመ)

“ጌታ ቀንሽ ነው ካላለ”

በለጤ ተሾመ በመተከል ዞን ድባጤ ወረዳ አልባሳ ቀበሌ ተወልዳ፣ አድጋለች። የ20 ዓመት ወጣት ስትሆን በህዳር ወር መጀመሪያ 2013 ዓ.ም. የተፈፀሙ ጥቃቶች የሷንና የቤተሰቧን ህይወቷ እንዳመሰቃቀለው ትናገራለች። ጥቃቶቹ የጦር መሳሪያ፣ ቀስትና ስለቶችን በመጠቀም እንደሚፈጸሙ የአይን ምስክሮች ይናገራሉ። ከህጻናት ጀምሮ እስከ አቅመ ደካሞች ድረስ የጥቃቱ ሰለባዎች ናቸው። በጥቃት በምትናጠው ድባጤ ወረዳ በሚገኙት አልባሳ፣ ስምቦሰሪ፣ ቆርቃ፣ ገፈሬ እና ሙዘን ቀበሌዎች ጥቅምት 27፤ 2013 ዓ.ም..፣ ህዳር 5 እና 6፤ 2013 ዓ.ም. በተፈፀሙ ጥቃቶች ንጹሀን ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በበለጤ መንደር ታጣቂዎች ጥቃት ሲያደርሱ  ሕይወታቸውን ለማትረፍ ከባለቤቷና ከእናቷ ጋር ወደ አጎራባች ቀበሌዎች እግሬ አውጭኝ አሉ። የጭንቅ ጉዟቸውን ፈታኝ ያደረገው በለጤ የዘጠኝ ወር ነፍሰ-ጡር መሆኗ ነበር። “እንደ ማዕበል ነው የወረሩን” ስትል መራራዋን ቀን ታስታውሳለች። ወንድሟና የእናቷ ባለቤት (የእንጀራ አባቷ) በጥቃቱ ተገደሉ። በለጤ የእልቂቱን ግዝፈት ስትገልፅ “ጨርሰውናል እንጂ” በማለት ከመንደራቸው ሁለት መኪና አስከሬን መውጣቱን ትናገራለች። በሕይወት መትረፏን “ጌታ ቀንሽ ነው ካላለ” በሚል የእምነት ቃል የመትረፏን ተኣምር ታነሳለች።

ጥቃቱን ለማምለጥ ሲሉ በተፈጠረው ወከባም “እርስ በእርስ ተላግተን (ተጠላልፈን) አልቀን ነበር” በማለት ሁነቱን ትናንት እንደተፈጠረ ያህል ታስታውሰዋለች። የዘጠኝ ወር ነፍሰ-ጡር ሆና ለመሸሽ የተገደደችው በለጤ፤ ጉዞዋ ድካም የተሞላበት እንደነበር ትናገራለች። አጎራባች ወደ ሆነው ጋሌሳ ቀበሌ ለመድረስ የተጀመረው እግር ጉዞ በቀላሉ የሚገፋ እንዳልነበረ ታስታውሳለች። “ርዝመቱ፣ አቀበቱ፣ ቁልቁለቱ አላህ ነው ያወጣን” ትላለች በለጤ። ጋሊሳ ዘመድ ቤት ተጠግታ ወንድ ልጇን ተገላገለች። ነገር ግን በጋሊሳ በጥር ወር በተነሳ ሌላ ጥቃት እፎይ ብላ ሳትጨርስ፤ የአራስነት ገላዋ ሳያርፍ በድጋሚ ወደ ድባጤ እንድትሰደድ አስገደዳት።

ዛሬ አቡሽ አንድ ዓመት ከመንፈቅ ደፍኗል። መጠለያ ጣቢያን ብቻ የሚያውቀው አቡሽ፤ እናቱ በለጤ ይህን ቃለ-ምልልስ ስታደርግ ህመም ቢጤ ገጥሞት ነበር። የጣቢያው ሀኪሞች (በነጻ የሚያክሙ) እስኪገቡ ደረስ በጀርባዋ ልጇን አዝላ ውሃ ለመቅዳት እየዳዳች ነበር የተገናኘነው።

በለጤ፣ አቡሽ፣ ባለቤቷና እናቷ መጠለያ ጣቢያን በሸራ የተወጠረ ቤት መኖሪያቸው ካደረጉ ከረምረም ብለዋል። ብቻዋንም አይደለችም። ይህ እጣ የገጠማቸው በመቶ ሽህዎች የሚቆጠሩ የመተከል ዜጎች ጋር እንደ አዲስ የሕይወትን ኑሮ እየመሩ ይገኛሉ። 

በለጤና ቤተሰቦቿን ጨምሮ 300 ሽህ የሚሆኑ ሰዎች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በተነሱ የተለያዩ ግጭቶችና ጥቃቶች ሳቢያ ከቀያቸው ተፈቅናለው በተለያዩ መጠለያዎች ይገኛሉ። 

