ግንቦት 7 ፣ 2013

በጥባጩ ዲያስፖራ

City: Jigjigaዜናዎች

ስድቡንና ከፋፋይ ሐሳቦችን አጭቆ ከራሱ እና ከሐውልቱ ጋር አጣምሮ ያዘጋጀውን 'ቪድዮ' በማኅበራዊ ትስስር ገጹ (ፌስቡክ) ለቆታል።

Avatar: sharif
ሸሪፍ

በጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን የመጀመሪያ ዲግሪ አለኝ፡፡ በሰላምና ደህንነት መስኮች፣ የጋዜጠኝነት እና የመገናኛ ብዙሃን ቁጥጥር እና በአጠቃላይ የመረጃ አያያዝ ሥራዎችን እንዲሁም የጋዜጠኝነትና ትምህርት በማስተማር ልምድ አለኝ፡፡ OBN፣ SRTV፣ ፋና ሰርቻለሁ፡፡ የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነኝ።

 በጥባጩ ዲያስፖራ

ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት መነሻ የሆነኝ የአንድ ሰው ድርጊት ነው። ግለሰቡ ጅግጅጋ ከተማ የሚገኘውን የሰዒድ አብዱላሂ መሀመድ ሐሰን ሐውልት ተጠግቶ በቀረጸው ተንወሳቃሽ ምስል የአርበኛውን ክብር አጣጥሏል። ስድቡንና ከፋፋይ ሐሳቦችን አጭቆ ከራሱ እና ከሐውልቱ ጋር አጣምሮ ያዘጋጀውን 'ቪድዮ' በማኅበራዊ ትስስር ገጹ (ፌስቡክ) ለቆታል። Müller Jarmal በሚል የፌስቡክ ስያሜ የሚጠቀመው ግለሰቡ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በሶማሊኛ ቋንቋ ባሰራጨው አጭር ተንቀሳቃሽ ምስል የአርበኛውን ክብር የሚነካ፣ የሶማሌን ሕዝብ የሚያወዛግብ መልእክት አስተላልፏል። አርበኛው ሰኢድ አብዱላሂ የመላው ሶማሌ ሳይሆን የኦጋዴን ብቻ እንደሆነ፣ ኦጋዴን ጎሳ እንደሆነ እና እዚህ [ጅግጅጋ] ቦታ እንደሌለው፣ ሐውልቱ አስፈላጊ እንዳልሆነ ተናግሯል። የማኅበራዊ ሚድያዎች መጨቃጨቂያ ሆኖ የከረመው ይህ ርዕሰ ጉዳይ አንድ ሁለት የሚያባብሉ ጉዳዮች አዝሏል።

  1. ማንም ሰው ሐሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዳለው እርግጥ ቢሆንም ግለሰቡ የሌሎችን ቁጣ በሚቀሰቅስ መንገድ ለምን አደረገው?
  2. ኢትዮጵያ እና ሶማሌ ክልል ከሚገኙበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ርዕሰ ጉዳዩን በዚህ ሰዓት ማንሳት ለምን አስፈለገ?
  3. ይህ ሰው አርበኛውን በእርግጥ ያውቀዋል?
  4. ሰውየው ቪድዮውን ሲለቅ የት ወይም በምን ሁኔታ ውስጥ ነበር?

የሚሉትን መሰረታዊ ብዬ ያሰብኳቸውን ጥያቄዎች በተከታዮቹ ርዕሶች ለመመለስ እሞክራለሁ።

ጥቂት ስለ ሐውልት

ሐውልቶች ርዕዮተ ዓለምን ለማስተዋወቅ፣ ጀግኖችን ለማወደስ፣ ታሪክን ለማስታወስ፣ ልዩ መለያ ቀለምን ለመግለጥ እና ለመሳሰሉት ዓላማዎች ይገነባሉ። የሟች አካል ያረፈበትን ለመለየት ከሚገነቡት የመቃብር ስፍራ ሐውልቶች ጀምሮ አደባባዮችን እስከሚያደምቁት ድረስ ዓላማቸው ልዩ ልዩ ነው። ይዘታቸውም ፖለቲካዊ፣ ሕዝባዊ፣ ሐይማኖታዊ ሊሆን ይችላል። የሰዎችን፣ የእንስሳትን ወይም ሌላ ወካይ ምስል ሊይዙም ይችላሉ። ሐውልቱ የተቀረጸለት ሰው በሕይወት እያለ ወይም በሞት ከተለየ በኋላ ሐውልቶች ሊቀረጹ ይችላሉ። ከሞት በኋላ የተሰሩ ሀውቶች ቅርስ ሆነው የመኖር እድላቸው ሰፊ ነው፡፡ በተለይ አምባገነን የሆኑ መሪዎች የራሳቸውን ምስል በመሪነት ዘመናቸው አስቀርጸዋል። የኢራቁ ሳዳም ሁሴን፣ የሰሜን ኮርያው ኪም ኤል ሱንግ፣ የኮንጎው ሞቡቱ ሴሴሴኮ፣ የኢትዮጵያው መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ የቻይናው ማኦ ሴቱንግ፣ የሊቢያው መሐመድ ጋዳፊ በምሳሌነት ሊቀመጡ ይችላሉ። የዚህ ዓይነቶቹ ሐውልቶች መሪዎቹ ሥልጣናቸውን ሲያጠናቅቁ የሐውልቱ እድሜም አብሯቸው ይጠናቀቃል።

