ጥቅምት 16 ፣ 2013

የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ፣ የጤና ሚንስቴር መመርያና የጠቅላይ አቃቤ ህግ የቅጣት አወሳሰን

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎችፊቸርበብዛት እየተወራ ያለጉዳይ

የተለያዩ የአለማችን ማህበረሰቦችን አንድ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል የሰው ልጆች በህግ መመራት እና መተዳደር አንዱ ነው። የህግጋት አመጣጥ፣ ምንጭ፣ መብትን…

የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ፣ የጤና ሚንስቴር መመርያና የጠቅላይ አቃቤ ህግ የቅጣት አወሳሰን

የተለያዩ የአለማችን ማህበረሰቦችን አንድ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል የሰው ልጆች በህግ መመራት እና መተዳደር አንዱ ነው። የህግጋት አመጣጥ፣ ምንጭ፣ መብትን ማስጠበቅና አለማስጠበቅ (ብሎም መጣስም ሊሆን ይችላል) እንዲሁም ህግጋት የሚወጡበት የህግ ስርዓት ቢለያይም በአለማችን በሁሉም አቅጣጫ የሚኖሩ ህዝቦች ሁሉ በህግ እንደሚተዳደሩ የሚታወቅ ነው። 

በአንድ ህግ ዙርያ አግባብ ያለው ህግ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ አቅጣጫዎችን መስፈርቶችን መጠቀም ይቻላል። የተለያዩ ፈላስፋዎችና የህግ ባለሙያዎች ለዚህ ጥያቄ የተለያዩ መላምቶችን አስቀምጠዋል፣ ወደፊትም ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። በቀደሙት ጊዜያት የነበሩት እንደ ቶማስ አክዊናስ የመሳሰሉት ፈላስፋዎች ህግን ከአለምና ከሰው ተፈጥሮ አንዲሁም ከግብረ ገብ (morality) አንፃር ሲገልፁት እንደ ቶማስ ሆብስና ጆን ሎክ የመሰሳሉ ፈላስፋዎች በአንፃሩ ህግን ከህግ አውጪው አንፃር በመግለፅ ከሰው ተፈጥሮም ሆነ ሞራሊቲ የተነጠለ እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ የፍልስፍና ሀሳቦች በተለያዩ ተመራማሪዎችና በተለያዩ ወቅቶች መላምታቸውን አስቀምጠዋል። 

ነገር ግን ምንም እንኳን ስለህግጋት አመጣጥ፣ አግባብነትና አስፈላጊነት መመራመር የህግ የበላይነትንም ለማስፈን ሆነ ህግጋት በፍትህ ስርዓት ውስጥ ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ አስፈላጊ ቢሆንም የአንድን ህግ አግባብነት ለመለካት ግን ከላይ ከተጠቀሰው ፍልስፍና ነክ ክርክር ይበልጥ በተለያዩ አገር አቀፍ፣ አህጉራዊና አለም አቀፍ ህግጋት ላይ ይተደነገጉ መስፈርቶችን መጠቀም የበለጠ ተገቢ ነው። ህገ መንግስቱን እንደምሳሌነት ለመውሰድ (ምንም እንኳን የራሱ የሆኑ የአግባብነት ጥያቄዎች ቢኖሩበትም) በአገሪቱ የሚደነገጉ የተለያዩ በፌደራል መንግስትና በክልላዊ መንግስታት ደረጃ የሚወጡ ህግጋትን አግባብነት ለመለካት እንደካርታ እንደሚያገለግል በህገመንግስቱ አንቀፅ 9 ላይ በግልፅ ተቀምጦ ይገኛል። በተጨማሪም በተለይም ሰብዓዊ መብቶችን ከሚመለከቱ ህግጋት አንፃር የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮንቬንሽኖች፣ የማብራርያ ሰነዶችና አለም አቀፍ ውሳኔዎች የህግጋትን አግባባዊነት ለመለካት ከሚጠቅሙ ወሳኝ መለክያ መስፈርቶችን አካተው ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ መንግስት የኮሮና ቫይረስን በአግባቡ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ያስችለው ዘንድ በዓለም ዙርያ እንደተደረገው በመጋቢት ወር የተለያዩ ግዴታዎችን የያዘ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን አዋጁ ከአምስት ወራት ትግበራ በኋላ በመስከረም ወር በተጠናቀቀበት ወቅት የጤና ሚንስቴር መመርያ ማውጣቱ የሚታወቅ ነው። የመመርያውን ተግባራዊነት ለማረጋገጥም የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ቀን ባወጣው መግለጫ ማንኛውም ከላይ የተጠቀሰውን መመርያ ተላልፎ የሚገኝ ግለሰብ እስከ ሁለት አመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጣ አስታውቋል። ይህም ማለት ማስክ አለማድረግ፣ የህመሙ ምልክት በሚታይበት ወቅት ለሚገባቸው የመንግስት አካልት ማሳወቅ፣ እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ በመመርያው የተጠቀሱ በአይነታቸው ከፍተኛ ያልሆኑ ጥፋቶች በሁለት አመት የእስር ቅጣት ይቀጣሉ ማለት ነው።