ምድራዊ ገነት

ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ሦስት ዞኖች መተከል አንዱ ነው። መተከል ከአዲስ አበባ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ በ547 ኪ.ሜ ከክልሉ መቀመጫ ከአሶሳ ደግሞ በስተ ምስራቅ አቅጣጫ በ387 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች። የዞኑ ዋና ከተማ ግልገል በለስ ስትሆን፤ ዞኑ ሰባት ወረዳዎችን አቅፎ የያዘ ነው። ክልሉ “ባለቤቴ ናቸው” ካላቸው አምስት ብሄሮች ውስጥ ሁለቱ (ጉምዝና ሽናሻ) በዞኑ ይኖራሉ። ከዚህ ባሻገርም እንደ አማራ፣ አገው፣ ኦሮሞ፣ ሀድያ፣ ወላይታ ያሉ 13 ብሄሮች ዞኑ አሉኝ ከሚለው 450 ሺህ ገደማ ነዋሪዎች መሀል ሆነው ኑሯቸውን ቀልሰው ይኖራሉ። የመተከል ዞን አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ መተከልን በሕዝብ ስብጥሯ (ብዝሃነት) “ትንሿ ኢትዮጵያ” ይሏታል። የተለያዩ ኃይማኖቶችም ቤተ-እምነታቸውን አንፀው መኖር ከጀመሩ ዘመናት ተቆጥረዋል።

የቀድሞው ጎጃም ክ/ሀገር መተከል አውራጃ የአሁኑ የመተከል ዞን በሰሜንና ሰሜን ምስራቅ አማራ ክልልን፣ በደቡብ ካማሺን (ቤንሻንጉን ጉሙዝ ክልል)፣ በሰሜን ደግሞ ሱዳንን (ብሉ ናይል ግዛት) ተጎራብቶ፤ ግብርናን የእንጀራ ገመዱ ያደረገ ማሕበረሰብ የሚኖርበት ነው። ሰሊጥ፣ ኑግ፣ ለውዝ፣ ቦሎቄ፣ አኩሪ አተር፣ ጥጥና ቡና የመሰሉ ሰብሎችን የሚያመርት መሬት ከመታደሉም ባለፈ ከዓመት እስከ ዓመት የሚፈሱ እንደ በለስ (አባት በለስና ግልገል በለስ)፣ ጎሸር፣ ሻር እና አይማ የመሰሉ ወንዞች ታድሏል። ወርቅ፣ ኦፓልና እብነ-በረድ የመሰሉ ማዕድኖች የሚዛቁበትም ነው።

ላለፉት አስር ዓመታት እየተገነባ ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መተከል በተለየ ሁኔታ አይን እንዲጣልባት አድርጓል። በአጭሩ በመልከዓ-ምድር፣ በተፈጥሮ ፀጋና በአየር ንብረት ስለመታደሏ ምስክሮቹ አያሌዎች ናቸው።

እውነታው ይህ ከሆነ የአንድነት እሴትን የተላበሱ፣ ልዩነትን ያሽቀነጠሩ ማሕበረሰቦች ስለምን በደም ታጠቡ? ለምን አሳዳጅና ተሳዳጅ ሆኑ? የሚሉ ጥያቄዎችን በብዙዎች ዘንድ ያጭራል።

አባ ነመራ ጌቱዌ በሰባዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙ የመተከል ነዋሪ ናቸው። ተወልደው ያደጉትም በድባጤ ወረዳ ነው። ከቀበሌ እስከ ወረዳ የመንግስት ሰራተኛ ሆነው ያገለገሉት አባ ነመራ በአካባቢው ነዋሪዎች የተከበሩ ሠው ናቸው። መተከል የግጭት ቀጠና ከመሆኗ በፊት ማሕበረሰቡ ይኖርበት የነበረው ሁናቴ እንዴት እንደነበር ለተነሳላቸው ጥያቄ፤ “አይ ልጄ የድሮውንማ ተናግረን አንጨርሰውም” ነበር መልሳቸው።

“አንድነታችን፣ የድሮ ፍቅራችን፣ የድሮ አብሮነታችንን ተናግረንም አንጨርሰውም። ይሄ ብሄር አማራ ነው፣ ይሄ ብሄር ኦሮሞ ነው፣ ይሄ ብሄር ሽናሻ ነው፣ ይሄ ጉሙዝ ነው፣ ይሄ አገው ነው የሚባል የለም። ሁሉም እንደ ወንድማማች ነው የኖረው። እየተጋባ፣ እየተዋለደ፣ በአንድ ላይ ደቦ እየሰራ፣ በአንድ ላይ ማህበር እየገባ፤ በሰርጉ፣ በክርስትናው… በሁሉም አንድ ነን።” ሲሉ ይገልፁታል። 

አባ ነመራ ተወልደው ባደጉባት፤ ልጆችና የልጅ ልጆች ባፈሩባት ወረዳ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጓሮአቸውን እንኳ ቆፍረው ለመዝራት ተስኗቸው ባጅቷል። “የአፈሩ ሽታ ናፍቆን አለፈ” ይላሉ።

የቡለን ወረዳ ተወላጅ የሆኑትና የአዲሱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ሰብሳቢ ዶ/ር መብራቱ አለሙ መተከል ልዩ አካባቢ መሆኑን ይናገራሉ። “ከተማው ገጠሩ ኢትዮጰያዊነትን የተላበሰ ነው” ሲሉ፤ እንደ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ብዝሃነቱ ከተማን ብቻ ያማከለ እንዳልሆነ ያስረዳሉ። ዶ/ር መብራቱ የሽናሻ ተወላጅ ሲሆኑም በአማርኛ ቋንቋ አፋቸውን ፈተው በአካባቢው የሚነገሩ ሌሎች ሦስት ቋንቋዎችን በመናገር እንዳደጉም ይናገራሉ። የመተከል ነዋሪ ብሄር ሳያጥረው “የተጋባ፣ የተዛመደ የተጋመደ” እንደሆነም ተወላጁ ያነሳሉ።

“ስለብሄር የሰማነው ዩኒቨርስቲ ገብተን ነው። ከዛ በፊት ሁሉም አንድ ማሕበረሰብ ነበር የሚመስለን። ይህን ያህል ልዩነት፤ ውጥረት ያለም አልመሰለንም። ዩኒቨርስቲ ውስጥ ነው ብሄርተኝነትንም፤ ዘረኝነትም ለማየት የቻልነው እንጂ  መተከል ላይ ስናድግ እንደዛ አይነት ስሜትም አስተሳሰብም አልነበረም” ይላሉ ዶ/ር መብራቱ

ይህን የአንድነት ሀሳብ መተከልን የሚያውቁ ሁሉ ይጋሩታል። ጥያቄው ግን የብዝሃነቷ ንግስት፤ የምድር ገነቷ እንዴት የግጭት አውድማ ሆነች? የሚለው ነው።

የደም ምድር ?

