ግንቦት 9 ፣ 2013

የክሪፕቶ ገንዘብ ገበያ እና ግብይት

ባለሙያነትምጣኔ ሃብት

አንዳንዴ ዋጋውን ለማዋደድ እርስ በእርሳቸው ይሻሻጣጣሉም። ያኔ ሰው አውነት ዋጋ ያለው መስሎት ጥሬ ገንዘቡን አውጥቶ ይገዛል።

የክሪፕቶ ገንዘብ ገበያ እና ግብይት

የሚቀጥሉትን ሁለት የቢትኮይን ዋጋ ግራፎች አንመልከት። የመጀመሪያው ከኦክቶበር እስከ ሜይ አጋማሽ ድረስ ያለውን የዋጋ ግሽበት ያሳያል። አንደ ዜና ዘገባዎቹ ኤሎን መስክ $1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን የገዛው በኖቬምበር 2020 አካባቢ ነው። 

በዚህን ጊዜ የቢትኮይን ዋጋ 20ሺህ ዶላር አካባቢ ነበር።   ይህ በአግዳሚ ሰማያዊ መስመር ይታያል። አሁን ባለንበት ሜይ ወር የቢትኮይን ዋጋ $65ሺህ የአሜሪካ ዶላር ደረሷል።

ይህ ማለት የኤሎን መስክ $1.5 ቢሊዮን  ዶላር ወደ $4.5 ቢሊዮን ዶላር ደረሰ ማለት ነው። ይህ ማለት በ6 ወር ውስጥ ቢያንስ $3 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ አግኝቷል።

ለንጽጽር አንደ  WSJ ቴስላ (Tesla) የኤሎን መስክ በዓለም ታዋቂው የኤሌክትሪክ መኪና ኩባንያ በ2020 ዓ.ም. ሙሉ ዓመት ያገኘው ትርፍ  $721 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።  

NASA ለስፔስኤክስ (SpaceX)  ወደ ጨረቃ በ2024 የሚወስድ መንኩራኩር አንዲሰራ የከፈለው $2.9  ቢሊዮን  ዶላር ብቻ ነው። ከወጪ ቀሪ ትርፉ በስራው መጨረሻ ቢሰላ ከጥቂት ሚሊዮኖች አይ አይበልጥም። 

ይህ የሚቀጥለው ግራፍ የሚያሳየው በሜይ 13 ቀን አኩለ ቀን በምሳ ሰዓት አካባቢ የሆነውን ነው። ቀይ መስመሮች የሽያጭ ዋጋና መጠን ሲያሳዩ አረንጓዴ መስመር የግዥ መጠንና ዋጋን ያሳያል። 

ኤሎን  መስክ በፈረንጆች ሜይ 13 በታዋቂው SNL የቴሌቪዥን ፕሮግራም ቀርቦ ቢትኮይን ብዙ ኤሌክትሪክ  ስለሚጠቀም ካሁን በኋላ አልቀበልም ብሎ አሳወቀ። በዕለቱ ሰው ተደናግጦ በጁ ያለውን ለመሸጥ ሲሯሯጥ የቢትኮይን ዋጋ መውደቅ ጀመረ። 

ልክ 1300 ሰዓት ላይ ዋጋው የተወሰነ ደረጃ ሲደርስ ገበያው ላይ ቀርቦ የነበረው ቢትኮይን ሁሉ በአንዴ ተገዛ። 13 ባለችበት አረንጓዴ መስመር የሚያሳየው ይህንኑ የተገዛውን ቢትኮይን።

