ሐምሌ 13 ፣ 2013

የአረፋ በዓል ገበያ እንዴት አለፈ?

City: Addis Ababaገበያአካባቢንግድ

ሀይማኖታዊ በአላት ሲከበሩ ከሃይማኖታዊ ይዘት ባሻገር ምግቦች፣ አልባሳት እና የተለያዩ መዋቢያ ቁሳቁሶች ለበአሉ ድምቀት ሲሆኑ ይስተዋላል። በዘንድሮው የኢድ-አል አድሀ አረፋ በአል የገበያ ሁኔታ ምን ይመስላል? አዲስ ዘይቤ ቃኝታለች!

Avatar: Haymanot Girmay
Haymanot Girmay

የአረፋ በዓል ገበያ እንዴት አለፈ?

ሀይማኖታዊ በአላት ሲከበሩ ከሃይማኖታዊ ይዘት እና አከባበር ባሻገር ለእለቱ ማድመቂያ የተለያዩ ምግቦች ይዘጋጃሉ። አልባሳት እና የተለያዩ መዋቢያ ቁሳቁሶች ለበአሉ ድምቀት ሲሆኑም ይስተዋላል። በዘንድሮ 2014 ዓ.ም የኢድ-አል አድሀ አረፋ በአል የገበያ ሁኔታ ምን እንደሚመስል አዲስ ዘይቤ ለመቃኘት ቅኝት አድርጋለች።

"በአረፋ በአል ብዙ ጊዜ ለእርድ የሚፈለጉት በሬ ወይም ቀንድ ያለው በግ ነው" የሚለው ፀጋዬ ተመስገን በአዲስ አበባ በካራቆሬ ገበያ በሬ፣ በግ እና ፍየል ይሸጣል። በሬ አነስተኛው ከ15 እስከ 20 ሺህ ብር፤ መካከለኛው ከ25 እስከ 30 ሺህ ብር፤ ከፍተኛ ደግሞ ከ35 እስከ 50 ሺህ ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ይናገራል።

እንደ ፀጋዬ ገለፃ ከሳምንታት በፊት ከነበረው የበሬ ዋጋ ከ6 እስከ 8ሺ የዋጋ ጭማሪ ያለ ሲሆን በግ ላይም በአንድ ሳምንት ውስጥ የ5 መቶ ብር ጭማሪ አለ። የዋጋ መጨመር የመጣው እንደ ማንኛውም እቃ መጨመር ምክንያት ሆኖ እንጂ በአውደአመት የአቅርቦት ችግር ስለማይከሰት እንዳልተወደደ የሚናገረው ይህ ነጋዴ በጎች የሚመጡበት ቦታ ግን የዋጋ መጠን ላይ አስተዋፅኦ እንዳለው በማብራራት ይናገራል።

ጊንጪን ተከትሎ የወላይታ እና ተጂ በጎች ጣእማቸው ተወዳጅ እንደሆነ የሚናገረው ፀጋዬ ከሌላ አከባቢ የሚመጡ በጎችንም የጊንጪ ናቸው በማለት እንደሚሸጥ ይገልፃል። እንደምክንያት ያስቀመጠው አብዛኛው ገዢ ቢያንስ የ5መቶ ብር የዋጋ ጭማሪ የተፈጠረው ከበጎቹ የጠአም ልዩነት መሆኑን ስለማይረዳ እና ገበያ ለማግኘት ሲባል ለመዋሸት መገደዱን ነው። 

ፀጋዬ አክሎም ከሌላው የበአል ወቅት አንፃር የዘንድሮ የአረፋ በአል ሽያጭ መቀዛቀዙን ተናግሯል።

በተመሳሳይ መርካቶ አከባቢ ቅቤ፣ እንቁላል እና ሽንኩርት ሲገዙ ያገኘናቸው ወ/ሮ ሰአዳ በሽር ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ገበያው ቀዝቀዝ ማለቱን ታዝቤያለው ይላሉ። "12 እንቁላል ገዝቼ ከ1 መቶ ብር 4 ብር ብቻ ተመለሰልኝ" በማለት በግርምት በለበሱት ሻርፕ አፋቸውን ሸፈን አደረጉ። 

