ግንቦት 6 ፣ 2013

ምርጫ ቦርድ ገንዘብ አዘግይቶብናል ሲሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅሬታ አቀረቡ

ምርጫ 2013

ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ በማድረግ ለሁሉም ተደራሽ ለመሆን አስበን የነበረ ቢሆንም ምርጫ ቦርድ ሊሰጠን የሚገባውን ገንዘብ በማዘግየቱ ምክንያት በፈለግነው መጠን ልንቀሳቀስ አልቻልንም::

Avatar: Haymanot Girmay
Haymanot Girmay

ምርጫ ቦርድ ገንዘብ አዘግይቶብናል ሲሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች  ቅሬታ አቀረቡ

ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ በማድረግ ለሁሉም ተደራሽ ለመሆን አስበን የነበረ ቢሆንም ምርጫ ቦርድ ሊሰጠን የሚገባውን ገንዘብ በማዘግየቱ ምክንያት በፈለግነው መጠን ልንቀሳቀስ አልቻልንም ሲሉ እናት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

"ከምርጫ ቦርድ ለምርጫ ቅስቀሳ የሚሆን 483ሺ ብር  ከተቀበልን ከ15 ቀን አይበልጥም" የሚሉት የእናት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ ጌትነት ወርቁ፤ ይህም በተዘዋዋሪ ከምርጫው ውድድር (ፉክክር) የሚያስወጣ ተግባር እንደሆነ ይናገራሉ። የመጀመሪያው ዙር ገንዘብ በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ተሳታፊ ለሆኑት ሁሉም ፓርቲዎች እንደተሰጠ የሚናገሩት ዋና ፀሐፊው ይህ መፈጸም ከነበረበት ጊዜ አኳያ የዘገየ እንደሆነና ቅስቀሳው ቀደም ብሎ እንደመጀመሩ የሚፈለገውን ያህል በገንዘብ እጥረት ሳቢይ ማሳካት እንዳልቻሉ ገልጸዋል። ከመጋቢት 18 ጀምሮ ለተከታታይ ሳምንታት በዋናነት በ8 ከተሞች እንዲሁም በየክልሉ ባሉ ዞኖች እና በአዲስ አበባ በሚገኙ ክፍለ-ከተማዎች  ቅስቀሳው መካሄዱን ተናግረው በአዲስ አበባ ብቻ ወደ 60 ሺህ ብር ገደማ ወጪ ማድረጋቸውን እና የተሸፈነውም ሙሉ በሙሉ በፓርቲው እንደነበረ ተናግረዋል። 

"ከጥር 12 ጀምሮ የፓርቲ እውቅና ባገኘንበት ሳምንታት ውስጥ ሊሰጠን ይገባ ነበር" የሚሉት ዋና ፀሐፊው ለህብረተሰቡ ተደራሽ መሆን የነበረባቸው ጉዳዮች በዘገዩበት የጊዜ መጠን ልክ ከምርጫው ውድድር የመውጣት እድል እንደሚሰፋ ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል። "ዋናው ስራችን ገንዘብ ላይ እንዲንጠለጠል አንፈልግም፤ ፓርቲያችን ሲመሰረት ገንዘብ ላይ የተመሠረተ አይደለም" ያሉት አቶ ጌትነት ከመንግስት በምርጫ ቦርድ በኩል የሚሰጠውን ገንዘብ ላለመውሰድ ወስነው እንደነበር ተናግረዋል። ዋና ፀሐፊው እንደሚሉት ሀሳባቸውን ቀይረው እንዲወስዱ ያደረጋቸው የአባላቶቻቸው የገንዘብ አቅም የተለያየ መሆኑና የተበጀተው ገንዘብ የሕዝብ እንደሆነ በማሰባቸው ነው።

በኢትዮጵያ የመንግስት እና የፓርቲ ልዩነት በቅጡ አለመለየቱን የሚገልፁት ዋና ፀሐፊው “ከመንግስት ካዝና ለፓርቲ ቅስቀሳ የአበል ገንዘብ ወጪ ይደረጋል” ሲሉ ክስ ያቀርባሉ።

