መጋቢት 17 ፣ 2014

ነገ ሰላማዊ ሰልፍ እንደማይካሄድ የደብረ ማርቆስ እና የባህርዳር ከተማ ጸጥታ ቢሮዎች ቢያሳውቁም አዘጋጆቹ የተቀየረ ነገር የለም ብለዋል

City: Gonderዜና

የባህርዳር ፀጥታ ቢሮ በመግለጫው “ከከተማ አስተዳደሩ ዕውቅና ውጭ የሚደረግ ማንኛውም ሰልፍ ላይ ለሚደረስ ጥፋት ከተማ አስተዳደሩ ኃላፊነት አይወስድም።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ነገ ሰላማዊ ሰልፍ እንደማይካሄድ የደብረ ማርቆስ እና የባህርዳር ከተማ ጸጥታ ቢሮዎች ቢያሳውቁም አዘጋጆቹ የተቀየረ ነገር የለም ብለዋል
Camera Icon

ፎቶ፡UNESCO

የ12ተኛ ክፍል ፈተና ውጤትን ተከትሎ ነገ እሁድ መጋቢት 18 የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በአስተዳደር ከተማቸው እንደማይካሄድ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር እና የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ጸጥታ ቢሮዎች በዛሬው እለት አሳውቀዋል።   

የባህርዳር ፀጥታ ቢሮ በመግለጫው “ከከተማ አስተዳደሩ ዕውቅና ውጭ የሚደረግ ማንኛውም ሰልፍ ላይ ለሚደረስ ጥፋት ከተማ አስተዳደሩ ኃላፊነት አይወስድም። በመሆኑም የከተማችን ነዋሪዎች፣ ተማሪዎችና መምህራን ከእንደዚህ ዓይነት ተግባር ራሳችሁን በማቀብ የክልሉ መንግሥት የጀመረውን ትግል የመጨረሻ ውጤት በትእግስት እንድትጠብቁ በጥብቅ እናሳስባለን” ብሏል።

የደብረማርቆስ ጸጥታ ቢሮ በበኩሉ በሰላማዊ ሰልፍ ሐሳብን መግለጽ ሕገ-መንግሥታዊ መብት መሆኑን አስቀምጧል። በተጨማሪም ‹‹የክልላችን መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ባለበት ወቅት፣ በክልላችንና በከተማችን ከአለው ወቅታዊ የፀጥታ ስጋት እንዲሁም የፀጥታ ኃይላችን በሌሎች ወቅታዊ የፀጥታ ስራ ስምሪት ላይ የሚገኝና ጥበቃ ለማድረግ ጫና ያለበት በመሆኑ ሰልፉ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን ስለሆነ የከተማ አስተዳደሩ ሰልፉን እውቅና ያልሰጠና በሚፈጠረው ማንኛውም ችግር ኃላፊነት የማይወስድ መሆኑን ይገልጻል›› ብሏል።

የባህር ዳር ከተማ እና የደብረ ማርቆስ ፀጥታ ቢሮዎች በመግለጫቸው ይህንን ይበሉ እንጂ የሰልፉ ጠሪ የሆነው የአማራ ተማሪዎች ማኅበር (አተማ) ፕሬዝዳንት አቶ እሸቱ ጌትነት ‹‹ሰልፉ አይቀርም›› ብለዋል። አቶ እሸቱ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት “ነገ የተጠራው ሰልፍ ይካሄዳል”

የባህር ዳር እና የደብረማርቆስ ከተማ ፀጥታ ቢሮ የሰልፍ ጥሪዎች በተለያዩ መንገዶች መሰራጨታቸውን ተከትሎ “በጉዳዩ ላይ ውይይት እና ምክክር ከአካሄደ በኋላ ከተለያዩ ሀገራዊ እና ክልላዊ እንዲሁም ከከተማችን ነባራዊ ሆኔታ በመነሳት በተለይም ከደህንነት ሰጋት አኳያ ተመዝኖ ሰልፉ በከተማችን ለጊዜው መካሄዱ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ ዕውቅና የሰጠው ስልፍ የለም” ብሏል በመግለጫው።

ሀገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ የ12ኛ ውጤትን ተንትኖ የውሳኔ ሀሳብ ካቀረበ በኋላ ትምህርት ሚኒስቴር ውጤቶቹን ተንትኖ ፍትሐዊ የኾነ የመቁረጫ ነጥብ መወሰንና ግልጸኝነት የመፍጠር ኃላፊነት አለበት። ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች የአማራ ክልል ተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ በመሆኑ ከፍተኛ ድንጋጤ እና ቁጣ ፈጥሯል ያለው መግለጫው አስራ አንድ አባላት ያሉት ግብረ-ኃይል ወደ ትምህርት ሚንስትር የተላከ ሲሆን በሂደት ላይ መሆኑን ገልጿል።

የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የማለፊያ ነጥብ ይፋ ከተደረገ በኋላ በአማራ ክልል ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በርካታ ተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት በመመዝገቡ ቅሬታዎች መበራከታቸው ይታወቃል። ከእዚህ ቀደም የክልሉ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምም ጭምር ለፌደራል መንግስት ጥያቄ አቅርበዋል።