ሐምሌ 12 ፣ 2013

መልከ ብዙ የአዲስ አበባ የጥበብ ምሽቶች

City: Addis Ababaየጥበብ ዐውድ

በአለም ላይ የኪነጥበብን ሚና በተመለከተ የተለያዮ አከራካሪ አተያዮች ቢኖሩም የትውልድን አስተሳሰብ በማነፅና አመዛዛኝና ጠያቂ ማህበረሰብ በመፍጠር አንፃር በምታበረክተው ጉልህ ድርሻ ላይ ግን አብዛኞቹ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

መልከ ብዙ የአዲስ አበባ የጥበብ ምሽቶች

"በስራ የተጨናነቀ አእምሮዬን ፈታ በማድረግ መዝናናት ስፈልግ አንዱ ምርጫዬ የጥበብ ምሽቶች ላይ መታደም ነው። በከተማችን እንዲህ ያሉ መድረኮች አሁን አሁን እየተስፋፉ እና ታዳሚዎቻቸውም እየበረከቱ መሄዳቸው ደግሞ የመዝናኛ አማራጭሽን ያሰፉልሻል" የምትለዉ ፅዮን ፍሬው ነዋሪነቷ በአዲስ አበባ ከተማ የ24 ዓመት ናት ።

አሁን ላይ የጥበብ ምሽቶች በአይነትም ሆነ በይዘት ተሻሽለው መምጣታቸውን የምትናገረው ፂዮን በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ የኪነጥበብ መድረኮች የስነጽሑፍ፣ የፍልስፍና፣ የሙዚቃ፣ የስዕል እና የመሳሰሉ የጥበብ ዘርፎችን ለማካተት መሞከራቸውን እንደ መልካም ጅማሮ ትወስደዋለች።

በአለም ላይ የኪነጥበብን ሚና በተመለከተ የተለያዮ አከራካሪ አተያዮች ቢኖሩም የትውልድን አስተሳሰብ በማነፅና አመዛዛኝና ጠያቂ ማህበረሰብ በመፍጠር አንፃር በምታበረክተው ጉልህ ድርሻ ላይ ግን አብዛኞቹ ይስማማሉ።

በየዘመኑ ለታዳሚ የሚደርሱ የጥበብ ስራዎች የወቅቱን አስተሳሰብ የሚያንፀባርቁ መዘክሮች እንደሆኑም ይታመናል። ማህበረሰብ የታፈነ ሲመስለው የሚተነፍስበት፤ ሲከፋው የሚፅናናበት፤ ተስፋ ሲቆርጥ የሚጀግንበትን አቅም ጥበብ ያለ ስስት ትለግሰዋለች።  

አዲስ ዘይቤ "እነዚህ ምሽቶች ለኪነጥበብ እድገት እና መስፋፋት ምን ያህል አስተዋፅኦ አድርገዋል? ስንቶችንስ አሳትፏል? ለታዳሚውስ ምን ጠቅሟል?" የሚሉትን ጥያቄዎች ይዛ የተወሰኑ የፕሮግራም አዘጋጆችን እና ታዳሚዎችን አናግራለች።

"የጥበብ ምሽቶች  ቋንቋም ሆነ ድንበር አይገድባቸውም። ዘመናትን ሳይሰለቹ መሻገር መቻላቸውም ሌላው መገለጫቸው ነው። ዛሬ ዛሬ ፖለቲከኞቹም የጥበብን ጉልበት ልብ እያሉት ይመስላል።  የስነፅሁፍ ምሽቶቹ  ሰላምን የሚሰብኩ ፣ ፍቅርንና አንድነትን የሚያጠነክሩ እንዲሆኑ የማበረታታት ፍላጎት እያሳዩ መምጣታቸው የሚደነቅ ነው።" የምትለው የጦቢያ ግጥም በጃዝ አዘጋጇ ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ ናት።

"ለምሳሌ በኛ ግጥም ምሽት ላይም የከተማዋን ምክትል ከንቲባ ጨምሮ ፖለቲከኞችም ይታደሙበታል ብሎም ለኅብረተሰቡ ይበጃል ያሉትን መልዕክት ያስተላልፉበት ጀምረዋል።" የምትለው ምስራቅ ይህ በራሱ አዳዲስ ሀሳቦች ወደ ጥበብ መድረክ እንዲመጡ ያበረታታል ትላለች።

በሌላ በኩል ደግሞ የጥበብ ምሽቶቹ አሳታፊነት አንደሚጎላቸዉ፣ በርካቶቹ ገንዘብ ከመሰብሰብ ያለፈ ጥበባዊ ፋይዳ እንደሌላቸውና ጥራት በሌላቸዉ ስራዎችና በተደጋጋሚ መድረኩን በሚሞሉት ተመሳሳይ ፊቶች ምክንያት ወቀሳ ይነሳባቸዋል፡፡

"ጥበብ ክፍያ አትሻም፤ አንዲህ ያሉ ዝግጅቶች ክፍያ ሊጠየቅባቸዉ አይገባም፡፡ አሁን አሁን የምናያቸዉ ዝግጅቶች የአዘጋጆቹን ኪስ ከማደለብ ያለፈ ፋይዳ " የላቸዉም በማለት ቅሬታ የሚያሰሙ የጥበብ አፍቃሪዎች ቁጥርም ጥቂት አይደለም።  

