ጥር 17 ፣ 2013

ድሬዳዋ: ዝቅተኛ ደሞዝ  የኢንዱስትሪያል ፓርክ ሰራተኞችን አማረረ

City: Dire Dawa

አብዛኛው የፓርኩ ሰራተኛ ዝቅተኛ የደሞዝ ተከፋይ  በመሆኑ ምክኒያት በፓርኩ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞቹ ከእጅወደ አፍ የሆነ ኑሮ ለመግፋት ተገደናል ይላሉ፡፡

Avatar: Lidiya Fikru
ሊዲያ ፍቅሩ

Lidiya Firkru is a mobile journalist from Dire Dawa city at Addis Zeybe

ድሬዳዋ: ዝቅተኛ ደሞዝ  የኢንዱስትሪያል ፓርክ ሰራተኞችን አማረረ

የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጥቅምት 19 ፣2013 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስቴር  አብይ አህመድ ተመርቆ በይፋ ስራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ የድሬዳዋ ኢንደስትሪ ፓርክ  በውስጡ ስራ የጀመሩ 3 ፋብሪካዎች ያሉት ሲሆን በአጠቃላይ 700­­­ ሰራተኛ በውስጡ ይዟል፡፡

በሀገራችን በህግ የተደነገገ ዝቅተኛ የደሞዝ መጠን ስለሌለ  የሰራተኛ ደሞዝ ከድርጅት ድርጅት መለየቱ የተለመደ ነው፡፡ አብዛኛው የፓርኩ ሰራተኛ ዝቅተኛ የደሞዝ ተከፋይ  በመሆኑ ምክኒያት በፓርኩ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞቹ ከእጅወደ አፍ የሆነ ኑሮ ለመግፋት ተገደናል ይላሉ፡፡

በፓርኩ ስራ ከጀመረ ወራትን ማስቆጠሩን የገለፀልን ወጣት ኢብሳ አብዱላኪም ‘’ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ጭራሽ የማይመጣጠን ክፍያ ነው የሚከፈለኝ ፡፡ ከኖርኩት ብዙውን እድሜዬን ትምርት ላይ ነው ያሳለፍኩት ግን ከሁለት ቀን የማይዘል ደሞዝ ነው የሚከፈለኝ’’ ሲል ቅሬታውን ገልፆልናል፡፡

በኢንድስቱሪያል ፓርኩ ውስጥ የስራ አመራር ላይ የሚግኝ ምንጭ ይሄነው የሚባል አነስተኛ የደሞዝ መጠን በህግ ስላልተቀመጠ  በፓርኩ ውስጥ የሚከፈለው የደሞዝ መጠን አናሳ መሆኑን ገልፆልናል፡፡ 

ወጣት አስቴር ጌታቸው ደግሞ በበኩሏ ፓርኩ ውስጥ ስራ ከጀመረች 4 ወራት ማስቆጠሯን ገልፃ ‘’ሰርቼ አደለም ለቤተሰብ ለራሴ የሚያስፈልገኝን ነገር ለሟሟላት እንኳን የሚከብድ ሁኔታ ውስጥ ነኝ ወሩን ሙሉ 8 ሰአት ሰርተሀ 900 ብር ሲከፈልህ ተስፋ ነው የሚያስቆርጠው፡፡ በዚህ ሁኔታ እለወጣለው ብሎ ማስበ እራሱ ከባድ’’ ነው ስትል ሀሳቧን አጋርታናለች፡፡

ይህ ጉዳይ የድሬዳዋ ኢንደስትሪ ፓርክ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢንደስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚታይ መሆኑን የገለፀው የአዲስ ዘይቤ ምንጭ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢንደስትሪውን እይጎዳው ነው ያለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም “የደሞዙ ማነስ ሰራተኛውን በስራ ላይ እንዳይቆይ ማለትም የሚከፈለው ደሞዝ እና የሚሰራው ስራ አልመጣጠን ሲለው ሰራተኛው ስራ ይለቃል፤ ይሄ ደግሞ የዚህ የኢንደስትሪ ፓርክ መቋቋም ዋናው ጠቀሜታ የእውቀትት ሽግግር በመሆኑ ሰራተኛው ቶሎ ቶሎ የሚለቅ ከሆነ እቅዱ አይሳካም። በምርታማነት ረገድ ሲታይ ሰው በተቀየረ ቁጥር አዲስ የሰው ሀይል ማሰልጠን ለአላስፈላጊ ወጪ ይዳርጋል ይህ ብቻ ሳይሆን  ጥራት ችግር ሊያመጣም  ይችላል።” በማለት ያለውን ችግር ለአዲስ ዘይቤ አስረድቷል።

ከምንም በላይ ደግሞ ፓርኩ ውስጥ የሚሰሩት ሰራተኞች ኑሮ መሻሻል አለመቻሉ በራሱ እሚያሳስብ ነገር እንደሆነ ነው ለአዲስ ዘይቤ የተናገረው። 

 

 

አስተያየት