ኅዳር 7 ፣ 2014

የድሬዳዋ ልጆች በአማርኛ ፊልሞች ውስጥ

City: Dire Dawaየጥበብ ዐውድ

መቼታቸውን የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ እና ተወላጆች ላይ ያደረጉ ፊልሞች የሚስሏቸው ገፀ-ባህሪያት በሁሉም ነገራቸው ፍጹም ተመሳሳይ ሊሆኑ ይችላሉ ወይ?

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

የድሬዳዋ ልጆች በአማርኛ ፊልሞች ውስጥ
Camera Icon

Illustration: Solomon Yimer

በአማርኛ ቋንቋ ተሰርተው ለዕይታ ከበቁ ፊልሞች መካከል ድሬዳዋን እና የድሬዳዋ ሰዎችን በልዩ ልዩ መንገድ ያነሱ ጥቂት አይደሉም። “አስታራቂ 1”፣ “አስታራቂ 2”፣ “የከበረ ድሃ”፣ “ሼመንደፈር”፣ “ባለጉዳይ” ለዚህ ተጠቃሽች ናቸው። ፊልሞቹ መቼታቸውን ድሬዳዋ ከተማ ላይ ያደረጉ ወይም የድሬዳዋ ነዋሪ እና ተወላጆች በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ከኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር የሚኖራቸውን የሕይወት ውጣ ውረድ እና መስተጋብር የሚያሳዩ ናቸው። የአብዛኛዎቹ ጭብጥ በፍቅር እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።

ገጸ-ባህርያቱ የድሬዳዋ ልጆችን ወክለው በፊልሙ ዓለም ሲንቀሳቀሱ የድሬዳዋን ነዋሪዎች እንደሚገልጹ ታምኖባቸው ከአለባበስ እና አነጋር ጀምሮ በደራሲዎች እና በአዘጋጆቹ የታመነባቸው ተመሳሳይ ባህርይ ተሰጥቷቸዋል። በተመሳሳይ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የሚመሳሰል ባህርይ መላበሳቸው ብዙ ላይገርም ይችላል። የኑሮ ዘይቤ፣ የአየር ንብረት፣ የኑሮ ደረጃ እና ሌሎች ሁኔታዎች ተመሳስሎን ሲፈጥሩ ያጋጥማል፤ እንሚሆንም ይጠበቃል። ጥያቄው ልክ እንደ ፋብሪካ ምርት በሁሉም ነገራቸው ፍጹም ተመሳሳይ ሊሆኑ ይችላሉ ወይ? የሚለው ነው። የፍላጎት፣ የአስተዳደግ እና ሌሎች ሁኔታዎች በአንድ ቤት ያደጉ ሰዎችን እንኳን ላያስማማ የሚችልበት አጋጣሚስ አይኖርም ወይ? ያደጉበት አካባቢ ብቻ ሳይሆን ግላዊ ምርጫ የሰውን አለባበስ እና አነጋገር አይወስንም ወይ? በአነጋገር፣ በባህርይ፣ በሚወዷቸው እና በሚጠሏቸው ነገሮች ፍጹም ተመሳሳይ ሆነው በጥበቡ ዓለም መቅረባቸው በገሀዱ ዓለም ነዋሪዎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አይኖርም ወይ? የሚለው ነው። በጥቂቱ እንመለከተዋለን።

ድሬዎች የተሳሉበት መንገድ

ሁሉም ገጸ-ባህርያት ጮክ ብለው ይናገራሉ። ትንሽ ነገር ሲጎድልባቸው ይነጫነጫሉ/ያመናጭቃሉ። ጉዳዮች የሚነገሩበትን ቦታ እና ሁኔታ አይመርጡም። ዝም ማለት አይችሉም። ስነ-ስርአት የላቸውም። ለሰዎች ስሜት አይጨነቁም/አይጠነቀቁም። ለሁሉም ነገር ግድ የላቸውም። ምስጢር አይጠብቁም። በአጠቃላይ ከኢትዮጵያዊነት ወግ እና ባህል ያፈነገጠ ባህርይ አላቸው። በምሳሌ እንመልከታቸው…

