በለሳ TV የተባለ ከ 47,000 በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገፅ ሚያዚያ 29፣ 2013 ዓ.ም በለቀቀው የፌስቡክ ልጥፍ ወታደሮችን እና ፍንዳታን የሚያሳዩ ምስሎችን አጋርቷል። በትግርኛ የተጻፈው ጽሁፍ ሲተረጎም “የሱዳን ጦር ወደ ምዕራብ ጎንደር በመግባት አዳዲስ ግዛቶችን እየተቆጣጠረ መሆኑን የሱዳን የዜና አውታሮች ዘግበዋል …” ሲል ይነበባል። ሆኖም ሀቅቼክ መረጃውን መርምሮ ከልጥፉ ጋር የተያያዙት ምስሎች የሱዳን ጦረ ምዕራብ ጎንደር መግባቱን እና ግዛቶችን መቆጣጠሩን የማያሳዩ መሆኑን አረጋግጧል። ሰለሆነም ምስሎቹ ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው በመሆኑ ሀቅቼክ መረጃውን ሀሰተኛ ብሎታል።
በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር አከባቢ ከህዳር 2013 ጀምሮ ግጭት ነበር። የሱዳን የመከላከያ ሰራዊት በኤል ገዳርፍ በሰላም በር እና ማሃጅ አከባቢ ያሉ ግዛቶችን ከኢትዮጵያ ጦር እና ከታጠቁ ሚሊሻዎች ማስመለስ መቻሉን ገልፁአል። ታህሳስ 22 2012 የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦማር ካማረዲን ከኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በተረከበው የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ዙሪያ ያሉትን ሁሉንም ግዛቶች መልሶ ማቋቋም እና ሙሉ ቁጥጥር ማድረጉን አስታውቀዋል። ሀገራቱ ጉዳዩን ለመፍታት እና ድንበሩን ለማካለል ውይይት እና ድርድር ሲያደርጉ ቆይተዋል። በቅርቡም ሱዳን በሚያከራክሩ ግዛቶች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትደራደር በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የቀረበውን ጥያቄ ተቀብላለች።
ሆኖም ሪቨርስ ኢሜጅ የተባለ የምስል ማጣሪያ እንደሚያሳየው ከልጥፉ ጋረ የተያያዘው የመጀመሪያው ምስል የተወሰደው በፈረንሳይኛ ተፅፎ ከታተመ ፅሁፍ ላይ ሲሆን ግንቦት 2006 ዓ.ም ነበር የተነሳው። ሁለተኛው ምስል የተወሰደው በአረብኛ ተጽፎ ከተለቀቀ የፌስቡክ ልጥፍ ጋር ሲሆን መጋቢት 2009 ዓ.ም ላይ መለቀቁን ያሳያል።
በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል የድንበር ግጭት መኖሩ እውነት ነው። ሆኖም በፊስቡክ ላይ የተሰራጨውን ልጥፍ ሀቅቼክ መርምሮ ምስሎቹ የሱዳን ጦረ ምዕራብ ጎንደር መግባቱን እና ግዛቶችን መቆጣጠሩን የማያሳዩ መሆኑን አረጋግጧል። ሰለሆነም ምስሎቹ ከጉዳዩ ጋር ምንም ኝኙነት የሌላቸው በመሆናቸው የፌስቡክ ልጥፉን ሀሰት ብሎታል።
አጣሪ፡ ሓጎስ ገብረአምላኽ
ተርጓሚ፡ ርሆቦት አያሌው
ይህ ፅሑፍ በአዲስ ዘይቤ የምርምርና ተቋም ግንባታ ቢሮ (Addis Zeybe Research & Development Department) በሚመራው ፤ ሀቅቼክ የተዘጋጀ ሲሆን ሀቅቼክ በአምስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) እየተዘጋጀ የሚቀርብ የተለያዩ መረጃዎችን ሀቅነት የሚመረምር የአዲስ ዘይቤ መርሀ ግብር ነው።