መስከረም 7 ፣ 2014 ዓ.ም ከ 35ሺህ በላይ ተከታይ ባለው የፌስቡክ ገጽ ላይ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ተሰራጭቷል። ከተንቀሳቃሽ ምስሉም ጋር “የአፋር ጀግኖች እና የመከላከያ ሰራዊት የሕውሃት ሃይሎችን ሲያባርሩ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ደርሶናል...” የሚል ጽሁፍ ተያይዟል። ይህ ጽሁፍ እስከተጻፈበት ጊዜ ድረስ ልጥፉ ከ 3800 ጊዜ በላይ ተጋርቷል።
ይሁን እንጂ በፌስቡክ ገጹ ላይ የተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል በአፋር ግምባር የተደረገን ወታደራዊ እርምጃ እንደማያሳይ እና ልጥፉ ሀሰት እንደሆነ ተረጋግጧል።
በጥቅምት 2013 ዓ.ም ሕውሃት በሰሜን ዕዝ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ሕውሃት ጦርነት መጀመሩ ይታወሳል። ጦርነቱ ከተጀመረ ከሶስት ሳምንታት በኋላ የፌደራሉ መንግስት መቀሌን ጨምሮ አብዛኛውን የክልሉን ከተሞች ተቆጣጥሯል። ነገር ግን ስምንት ወራትን ከፈጀው ጦርነት በኋላ የፌደራሉ መንግስት የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነትን በማወጅ በክልሉ የነበሩትን የመከላከያ እና የክልል ልዩ ሃይሎችን ከክልሉ እና ከአካባቢው አስውጥቷል።
በ ሰኔ 21 2013 ዓ.ም የፌደራል መንግስቱ የተናጥል የተኩስ አቁሙን ስምምነት ይፋ አድርጎ ከክልሉ ለቆ መውጣት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሕውሃት ሃይሎች የክልሉ ዋና ከተማ የሆነችውን መቀሌን መቆጣጠር ችለዋል። በአሁኑ ሰዓት ግጭቱ ወደ አማራ እና አፋር ክልል አጎራባች አካባቢዎች ተስፋፍቷል።
ይህ የፌስቡክ ልጥፍም ይህን በክልሉ እና አካባቢው ባለው ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ሲዘዋወር የነበረ ነው።
ይሁን እንጂ ፣ ከተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ በተወሰደ ምስል የጎግል ሪቨርስ ኢሜጅ የተገላቢጦሽ ምስል ፍለጋ እንደሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ወይም አሁን በሰሜኑ የሃገሪቷ ክፍል ካለው ግጭት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ተንቀሳቃሽ ምስሉ የተወሰደው ግንቦት 21 2013 በሳውዲ አረብያ ድንበር ላይ ጂዛን አክሲስ ተብላ በምትጠራው አካባቢ በሳውዲ እና በየመን ጦር መካከል የተደረገን ጦርነት የሚያሳይ ነው።
ስለዚህ መረጃውን ስናጣራ ባገኘነው መረጃ መሰረት በአፋር አካባቢ ከሕውሃት ሃይሎች ጋር የተደረገ ጦርነት ያሳያል ተብሎ የተስራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል ሀሰት ነው።