ከሕልፈታቸው በኋላ ተከታይ ትውልድ ሐውልታቸውን ከገነባላቸው መሪዎች መካከል ደግሞ ጎንደር የሚገኘው የአጼ ቴዎድሮስ፣ አዲስ አበባ የሚገኘው የምኒልክና የአቡነ ጴጥሮስ፣ የሐረሩ የተፈሪ መኮንን፣ ሽረ የሚገኘው የኃየሎም አርዓያ ሐውልቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን የሰዒድ አብዱላሂ መሀመድ ሐሰን ሐውልትም ከእነዚህ ውስጥ ይመደባል፡፡

አዲስ አበባ ብሔራዊ ቲያትር ጎን የሚገኘው የአንበሳ ምስል፣ የአክሱም ሐውልት ወይም መቀሌ የሚገኘው የሰማእታት ሐውልት፣ አዳማ መግቢያ ላይ፣ ሐዋሳ ከተማ የሚገኙት ሐውልቶች ቦታን አመላካች ወይም የአካባቢው መገለጫ በመሆን እያገለገሉ መሆኑ ይታወቃል።

ሐውልቶች ቅርስም ናቸው። እንደጥያ ትክል ድንጋዮች ያሉት የመቃብር ስፍራዎችን ብንመለከት የዓለም ቅርስ እስከመሆን የደረሰ ክብር ተችሯቸዋል። የአክሱም ሐውልት የዚህ ሌላው ምሳሌ ነው። በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የቆሙት የስድስት ኪሎው የሰማዕታት ሐውልት፣ የአራት ኪሎው የድል ሐውልት ደግሞ ታሪክን የሚያስታውሱ፣ ትላንትን የሚሰብኩ የታሪክ መዘክሮች ናቸው።

ሰዒድ አብዱላሂ መሀመድ ሐሰን ማን ነው?

ሰዒድ አብዱላሂ መሀመድ ሐሰን (1856-1920) በሶማሌ ማኅበረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጦረኛ፣ ወታደራዊና ሐይማኖታዊ መሪ ነው፡፡ ሰዒድ አብዱላሂ መሪ ብቻ ሳይሆን እውቅ ባለቅኔም ነበር፡፡ የቁርአንን ትምህርት አጠናቆ የሐጂ ጉዞ ካደረገ በኋላ ሐጂ ሐፊዝ (በጥሬ ትርጉሙ 'ጠባቂ'፣ 'ትውስታ' ማለት ሲሆን፤ ሙስሊሞች ቁርዓንን ለተሸከመ ሰው የሚሰጡት ስያሜ ነው) ወይም ሰኢድ የሚል ስያሜ አግኝቷል፡፡ በሶማሌ ብሔርተኝነት ላይ ባበረከተው ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እና ማዕከላዊ ኃይሎች ላይ ባሳደረው ተጽእኖ በምሁራን ዘንድ “የሶማሌ ብሔርተኝነት አባት” የሚል ስያሜ ያገኘ ሲሆን የኦቶማን መንግሥት ደግሞ “የሶማሌው አሚር”  ብሎ እንደጠራው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ከብሪታንያ፣ ከጣልያን፣ እና ከሌሎችም ተስፋፊዎች ጋር የነበሩ የ20 ዓመታት ውጊያዎችን ለመጋፈጥና ለመቋቋም ባደራጀው የ“ዴርቪሽ” ንቅናቄ ይበልጥ ይታወቃል፡፡ የደርቪሽ ንቅናቄ ከ1899 - 1920 የዳበረ የሕዝብ ንቅናቄ ነበር፡፡ ሰዒድ የእስልምና ሐይማኖት አባቶችን፣ የጎሣ መሪዎችን እና የሐገር ሽማግሌዎችን ያቀፈ “ኩሱሲ” የተባለ የገዢ ምክር ቤት አቋቁሞ፤ ከኦቶማን ግዛት ሙሐመድ አሊ የተባለ አማካሪ ጨምሮ ከጊዜ በኋላ የሶማሊያ ግዛት እንዲፈጠር ምክንያት የሆነ ብዙ ወገኖች ያሉት ንቅናቄ መፍጠር ችሏል፡፡ የብሪታንያን አስተዳደር በጠላትነት በመፈረጅ ቅኝ ግዛትን እና ገዢነትን ታግሎ አታግሏል፡፡ ታግሏል፡፡