በመተከል፣ ዜጎች በቆዳ ቀለማቸው ብቻ (ቀዮ በመባል) ተለይተው ተገድለዋል፤ ተጨፍጭፈዋል፤ ሰብዓዊ መብታቸው ተገርስሷል፤ ተፈናቅለዋል፤ ተሳደዋል፤ ከእምነታቸውና ከባህላቸው ውጭ በእስካቫተር ተገፍተው በጅምላ ተቀብረዋል። ይህ የመተከልን ያለፉት ዓመታትን ቀውስ በአጭሩ የሚጠቀልል ዓረፍተ ነገር ነው።

ግጭት በየትኛውም አብሮ የሚኖር ማሕበረሰብ  ውስጥ አልፎ አልፎ መከሰቱ “ተፈጥሯዊ ነው” በማለት ብዙዎች ይስማማሉ። በመተከል ግለሰባዊ ግጭቶች በተለይም ከሀብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በዘመናት መፈራረቅ እዚህም እዚያም መታየታቸው እሙን ነው። ነገር ግን ግጭቶቹ ግለሰባዊ እንጂ ብሄርን ያማከሉ አለመሆናቸውንም ነዋሪዎቹ ያሰምራሉ። ይሁን እንጂ ያለፉት አራት ዓመታት ለመተከል ዞን ነዋሪዎች ሕይወት “ገሀነም” ነበረች።

እሳት ጫሪዋ የወርሃ ሚያዚያዋ ቀን (ሚያዚያ 11፤ 2011 ዓ.ም.) ከሌሎች ቀናት የተለየች ነበረች። በሰባቱ የዞኑ ወረዳዎች አንዷ በሆነችው ዳንጉር ዋና ከተማ ከማንኩሽ ወደ ግልገል በለስ በነበረ ጉዞ በሹፌርና በተሳፋሪ መሀል የተከሰተ የታሪፍ አለመስማማት ጦስ ከባድ ነበር። በተፈጠረው አለመግባባት የተሳበችው ቃታ አላባራ ወዳለ ጥቃትና የመልስ ምት አምርታ የዛሬዋን የመተከል ገፅታ ጥላሸት የቀባች እርሳስ ሆናለች። ከሰባቱ ወረዳዎች ከፓዌ ወረዳ በቀር ሁሉም የመተከል ወረዳዎች ደም ፈሶባቸዋል።

ወ/ሮ መልኪቱ ወርቁ ወንበራ ወረዳ ዱራ ጄላ ቀበሌ ነው ውልደታቸው። ሦስት ልጆች ያሏቸው ወ/ሮ መልኪቱ ላለፉት 17 ዓመታት የጥቃቶች ማዕከል በሆነችው ድባጤ ወረዳ ኑሯቸውን እየገፉ ነው። ከእነዚህ አላባራ ካሉ ጥቃቶች በፊት ከብቶች እያረቡ ኑሯቸውን ይገፉ እንደነበር ይናገራሉ። “አገሩ ወርቅ ነበር። ብትቆፍሪው ወርቅ” ይላሉ የቀደም የማሕበረሰቡን ኑሮ ሲገልፁ። ቻግኒ ለአንድ ወር ተፈናቃይ እንዲሆኑ ያስገደዳቸውን የህዳሩን ጥቃት ሲያስታውሱም፤ ከቤት መውጣት ባለመቻላቸው ለሦስት ቀናት ምግብ እንዳልቀመሱ ይናገራሉ። ለሕይወታቸው ስለሰጉም መሸሽ ግዴታ ሆኖባቸው ከልጆቻቸው ጋር በእግር ጉዞ ይጀምራሉ። “ቤታችንን እንኳ አልዘጋንም። ነፍሴ አውጭኝ ነበር። ከብቶቻችንን ጥለን፤ ልጆቻንን ብቻ ይዘን እስከ መንታ ውሃ ቀበሌ ድረስ በእግር ሄድን” ይላሉ የነፍሴ አውጭኝ ትግሉን ሲያስታውሱ። “ልጆቹን፣ ደካማዎችን፣ እመጫቶችን ይዞ ሕዝቡ በለቅሶ እየጮኸ ተሰደደ።”  

“እኛ ነን የተረፍነው እንጂ በቡለን ወረዳና፣ በጋሊሳ ቀበሌ ያለው ዘመድማ አልቋል” ይላሉ ወ/ሮ መልኪቱ።

አንድ ወር ቻግኒ ተፈናቅለው ከቆዩ በኋላ የጸጥታ ኃይሎች መግባታቸውን ተከትሎ “የመጣው ይምጣ በሚል” ሲመለሱ 11 የቀንድ ከብቶቻቸው ተዘርፈው አገኟቸው።