ጮክ ብሎ መናገር

በበላይ ጌታነህ ተጽፎ በእውነት ፊልም ፕሮዳክሽን በቀረበው በ“አስታራቂ 1” የድሬዳዋ ልጆች የሆኑ ገጸ-ባህርያት በሙሉ ቀስ ብለው አይናገሩም። ዳይሬክተሮቹ ዮናስ አሰፋ እና ሮቤል ሰለሞን /ጃኪ/ ናቸው። በፊልሙ ውስጥ ዓለምሰገድ እና ሀናን የወከሏቸው ገጸ-ባህርያት ሙሉ ፊልሙን በጩኸት ንግግር ጀምረው በጩኸት ንግግር አጠናቀውታል። በፊልሙ ዳይሬክተሮች አረዳድ የድሬዳዋ ልጆች በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ ቀስ ብለው መናገር አይችሉም።  

በብርሀኑ ወርቁ የተጻፈው “ባለጉዳይ” የተሰኘው ፊልም “ባንጃው” የተሰኘ ገጸ-ባህርይ አለው። በዚህ ፊልም ላይም በተመሳሳይ ማንኛውንም ነገር ለማስረዳት ጮክ ብሎ የሚናገር ገጸ-ባህርይ ተስሏል። ከጩኸቱ በተጨማሪ እንደ አብዛኛዎቹ ፊልሞች ሁሉ “ባንጃው” ፍጹም መረጋጋት የሌለው ተደርጎ ቀርቧል። ገጸ-ባህርዩን ወክሎ የሚጫወተው ተዋናይ ሚካኤል ሚልዮን ነው።

በተጨማሪም የ“ሼመንደፈር” ፊልም ገጸ-ባህርይ አብዱልከሪም መረጋጋት የሌለውና ጮሆ ተናጋሪ ነው።

ስርአት አልባነት

“አስታራቂ” በሚል ርዕስ የተሰሩት ሁለት ፊልሞች ላነሳነው ንዑስ ርእስ ማሳያ ይሆናሉ። የድሬዳዋን ልጆች የወከሉት ሁለቱም ገጸ-ባህርያት ነጭናጫ ናቸው። ነጭናጫ ብቻ ሳይሆኑ ለጥቂት ጉድለት አብዝተው የሚያመናጭቁም ናቸው። በረባ ባልረባው ትንሽ ትልቁን ያመናጭቃሉ። ስርአት የላቸውም። ለንግግራቸው ቦታ አይመርጡም።

ለምሳሌ “አስታራቂ” ፊልም ቁጥር አንድ ላይ የሚገኘውን ትዕይንት እናንሳ። በፊልሙ ሦስት ደቂቃ ከ10 ሰከንድ ላይ የሚገኙት ገጸ-ባህርያት ከስርአት ያፈነገጡ ቃላት ይናገራሉ።

ተዋናይ ሚካኤል ሚልዮን የሚጫወትበት “ባለጉዳይ” ፊልም ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ የተጓዘን ገጸ-ባህርይ ገጠመኞች ያሳያል። አዲስ አበባ በእንግድነት የተቀመጠው ጓደኛው ቤት ነው። ሰውን ለመርዳት ፈጽሞ ፍላጎት የሌለውም። ነገሮችን ማቅለል ወደ ሁሉን ነገር የማቃለል ያመራ ይመስላል። ገጸ-ባህርዩ የማገዝ ፈቃደኝነት ሳይኖረው ለትንሽ ጉድለት ይነጫነጫል።  

