ግንቦት 11 ፣ 2013

የባህል፣ የታሪክ፣ የቋንቋ ሲምፖዚየም በኮንታ

የጥበብ ዐውድ

አከባቢው የ“ጨበራ ጩርጩራ” ብሔራዊ ፓርክ ጥቅጥቅ ደንን ጨምሮ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች መገኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡

Avatar: Muluneh Kassa
ሙሉነህ ካሳ

በፎክሎር (በባህል ጥናት) እና በሽያጭና በገበያ ጥናት ዲግሪ አለኝ፡፡ በአዲስ ዘይቤ ዲጅታል መጽሔት ላይ በሪፖርተርነት እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡

የባህል፣ የታሪክ፣ የቋንቋ ሲምፖዚየም በኮንታ

በደቡብ ክልል ኮንታ ልዩ ወረዳ ትላንት እና ከትላንት በስተያ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የባህል፣ የታሪክ እና የቋንቋ ሲምፖዚየም ተካሂዷል። በልዩ ወረዳው ባህል ቱሪዝም እና ስፓርት ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት እውን የሆነው ሲምፖዚየም የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ፣ አመራሮች፣ ምሁራን፣ የብሄረሰቡ ተወላጆች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈውበታል።

የኮንታ ብሔረሰብ በዋናነት በኮንታ ልዩ ወረዳ በሚገኙ በገጠር እና የከተማ ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖር ሕዝብ ነው፡፡ በ1999 ዓ.ም. በተደረገ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ የህዝብ ብዛቱ ከ117 ሺህ በላይ የነበረ ሲሆን በአሁን ሰዓት ከ3 መቶ ሺህ በላይ እንደሚገመት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የኮንታ ብሔረሰብ መኖሪያ ሜዳማ፣ ተራራማና ሸለቋማ የሆነ መልክአ ምድራዊ ገጽታ አለው፡፡ የብሔረሰቡ የኢኮኖሚ መሠረት እርሻና ከብት እርባታ ሲሆን የተወሰነው የኀብረተሰብ ክፍል የተለያዩ የዕደ ጥበብ ምርቶች ላይ ተሰማርቶ ህይወቱን ይመራል፡፡

የኮንታ ህዝብ ተለይቶ ከሚታወቅባቸው ባህላዊ እሴቶቹ መካከል ተዋረዳዊ ኃላፊነትና ተግባር ባላቸው የተለያዩ ክፍሎች የተደራጀው ባህላዊ የአስተዳድር መዋቅር አንዱ ነው፡፡ “ካዎ” ወይም ንጉሥ በመባል የሚታወቀው መሪ ከማላ ጎሳ የሚመረጥ ነው፡፡

ሌላው የማኅበረሰቡ መለያ የባህላዊ ጋብቻ ስርአቶቹ እና ዐይነቶቹ ናቸው፡፡ የኮንታ ብሔረሰብ ስድስት ባህላዊ የጋብቻ ዓይነቶች አሉት፡፡ በቤተሰብ ስምምነት የሚፈጸም ጋብቻ (ቦሣ)፣ የጠለፋ ጋብቻ (ላታ)፣ በተጋቢዎች ስምምነት የሚፈጸም ጋብቻ (ማቆ)፣ የቃል ጋብቻ (ያኤኤኩዎ) እና የምትክ ጋብቻ (ሚሽቶ) በመባል ይታወቃሉ፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን በአብዛኛው ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው የጋብቻ ዐይነት የ“ቦሳ” ጋብቻ ነው፡፡

ፂፄ፣ ጫቻ፣ ዛይ፣ ዲንኬ እና ኡልዱዶ የተባሉት የሙዚቃ መሳሪያዎችም ተጠቃሽ የማኅበረሰቡ ልዩ ባሕላዊ እሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህ የትንፋሽና የምት የሙዚቃ መሣሪያዎች ለለቅሶና ለደስታ ጊዜ ያገለግላሉ፡፡ በተለይ ኡላዱዶ የተሰኘው የትንፋሽ መሣሪያ ከድኩላ ቀንድ የሚሠራ ሲሆን እረኞች ከብቶቻቸውን ሆራ (ጨውነት ያለው ውሃ) ሊያጠጡ ይጫወቱታል፡፡

የኮንታ ባህላዊ የቤት አሠራር ከፍልጥ እንጨት፣ ከቀርከሀ ከሰንበሌጥና ከሣር የሚዘጋጅ ሲሆን በደጋውና በቆላው አካባቢ ልዩነት አለው፡፡ ሱልሶ፣ ሲሊሶ፣ ኡስታ፣ ጨዲያ፣ ኩበዋ፣ ቦሩዋ (ዱቢያ) እና ባጨራ የኮንታ ብሔረሰብ ዋነኛ ባህላዊ ምግቦች ናቸው፡፡

የኮንታ ብሔረሰብ መኖሪያ ሜዳማ፣ ተራራማና ሸለቋማ የሆነ መልክአ ምድራዊ ገጽታ አለው፡፡ የብሔረሰቡ የኢኮኖሚ መሠረት የሆነው እርሻና ከብት እርባታ ሲሆን የተወሰነው የኀብረተሰብ ክፍል የተለያዩ የዕደ ጥበብ ምርቶች ላይ ተሰማርቶ ህይወቱን ይመራል፡፡

በሁለት ቀናቱ ሲምፖዚየም የኅብረተሰቡን ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪክ የሚያወሱ መጽሐፎች በይፋ ተመርቀዋል፡፡ በኮንታ ባህል፣ ታሪክ እና ቋንቋ ዙሪያ የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቦ ሂሳዊ ትንተና እና ውይይትም ተካሂዶበታል።

የልዩ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፋንታሁን ብላቴ የልዩ ወረዳው ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ሳይበረዝ የዘመነ ሉላዊ ተፅዕኖን ተቋቁሞ፣ የህዝቡን እሴት ጠብቆ ማቆየት አስፈላጊ መሆኑን በጥልቀት በመገንዘብ ሲምፖዚየሙ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

የበርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች ባለቤት የሆነው የኮንታ ልዩ ወረዳ ያለውን እምቅ ሀብት በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አሉታዊ ተፅዕኖዎች ሳቢያ በሚፈለገው ደረጃ ማልማት አለመቻሉንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

አከባቢው የ“ጨበራ ጩርጩራ” ብሔራዊ ፓርክ ጥቅጥቅ ደንን ጨምሮ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች መገኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የብሔረሰቡ የአፍ መፍቻ ቋንቋ የሆነው "ኮንቲኛ"  ከ1990 ዓ.ም. ወዲህ ከንግግር ቋንቋነት ባሻገር የትምህርትና የሥራ ቋንቋ በመሆን አገልግሎት እየሰጠም ይገኛል። አብዛኛው የብሔረሰቡ አባላት ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጨማሪ ዳውሮኛ፣ ጋሞኛ፣ ወላይትኛና አማርኛ ቋንቋዎችን አዘውትረው ይናገራሉ።

አስተያየት