ግንቦት 2 ፣ 2013

"ዲሞክራሲና ብሎክቼይን"

City: Addis Ababaባለሙያነትምጣኔ ሀብት

ብሎክቼይን፣ ሕዝብ በአገሩ አስተዳደር ውሳኔ ላይ አንዳይሳተፍ የነበረውን እንቅፋት ያነሳል።

"ዲሞክራሲና ብሎክቼይን"

በአገራችን ከአንድ ሁለት ራስ ይሻላል የሚባል አባባል አለ። በብዙ አገሮች የፍርድ ችሎት የሚወሰነው ብዙ ዓመት በተማሩና ልምድ ባላቸው ዳኞች ሳይሆን ከሕዝቡ መሃል ከተመረጡ ከሕግ ሙያ ጋር ብዙም ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች ነው። ከአንድ አዋቂ ውሳኔ ይልቅ የ12 ተራ ዜጎች ውሳኔ ፍትሃዊ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ። አዋቂዎቹ አማካሪ ሆነው ሕዝብ ሲወስን የሚመጣው ውጤት  የተሻለ ወደ እውነተኛ ፍትሃዊነት የተጠጋ ፣ ቅቡልነት(legitimacy) ያለው እንደሚሆን ከጥንት ከአርስቶትል ጀምሮ የተጻፈ ሲሆን፣ በአገራችንም ቤተክርስቲያን ውስጥ ሳይቀር የሚሰራበት ስርዓት ነው።

ይህ ዕውቀት ግን ከፍተኛ የሆነ አለመተማመን ባለበት የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ብዙም ጥቅም ላይ አይውልም። በአገራችን ብቻ ሳይሆን የዲሞክራሲ ቀንዲል ተብላ በሚትታመነው አሜሪካ አንኳን ሕዝብ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ከሁለት ሰዎች አንዱን ምረጥ ነው የሚባለው። ስለሌላው የአገሪቱ ጉዳይ አይገባውም እንደማለት። በጽሁፍ የተላለፈ ታሪክ የሚነግረን፣ ዲሞክራሲ በተጀመረበት አቴና (አኛ ነን ብለው ስለጻፉ ብቻ) በማንኛውም ውሳኔ ላይ የዜጎች መሳተፍ የግድ አንደነበረ ነው። አያደር የተሳታፊ ዜጎች ቁጥር ሲበዛ ይህንን አይነት ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ በመሆኑ አሁን ወዳለንበት የተወካይ (delegative) ዲሞክራሲ ተሻገረ። በዛውም ህዝባዊ-ፍትህ ከፖለቲካ ተለያዩ።

ብሎክቼይን፣ ሕዝብ በአገሩ አስተዳደር ውሳኔ ላይ አንዳይሳተፍ የነበረውን አንቅፋት ያነሳል።

ለምሳሌ ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም አያንዳንዱ አሜሪካዊ በተለመዶ ኮንግረሱ፣ ሰኔቱ ወይም ፕሬዚደንቱ የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች ላይ ቀጥታ ተሳትፎ፣ ከዛ ዝቅ ቢል ማጽደቅና ማሻር ይችላሉ። ስዊዘርላንድ ከሞላ ጎደል አንዲህ ነው የሚሰራው። ፓርላማው ያሳለፈውን ውሳኔ ዜጎች ውሳኔ ሕዝብ በማድረግ መሻር ይችላሉ።

 

በብሎክቸይን የህዝብ ተሳትፎን በመጨመር ዲሞክራሲን የሚያጠናክሩ፣ አሁን ካለው የህዝብ ድምጽ አሰጣጥ ላቅ ያሉ የተለያዩ የምርጫ ዘዴዎችን ለመጠቀም ያስችላል። ከነዚህ ሁለቱ በአማርኛ ሕያው ዲሞክራሲና ብለን ልንጠራው የምንችለው (Liquid Democracy) ሲሆን ሌላው ባለ ሁለት ሃይል ድምጽ (Quadratic voting) የሚባሉት ናቸው። እነዚህን የድምጽ አሰጣጥ ስርዓቶች በወረቀትና በቀለም መተግበር ቢቻልም፣ አሰራሩ ውስብስብ ይሆናል። ብሎክቼይን ግን በቀላሉ፣ ያለብዙ ውጪ ሊተገብረው ይችላል። 

ሕያው ዲሞክራሲ (Liquid Democracy)

ሕያው ዲሞክራሲ በቀጥታ የህዝብ ተሳትፎና፣ የአዋቂዎችና ታማኝ የሆኑ ግለሰቦችን ትሩፋቶች በአንድ ላይ አጣጥሞ ለመጠቀም የታሰበ አሰራር ነው።

በዚህ ስርዓት ዜጎች በቀጥታ በውሳኔ ሃሳብ ላይ የመሳተፍ መብት አላቸው። ነገርግን ስለጉዳዩ በቂ አውቀት የለኝም ብሎ የሚያስብ ዜጋ ስለጉዳዩ ከኔ የተሻለ ያውቃል፣ አምነዋለሁ ብሎ ለሚያስበው ሰው ድምጹን ያውሳል። ያ ሰው በዛ ጉዳይ ብቻ ይወስናል። ለምሳሌ አንድ ገበሬ ጤናን በሚመለከት ለሚያምነው ሀኪም፣ የአገር መከላከያን በሚመለከት ለአንድ ስመጥሩ የጦር መሪ ድምጹን ሊያውስና ግብርናን በሚመለከት የመወሰን መብቱን ራሱ ሊጠቀምበት ይችላል።

