ጥር 20 ፣ 2013

ጥር 13 በደጀን ወረዳ በተከሰተ የመኪና አደጋ የ39 ሰዎች ህይወት አልፏል?

HAQCHECKFact checking

በ13 ጥር 2013 ዓ.ም በአማራ ክልል ደጀን ወረዳ በደረሰ የመኪና አደጋ የ39 ሰዎች ህይወት ማለፉን የሚገልፀው መረጃ ሀሰት መሆኑን ሀቀቼክ አረጋግጧል።

Avatar: Rehobot Ayalew
ርሆቦት አያሌው

Rehobot is a lead fact-checker at HaqCheck. She is a trainer and a professional who works in fact-checking and media literacy.

ጥር 13 በደጀን ወረዳ በተከሰተ የመኪና አደጋ የ39 ሰዎች ህይወት አልፏል?

ብሩክ አይናለም የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ በ13 ጥር 2013 ዓ.ም የጨዋዎች ግሩፕ በተባለ (ከ142,000 በላይ አባላት ባሉት) የፌስቡክ ግሩፕ ላይ በአማራ ክልል የመኪና አደጋ ደርሶ 39 ሰዎች መሞታቸውን የሚገልፅ መረጃ አጋርቷል። በልጥፉ ላይ የተፃፈው ፅሁፍ “... ከአዲስ አበባ ወደ በባህርዳር 65 ሠዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ተገልብጦ የ39 ሠዎች ህይወት አልፏል። አደጋው የደረሰው ዛሬ (13 ጥር 2013 ዓ.ም) ከቀኑ 5:35 አውቶብሱ በአማራ ክልል፤ ደጀን ወረዳ፤ ባልበሌ ቀበሌ አካባቢ በሚገኝና 50ሜትር ጥልቀት ባለው ገደል ገብቶ ነው። ማንነታቸው ስላልታወቀ ከቤተሰቦቻቸው እናገናኛቸው አስክሬናቸው በደጀን ሪፈራል ሆስፒታል ይገኛል…” ሲል ይነበባል። ልጥፉ በሌሎች የተለያዩ የፌስቡክ ግሩፖች ውስጥ እየተሰራጨ እና በብዙ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የተጋራ ይገኛል። ሆኖም ሀቅቼክ ባደረገው ምርመራ በምስሉ ትክክለኛ ያለመሆን እና በልጥፉ ላይ በተገለፁት ማስረጃዎች ምክንያት ልጥፉ ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል.

በዓለም ላይ ከፍተኛ የመኪና አደጋዎች ካሉባቸው አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ እንደሆነች የሚታወቅ ነው። ባለፈው የበጀት ዓመት (2012 ዓ.ም) በመላው አገሪቱ በትራፊክ አደጋ የ4,133 ሰዎች ህይወት ማለፉም የሚታወቅ ነው። ስለዚህም አማራ ክልልንም ጨምሮ በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች የትራፊክ አደጋ ከባድ እና አሳሳቢ ችግር መሆኑ እርግጥ ነው።

ሆኖም አዲስ ዘይቤ የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አናግራ በ13 ጥር 2013 ዓ.ም በደጀን ወረዳ 39 ሰዎችን የገደለ የመኪና አደጋ አለመኖሩ አረጋግጣለች። የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው “መረጃው በፍፁም ከእውነት የራቀ ነው” ሲሉም አረጋግጠዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በፌስቡክ ልጥፉ ላይ የሟቾቹ አስከሬን በደጀን ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ እንደሚገኝ የተገልፀ ቢሆንም በወረዳው ሪፈራል ሆስፒታል እንደሌለ እና በአቅራቢው ያለው ሪፈራል ሆስፒታል የሚገኘው ከደጀን በ61.5 ኪ.ሜ ርቀት በምትገኘው ደብረ ማርቆስ ከተማ መሆኑን ለማረጋግጥ ተችሏል።

በተጨማሪም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው መረጃውን ለመደገፍ ጥቅም ላይ የዋለው ምስል የተነሳው በ8 መጋቢት 2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 (Boeing 737 MAX 8) አውሮፕላን በተከሰከስ ወቅት ለአደጋው ሰለባዎች በተደረገው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መሆኑን ያሳያል። አደጋው የተከሰተው 1 መጋቢት 2011 ዓ.ም ላይ አውሮፕላኑ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ለማቅናት እንደተነሳ ብዙም ሳይቆይ ሲሆን ተሳፍረው የነበሩ 157 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው።

በመጨረሻም ሀቅቼክ ጉዳዩን መርምሮ በአማራ ክልል በደጀን ወረዳ በደረሰ የመኪና አደጋ የ39 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና የሟቾች አስከሬን በደጀን ሪፈራል ሆስፒታል እንደሚግኝ የሚገልፀው የፌስቡክ ልጥፍ ትክክለኛ ያልሆነ እና ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

 

አጣሪ፡ ርሆቦት አያሌው

ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው

አርታኢ፡ ብሩክ ነጋሽ

ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው። 

 

አስተያየት