ወጣት ፅዮን ፍሬው ግን ትችት እና ነቀፋዉን ወደ ጎን ትተን ዘርፉ የሚበረታታበት መንገድ ላይ ብናተኩር ጥሩ ነዉ ትላለች፡፡ "አሁን ላይ ገና በማደግ ላይ ያለ ዘርፍ በመሆኑ መድረኮቹም ትንሽ በመሆናቸው ሊበረታቱ ነዉ የሚገባዉ፡፡  ይብዙልንና ከዛ በኋላ ባይሆን ለመተቸትም ይደርሳሉ " ስትልም አስተያየቷን ሰጥታለች።

ቢኒያም ጌታነህ ከሰኞ ሀምሌ 12፤ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለታዳሚ መቅረብ የሚጀምረው "የግጥማዊ ቅዳሜ" የተሰኘ አዲስ የግጥም መድረክ ውስጥ ከአዘጋጆች እና ከመስራቾች መካከል አንዱ ነው። "የጥበብ ምሽቶች የተለያዮ ሀሳቦችን የሚያስተናግዱና አሳታፊ ሊሆኑ ይገባል"  ይላል።

"አሁን ላይ በተለይ ወጣቱ እነዚህን ፕሮግራሞች አዘምነህ ስታቀርብለት በጉጉት ነው የሚከታተልህም፡፡ እኛም የመጣነዉ የሀገራችንን ወጣቶች ተማምነን ነው ይሄን ውድድር ያቀረብነው ምላሹንም ከሚመጣው ሳምንት ጀምሮ የሚታይ ይሆናል" በማለት በአይነቱ ለየት ያለ ነው ስላለው ግጥማዊ ውድድሩ ያነሳል።

የሰምና ወርቅ የግጥም ምሽት አዘጋጅ አቶ ጌታቸው አለሙ በበኩሉ "ወጣቱ እንደዚህ ባሉ የግጥም ምሽቶች ላይ መታደም እየተወ ነው።" በማለት ይጀምራል፤ አክሎም "የማንበብ ባህል ከመጥፋቱ ጋር ተያይዞ ይመስላል መድረኮቹ እየተቀዛቀዙ ነዉ ፣ ይሄ ደሞ የወጣት አርቲስቶችን ሞራል እየጎዳ መሄዱ ስለማይቀር ከጊዜ ወደ ጊዜ የእነዚህ ምሽቶች ቀጣይነት አሳሳቢ ነው፣ ኮቪድ ነው እንዳንል ደግሞ በሌሎች ፕሮግራሞች ላይ የሚታየው ነገር ሌላ ነው በተጨማሪም ኮቪድ ከመከሰቱ በፊትም መቀዝቀዝ ይታይበት ነበር" ብሏል።

እነዚህና ሌሎች መሰል ፕሮግራም አዘጋጆች የጥበብ ምሽቶችን ሲያሰናዱ ያጋጠማቸዉን ሲጠየቁ በተደጋጋሚ የሚያነሱት እንደነዚህ አይነት ፕሮግራሞችን የሚያግዙ ባለሀብቶች እና ስፖንሰር አድራጊዎች ጥቂት መሆናቸውን ሲሆን ባለሀብቶች ዝግጅቶቹን ቢደግፉ ለጥበብ እድገት የሚኖረዉ አስተዋፅኦ ከፍተኛ አንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

በእነዚህ መድረኮች ላይ በአቅራቢነት ከሚሳተፉ ወጣቶች መካከል አንዷ የሆነችው ወጣት ዶክተር ፌቨን ፋንጮ "እንደዚህ አይነት መድረክ ለእንደኔ አይነት የሌላ ሙያ ባለቤት ሆነው በአርቱ በኩልም ተሰጥኦዋቸውን ማውጣት ለሚፈልጉ ወጣቶች እጅግ ጥሩ መንገድ ነው። ምክንያቱም አርትን ከፈለግነው ያለንበት ሁኔታ ከመስራት እንደማያግደን የተማርኩበት ነው" ትላለች።

በቲያትር እና ስነፅሁፍ ዘርፍ ታዋቂ ባለሙያ የሆኑት አርቲስት ስዩም ተፈራ በበኩላቸው "በእንደዚህ አይነት ፕሮግራሞች ስጋት አለኝ" ይላሉ "እኔ የጥበብ ትሩፋት የሆኑ ፕሮግራሞች ቢዘምኑ እና ለትውልዱ እንዲመጥኑ ተደርገው ቢሰሩ ደስ ይለኛል። ግን እውነት እነዚህ ዘመናዊ የተባሉት መድረኮች አላማቸው የጥበብ ምሽትን ማሻሻል እና ስነጥበብን ማሳደግ ነው ወይ? ከሆነ ጥሩ ነው! እኔ ግን አንዳንድ ስም በማልጠቅስባቸው ምሽቶች የታዘብኩት ለወጣቱ ከግጥም እና ወግ ጋር መጠጥ እና ሲጋራም በነፃ ይሰጣል። እንደማስታወቅያም በግላጭ 'ወደኛ ሲመጡ ቢራ አለ' እየተባሉ ነው የሚጠሩት። እና እውነት ይሄ ወጣቱን በጥበብ ማንቃት ነው ወይስ ማደንዘዝ  የያዘው?" ብለዋል።

አስተያየት