"ምርጫ ቦርድ ዘግይቶ የሰጠውን የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ ተከትሎ ለሁለተኛ ጊዜ የሚሰጠው ገንዘብ ቁርጥ ያለ ቀን አልተሰጠውም። ምርጫው በጣም ተቃርቧል ስለሆነም ገንዘቡ ለቅስቀሳ ጥቅም ላይ ሳይውል ከምርጫው በኃላ ለጉዳት ማዋያ እንዳይውል" በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

"በዚህ ወቅት ቢሮ መከራየት፣ ሰራተኛ መቅጠር እና ሌሎች ስራዎችን መስራት ከገንዘቡ የመግዛት አቅም ማነስ እንዲሁም አገልግሎት ሰጪዎች ስለ ፓርቲ ካላቸው አስተሳሰብ አንፃር ከባድ ነው" የሚሉት  ፀሐፊው ምክንያቱ ደግሞ ስለ ምርጫ በስፋት የሚነገርበት ሰዓት በመሆኑ በፍራቻ ፍቃደኛ አይሆኑም፤ ከሆኑም የሚጠይቁት የገንዘብ መጠን የተጋነነ ነው ሲሉ ነግረውናል።  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (አብአፓ) ሊቀ-መንበር አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር በበኩላቸው "ዋጋው ውድ ነው፤ የመደቡት ገንዘብ በቂ አይደለም አንሶናል፤ ምርጫ ቦርድ ገንዘብን ሰጥቷቸዋል ሲባል የበለጠ ዋጋ ይጨምራሉ" ይላሉ።

በእጩዎች የቁጥር ብዛት፣ በፓርቲ ውስጥ ባሉ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችን ቁጥር ግምት ውስጥ በማስገባት የሚሰጠው ሁለተኛ ዙር የገንዘብ ድጋፍ ተከፋፍሎ ቢሆን የተሻለ ስራውን ሊሸፍን ይችላል ሲሉ አክለዋል።

እርሳቸው በሊቀ-መንበርነት የሚመሩት አብአፓ በዘንድሮው አገራዊ ምርጫ ለ4ኛ ጊዜ እንደሚሳተፍ የገለፁት አቶ ዘሪሁን፤ ከዚህ ቀደም በነበሩት ምርጫዎች በጀት አንድ ወይም ሁለት እጩዎች እንደተመዘገቡ ይሰጥ እንደነበረ ጠቅሰው የዘንድሮም በተመሳሳይ መልኩ መካሄድ እንደነበረበት ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መዝገቡ ፋንታሁን የፓርቲው አቅም ውስን በመሆኑ የተፈለገውን ያህል ማድረግ አለመቻላችውን ገልፀው ምርጫ ቦርድ ግን የተመደበውን ገንዘብ ለመስጠት ዘግይቷል ሲሉ ነግረውናል። "መዘግየቱን ለምርጫ ቦርድ በስልክ አሳውቀናል" የሚሉት ኃላፊው "እንደ አጠቃላይ በተሰጠ መግለጫ ምክንያቱ የፓርቲዎች ቁጥር መብዛት እና እና ያልተሟሉ መረጃዎች መኖራቸውን ሰማን እንጂ ለፓርቲያችን የተሰጠ ምላሽ የለም" ብለዋል።

ኃላፊው እንደሚሉት የፓርቲዎች ቅስቀሳ በተወዳዳሪነት ላይ ከፍተኛ ልዩነት ያመጣል። ፓርቲው "ከውስጥ ምንጭ አቅማችንን ማደራጀት" የሚል መፍትሄ ላይ መድረሱንም ኃላፊው ነግረውናል።

ምርጫ ቦርድ ከመንግስት የሚሰጠውን የድጋፍ በጀት ለማከፋፈል የዘገየበት ምክንያት በተመለከተ በድረ-ገፁ ላይ ባሰፈረው መረጃ እንዳለው ከሆነ ከአንድ ፓርቲ በስተቀር ሌሎች ፓርቲዎች የእጩዎቻቸውን ቁጥር ባለማሳወቃቸው እና ማሟላት የነበረባቸውን መረጃ ባለማሟላታቸው ነው።

አስተያየት