You can paste your entire post in here, and yes it can get really really long.
የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊሰ ታህሳስ 19/1917 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ፡፡ ለቤተሰባቸው ሁለተኛ ልጅ ሲሆኑ በፈረስ ግልቢያ ችሎታቸው ምክንያት በአባታቸው ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ነበሩ፡፡የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በተፈሪ መኮንን ት/ቤት የተከታተሉት ፕሬዝዳንቱ በኃላም ሆለታ ገነት ወታደራዊ የጦር ሃይል በመግባት የመቶ አለቃ ማእረግ አግኝተዋል፡፡ በወቅቱ በዳንስ ተሰጥኦአቸው ይታወቁ እንደነበር ስለ ፕሬዝዳንቱ በሚያትተው መጽሃፍ ላይ ልጆቻቸው ተናግረዋል፡፡የተለያዩ የመንግስት የሃላፊነት ቦታዎችን ተረክበው ያገለገሉ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ እንዲሁም የኤትርራ ሲቪል አቪዬሽን፣ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መ/ቤቶችን አስተዳድረዋል፡፡በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ የንግስና ዘመንም የፓርላማ አባል ነበሩ ፡፡ ንጉሱ ከስልጣን ከተወገዱም በኃላ በደርግ መንግስት ጋባዥነት በመንግስትና ህገ መንግስት አመሰራረት ዙሪያ ሰርተዋል፡፡ባላቸው ንቁ የሀገርና የህዝብ አገልጋይነት ስሜት የሚደነቁ ሲሆን በ77 አመታቸው በ1994 ዓ. ም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሆነው ለ12 ዓመታትም አገልግለዋል፡፡ በስልጣን ቆይታቸውም በአካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ብዙ የሰሩ ሲሆን የደን ጭፍጨፋን በጥብቅ ይቃወሙ ነበር ፡፡ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ከአማርኛ ውጪ ኦሮምኛ፣ አፋርኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ጣሊያንኛ እንዲሁም ፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን አቀልጥፈው እንደሚናገሩ በስፋት ይነገራል፡፡ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊሰ በ94 አመታቸው ታህሳስ 05 ሌሊት ላይ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ከአንድ አመት በፊት ካረፉት ባለቤታቸው ወ/ሮ ሳሌም አምስት ልጆችን ወልደዋል፡፡የመተንፈሻ ህመም የነበረባቸው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ለረጅም አመታትም በተሸከርካሪ ወንበር እርዳታ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡የቀብር ስነስርአታቸው በቅድስት ስላሴ ቤ/ክ በመጪው ረቡዕ እንደሚፈጸም ተነግሯል፡፡አዲስ ዘይቤ ለቤተሰቦቻቸውንና ወዳጆቻቸው መጽናናትን ይመኛል፡፡