የደርቪሽ ንቅናቄ ከ1899 እስከ 1900 ዓ.ም. በነበሩ ጦርነቶች ከ5ሺህ እስከ 6ሺህ ጦረኞችን የማረከ ግዙፍ ጦር እስከ ማቋቋምም ደርሶ ነበር፡፡ 

የሙለር ጀማል ደባ

የውዝግቡ መነሻ የሆነውን ቪድዮ በተንቀሳቃሽ ስልኩ ቀርጾ በማኅበራዊ ሚድያ ያጋራው ግለሰብ ነዋሪነቱ ከሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ውጭ ነው፡፡ ከጅግጅጋ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያም ውጭ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ማጣራት እንደቻለው ሙለር የሶማሌላንድ ዜግነት ያለው ሲሆን ነዋሪነቱም በእንግሊዝ ነው፡፡ ጅግጅጋ ላይ የቀረጸውን የቪድዮ መልእክት በማኅበራዊ ሚድያ ያጋራው ጅግጅጋን ለቆ የእንግሊዝን ምድር ከረገጠ በኋላ መሆኑ ለምን የሚል ጥርጣሬ ያጭራል፡፡ የማኅበረሰቡን እሴቶች የሚያጠፋ ተግባር ሲያከናውን ራሱን አሽሽቶ በለኮሰው እሳት ምክንያት የሚመጣውን ችግር ሌሎች እንዲጋፈጡ ማድረግ ለምን ፈለገ?

እንደሚታወቀው የሶማሌ ህዝብ በርካታ ጎሳዎች አሉት፡፡ እርስ በርሱ ተቻችሎና ተከባብሮ ዘመናትን ባሳለፈው ጎሳ መሐል ከፋፋይ ሐሳቦችን የማምጣትን ውጤት ለመገመት ጠቢብ መሆን አያስፈልግም፡፡ ህዝቡ ለዘመናት ያጋጠሙትን ተፈጥሯዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ችግሮች ሲጋፈጥ፣ ሲታገልና ሲፈታ የቆየ እንደመሆኑ ተቃርኖዎችም አያጣም፡፡ በሥልጣን፣ በተፈጥሮ ሐብቶች፣ በታሪካዊ ርዕሶች ተቃርኖ እና በመሰል ውስጣዊ ጉዳዮች ቅራኔዎችና መገፋፋቶች ይኖራሉ፡፡ የከረረው የጎሳዎች ጠብ በጎሳ መሪዎችና በሐገር ሽማግሌዎች ምክርና ተግሳጽ እየረገበ ሕዝቡ አሁን ያለበት ላይ ደርሷል፡፡ አቶ ሙለር ይህንን ረዥም ዘመናት ያስቆጠረ የሕዝብ ትስስር በአጭር ቪድዮ ሊንድ ሲነሳ ከድርጊቱ ምን ውጤት ጠብቋል?

በአሁን ሰዓት ሀገሪቱ የተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ አይደለችም፡፡ የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች፣ የብሔርና የጎሳ ግጭቶች፣ ተፈጥሯዊ አደጋዎች፣ የውጭ ኃይሎች ግፊትና ጣልቃ ገብነት፣ የኢኮኖሚና የዋጋ ግሽበት፣ ሰላምና መረጋጋት በሁሉም አቅጣጫ የተሰለፉ መፍትሔ ፈላጊ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ 6ኛው ሐገራዊ ምርጫም ሌላ ትኩረት የሚሻ እና በጥንቃቄ መከወን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በእነዚህ መሀል አዲስ የብጥብጥ አጀንዳ ማቀበል ማንን የበለጠ ጠቅሞ ማንን ይጎዳል? የሚለው ሌላው የሰውየውን ድርጊት በጥርጣሬ ለመመልከት የሚጋብዝ ጥያቄ ነው፡፡

ማጠቃለያ

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እንደዋዛ የተወረወሩ ሐሳቦች የሚያስከትሉትን ጠንቅ የመመርመር ፍላጎት እንጂ ሐሳብን የማፈን ዐላማ የለውም፡፡ ራስን የተሻለ የደህንነት ቦታ ላይ አስቀምጦ ሰዎች ከውይይትና ንግግር ባለፈ ከፍ ወዳለ አለመግባባት እንዲያመሩ የሚያደርግ ድርጊት መፈጸም ግን በዝምታ ሊታለፍ አይገባም፡፡

ማኅበረሰብ የሚያከብራቸውን እሴቶች በአደባባይ መተቸት ወይም ስህተት ያሉትን ነቅሶ ለማሳየት በመጣርና በአዋቂነት ትእቢት ዋኖችን መዝለፍ መካከል ሰፊ ርቀት አለ፡፡