የወ/ሮ ሰአዳን ሀሳብ የማይጋራው ዘነበወርቅ አከባቢ የሚገኝ የሽንኩርት ነጋዴ ሙኒር ይማም 1 ኪሎ ሽንኩርት በ15 እና 20 ብር እየተሸጠ መሆኑን በመጥቀስ የዋጋ ጭማሪ የለም ይላል። እንዲሁም የነጭ ሽንኩርት ዋጋም ቢሆን እንደ ሽንኩርት አይነት በ70 እና 90 እንደሚሸጥ ይናገራል። እንደሚለው ገበያው ሞቅ ሞቅ ያለ አውደ አመት የመሰለ ነው።

ለምግብ ፍጆታ ከሚውሉ ቁሳቁሶች በተጨማሪ አልባሳትን የሚገዙ እንዲሁም በሂና እጅ እና እግራቸውን የሚያስውቡ ሴቶች ከበአሉ 1 እና 2 ቀን ቀደም ብሎ በአ.አ ከተማ ውስጥ ሽር ጉድ ሲሉ አዲስ ዘይቤ ቅኝት ባረገችበት ግዜ አስተውላለች።

የእምነቱ ተከታዮች የሚለብሱትን የተለያየ አልባሳት የሚሸጥበት ሱቅ ቅኝት ለማድረግ ወደ ውስጥ በዘለቅንበት ወቅት ደጃፍ ላይ ተሰልፈው እጆቻቸው ላይ በሂና የተለያየ ቅርፅ የያዘውን ስእል መሳይ መዋቢያ የሚመለከቱ ወጣት ሴቶች ይገኛሉ።

ከእነዚህ ታዳጊ እና ወጣት ሴቶች መካከል አይሻ ሞሀመድ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገረችው በየአመቱ የአረፋ በአል ሲመጣ እራሷን ማስዋብ ደስ ይላታል። በተለይም አይሻ ክብረበአሉን የምታከብረው ክፍለ ሀገር ስልጤ ዞን በመሄድ ከዘመድ አዝማድ ጋር በመሆኑ ልዩ ስሜት እንደሚፈጥርባት ትናገራለች። እንዲሁም ለዘመድ አዝማድ አልባሳትን መውሰድ ልምድ መሆኑን የምትናገረው አይሻ የምትገዛቸው ልብሶች ላይ ከአምናው አንፃር የ4 እና የ5 መቶ ብር ብልጫ መኖሩን ታነሳለች።

የአይሻን ሀሳብ በመጋራት ከባለፈው አመት አንፃር የአልባሳት ዋጋ መጨመሩን የሚጋሩት የልብስ ሻጭ የሆኑት ወ/ሮ ዚያዳ ይህ ግን ከክብረበአሉ ጋር ተያያዥነት የለውም ይላሉ። እንደማንኛውም እቃ ከጊዜው ጋር መጨመሩን በመግለፅ ገበያው ግን አለመቀነሱን እንደውም በገበያ ብዛት ፋታ ማጣታቸውን ይናገራሉ። 

የእምነቱ ተከታይ የሆኑት ወ/ሮ ዚያዳ የአረፋን በአል ከእለቱ ባሻገር ለተከታታይ 3 ቀናት የስራ ቦታቸውን ዘግተው እንደሚያከብሩ የሚናገሩ ሲሆን ይህም በክብረበአሉ ለብዙ ጊዜ ሳይገናኙ ከቆዩ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ለማሳለፍ መሆኑን በመናገር ነው።

የኢድ-አል አድሀ አረፋ በአል በአላህ ትእዛዝ መሰረት ኢስማኤል በአባቱ በነብዩ ኢብራሂም ለመስዋዕትነት ሲዘጋጁ አላህ ለመስዋዕት የሚሆን ሙክት በግ ማዘጋጀታቸውን ለመዘከር ታስቦ እንደሚከበር የእምነቱ አባቶች ይናገራሉ።

የበዓሉ የእርድ ስነስርአት ሲደረግም ሆነ በአሉ ሲከበር በመሰባሰብ እና በመረዳዳት መሆኑን ነግረውናል።

አስተያየት