የኮሮናቫይረስ ወረርሺኝና የህጋዊ ግዴታዎች አስፈላጊነት

የጠቅላይ አቃቤ ህግ መግለጫን በተመለከተ በዋነኝነት የሚጠቀሰው የጥፋቱና የቅጣቱ ተመጣጣኝነት አንፃር የሚነሱ ጥያቄዎች በተቀዳሚነት ይነሳሉ። በርግጥ እንደ ኢንስቲቲውት ፎር ሄልዝ ሜትሪክስ ኤንድ ኢቫልዌሽን (Institute for Health Metrics and Evaluation) ገለፃ ከሆነ በኢትዩጵያ እየተስፋፋ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ለመከላከል የማስክ አጠቃቀምን በተለያዩ ወቅቶች እንደቁልፍ ተለዋዋጭ (key variable) ማንሳታቸው የማስክ አግባባዊ አጠቃቀም በህግ ግዴታም ቢሆን በጤና ሚንስቴሩ በአትኩሮት ሊሰራባቸው ከሚገቡ የመከላከያ መንገዶች አንዱና ዋነኛው መሆኑን መካድ አይቻልም። 

አዲስ ዘይቤ በጉዳዩ ዙርያ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ሀላፊ አቶ አዎል ሱልጣን እንደገለፁት ከሆነ ከወረርሺኙ ከፍተኛ የመሰራጨት አቅም አንፃር የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል ህግጋትን ማውጣት አስፈላጊ ነው ያሉ ሲሆን “በሽታው እየተስፋፋ በመጣበት ሁኔታ ላይ ህጋዊ ግዴታዎችን ማላላት ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍል ስለሚችል በመመርያ ግዴታዎችን መጣል አስፈላጊ ነው።” በማለት የህጉን አስፈላጊነት ተናግረዋል። አክለውም “በተለያዩ የአገሪቱ ከተማዎች የምታስተውለው በቸልተኝነትና ባለማወቅ የመዘናጋት ሁኔታ ህጉ የበለጠ እንዲያስፈልግ አድርጎታል ” በማለት በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታየውን ቸልተኝነት እንዲሁም የንቃተ ህሊና ችግር አንፃር መመርያው ትልቅ ሚናን ይጫወታል ያሉት አቶ አወል አክለውም ይህ ችግር በተለይም ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ ከተሞችና ገጠራማ ክፍሎች በሰፊው ይስተዋላል በማለት ተናግረዋል። 

የአፍና አፍንጫ መከላከያ ጭንብሎች በአግባቡ መጠቀም አገሪቱ በሽታውን ለመከላከል በምታደርገው ጥረት ላይ ከሚጫወተው ሚና በተጨማሪ በሌሎች አገሮችም የተለመደ አሰራር መሆኑ ህግ ያስፈጋል ወይ ለሚለው ጥያቄ እንደመልስ ሊቀመጥ ይችላል። እንደምሳሌነት በደቡብ አፍሪካ መንግስት በቫይረሱ ዙርያ የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመቆጣጠር የተተገበረውን ህግ ማንሳት ይቻላል። ኮሚቲ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ (Committee to Protect Journalists) ገለጻ ከሆነ በመጋቢት ወር የወጣው የደቡብ አፍሪካ ህግ በቫይረሱ ዙርያ የተሳሳተ መረጃን በሚያሰራጩ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ የተለያዩ ህጋዊ ግዴታዎችንና ቅጣቶችን ይጥላል። ከዚህ በተጨማሪ በድንበር ዘለል ወንጀሎች ላይ የሚሰራው ግሎባል ኢኒሽዬቲቭ አጌንስት ትራንስናሽናል ኦርጋናይዝድ ክራይም (Global Initiative against Transitional Crime) እንደተሰኘው ድርጅት ከሆነ ተመሳሳይ ህጎች በተለያዩ አገራት እንደወጡ በመካነ ድሩ ላይ ገልጿል። በዚህ ረገድ በአየርላንድ መንግስት በድጋሚ የተደነገገውን ከቤት ያለመውጣት ትዕዛዝ ያስታወሱት አቶ አወል ህግጋት በተለያዩ አገራት ቫይረሱን ለመከላከል እንደቁልፍ መሳርያ  እንደሚያገለግል ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