ወ/ሮ አበዜ አህመድ 1970ዎቹ መጀመሪያ ከጎንደር አካባቢ ወደ መተከል መጥተው በግብርና ስራ የተሰማሩ የዛሬዋ ተፈናቃይ ናቸው። ስድስት ልጆቻቸውን ይዘው ከሳስማንደን ቀበሌ በመሸሽ በሕይወት በመትረፋቸው ያመሰግናሉ። ሀብታቸው ዶግ አመድ በመሆኑ መልሶ ለመቋቋም እጃቸው ባዶ ነው። “ቤታችን ተቃጥሏል። መግቢያ የለኝም። ከልጆቼ ጋር አራት ቤት ነው የተቃጠለብን። መመለስን ብመኝም የት እናገኘዋለን? ሲሉ ኦና የሆነባቸውን የወደፊት ተስፋቸውን ይናገራሉ።

ወ/ሮ ጀማነሽ ቶሎሳም በሺዎች ከሚቆጠሩ የመተከል ተፈናቃዮች አንዷ ናት። “ንብረታችን ወድሟል፤ እኛ ሮጠን ነፍሳችን ወጣ። ንብረታችን እንደተዘራ፣ የተዘራው ሳይታጨድ፣ የተከመረው ሳይወቃ መና ሆኖ ቀረ” ትላለች።

በመተከል የደረሰውን ሰብዓዊ ቀውስ በአሀዝ እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር ከባድ ሆኗል። ለቆጣሪውም ከግድያው አይነትና መጠን ጋር ተያይዞ የተወሳሰበ መስሏል። በወርሃ ጥር አጋማሽ 2013 ዓ.ም. “ለመተል ድምፅ እንሁን” ያለ ተቆርቋሪ ቡድን በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ከ2012 ዓ.ም. መገባደጃ (ጳጉሜን) እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ በግርድፉ አንድ ሺህ ዜጎች ተገድለዋል ብሏል።

ቡድኑ የቀውሱን ልክ ለማሳየት በሰጠው መግለጫ ታሪካቸውን እንዲያጋሩ ያደረጋቸው ግለሰብ፤ ታሪካቸው ለመተከል ቀውስ መስታወት ነገር ግን የአያሌዎች የጋራ ህመም እንደሆነ ተናግረዋል። ታሪካቸውን በጊዜው ያጋሩት አቶ አለሙ የተባሉት ግለሰብ በአካባቢያቸው ከተነሳው ጥቃት ቤተሰቦቻቸው እንዲያመልጡ በመኪና ወደ ቻግኒ ቢሸኟቸውም ዳግም በአይነ ውሃ ማየት የቻሉት ግን አስከሬናቸውን ብቻ ነው። አቶ አለሙ ሦስት ልጆቻቸውና የስድስት ወር ነፍሰ-ጡር የሆነችው ባለቤታቸው ከአንድ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ሙሉ ንፁኃን ጋር ተገድለውባቸዋል። ሳግ በተሞላ ድምፅ “ሁለት ወንድ ልጆቼ፣ አንድ ሴት ልጄና ባለቤቴ የስድስት ወር እርጉዝ ነበረች። አረዷቸው በቃ” በማለት ኃዘናቸውን ይገልፃሉ። አገዳደላቸው እጅግ ዘግናኝ እንደነበር ነጥብ በነጥብ ሲያስረዱ፤ “የሚሰማ ካለ ብዬ ነው እዚህ መጥቼ የምናገረው” አሉ በሀዘን በተሞላው አንደበታቸው እንባቸው እያቀረረ።

የመተከል ችግር ለምን ተወሳሰበ? 

ከአገር ቤት እስከ ጎረቤት የረዘሙ እጆች

የመተከልን ውጥንቅጥ ለማረቅ ያልተመላለሰ መሪ የለም ማለት ይቻላል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ሠላምን ለመፈለግ ቢወጡ ቢወርዱም የባለስልጣናቱን እግር ጠብቀው ጥቃቶች ተሰንዝረዋል። ዜጎችን በማስታጠቅ ራሳቸውን እንዲጠብቁ ውሳኔ ከማሳለፍ ጀምሮ ዞኑ በተቀናጀ ኮማንድ ፖስት እንዲተዳደር ከተደረገ እነሆ ሁለት ዓመታት እየተቃረቡ ነው። በዞኑ ዋና ከተማ ግልገል በለስና በወረዳዎች መከላከያን ጨምሮ ለመለየት በሚያስቸግር ሁኔታ የሁሉም ክልል ልዩ ኃይሎች አሉ ማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ተሰማርተዋል። (የሌሉ የክልል ልዩ ኃይሎችን መቁጠር ይቀላል።)

የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት ፖለቲከኛ ዶ/ር መብራቱ አለሙ ለቀውሱ እዚህ መድረስ በዋነኝነት ከሚጠቀሱ ነገሮች መካከል አሰፍስፈው የሚጠብቁ የፖለቲካ ኃይሎች መበራከታቸው ነው ይላሉ።

“በዋነኝነት፣ ችግሩ አመራር ውስጥ ሆኖ ችግር ጠንሳሽ አለ። ልክ በሬ የሰረቀው ሠው ራሱ ማነው የሰረቀው ብሎ አብሮ እንደመፈለግ ማለት ነው። ስለዚህ በመንግስት አመራር ውስጥ ያሉ አካላት እጃቸው ካለበት ችግሩ አይፈታም። ሁለተኛ በዚህ ግጭት ውስጥ የሚያተርፉ አካላት አሉ። ኮንትሮባንድ የሚነግዱ፣ ጥይት የሚነግዱ፣ ወርቅ የሚነግዱም አሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎም ተጀመረ የተባለውም ለውጥ እዚያ አልደረሰም። እና እነዚህ ነገሮች ተደማምረው ችግሩ እንዳይፈታ አድርጓል” ይላሉ።