Description: liquid.png

 

የምስል ምንጭ፡  1HIVE 

 

ባለ ሁለት ኃይል ድምጽ (Quadratic voting)

ይኸኛው የድምጽ አሰጣጥ ዘዴ “አንድ ሰው አንድ ድምጽ” የሚባለው አሰራር ችግሮችን ለመቅረፍ የተዘየደ አሰራር ነው። ምንም አንኳን ዜጎች ውሳኔ የመስጠት መብት ቢኖራቸውም  በሁሉም ውሳኔዎች ዜጎች አኩል ስሜት፣ አኩል ተጠቃሚ፣ ወይም አኩል ጉዳት የሚደርስባቸው አይሆንም። ይህ ሁኔታ የዜጎች ድምጽ አንዲባክን  ወይም፣ ምንም ባላሰቡበት ነገር ላይ ድምጽ ሰጥተው ያስበበትን ሰው ድምጽ አንዲሽሩ ያደርጋቸዋል። ይህ መጥፎ የፖለቲካና የማህበራዊ ስርዓት ይፈጥራል።

ለዚህ አንደ መፍትሄ የቀረበው፣ ሁሉም ዜጋ አኩል ወርሃዊ የድምጽ ኮታ ይኖረዋል። የድምጽ ኮታ ካለ ዜጎች በጣም በሚገዳቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ድምጽ ይሰጣሉ።

ይህንን ስርዓት የበለጠ ለማሻሻል፣ በአንድ ጉዳይ ላይ ከሌላው ዜጋ የበለጠ የሚገደው ካለ ሁለት ወይም ከዛ በላይ ድምጽ መስጠት ይችላል። ይህ ከሆነ ግን ከኮታው በሰጠው ድምጽ ተባዝቶ ይከፍላል ማለት ነው። ይህ ማለት 2 ድምጽ መስጠት የፈለገ 2^2=4 ወይም x የሚቆጠር ድምጽ ቢሆን  x^2 ድምጽ ይቀነስበታል። 3 ድምጽ መስጠት የፈለገ 3^2=9 አያለ ይሄዳል። 

ይህ ዜጎች በሚያውቂት፣ ግድ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲሳተፉ ያደርጋል። ስለዚህ ውሳኔዎች የተሻለ ጥራት እንዲኖራቸውና ጤነኛ ያልሆነ ፉክክር እንዳይኖር ያደርጋል። አብዛኛው ሰው በማያገባው፣ ወይም ሌላውን ለመጉዳት ድምጹን ከሚያባክን ራሱን ወይም አገሩን ይጠቅማል ብሎ ከልብ በሚያምናቸው፣ በሚያውቃቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ይሳተፋል።

ይህ የበለጠ መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ ሰላምን ይፈጥራል። 

Description: Screenshot from 2021-05-10 12-28-25.png

የምስል ምንጭ፡  www.therisk.global

በ 2020 የአሜሪካ ፕሬዚደንት አጩ ምርጫ በተወሰኑ ስቴቶች የዲሞክራቶች ካውከስ የመረጡት በዚህ ዘዴ ነው። ይህ ዘዴ በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሎ ያታሰባል። የአሜሪካንን ሙሉ የፖለቲካ ስርዓት ወደዚህ ለመቀየር ጥቅሙ የሚነካበት ከፍተኛ አቅም ያለው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ልሂቅ መደብ ስለማይፈቅድ በቀላሉ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም።

በአፍሪካ ግን  ህዝቡ የመምረጥ መብቱን (በዲጂታል መታወቂያውና  በብሎክቸይን ምክንያት) ካገኘና ከወሰነ ሊያስቆመው የሚችል ጠንካራ የልሂቃን መደብ  ባለመኖሩ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። በጠንካራ የሕግ ማነቆዎች ውስጥ ባለው ምዕራቡ ዓለምና በባህል ተጠፍሮ ባለው የምስራቁ ዓለም ይህ ቴክኖሎጂ ያመጣውን ትርፋት ህዝቡ ሙሉ በሙሉ አንዲቋደስ በቀላሉ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም።

አፍርካ ግን፣ ከኋላ ቀርነቱ፣ ጠንካራ የሕግ ሥርዓት ካለመኖሩ አንጻር፣ የነበረው ርግማን ወደ ምርቃት ሊቀየርና የምዕራብና ምስራቅ አገራትን በዚህ ረገድ ጥሎ በመሄድ የተሻለ የፖለቲካ መረጋጋት ይኖራል ብሎ ማለም የሚቻልበት ጭላንጭል ማየት ይቻላል። በቂ የፖለቲካ ልሂቅ ከተቀበለ፣ በቂ ሕዝብ ካወቀ፣ ይህንን ቴክኖሎጂ ስራ ላይ እንዳይውል ለማስቆም አቅም ያለው ልሂቅ በአፍሪካ የለም።

ኢትዮጵያ ከሁሉ ቀድማ ይህንን ቴክኖሎጂ ስራ ላይ በማዋል ግምባር ቀደም ቦታ ይዛለች። ይህ እንዲሆን ለሙከራ ጭብጥ ያስያዙን የትምህርት ሚኒስትሩና የስራ ባልደረቦቻቸው ምስጋና ይገባቸዋል።

አስተያየት