ጥቅምት 6 ፣ 2013

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የልጆች ቴሌቪዥን የፋይናንስ ችግር እንዳጋጠመዉ ገለጸ

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የልጆች ቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነው የኢትዮጵያ ልጆች የፋይናንስ ችግር እንዳጋጠመው ገለፀ። አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው ስማቸዉን መግለጽ…

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የልጆች ቴሌቪዥን የፋይናንስ ችግር እንዳጋጠመዉ ገለጸ

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የልጆች ቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነው የኢትዮጵያ ልጆች የፋይናንስ ችግር እንዳጋጠመው ገለፀ። አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው ስማቸዉን መግለጽ ያልፈለጉ የኢትዮጵያ ልጆች ቲቪ ሰራተኛ እንደገለጹት ከሆነ በኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ ማስታወቂያን ህግ ድርጅቱን በከባድ ደረጃ እየጎዳዉ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ህግ መሰረት ማስታወቂያ በማንኛዉም በልጆች ፕሮግራም ላይ ማስተዋወቅ አለመቻሉ ጣቢያውን ችግር ውስጥ እየከተተው እንደሆነ የገለፁት የጣቢያው ሰራተኛ ምንም እንኳን እንደ ሰላም ሚንስቴር እና የህጻናት እና ወጣቶች ሚንስቴር ያሉ የመንግስት አካላት ለቴሌቭዥን ጣቢያዉ ድጋፍ የሚያደርጉ ቢሆንም በቂ እንዳልሆነ አያይዘው ተናግረዋል፡፡

የተፈጠረዉን የፋይናንስ ችግር አስመልክተን በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸዉ የጣቢያዉ መስራች አቶ ቢንያም ከበደ በበኩላቸዉ አዳዲስ ስራዎችን እየሰራን ስለሆነ ሲጠናቀቁ አንድ ላይ ለህዝቡ እናሳውቃለን ቢሉም የኮሮና ቫይረስ ግን እንደማንኛዉም ዘርፍ እነሱም ላይ ተጽእኖ እንደፈጠረ አስረድተዋል፡፡ አያይዘዉም የተለያዩ አደረጃጀታዊ ለዉጦችን እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አዲስ ዘይቤ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ቢደዉልም መልስ ሊያገኝ አልቻለም፡፡

የኢትዮጵያ ልጆች ቲቪ በኢትዮጵያ ህፃናት ላይ የሚያተኩር የኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው፡፡ ቻናሉ በዋናነት አማርኛ ፕሮግራሞችን የሚያስተላለፍ ሲሆን አንዳንድ እንግሊዝኛ ፕሮግራሞችም በቻናሉ ላይ ይተላለፋሉ፡፡ ከጋዜጠኝነት ፣ ከሥነ ጥበባት ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፣ ከብዙኃን መገናኛ ፣ ከትምህርትና ከሌሎችም ከማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፎች በተውጣጡ ሰባት ባለሙያዎች የተመሰረተው ለሕፃናት መርሃ ግብር የሚያዘጋጀው የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ጣቢያ በ 30 ሚሊዮን ብር ኢንቬስትመንት ተመሠረቶ በአፍሪካ የሕፃናት ቀን  ክብረ በአል ላይ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

አስተያየት