ተገፋን የሚሉ ማሕበረሰቦችን (በዋናነት የጉሙዝ ማሕበረሰብን) ያኮረፉ የጉሙዝ ፖለቲከኞች ‘አክራሪነትን’ ከጠብ-መንጃ ጋር አስታጥቀዋል የሚሉ ወገኖች አያሌዎች ናቸው። የቀውሱ ተዋንያን ከአገር ቤት እስከ ጎረቤት መገኘታቸው ችግሩ ውስብስብ እንዲሆንና እንዲገዝፍ አድርጓል በማለት የክልሉ መንግስት ይናገራል።

መንግስት እንደሚለው የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (የጉሕዴን) ታጣቂ ቡድን በተለያዩ አካላት ተደግፎ መተከልን የጦር አውድማ ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል። በመተከል ቀውስ ጣቱ የማይቀሰርበት የአገር ውስጥና የጎረቤት ኃይል የለም ማለት ይቻላል። ሕወሃት፣ ኦነግ ሸኔ፣ ሱዳንና ግብፅ እጃቸው በሰሜን ምስራቃዊዋ ዞን ረዝሟል የሚሉ በርካታ ትችቶች ይሰነዘራሉ። 

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ፤ መተከልን የግጭት ቀጠና ለማድረግ ቆርጠው የተነሱ ኃይሎች መበራከት የችግሩ ስረ መሰረት ነው ይላሉ። ከእነዚህ ኃይሎች ውስጥም አንዱ ነው የተባለው ሕወሃት ወጣቶችን፤ ግለሰቦችን በማደራጀት የብሄር ይዘት ያላቸው ጥቃቶች እንዲሰነዘሩ አድርጓል ይላሉ። ኃላፊው ሠላም ለማስፈን ለክልሉ መንግስት ለምን ፈተና ሆነ ለሚለው ሦስት ምክንያቶችን ያቀርባሉ።

እንደ አቶ አብዮት አስተያየት የታላቁ የህዳሴ ግድብ መተከል ላይ መገንባት ዞኑ ኢላማ ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ ከፊት የሚመጣ ነው። ይህም ሱዳንና ግብፅ ከመሰሉ ጎረቤት አገራት ጋር ጠላት ጥምረት እንዲፈጥር በማድረግ ጥቃቶች እንዲፈፅሙ በር ስለመክፈቱ ይናገራሉ።

ይህን ምክንያት አስረግጠው የሚደግሙት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ “ሸኔን” የመሰሉ የአገር ውስጥ ኃይሎችና የጎረቤት አገራት እጃቸው እንዳለበት የቃልና የሰነድ ማስረጃ መኖሩን ይናገራሉ።

“ስብሰባ አብረው ነው የሚያደርጉት፤ ሎጀስቲክም ጥይትም ይተጋገዛሉ” የሚሉት አስተዳዳሪው፤ ቡድኑ ከወለጋ ተሻግሮ የመተከልግጭት ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ይጠቅሳሉ።

የውጭ እጆችን በተመለከተ አቶ ጋሹ ዱጋዝ ሱዳን ለግብፅ ድልድይ ሆኗ ትጥቅ እያቀበለች ነው ሲሉ ይከሳሉ። “ሱዳን ከግብፅ ቀጥታ መሳሪያና ገንዘብ ትቀበላለች። ከዚያ መሳሪያውን ሽፍቶች በድንበር በኩል ተቀብለው ጥቃት እየፈፀሙበት ነው” ሲሉ ችግሩ ዙሪያ መለስ እንደሆነ ይናገራሉ። ለዚህም ማስረጃው ታጣቂዎቹ የሚጠቀሙት “የቡድን መሳሪያ፣ ጸረ ተሽከርካሪና ጸረ ፈንጅዎች የግብፅ ስሪት ናቸው” የሚሉት አስተዳዳሪው ይህንን ከማረክናቸው መሳሪያዎች መረዳት ችለናል ይላሉ።

የክልሉ የሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ለተወሳሰበው የመተከል ችግር በሁለተኛነት የሚጠቅሱት መንስኤ የአስተዳደሩ በሰርጎ-ገቦች መበረዝ ነው።

“እዚህ አካባቢ እስከ ታችኛው የፖለቲካ መዋቅር ጭምር እየተፈጠረ ያለው ግጭት ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እጃቸው የነበረበት የፖለቲካ አመራሮች ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ነበሩ። በጸጥታው መዋቅር ጭምርም ነገሮችን በሚፈለጉበት ጊዜና ወቅት ለማስቆም ሰርጎ ገብነት አስቸግሮን ነበር። ከጸጥታው መዋቅር ጋር አብረን የመከርንበት መረጃ ቀድሞ ለጠላት የሚወጣ ከሆነ ነገሩ እየተወሳሰበ የሚሄድበት ሁኔታ ቀላል አልነበረም” ይላሉ።

በጥቃቶቹ እጃቸው አለበት አሊያም ኃላፊነታቸውን ቸል ብለዋል የተባሉ ከፌደራል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያሉ አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል። በታህሳስ አጋማሽ 2013 ዓ.ም. የቀድሞው ሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ (የአሁኑ ሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር) ሚኒስትር ዴኤታና የቀድሞውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደርን ጨምሮ 10 የሚደርሱ የክልሉና የዞን አመራሮች በሕግ ጥላ ስር እንዲሆኑ መደረጉ አይዘነጋም። 50 የሚደርሱ የወረዳ አመራሮችም ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርጓል።