ከመገዛቱ በፊት የነበረውን ከፍተኛ ወደገበያ የቀረበው ብትኮይን በአንድ ወይም በሁለት ሰው የሚቀርብ አይደለም። ቀዩ አየተንደረደረ የሚወርደው ዋጋ የተደናገጡ ሰዎች ቶሎ ለመሸጥ በዋጋ ሲወዳደሩና ዋጋውን በአጭር ጊዜ ሲያወርዱት የሚያሳይ ሲሆን በጥቁር የተከበበው አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ጠብቀው የቀረበውን ሁሉ ባንዴ ሲገዙት ነው።  ሁለተኛው አረንጓዴ መስመር የሚያሳየው የመጀመሪያው ከገዙ በኋ ዋጋው ከፍ ቢልም ብዙም ተፎካካሪ ስላልነበረ ይህንን ያህል ከፍ አንዳለላ ነው። 

ከነዚህ ሁለቱ ምስሎች ልንገምት የምንችለው፣ ኤሎን መስክ ቢትኮይን አልቀበልም ሲል ተሽቀዳድመው የሸጡ ሰዎች ኤሎን መስክ ገዛ ብለው በከፍተኛ ዋጋ የገዙ ሰዎች መሆናቸውን ነው። 

አሎን መስክ የሰበሰበው አይነት ከቢትኮይን የሚገኘው ከፍተኛ ትርፍም ብዙ ጊዜ የሚመጣው ጉዳዩ በደምብ ሳይገባቸው አንድ ታዋቂ ሰው አደረገ ወይም አለ ብለው ክርፕቶገንዘብከሚገዙና ከሚሸጡ ሰዎች ነው። አብዛኛዎቹ በቀላሉ ብዙ ያተረፉ አየመሰላቸው በጥሪታቸው፣ ቤተሰቦቻቸውን አስርበው፣ ወይ ተበድረው ነው የሚገዙት።

ይህ አይነት የክርፕቶገንዘብ ንግድ pump and dump ይባላል። ዋጋውን አንዴ  ወደ ላይ ሌላ ጊዜ ወደታች አንዲወርድ በማድረግ የሰውን ገንዘብ አገኘሁ ሲል የመጓጓት አጣሁ ስል የመደንገጥ  ስሜት በመበዝበዝ የሚደረግ ንግድ ነው። የማያውቁ ሰዎችን ማለብ ነው።

አነዚህ ሰዎች የሰዎችን ስሜት የሚለኩና በስቶክ ማርኬት የተለመደውን ቴክኒካል አናሊሥስ  የሚሰሩ በዚህ ሙያ የሰለጠኑ ሰዎችን ቀጥረው ያሰራሉ። 

ኤሎን መስክ ይህንን ያደረገው ሆን ብሎ ትርፍ ለማግኘት ነው ብለን በርግጠኝነት መናገር አንችልም። ነገርግን አንድ ሰው አመትና ሁለት ዓመት ሰርቶ ያላገኘውን ትርፍ በግማሽ ዓመት ሲያገኝ ያንን ለማድረግ አይጓጓም ለማለት ትልቅ የዋህነትን ይጠይቃል።

ክሪፕቶገንዘብ ብዙ ሰዎችን ሃብታም አድርጓል። ይኸውም በሁለት መንገድ ይካሄዳል። አንደኛው ከላይ አንደተገለጸው የማያውቁ ሰዎችን በማለብ ነው። 

ሁለተኛው መንገድ በጥንቃቄ የክርፕቶገንዘብን ጥቅምና ቴክኖሎጂውን መርምሮ፣ ወደፊት የትኞቹ እሴት ሊኖራቸው ይችላል ብሎ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ግምት ወስዶ በመግዛትና በማስቀመጥ ነው። ይህንን ለማድረግ ግን በቂ ስለክርፕቶገንዘብ ቴክኖሎጂ፣ አሰራሩንና ከባህላዊው  ገንዘብ አንዴት አንደሚለይ፣ ከክሪፕቶገንዘብ ኋላ ያለው ቴክኖሎጂ፣ የአምራቾቹና ጀማሪዎቹ እውቀትና ልምድን፣ የትኛው ታስቦበት ጥቅሙ ተለይቶ አንደተሰራ፣ የትኛው የማጭበርበር አንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ብዙዎቹ የማጭበርበር ናቸውና። 

