መጋቢት 18 ፣ 2014

የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች በአብዛኛዎቹ የመንግሥት ቢሮዎች አገልግሎት አሰጣጥ መማረራቸውን ተናገሩ

City: Dessieዜና

ከሚቀርቡት ምክንያቶች መካከል መዝገብ ቤት ታሽጓል፣ ማህተም በወረራው ወቅት ስለተዘረፈ እስኪቀረጽ ጠብቁ፣ ፋይል በማጣራት ላይ ስለሆንን ትንሽ ጠብቁ፣ የሚሉ እንደሚገኙበት ሰምተናል።

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች በአብዛኛዎቹ የመንግሥት ቢሮዎች አገልግሎት አሰጣጥ መማረራቸውን ተናገሩ
Camera Icon

ፎቶ፡ Kombolcha City communication

በመንግሥት ሴክተር መስሪያቤቶች በሙሉ አቅማቸው በመስራት ላይ ባለመሆናቸው የእለት ተእለት እንቅስቃሴአቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳሳደረ የኮምቦልቻ ነዋሪዎች ተናገሩ። ለአዲስ ዘይቤ ሐሳባቸውን የሰጡት የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት የመንግሥት ሰራተኞች በሥራ ሰዓታቸው የሥራ ገበታቸው ላይ ስለማይገኙ ነዋሪውን ለእንግልት እና መጉላላት ዳርገዋል።

በኮምቦልቻ ከተማ ልዩ ስሙ “ቁጠባ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩት ወ/ሮ የተመኝ ኃ/ማርያም በተነሳው ርዕሰ-ጉዳይ ላይ በሰጡት አስተያየት “የከተማ አስተዳደር ሕንጻ ሹም ቢሮ መመላለስ ከጀመርኩ አንድ ወር አልፎኛል” ብለዋል። ከሥራ ሰዓት መግቢያ ቀድመው የሚመለከታቸውን የክፍሉን ሰራተኞች ለማግኘት ቢሞክሩም እንዳልተሳካለቸው ይናገራሉ። “ከ3፡30 በፊት ቢሮ የሚገባ ሰራተኛ የለም። ቢገቡም ሥራ አይጀምሩም። ተገልጋይ ‘ለምን’ ብሎ ለሚያቀርበው ጥያቄ ምክንያት ከመደርደር በስተቀር በቂ ምላሽ አይሰጡም” ሲሉ ያጋጠማቸውን በምሬት ተናግረዋል።

ከሚቀርቡት ምክንያቶች መካከል መዝገብ ቤት ታሽጓል፣ ማህተም በወረራው ወቅት ስለተዘረፈ እስኪቀረጽ ጠብቁ፣ ፋይል በማጣራት ላይ ስለሆንን ትንሽ ጠብቁ፣ የሚሉ እንደሚገኙበት ሰምተናል።

ሌላው ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረው ቆይታ ተመሳሳይ ሐሳብ የሰጠን አግዋር ከማል ነው። "ጉዳይ ኖሮህ ወደ አገልግሎት ጽ/ቤት ስትሄድ ምን አገልግሎት ፈልገህ እንደመጣህ ጠይቆ ከማስተናገድ ይልቅ የ1 እና የ2 ሳምንት ቀጠሮ ይሰጡሃል። ለምን ብለህ የምትጠይቀው እንኳን የለም። ለበላይ አለቃ ብታመለክትም ከንቱ ድካም ነው። መፍትሄ የሚሰጥህ የለም። እንዲያውም ቂም ይያዝብህና ለሌላ ከባድ ወጪና መጉላላት ሊዳርጉህ ይችላሉ" ብሏል።

አቶ አማረ ጥላሁን በበኩላቸው “ከቀበሌ ጀምሮ እስከላይኛው የከተማ አስተዳደር ቢሮ ያለው አሰራር ተበላሽቷል። ለሙስና የተጋለጠ ነው። ከቀበሌ ማንነትን የሚገልጽ መታወቂያ ለማውጣት እንኳን መጉላላት አለ። ዛሬ ነገ እያሉ ያመላልሱሃል። መታወቂያ ማግኘት መብት መሆኑ እስከሚዘነጋ ድረስ ጉቦ ይጠየቅበታል” ብለዋል። አቶ አስማረ ንግግራቸውን ሲቀጥሉ ማዘጋጃ ቤትን ጨምሮ ሌሎች ቢሮዎችም ተመሳሳይ እንግልት መኖሩን ተናግረዋል።

“የቢሮ ኃላፊዎቹ በየቀኑ ጉዳይ አያጣቸውም። ስብሰባ ላይ ናቸው፣ ለመስክ ስራ ወጥተዋል፣ ለሥልጠና ከቢሮ ውጭ ናቸው። የሚሉ ምክንያቶች ዘወትር ይደመጣሉ” ብለዋል።

ለተነሱት ቅሬታዎች ምላሽ የሰጡት የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከድር ኢድሪስ በጦርነቱ ወቅት ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል ኮምቦልቻ አንዷ መሆኗን አንስተዋል። በመንግሥት ቢሮዎች የደረሰባቸውን ውድመት በመተካት ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነግረውናል። “ቢሮዎችን ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል ቁሳቁስ አሟልተናል” ያሉት ኃላፊው ባለጉዳዮችን አላግባብ የሚያጉላሉ ሠራተኞች እንዳሉ በግምገማ ስለደረሱበት ከደሞዝ ቅጣት ጀምሮ አስተዳደራዊ እርምጃ ስለመውሰዳቸው ይናገራሉ።

“ሰራተኛው አቅሙ በፈቀደ ያለውን ጫና ተቋቁሞ የማገልገል ግዴታ አለበት። በእኛ በኩል የቁጥጥር ማነስ መኖሩን እናምናለን። ይሄንንም አስተካክለን ሕብረተሰባችንን እናገለግላለን" ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ መሀመድ አሚን የሕብረተሰቡ ቅሬታ እውነት መሆኑን አምነው ከተማ አስተዳደር ቢሮዎች ላይ የለውን የአሰራር ችግር በዘላቂነት ለመፍታት አየተሰሩ ያሉትን ሲገልጹ "ኮምቦልቻ ከተማ ከዚህ በፊት በአንድ ማዘጋጃ ቤት ስትተዳደር የቆየች ሲሆን ከከተማዋ መስፋት ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለማስተካከል በአራት ክፍለ ከተማ በማዋቀር ስራዎችን ወደ ክፍለ ከተሞቹ እንዲወርድ እያደረግን ነው። ክፍለ-ከተሞቹም በስራቸው በርካታ የቀበሌ አደረጃጀት ስለሚኖር በየሴክተር ቢሮዎች ላይ ያለውን መጉላላት ይቀርፈዋል። በሰራተኞች ላይ  የተነሳውንም ቅሬታ ለማስተካከል እየሰራን ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አስተያየት