አመራሩ ከታጣቂዎች ጋር ያለው “ቤተሰባዊ ግንኘነት” መረጃ እንዲሾልክ አለፍ ሲልም የመንግስት ኃይሎች ያደፈጠ ኃይል እንዲጠብቃቸው አልያም ታጣቂዎቹ እንዲሸሹ ስለማድረጉም አስተዳዳሪው አቶ ጋሹ ዱጋዝ ይናገራሉ።

ሌላው ኃላፊው ሠላም ለማስፈን እክል ሆኗል ያሉት “ፅንፈኞች” መበራከታቸውን ነው። “መተከል የእኛ ርስት ነው” የሚሉ ወገኖች ታጣቂዎች ትጥቃቸውን እንዲያፋፍሙና የሞት ሽረት ትግል እንዲያደርጉ ማስቻሉን የሚጠቅሱት ኃላፊው፤ ይህን ሁኔታ አላባራ ላለው ለመተከል ውጥንቅጥ እንደ አንድ ምክንያት ያነሱታል።

የጉሕዴን ታጣቂዎች

መተከል ላይ አነጣጥረዋል የሚባሉት የጉሕዴን ታጣቂዎች እነማን ናቸው? ለምንስ መንግስትን ፈተኑት?

ጉሕዴን እስከ ጥር 2013 ድረስ ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሰውነት የነበረው ድርጅት ነበር። ይሁን አንጂ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባና የምርጫ አዋጅ መሰረት 30 የሚሆኑ ፓርቲዎችን ሲሰርዝ ጉሕዴን አንዱ ነበር። የተሰረዘበት ምክንያትም ከመስራች አባላት ፊርማ ጋር በተያያዘ በሰነዶች ላይ ማስተካከያ እንዲያደርግ ተጠይቆ ማስተካከያ ባለማድረጉ መሆኑን ቦርዱ አሳውቋል።

የንቅናቄው ሊቀ-መንበር የነበሩት አቶ ግራኝ ጉደታ ባለፈው ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. ግንቦት 24 ካማሺ ዞን በነበረው ግጭት “አመፅ ለማነሳሳት ሞክረዋል” በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል። ሐምሌ 16 በነጻ መለቀቃቸውን የነገሩንና ከሚኖሩበት ካማሺ ዞን በባለቤታቸው ተንቀሳቃሽ ስልክ ያገኘናቸው ሊቀ-መንበሩ፤ የሚቀርብባቸውን ውንጀላ አጣጥለዋል። “ጉሕዴን ታጣቂ የለውም” ሲሉ በመተከል ቀውስ እጃቸው እንደሌለበት የሚናገሩት አቶ ግራኝ፤ “በስማችን የሚጠቀሙና መንግስትም የእናንተ ታጣቂዎች ናቸው የሚለን ታጣቂዎች አሉ” ይላሉ። እርሳቸው እነዚህን ታጣዊዎች “የጉሙዝ ታጣቂዎች” ሲሉ ይጠሯቸዋል።  

“ንጹሀን መጨፍጨፋቸውን እናወግዛለን። እናዝናለንም። ማንም ዜጋ መሞት የለበትም። የመተከል ችግር መነሻው በገለልተኛ አካል መጣራት አለበት። ይህ ሲሆን ነው እውነቱ የሚወጣው። ይህንንም እየጠየቅን ነው” ይላሉ።

በ2006 ዓ.ም. በሠላማዊ መንገድ ለመታገል ንቅናቄውን ስለመመስረታቸው የሚያወሱት አቶ ግራኝ፤ መብታቸውን ማስከበር የፈለጉ የጉሙዝ ሕዝቦች (አባላቶቻቸውን ጨምሮ) በዋናነት የመንግስት ሠራተኞች፣ መምህራን፣ የጤናና የግብርና ባለሞያዎች ጫካ መግባታቸውን ይመሰክራሉ። አንድ ወር ተኩል ታስረው የተፈቱት ሊቀ-መንበሩ በአጠቃላይ ቀውሱን ሲገልፁ “ሕዝባዊ አመፅ” ይሉታል። ለዚህም ምክንያት ሲያቀርቡ ታጣቂዎቹ ለዓመታት ትምህርት፣ ጤናና የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ “የአመለካከትና የውስንነት ችግር አለባችሁ” እየተባሉ የተበደሉ ናቸው፤ እናም አሁን ይህን መብታቸውን ለማስከበር ትጥቅ አንግበዋል ይላሉ።

ከሕወሃት ጋር አላቸው ስለሚባለው ግንኙነትም “ጉዳዩ በፌደራሊስት ኃይሎች ከ20 ከሚልቁ ፓርቲዎች ጋር ያደረግነው ጥምረት ሲሆን መጋነኑ አግባብ አይደለም” ባይ ናቸው።

ከመተከል አስተዳደር ባገኘነው መረጃ ታጣቂ ቡድኑን “ጣሂር ትግሬ” የሚባል ሠው (በቅርብ ወራት በህመም ሕይወቱ እስኪያልፍ ድረስ) ይመራው ነበር። አቶ ግራኝ ከመሪው ጋር እውቅና ካላቸው ላነሳንላቸው ጥያቄ ስለ ግለሰቡ በስም ሲነገር እንደሚሰሙና መሪው ጉሙዝ ሳይሆን ሱዳናዊ መሆኑንም ገልጸዋል።