ለምሳሌ ዶር ሩጃ ኢግናቶቫ  (Dr Ruja Ignatova ) የተባለች (ምስሉ ላይ ቀይ ቀሚስ የለበሰች) ጀርመናዊ የሕግ ሰው የጀመረችው  ‘OneCoin’ የተባለ ክርፕቶገንዘብ በአንድ ወቅት በዓለም  ከቢትኮይን ቀጥሎ በጠቅላላ የገበያ ዋጋ ሁለተኛ ደረጃ ደርሶ ነበር። በመላው ዓለም ትትልቅ ሃብታሞችና ታዋቂ ሰዎች፣ በሴትዮዋ ተማምነው ዋጋው ወደፊት ይጨምራል በሚል ከUS$4 ቢሊዮን በላይ አውጥተው ክርፕቶገንዘቡን ገዝተዋል። ነገርግን ክርፕቶገንዘቡ ምንም ጥቅም የሌለው የማታለያ መሆኑ በመታወቁ ዋጋውን አጥቶ፣ በየአገሩ ያሉ የሴትዮዋ ግብረአበሮች ሲያዙ አስዋ ገንዘቡን ይዛ ተሰውራ ዛሬ በአለማቀፍ ደረጃ በማጭበርበር ወንጀል በመፈለግ ላይ ነች። 

 

 

ሌላው አንደ ዶጅኮይን Dogecoin (DOGE) አይነቱ ለቀልድ የተፈጠረ ክሪፕቶገንዘብ የወደፊት አድሉ ምን አንደሆነ በማያውቁ፣ በወሬ ብቻ በመነዳት፣ ዛሬ የገበያ ዋጋ ግምቱ  ከUS$67 ቢሊዮን በላይ ደርሷል። ይህ ገንዘብ አለኝ  ብሎ ለመሸጥ ሰው ቢነሳ የሚገዛ የለም። የዋጋው ግምት የሚወጣው ገንዘቡን ለመግዛት የሚጠይቁ ሰዎች በሚገዙበት ነው። አንዳንዴ ዋጋውን ለማዋደድ ርስበርሳቸው ይሸጣጣሉም። ያኔ ሰው አውነት ዋጋ ያለው መስሎት ጥሬ ገንዘቡን አውጥቶ ይገዛል። 

ስልክሪፕቶገንዘብ አወነቱ። 

ክርፕቶገንዘብ በመሰረቱ ምንም አሴት የለውም። አሴቱ የሚመጣው ያ ነገር ዋጋ አለው ብለው በሚገዙት ሰዎች እምነት ነው። ሁሉም በገንዘብነት የሚያገለግል ነገር ተመሳሳይ ባህሪ አለው። 

