መጋቢት 18 ፣ 2014

ከ7 በላይ የተለያዩ ማሽኖች የሰሩት የፈጠራ ባለሞያዎች በሐዋሳ

City: Hawassaማህበራዊ ጉዳዮች

ከሃይላንድ እና ከጄሪካን መፍጫ ማሽን በተጨማሪ በ30 ደቂቃ ውስጥ ከሁለት እስከ ሰባት ሺህ ሊትር ፈሳሽ ሳሙና ማምረቻ ማሽን፣ ደረቅ ሳሙና ማምረቻ፣ ፕላስተር መስሪያ ማሽን ሰርተዋል።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ከ7 በላይ የተለያዩ ማሽኖች የሰሩት የፈጠራ ባለሞያዎች በሐዋሳ
Camera Icon

ፎቶ፡ ኢያሱ ዘካርያስ

ውሃ መያዣ የፕላስቲክ ጠርሙስ፣ ጀሪካን እና ሌሎች በቀላሉ የማይበሰብሱ የፕላስቲክ ምርቶችን መልሶ መጠቀም እንዲቻል ፈጭቶ የሚያዘጋጅ ማሽን በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ሥራቸው ነው። የቀረጥ ክፍያን ሳይካተት ከ200ሺህ ብር በላይ በሆነ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሐገር ውስጥ የሚገባውን ማሽን ሐገር ውስጥ ማምረት የቻሉት ወጣቶቹ የሀገር ውስጡን ምርት ከ100ሺህ ብር በታች በመሸጥ ላይ እንደሚገኙ ነግረውናል።

የፕላስቲክ ምርቶችን የሚያደቀው ማሽን ዋነኛ ሥራ ፕላስቲክን መልሰው ጥቅም ላይ ለሚያውሉ ፋብሪካዎች ግብአት ማዘጋጀት ነው። የውሃ ፕላስቲክ፣ ጀሪካን እና ሌሎችንም የፕላስቲክ ምርቶች ወደ ደቃቅ ቁርጥራጭ የሚቀይረው ማሽኑ ወፋፍራም ገመዶችን፣ የጅንስ ጨርቅ ከሚያመርቱ ፋብሪካዎች የተዘጋጀ ግብአት እንደሚሆን ሰምተናል። በተጨማሪም ፕላስቲኩን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች በድጋሚ የፕላስቲክ ጠርሙስ ወይም ጀሪካን ሊያመርቱበት ይችላሉ።

“የፕላስቲክ ምርቶችን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ በተጨማሪ ለአካባቢ ጥበቃ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው” በሚለው በአቶ ጋሻው ኤዶኦ መሪነት ማሽን ያመረቱት ወጣቶች ከ7 በላይ ኑሮን የሚያቀሉ፣ ችግር የሚፈቱ ማሽኖች ሰርተዋል።

ከሃይላንድ እና ከጄሪካን መፍጫ ማሽን በተጨማሪ በ30 ደቂቃ ውስጥ ከሁለት እስከ ሰባት ሺህ ሊትር ፈሳሽ ሳሙና ማምረቻ ማሽን፣ ደረቅ ሳሙና ማምረቻ፣ ፕላስተር መስሪያ ማሽን ሰርተዋል። በተጨማሪም የሊጥ ማቡኪያ፣ የዳቦ መጋገሪያ፣ ፈሳሽ ሳሙና መቀላቀያ፣ የእንጨት ቤት ተረፈ ምርት እና በቀላሉ ከ 10 ኪሎ ግራም በላይ ቡና ለመፍጨት የሚዉለዉ  ማሽን ይጠቀሳሉ።  

የተለያየ ሙያ ያላቸው አምስቱ ወጣቶች ለአንድ ዓላማ የተሰባሰቡት ከ6 ዓመታት በፊት ነበር። በ2008 ዓ.ም. “ኤልሻሎም አጠቃላይ የኤሌክትሮ መካኒካል ኢንተርፕራይዝ” በሚል ስያሜ የሚጠራ ተቋም በ24 ሺህ ብር ካፒታል አቋቋሙ። በመዋጮ የሰበሰቡትን ገንዘብ፣ የከተማው መስተዳድር የሰጣቸውን መሬት፣ ለዓመታት ያካበቱትን ቴክኒካል ዕውቀት፣ ፍላጎታቸውን አስተባብረው ወደ ሥራ ተሰማሩ። ተግባራዊ እንቅስቃሴው ግን እንደ ሐሳቡ ቀላል አልሆነላቸውም።  

የፈጠራ ስራውን ሲጀምሩ አምስት የነበሩት ወጣቶቹ ሁለቱ በተለያዩ ምክንያቶች ሥራውን ቢያቋርጡም ሦስቱ አሁንም በእንቅስቃሴ ውስጥ ናቸው። የቡድኑ አባላት በጀነራል መካኒክ እና በአውቶ መካኒክ የተመረቁ ሲሆን ከ10 ዓመታት በላይ በሙያው ላይ ቆይተዋል። 

ጋሻው ኤዶኦ ሁኔታውን ሲያስታውስ “የመጀመርያ ሥራችን የብረት በር እና መስኮት ነበር” ይላል። ከወዳደቁ ብረቶች ለአንድ ግለሰብ ከሰሩት በር እና መስኮት በማስከተል የሊጥ ማቡኪያ ማሽን መስራታቸውን ይናገራል።

የስራ ፈጠራ ባለቤት  ጋሻው "እስካሁን ከሰራነው ጄሪካን እና የሃይላንድ መፍሻ ማሽን ለሦስት ሰዎች በመስራት ያስረከብን ሲሆን ከዚህ በኋላም ቀደም ብለው የታዘዙ ሁለት ማሽኖች አሉ" ብሏል። እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለጻ ኤልሻሎም አጠቃላይ ኤሌክትሮ መካኒካል ኢንተርፕራይዝ አሁን ላይ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ  ካፒታል አለው።

 ወጣቶቹ ላበረከቷቸው ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎች 20 በላይ የምስክር ወረቀቶችን እና 3 ሜዳሊያ ከተለያዩ አካላት አግኝተዋል። የወረዳ እና የቀበሌ ማበረታቻዎችን ጨምሮ እውቅና እና ሽልማቶቹን ከሰጧቸው ተቋማት መካከል ሐዋሳ ቴክኒክ እና ሙያ ተቋም፣ ከዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ የፌደራል ኢንተርፕራይዞች ልማት፣ የሐዋሳ ከተማ መስተዳድር፣ የሲዳማ ክልል መስተዳድር ይገኙበታል።