መንግስት ታጣቂ ቡድኑ ከሌሎች ኃይሎች ጋር በመጣመር፤ ወጣቶችንም በመመልመል ክልሉን እያመሰ እንደሆነ ይከሰሳል። የጉሙዝን ማሕበረሰብም ስለማገቱ የሚነገርለት ቡድን በሚጠቀመው የጦር ስልት (የጨበጣ ውጊያ) እና በሚያገኘው ድጋፍ ምክኛት በቁጥጥር ስር ለማዋል ፈተና ሆኗል። 

አቶ ግራኝ ጉደታ ከመንግስት ጋር የተጀመሩ ድርድሮች መሬት ቢረግጡ መፍትሄ ማምጣት ይቻላል ባይ ናቸው። ለዚህም የተዘጋጀ “ሰነድ” አለ የሚሉት ሊቀ-መንበሩ፤ አሁን ግን ወደ ጎን ተብሏል ይላሉ ወታደራዊ እንቅስቃሴ መበርታቱንና ይፈታሉ የተባሉ የፓርቲያቸው ሰዎች አለመፈታታቸውን በማስታወስ።

የገፈት ቀማሾቹ ውጣ ውረድ

“ከረሀብና ከጦርነት የቱ ይብሳል?”

ከግልገል በለስ በ56 ኪ/ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ድባጤ ወረዳ ለወራት ምዕራባዊና ሰሜናዊ ክፍሏ “በጉሕዴን ታጣቂዎች” ደቡባዊው ደግሞ “በሸኔ” ተይዞ ነበር። ከሁለት ወራት በፊት መከላከያ አዲስ ኃይል አስገብቶ ሰራው በተባለ ኦፕሬሽን ወረዳዋ “ነፃ” ብትወጣም የሠላም እጦት መከራው ግን እንደቀጠለ ነው።

መንግስት አሁን በመተከል አንጻራዊ ሠላም እንዳለ ይናገራል። ይህን ዘገባ ለመስራት ወደ መተከል ባቀናንበት ወቅት ታጣቂዎች ላይ ኦፕሬሽን እየተካሄደ የነበረ ሲሆን፤ ነዋሪዎችም በስጋት መናጥን ከኑሮ ውጣ ውረዱ ጋር አዲሱ መደበኛ ሕይወታቸው አድርገው እየገፉ ናቸው።

በዞኑ በአራት መጠለያ ማዕከላት 280 ሺህ ተፈናቃዮች አሉ። ይህም ማለት ከግማሽ የሚልቀው የዞኑ ነዋሪ ከቀዬው፤ ጎጆውን ከቀለሰበት አካባቢ ሳይወድ በግዱ እንዲለቅ ሆኗል ማለት ነው።

ጀማነሽ ቶሎሳ ሰባት ልጆቿን ይዛ በድባጤ ከተማ በተከራየቻት አንድ ክፍል ቤት ትኖራለች። መጠለያ ጣቢያዎች ሴት ልጅን ለአደጋ አጋላጭ ናቸው በሚል ተከራይቶ ኑሮን መግፋቱን ከመረጠች ወራቶች ተቆጥረዋል።  እንጨት በመልቀምና ውሃ በመቅዳት በምታገኘው አነስተኛ ገቢ የቤት ኪራይ ትከፍላለች።

ባለው “አንጻራዊ ሠላም” የአካባቢው መንግስት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እየወተወተ ነው። ምርጥ ዘር በመስጠትም ወደ ቀደመ ኑሯቸው ይመለሱ ዘንድ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ጀማነሽና ሌሎች ግን እስካሁን ስጋት ውስጥ ናቸው። በጓሮዋ በቆሎ ዘርታ ወደ ከተማ የተመለሰችው ጀማነሽ፤ “ዘራነው እንጂ አንበላውም” ትላለች በቀበሌያቸው ዝርፊያ እንደተበራከተ በመናገር።

“መንግስት ወደ ቀያችሁ ካልተመለሳችሁ እርዳታ አይሰጣችሁም ብሎ እያስፈራራን ነው” የምትለው ጀማነሽ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ቀዬዋ ለመመለስ የተስፋ ጭላንጭል ማጣቷን ታስረዳለች። እማማ አበዜም “ስጋታችንን ጥለን ብንሄድ እንኳ መውደቂያ የለንም” ይላሉ፤ ዶግ አመድ የሆነው ቤታቸውን ዳግም ለመቀለስ እንደ ሞት ቢከብዳቸው።

ላለፉት ሁለት ዓመታት እርሻ ባለመታረሱ የምግብ ፍላጎቱ ከፍ ብሏል። የኑሮ ውድነት ሸክም እየከበዳቸው እንደሆነ ከሚያነሱት ነዋሪዎች ውስጥ ወ/ሮ መልኪቱ ወርቁ አንዷ ሲሆኑ “እህሉ እሳት ሆነ” ይላሉ። 

“ምን እንብላ? ልጆቹ ምን ይብሉ? ከረሀብና ከጦርነት የቱ ይብሳል?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

ከመንግስትና ከረድኤት ድርጅቶች በሚቀርበው እርዳታም ደስተኛ ያልሆኑ አያሌዎች ናቸው። ይህን ችግር እንደሚረዱት የሚናገሩት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ “ትናንት 10 እና 15 ሄክታር መሬት ያርሱ የነበሩ፣ አልፎ ተርፎም ለገበያ ሲያቀርቡ የነበሩ ናቸው። ግን ዛሬ በመንግስት እጅ ብቻ መረዳቱ አያረካቸውም” ይላሉ።

