የሰላም ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ከተማ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ወሎ ሰፈር ከሚባለው አንስቶ እስከ ጎርጎርዮስ አደባባይ ጎዳና የሰላም ጎዳና በማለት የማስዋብ ስራ ሊሰራ እንደሆነ አስታወቀ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ወደስልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ እየተገበራቸዉ ካሉት ስራዎች መካከል የከተማ እና የተለያዩ ቦታዎችን የማስዋብ ስራዎች ተጨማሪ ስራ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል።
አዲስ የተቋቋመው የሰላም ሚኒስተር በቅርቡ የገባበት ዋና መስሪያ ቤቱ የሚገኝበትን ወሎ ሰፈር አካባቢ ለማልማት መነሳቱን አዲስ ዘይቤ ያገኘችው መረጃ ያሳያል፡፡ ከወሎ ሰፈር እስከ ጎርጎርዮስ አደባባይ ሊሰራ የታቀደዉ ስራ የሰላም ጎዳና ተብሎ እንደሚሰየም ተገልጿል። የማልማት ስራው የመንገድ እድሳት፣ የመንገድ መብራቶች ጥገና እና ኃይል ማሻሻያ ፣ ፍሳሹን በማስተካከል ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ ያቀደ ሲሆን ከተለያዩ አካላት የተዉጣጡ ኮሚቴ ተዋቅሮም ወደስራ መግባቱን ለማወቅ ተችሏል።
በፕሮጀክቱላ ላይም የኢትዮጵያ ከተማ ልማት ባለሞያዎች ማኅበር ያለ ምንም ክፍያ ጥናት እያደረገ ሲሆን እስካሁን በተደረገ ጥናትም የመብራት እና ፍሳሽን ወጪን ሳይጨምር ከ17 ሚልዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ታዉቋል። የመብራት ትራንስፎርመሮችንም አቅም ማሳደግ እና የመንገድ መብራቶችንም በአዳዲስ መቀየር የሚመለከታቸዉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ያከናዉናሉም ተብሎ ተግልጿል።
አዲስ ዘይቤም ስለጉዳዩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መረጃ እንዳለው ጥያቄ ብታቀርብም የአስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬተሪያት ስለፕሮጀክቱ መረጃ እንደሌላቸዉ ገልፀዋል ። ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጡን ወደ ሰላም ሚኒስተር ያደረግነዉ ተደጋጋሚ ጥሪም መልስ ሳያገኝ ቀርትዋል።
ከኢትዮጵያ ከተማ ልማት ባለሞያዎች ማህበር በስራዉ ላይ እየተሳተፉ ያሉት አቶ አቤል እስጢፋኖስ በበኩላቸዉ እየተሰራ ያለዉ ስራ የአካባቢዉን ማህበረሰብ ያካተተ በመሆኑ እና የአካባቢዉ ማህበረሰብ በጋራ የሚሰሩት በመሆኑ በአየነቱ የተለየ ነው ብለዋል። አያይዘዉም የዲዛይኑ ስራ ሲጠናቅ ከአካባቢዉ ማህበረሰብ ጋርም በዲዛይኑ ላይ ዉይይት እንደተደረገ ገልጸዋል።
ከቤተ መንግስቱ አንድነት ፓርክ በመጀመር የአብሮነት እና እንጦጦ ፓርክን በስኬት ያጠናቀቀው አስተዳደሩ በጎርጎራ፣ በወንጪ እና ኮይሻ ተመሳሳይ ስራዎችን ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሳይፈቱ ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ፕሮጀክቶች ላይ ማተኮራቸው ልክ አይደልም በሚል በብዙዎች ዘንድ ነቀፋ ቢያስከትልባቸውም ኢትዮጵያ ወደፊት ለምትደርስበት ብልፅግና ምልክት ነው በሚል ለተቺዎች ጆሮ የሰጡ አይመስልም፡፡