በአገራችን የማርያትሬዛ ብር ተፈላጊ ገንዘብ ነበር። ዛሬ ግን ያንን የሚቀበል አይኖርም። አሞሌ ጨው ሌላው ጥሩ ምሳሌ ነው። 

በጥቅም ላይ ውለው ከነበሩ ገንዘቦች ሁሉ ግን የክሪፕቶገንዘብ ተክኖሎጂ ሳፈተር ተመሳሳይ ባህሪ ይዞ አገልግሎት የሰጠ ገንዘብ በምስሉ ላይ የሚታየው በፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ በምትገኘው ያፕ በተባለች ደሴት ይገለገሉበት የነበረ በምስሉ ላይ የሚታየው የራይ ድንጊያ ነው። የራይ ድንጊያ ይሰራ የነበረበት ድንጋይ በያፕ ደሴት ባለመገኘቱ ይሰራ የነበረው ከደሴቱ ርቆ በሚገኝ ሌላ ደሴት ነበር። ከባድ በመሆኑ ያንን ድንጋይ በነበሩት ትትንሽ ጀልባዎች ማጓጓዝ አደገኛ በመሆኑ ብዙ ድንጋይ በያፕ ደሴት አይገኝም። በቀላሉ ሰው ሊሸከመው የማይችል በመሆኑ አንድ ቦታ ከተቀመጠም አይነሳም። ግን ማኅበረሰቡ ያ ድንጋይ የማን እንደሆነ ያውቃል። አንዳንድ ጊዜ በጀለባ እየተጓጓዘ ሲመታ ባሕር ውስጥ ድንጋዩ ሊገባ ይችላል። ነገግን ያም ቢሆን ያ ድንጋይ ባለቤት አለው። የደሴቷ ነዋሪዎች ሲገበያዩ አንዱ ለሌላው አሳ ሸጦለት ከሆነ ገዢው አንዱን ድንጋይ ለሻጪ ባለበቱነቱን እንዳስተላለፈ ለመንደሩ ይነግራሉ። ድንጋዩ ባህር ውስጥ ቢሆንም የመንደሩ ሰው ያ ድንጋይ ከዛን ቀን በኋላ የአሳ ሻጩ መሆኑን ያውቃል።

ለሺዎች ዓመታት በመላው ዓለም እንደ ገንዘብ ያገለገለው ወርቅ እንኳን ከድንጋዩ ጋር ተመሳሳይ ባህሪ ነው ያለው።   ወርቅ ሰዎች ዋጋ አለው ብለው እምነት ስለጣሉበት  አንጂ ጠቃምነቱ ከአሉምንየም ወይም ባሌስትራ ከሚሰራበት ብረት ያነሰ ነው። የባሌስትራ ብረት ባሌስትራነቱን ሲጨርስ ጥሩ ቢላ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ወርቅ ግን የዛን ያህል ተግባራዊ ጥቅም አይሰጥም። በጣም ሥስ በመሆኑ ለጌጥነት ለመጠቀም እንኳን ከመዳብ ጋር መቀላቀል አለበት። ንጹህ ወርቅ የሚያገለግለው ሰው ዋጋ አለው ብሎ ስለሚያስብ ለሀብት መሰብሰብያነት ብቻ ነው። 

ለወርቅ ዋጋ አንዲኖረው ያደረገው አንደለሎቹ ብረቶች (ለምሳሌ አሉሚኒየም) አንደልብ አለመገኘቱ ነው። ስለዚህ ወርቅ አንደገንዘብ አንደሃብት የያዘ ሰው ነገ ሁለት መኪና ሙሉ ወርቅ ገበያ አጥለቅልቆ ያለኝ ወርቅ ዋጋ ያጣል፣ ያወጣሁበትን አይመልስልኝም ብሎ አይሰጋም።   

የራይ ድንጋይም ሆነ ወርቅ ለገንዘብነት አንድያገለግሉ ያደረጋቸው አንደልብ የሚገኙ አለመሆናቸው ነው።

ብትኮይን ልክ አንደ ወርቅ ወይም ራይ ድንጊያ ምንም ሌላ ጥቅም የለውም። ማንም ሰው ተመሳሳይ ኔትዎርክ ፈጥሮ ልክ ብትኮይን የሚመስል ነገር ሊሰራ ይችላል። በሺዎች የሚቆጠሩ የሚመስሉም ተሰርተዋል።

ነገርግን ለዘላለም የሚኖረው የቢትኮይን መጠን 21 ሚሊዮን ብቻ ነው። ያንን መለወጥ አይቻልም። ዋጋ አንዲኖረው ያደርገውም ይህ አጥረት ነው።  

አንዳንድ የክርፕቶገንዘብ አድናቂዎች ብትኮይን ከወርቅ ይሻላል፣ አዲሱ ወርቅ ነውም  ይላሉ። ወርቅ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማመላለስ፣ አንደመገበያያነት ለመገለገል አስቸጋሪ ነው። ቢትኮይን ግን ተሸራርፎ ለመገበያያነት ያገለግላል፣ ከአንዱ የዓለም ክፍል ወደ ሌላው ግማሽ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ትልቅ መጠን ያለው ማስተላለፍ ይቻላል። 