ስሁት አረዳድ

የአልባሳት አጠቃቀም

ከላይ በተጠቀሱት ፊልሞች የድሬደዋ ልጆችን የሚወክሉት ሴት ተዋንያን ድርያ/ሺቲ ይለብሳሉ። አካባቢው ሙቀት እንደመሆኑ እና አብዛኛው ነዋሪ ሙቀቱን ለመቋቋም ሺቲ ስለሚለብሱ ድርጊቱ ትክክለኛ ይመስላል። ይሁን እንጂ “አስታራቂ 1” ፊልም ላይ የምትገኘው ገጸ-ባህርይ ከድሬዳዋ እስከ ጣልያን ሺቲ መልበስ አያሳምንም። ድሬዎች ሺቲ ያዘውትሩ እንጂ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሲጓዙ “መደበኛ” አለባበስ ይለብሳሉ። በተለይ አካባቢው ብርዳማ ከሆነ ከለመዱት ሙቀት አንጻር ከመደበኛው ነዋሪ በተለየ ልብስ ሊደራርቡ ይችላሉ እንጂ ያኔ በሙቀቱ አካባቢ የለመዱትን “ሺቲ” አይለብሱም። ይህ አረዳድ በአስታራቂ ብቻ ሳይሆን በ “ሼመንደፈር” እና “በከበረ ድሀ” ፊልሞች ላይም ይታያል። ሰርግ ቤትን ጨምሮ በሌሎችም ‘ፕሮቶኮል’ በሚጠየቅባቸው ቦታዎች ሺቲን መጠቀምና ሙሉ ልብስ አለመልበስ ነባራዊውን ሁኔታ አያንጸባርቅም።  

የሱስ ተጠቃሚነት

ለዚህ ጽሑፍ በማሳያነት እየተጠቀምንባቸው በምንገኘው በ“አስታራቂ 1 እና 2”፣ በ“የከበረ ድሃ”፣ በ“ሼመንደፈር” እና በ“ባለጉዳይ” ፊልሞች ውስጥ የሚገኙት ገጸ-ባህርያት ሱሰኛ ተደርገው ተስለዋል። በተለይ ጫትን አዘውትረው የሚጠቀሙት ገጸ-ባህርያቱ የድሬዳዋ ልጆችን ወክለዋል። ድርጊቱ በእውኑ ዓለም የሚገኙ የድሬዳዋ ልጆችን ቢገልጽም ሁሉም አንድአይነት ናቸው ብሎ መደምደም ግን አስቸጋሪ ነው። የሚቅሙ አሉ ወይም የሚቅሙ ይበዛሉ በማለት እና ሁሉም ቃሚዎች ናቸው በማለት መካከል ልዩነት አለ። የቃሚ ወጣቶች ቁጥር ይበዛል በማለት እና ከልጅ እስከ አዋቂ ይቅማል በማለት መካከል ልዩነት አለ።

የቃላት አጠቃቀም

በድሬዳዋ፣ በሐረር፣ በጅግጅጋ ነዋሪዎች ዘንድ የተለመዱ የአነጋገር ዘዬዎች አሉ። ከመካከላቸው እንደ “አቦ”፣ “ሀዬ”፣ “ሀይ”፣ “አብሽር” የመሳሰሉት ቃላት ይገኙበታል። በአብዛኛዎቹ ፊልሞች ላይ አነጋገሮቹን አላግባብ መጠቀም፣ መደጋገም፣ ይታያሉ። ዳይሬክተሮቹ ተዋናዮቻቸው መቼ እና በምን ሁኔታ ቃላቱን መጠቀም እንደሚገበቸው አላጠኑም።

ተመልካቾች ምን ይላሉ?

የድሬዳዋ ነዋሪ የሆነችው መቅደስ “ተመሳሳይ ባህርይ ያላቸው ወይም የሚያሳዩ የድሬዳዋ ልጆች መኖራቸውን መካድ አይቻልም። ሁሉም የድሬዳዋ ልጆች ተመሳሳይ ባህርይ ያሳያሉ ማለት ግን ስህተት ይሆናል” ብላናለች። “ዝምተኛ፣ ስርአት ያለው፣ ቀስ ብሎ የሚያወራ የድሬዳዋ ልጅ ፈጽሞ እንደሌለ መስሏል። እንደዛ ካልሆንሽ የድሬዳዋ ልጅ አይደለሽ   ም እስከማለት የደረሱ ሰዎች አጋጥመውኛል” የሚል ሐሳቧን ሰጥታናለች።