በዚህ ቀውስ ገፈት እየቀመሰና የእሳት እራት እየሆነ ያለው የጉሙዝ ማሕበረሰብ ነው። ማህበረሰቡ በሁለት ኃይሎች መሀል ተወጥሮ ይገኛል። የሰላምና ደህንነት ኃላፊው አቶ አብዮት አልቦሩ ከቀውሱ ሰለባዎች ዝርዝር ውስጥ ክፉኛ የተጎዳ ሲሉ የጉምዝ ማሕበረሰብን ያስቀምጡታል። እንደ አቶ አብዮት አስተያየት የማህበረሰቡ አባላት እንደ ጤና ካሉ ማሕበራዊ ግልጋሎቶች ተገለው ጫካ እንዲገቡ በታጣቂዎች ተገደዋል፤ ይህን ሀሳብ ነዋሪዎችም ይጋሩታል።

በ90 ቀናት መተከልን ነፃ ማውጣት

“ስለ መተከል እየዘመርን እስከመቼ?”

“መተከልን ከታጣቂዎች ለማፅዳት” የሦስት ወራት ቀነ ገደብ ወጥቷል። ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስራውን በማጣመር መተከልን ነፃ ለማውጣት መወጠኑን አስታውቋል። ወታደራዊ ኦፕሬሽን በማከናወን “እጅ አንሰጥም ያሉ ታጣቂዎች” ላይ እርምጃ መውሰድ አንደኛው የእቅዱ መርሀ-ግብር ነው የተባለ ሲሆን፤ ከሰኔ 2014 የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ የተጀመረው ኦፕሬሽንም ሳምንታት ተቆጥሯል።

“ከ37 እስከ 40 የሚደርሱ ቀበሌዎች በጠላት እጅ ናቸው” የሚሉት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሠላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት፤ “ከዚህ በኋላ ዜጎች ማሕበራዊ እረፍት ማጣታቸው ይበቃል ብለን ቆርጠን ተነስተናል። ስለ መተከል ችግር እድሜ ዘላለማችንን እየዘመር አንኖርም” ይላሉ።

ዘገባውን ለማሰናዳት በአካባቢው በተገኘንበት ወቅት ያለውን ይህን ሁኔታ መገንዘብ የቻልን ሲሆን ነዋሪዎችም ተልዕኮው እንዲሳካ ያላቸውን ፍላጎትና ስጋትም አጋርተውናል። ይህ ቢሆንም ቅሉ፣ ታጣቂዎች የጫካዎቹን መግቢያና መውጫ ማወቃቸውና በውጊያ የበላይ ሆነው መታየታቸው በአካባቢው አሁንም ስጋት እንዲያንዣብብ አድርጓል።

የሰላምና ደህንነት ኃላፊው እንደሚሉትም ታጣቂዎች የጨበጣ ውጊያን መምረጣቸው “የህግ ማስከበሩን እርምጃ” በቶሎ እንዳይቋጭ አድርጓል።

“ሕዝቡን ከጠላት እጅ መንጠቅ” ደግሞ እንደ አስተዳዳሪው ገለፃ ትልቁ የፖለቲካ ስራ ነው። የጉሙዝ ማሕበረሰብ ከአኗኗር ዘይቤው ጋር ተያይዞ በአብዛኛው በገጠራማው የዞኑ አካባቢዎች የሚኖር ነው። ኦፕሬሽን እንደ ልብ እንዳይሰራ ታጣቂዎች ሕዝቡን አፍነው በመያዝ እንደ ጋሻም እየተጠቀሙበት መሆኑን የዞኑ አስተዳዳሪ አልሸሸጉም። ይህም በመሆኑ ሕዝቡን ከታጣቂዎች የመነጠል ስራ የፖለቲካ አመራሩ እየሰራ ነው ብለዋል። እንደ ኃላፊው ገለፃ “ነፃ በወጡ ቀበሌዎች ሕዝብ በማወያየት የፈረሰውን መዋቅር የመመለስና ሚሊሻ በማደራጀት የጥበቃ ስራ በመሰራት ላይ ነው”።

ከችግሩ ስፋትና ከተዋንያኑ አንጻር የተቆረጠው ቀን ምን ያህል በቂ ነው?

አቶ አብዮት “ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አይደለም። ሰርጎ ገቦችን አጽድተናል። ነገር ግን አሁንም በተለይ በፖለቲካ አመራሩ ውስጥ አይኖሩም ማለት አይደለም። ግን የተሻለ ሁኔታ ላይ ነን” ሲሉ ቀውሱን በአጭር ጊዜ ለመፍታት ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ይናገራሉ። የሴራዎች መቀነስ፣ የተደራጀ የሚሊሻ ኃይል መገንባትና ማሕበረሰቡ (ጉሙዝ) ወደ ሠላም ለመመለስ እያሳየው ያለው ቁርጠኝነት “ተስፈኛ” እንዲሆኑ አድርጎኛል ባይ ናቸውም።

ከምድረ ገነትነት ለብዝኻ ነዋሪዎቿ ሲኦል የመሰለችው መተከል ወደ ቀደመው ፀጋዋ ለመመለስ እርቀ-ሠላም ላይም አይኗን ጥላለች። በደህንነት ስጋት ተሸብባ፣ በምጣኔ-ሀብትም ደቃ የነገን የተስፋ ጀነበር መውጣት የምትጠባበቅም ናት፤ መተከል። እንደነ በለጤ ተሾመ ያሉ ተጎጂዎችም የነገን ደህና መሆን በተስፋ እየጠበቁ ናቸው።

አስተያየት