ቢትኮይን በተፈጠረባቸው ጥቂት አመታት፣  ይህ ባህሪው፣ ገንዘባቸውን ከመንግስት ለመደበቅና፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ለማሸሽ በሚፈልጉ ዘንድ ተወዳጅ ሆኖ ነበር። ነገርግን የጸጥታ አካላት የመከታተል አቅማቸው አየተሻሻለ ሲሄድ ቢትኮይንን ለወንጀል መጠቀም አደገኛ ሆኗል። አያናንዱ የቢትኮይን ግብይት ሕዝብ በሚያየው መዝገብ ላይ ስለሚመዘገብ ለጸጥታ አካላት ተከታትሎ ወነጀልኛውን ለመያዝ ያቀለዋል።

ክርፕርቶገንዘብ መግዛት የሚፈልጉ።

ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ምክንያቱ ክርፕቶገንዘብ አንዴት መግዛት አችላልሁ የሚሉ ጥያቄዎች ለጸሐፊው ብዙ ጊዜ ስለሚቀርቡ ለጠያቂ ግለሰቦች የሚመክረውን ምክር ለሁሉም ለማካፈል ነው። 

በቅድሚያ አንድ ሰው ክሪፕቶገንዘብ አንዴት መግዛት ይቻላል ብሎ ከጠየቀ የዚህ ጸሐፊ ምክር አትግዛ የሚል ነው። ምክንያቱም ማንም “አንዴት ልግዛ?” ብሎ  የሚጠይቅ ሰው ስለክርፕቶገንዘብ ያለው አውቀት በጣም ትንሽ ነው። እውቀት ሳይኖረው ክርፕቶገንዘብ የሚገዛ ሰው ቁማር ከሚጫወት ሰው የተለየ አይደለም። 

ስለክሪፕቶገንዘብ ምንነት፣ አንዱ ከሌላው አንዴት አንደሚለይ አንድ ሰው ካወቀ በኋላም አንዴት ሳይጠፋ ደህንነቱን ጠብቆ አንድሚቀመጥ ማወቅ አለበት። ወርቅ ጓሮ መቅበር፣ ወይም ባንክ ቤት ማስቀመጥ ይቻላል።

ክርፕቶገንዘብ ግን በሰው በራሱ ኮምፑተር ውስጥ የሚቀመጥ ስለሆነ በቀላሉ በሃከሮች መሰረቅ ይችላል። ስለዚህ ክርፕቶገንዘብ መግዛት የሚፈልግ ሰው የኮምፑተር ደህንነትንም በደምብ መረዳት አለበት።

ሰውን አምኖ አስቀምጥልኝ ማለትም አይቻልም። ቁልፉን ያወቀ ሰው ባለቤት ይሆናል። ይህም ሆኖ ሰዎች በክርፕቶገንዘብ ይከብራሉ። ነገ ግን አንድ ቀን ይህ ሁሉ ዋጋ ዜሮ አንዳይገባ ምንም መተማመኛ የለም።  ይህንን አውቀት ከያዙ በኋላ ብቻ ሰዎች ሕግን ባልጣሰ መንገድ የተወሰነ ገንዘብ ክርፕቶገንዘብ ላይ ቢያውሉ ወደፊት ሊጠቀሙ ይቻላሉ።

ምን ያህል ገንዘብ መዋል አንዳለበት ባለቤቱ ብቻ የሚያውቅ ቢሆንም ብዙ አዋቂዎች የሚስማሙበት በጥሬ ገንዘብ ሰው ከሚያስቀምጠው ገንዘብ 1% የሚሆን በክርፕቶገንዘብ ቢያስቀምጥ ይመከራል። ግን ዋናው መታወቅ ያለበት ይህ ገንዘብ ነገ ሙሉ በሙሉ ዋጋ ቢስ ቢሆን ይህ ሰው ወይም ቤተሰቡ ምንም የማይጎዳ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።