አቶ አማኑኤል ሳምሶን ተወልዶ ያደገው ድሬዳዋ ከተማ መሆኑን ይናገራል። እስካሁን የተመለከታቸው የድሬዳዋን ነዋሪ የወከሉ ገጸ-ባህርያት ያሉባቸው ፊልሞች ተመሳሳይ ዕይታ ብቻ እንዳላቸው ታዝቧል። “የድሬዳዋ ልጅ ነጻ ነው፣ ጭንቅ አያውቅም፣ ጣጣ የለውም የሚለው አባባል በተሳሳተ መንገድ እየተተረጎመ ነው። ዝም ብሎ ማውራት፣ ስርአት ማጣት አድርገው ነው የተረዱት” ብሎናል።

ድሬዳዋ ተወልዳ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪዋን የተቀበለችው ቅድስት ሳህሉ በዩንቨርሲቲ ቆይታዋ የድሬዳዋ ልጅ ነኝ ብላ ለሰዎች ለማሳመን እንደከበዳት ትናገራለች። “የማይቅም፣ ዝግ ብሎ የሚናገር፣ በራሱ ፕሮግራም የሚመራ ሰው የድሬዳዋ ልጅ የማያመስላቸው በጣም ብዙ ናቸው። በአንድ ወቅት ከጓደኞቼ ጋር በጉዳዩ ላይ በነበረን ክርክር በማስረጃነት የቀረቡት ፊልሞቹ ነበሩ። የድሬዳዋን ምድር ረግጠው የማያውቁ ሰዎች ዘፈን በመስማት እና ፊልም በማየት ብቻ እንደዚህ ናችሁ ሊሉ ይፈልጋሉ። በሌሎች ከተሞች ላይ እንደሚሰሩት ፊልሞች ሁሉም ዓይነት ሰው እንደሚገኝ ቢያሳዩ መልካም ነው” ስትል ሐሳቧን ትደመድማለች።

“የኪነ-ጥበብ ሰዎች ባልተገደበ ምርጫ የፈለጉትን የሕይወት ክፍል የማሳየት መብት አላቸው። የነዋሪዎችን ህይወት እስከ መረበሽ ከደረሰ ግን ቆም ብሎ ማሰብ ይጠይቃል” የሚለው ደግሞ የፊልም ባለሙያው ፍቅሩ ሽፈራው ነው። አቶ ፍቅሩ በድሬዳዋ የሚንቀሳቀሰው የአቢሲንያ ቲአትር ቡድን ሰብሳቢ ነው። “የድሬዳዋ ሰዎችን በታሪካቸው ውስጥ ያካተቱ ፊልሞች ተመሳሳይ ገጸ-ባህርይ ሊቀርፁ የቻሉት ከፊልም ባህርይ የተነሳ ነው። ፊልም በባህሪው ለየት ያለን ጉዳይ አጉልቶ ለማስቀመጥ ይሞክራል። ፊልም ሰሪዎቹ የድሬዳዋ ሰዎችን ከሚገልጽላቸው ልዩ ነገሮች ውስጥ ለየት ያለውን ወስደዋል። ይህ በራሱ ስህተት አይደለም። የሁሉም ምርጫ ተመሳሳይ ሲሆን ግን ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። በተለይ እንደኛ ማኅበረሰብ ላለ ተመልካች የፊልም ህይወትን ከተዋናዩ እና ከማኅበረሰቡ ጋር አንድ ማድረግ ይታያል። ስለዚህ መጠንቀቅ እና በተቻለ መጠን ሁሉም ዓይነት ሰዎች በአካባቢው እንደሚገኙ ለማሳየት መሞከር ይጠበቃል። ዳይሬክተሮችም በተለመደው መንገድ ብቻ ከመጓዝ አዲስ ነገር ማየት ያስፈልጋል” ብሎናል።

አስተያየት