የቅጣቱ ተመጣጣኝነት

ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው ከቫይረሱ አስጊነት፣ መስፋፋቱ በተለያዩ መመርያው ላይ በተዘረዘሩ የመከላከያ መንገዶች ላይ ሙሉ በሙሉ መመስረቱ እንዲሁም በተለያዩ አገራት በህግ ተደግፎ ቫይረሱን መከላከል የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ ህግጋት ያስፈልጋሉ ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ላያዳግት ይችላል። በመሆኑም አዲስ ዘይቤ ለአቶ አወል በመቀጠል ያቀረበችው ጥያቄ በጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ በወጣው መግለጫ ላይ ስለተቀመጠው የቅጣት መጠንና ስለተመጣጣኝነቱ ነበር። 

“በመጀመርያ ማኅበረሰቡ ሊረዳ የሚገባው ነገር ቅጣቱ በወንጀል ህጉ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ነው።” በማለት ምላሻቸውን የጀመሩት አቶ አወል የቅጣት መጠኑ በአገሪቱ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 522 ላይ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የተወሰነ ውሳኔ እንደሆነ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። በጤና ሚንስቴር በመስከረም ወር በወጣው መመርያ አንቀፅ 30 መሰረት በመመርያው የተከለከሉ ተግባሮችን መፈፀም በተገቢው ህግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ያስታወሱት አቶ አወል በዚህ መሰረት የጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ውስጥ ከተጠቀሱት ተግባራትና ከቫይረሱ ጋር የሚያያዙ አንቀፆችን በመመርመር ተገቢውን ቅጣት አስቀምጧል ብለዋል። “በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ አንቀፅ 522 እንደተደነገገው ከሆነ አንድ ግለሰብ መንግስት ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያወጣቸውን መመርያዎች የሚተላለፍ ሰው እስከ ሁለት አመት ድረስ በሚደርስ እስራት ይቀጣሉ።” ያሉት አቶ አወል በአንቀፁ ላይ የተቀመጡት መስፈርቶች ስለተሟሉ የቅጣት መጠኑ እስከ ሁለት አመት ድረስ እንዲደርስ እንደተደረገ ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል። 

ነገር ግን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ የሚገባው ነገር ሁለት አመት የቅጣቱ ጣርያ እንጂ በሁሉም ጥፋቶች ላይ የሚጣል ቅጣት እንዳልሆነ ነው ያሉት አቶ አወል “በአገሪቱ የፍትህ ስርዓት ውስጥ ቅጣት በሚደነገግበት ወቅት በተለያዩ እርከኖች ተከፍሎ ነው።” በማለት እንደጥፋቱ ክብደት የቅጣቱ መጠን የሚተመንበት ህጋዎ ቀመር አለ በማለት አስረድተዋል። “ለምሳሌ በሽታው እንዳለበት በሚያውቅበት ሁኔታ ማህበረሰቡን የሚቀላቀል ግለሰብና የአፍና የአፍንጫ መሸፈብያ ጭንብልን ረስቶ በወጣ ሰው ላይ እኩል ቅጣት መቅጣት አይቻልም።” በማለት ቅጣቱ በሚጣልበት ወቅት ፍርድ ቤቱ የተለያዩ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ እንደሚያስገባ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሁለት አመት የቅጣቱ ጣርያ ነው ያሉት አቶ አወል ቀላል በሚባሉ  ቅጣቶች ላይ ከ10 ቀን እስከ ሶስት አመት ድረስ ፍርድ ቤቱ እንደሚቀጣ ለአዲስ ዘይቤ አስታውሰዋል። 

አዲስ ዘይቤ ከጤና ሚንስቴር የህዝብ ግንኙነት ቢሮ እንደሰማው እንዲሁም ከአቶ አወል እንዳረጋገጠው ከሆነ ማህበረሰቡ በመመርያው የተከለከሉትን ተግባራትና ተጓዳኝ ቅጣቶችን በሚገባ እንዲያውቅና መብቱን እንዲያስከብር እንዲሁም ህግ በማስከበር ስርዓቱ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን በተገቢው መልኩ ለማሰልጠን ስራዎችን በመሰራት ላይ ይገኛሉ። አቶ አወል ከዚህ ጋር አያይዘው ማንኛውም የመንግስት አካል ህጉን በመጠቀም የትኛውንም ግለሰብ መብቱ እንዳይጣስ ተገቢው ስራ እንደሚሰራ የገለፁ ሲሆን ማህበረሰቡ መሰል የመብት ጥሰት በሚያጋጥምበት ወቅት ለተገቢዎቹ የመንግስት አካላት ማሳወቅና ፍትህን ማግኘት ይችላል ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። 

አስተያየት