ሌላው አንዴ ከገዙ በበኋላ ዋጋውን አየተመላለሱ አለማየት ነው። ገዝቶ በጥንቃቄ አስቀምጦ መርሳት ወይም በሁለት በሶስት ወር ከአንድ ጊዜ በላይ አለመጎብኘት ይመከራል። ምክንያቱም የክርፕቶገንዘብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ  ከፍና ዝቅ ስለሚል ላልተለማመደው ሰው ከፍተኛ የሆነ መረበሽን ይፈጥራል። ዋጋው ሲወርድ በመደናገጥ ከስሮ ለመሸጥ ይከጅላል፣ ዋጋው ከፍ ሲል ሁሌም ከፍ የሚል እየመሰለው ለመግዛት ያነሳሳዋል። ይህም አንደቁማር ሱስ ሊሆን ይችላል። 

በተለይ በተለያዩ የሶሻል ሜድያ ላይ ነገ ይኸኛው ይወርዳል፣ ያኛው ይወጣል አያሉ ኤክስፐርት መስለው የሚቀርቡ የዚህ የማታለያና የማለቢያ ኔትዎርክ አባላት ናቸው። ማንም ሰው ሊሰማ አይገባም። ምክንያቱም ማንም ሰው ክርፕቶገንዘብ መቼ፣ አንዴት፣ ለምን፣ አንደሚወጣ የሚያቅ ሰው የለም። ሊታወቅም አይችልም። ይህንን ቢያውቁ ሰዎች ሌላውን አይመክሩም። 

በስቶክ-ገበያ ቴክኒካል አናሊሥስ የሚባል የመገመቻ መንገድ አለ። ይህ ትምህርትና ብዙ ልምድ የሚጠይቅ ሲሆን በክርፕቶገንዘብ ገበያ ላይ ጥቅም ላይ ይውላል። ያም ሆኖ ብዙ ጊዜ ግምቱ ስህተት ይሆናል። ውስጣዊ አውቀት ሳይኖር በትክክል የዋጋ መውጣትና መውረድን መገመት ያው ግምት አንጂ አውነት አይደለም።

ሌላው ስትራቴጂ ምን ያህል ገንዘብ ኢንቨስት ለማድረግ በመጀመሪያ ከወሰኑ በኋላ ያንን ገንዘብ ከፋፍሎ በተወሰነ የጊዜ ገደብ (ለምሳሌ በአመት 12 ጊዜ በየወሩ የመጀመሪያ ቀን) እኩል መጠን ያለው ገነዘብ ኢንቨስት ማድረግ ይቻላል። ይህ በኢንቨስትመንት ቋንቋ (Dollar-Cost Averaging (DCA)) በመባል ይታወቃል። ይሄ በዋጋ መውጣትና መውረድ የሚፈጠረውን ኪሳራ ያጣጣል፣ ስሜታዊ ሆኖ ስህተት ከመስራትም ይጠብቃል።

ከዚህ በተጨማሪ የክሪፕቶገንዘብ ላይ የየአገሩ የቀረጥ ሕግ እንደሚሰራና፣ ምን አይነት ግዴታ እንዳለ ማወቅ ያስፈልጋል። 

ጸሐፊው ትምህርቱ በቴክኖሎጂና የቴክኖሎጂ ስነትምህርት መስክ ሲሆን በብሎክቸይንና ክርፕቶገንዘብ መስክ ከ10 ዓመት በላይ ልምድ አለው። ለግለሰቦችና ድርጅቶች፣ ስለብሎክቸይንና ክሪፕቶገንዘብ ያማክራል፣ ስልጠና ይሰጣል።

አስተያየት