ሐምሌ 15 ፣ 2013

'ሞገደኞቹ' ጫኝ እና አውራጅ ቡድኖች

City: Addis Ababaአካባቢማህበራዊ ጉዳዮች

በአዲስ አበባ በኪራይ ቤት የሚኖሩ ዜጎች ቤት ቀይረው ወይም በሌላ ምክንያት እቃ ሲያጓጉዙ ዕቃውን በሚያስገቡበትም ሆነ በሚያወጡበት ወቅት በየሰፈሩ ካሉ እቃ ጫኝ እና አውራጅ ቡድኖች ጋር የሚገጥሙት አተካራ የሚያስመርር ሆኖባቸዋል።

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

'ሞገደኞቹ' ጫኝ እና አውራጅ ቡድኖች

በአዲስ አበባ ቤት ቀይሮ ወይም በሌላ ምክንያት እቃ ማጓጓዝ ለብዙዎች እንቅልፍ የሚነሳ ጉዳይ ሆኗል በተለይም በኪራይ ቤት የሚኖሩ ዜጎች ዕቃ በሚያስገቡበትም ሆነ በሚያወጡበት ወቅት በየሰፈሩ ካሉ እቃ ጫኝ እና አውራጅ ቡድኖች ጋር የሚገጥሙት አተካራ የሚያስመርር ሆኖባቸዋል።

"እቃዬን ራሴ ጭኜ ራሴ አወርዳለሁ" ወይም "አጋዥ ዘመድ ከጎኔ አለ" ማለት የሚታሰብ አይደለም። 

ሳይፈቀድላቸው ወደ ቤት ሰተት ብለው የሚገቡ፣ ባላቤቱን ሳይቀር "እቃህን አትነካም" ብለው የሚያስፈራሩ እና ስራውን በሃይል የሚወስዱ ጫኝ እና አውራጆች በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች መኖራቸውን አዲስ ዘይቤ ተረድታለች። ወጣቶቹ የስራ እድል ማግኘታቸው የሚደገፍ ቢሆንም እንዲህ ካለባለቤቱ ፍቃድ ስራውን ካልሰራን ማለታቸው ግን ነገሩ ከስርዓት ያፈነገጠ መሆኑን ማሳያ ነው። የባሰው ችግር ደግሞ እነዚህ ወጣቶች ለስራው የሚጠይቁት ክፍያ እጅግ የተጋነነ መሆኑ ነው። በአንድ መኪና በትንሹ 5,000 ብር ከፍ ሲል ደግሞ እስከ 20,000 ብር እንደሚጠይቁ ሰምተናል።

ለአዲስ ዘይቤ ሃሳባቸውን ካጋሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ጌጤነሽ ዘርዓብዛ ከባለቤታቸውና ከወንድማቸው ጋር በመሆን እቃቸውን ጭነው ገላን ኮንዶሚኒየም ወደተከራዩት ቤት ይሄዱና እቃውን ማውረድ ሲጀምሩ በአካባቢው የተሰባሰቡ ወጣቶች 'እቃውን የምናወርደው እኛ ነን' በማለት እንደሞገቷቸው ይገልፃሉ።

"ለማውረድ እኛ እንበቃለን ስንላቸው 'አሻፈረኝ' ብለው መኪናውን ከበው ቆሙ። ይባስ ብሎ ለማውረድ ስድስት ሺህ ብር ጠየቁን። አልሰማ ሲሉን ፖሊስ ጋር ብንደውልም ሊመጡልን አልቻሉም" በማለት ያጋጠማቸውን በምሬት ይናገራሉ።

ከብዙ ንትርክ በኋላ የኮንዶሚኒየሙ ነዋሪዎች መጡ እና "አስቸጋሪዎች ናቸው ብትከፍሉና ብትገላገሏቸው ነው የሚሻላችሁ" በማለት ሲነግሯቸው የጠየቁትን ብር ለመክፈል መገደዳቸውን ተናግረዋል።

አቶ ኢሳያስ አምደፅዮን የተባሉ ነዋሪነታቸው ወደ ጋርመንት ኮንዶሚኒየም ነው፣ "እኛ በፊትም እንደዚህ አይነት ድርጊቶች መኖራቸውን ጭምጭምታ ስለምንሰማ እና ስጋት ስላለ እቃችንን ይዘን የመጣነው ወጣቶቹ አይኖሩም በሚል እሳቤ ሌሊት 10:00 ገደማ ነበር። ከዛ ደርሰን እቃችንን ማውረድ እንደጀመርን የኮንዶሚኒየሙ ጥበቃ ደውሎላቸው ነው መሰል መጡ። ሲመጡ ብዙ አውርደን ልንጨርስ ትንሽ ነበር የቀረን እና ከልመና እና ከልምምጥ ጋር 1000 ብር ሰጥተናቸው ነው የሄዱልን።" ሲሉ ገጠመኛቸውን አጋርተውናል።

'ህብር እቃ ጫኝና አውራጆች' የተሰኘ 'በህግ የተደራጀ' የተባለ ቡድን መሪ የሆነውን ወጣት ፍራንቦን አቶምሳ ስለሚባለው ነገር ለቀረበለት ጥያቄ "እንዲህ አይነት ቡድኖች መበራከታቸው ገልፆ የእነሱ ማህበር ከመንግስት እውቅና አግኝቶ ወደ ስራ እንደገባ" ይናገራል።

"እኛ በህግ እና በአግባብ በተመጣጣኝ ዋጋ በባለቤቱ ፍቃድ ላይ ተመስርተን ነው ምንሰራው። ግን እነዚህ ወንበዴ ቡድኖች የኛንም እንጀራ እየዘጉ እና ተዓማኒነታችንን እያጠፉ ስለሆነ መፍትሄ ቢፈለግልን ብለን ነው ከህዝቡ እኩል ምናማርረው" ሲል ተናግሯል።

አዲስ ዘይቤም "ለመሆኑ ይህ ችግር በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ይታወቅ ይሆን? ከታወቀስ ኮሚሽኑ ችግሩን ለመፍታት ምን እየሰራ ነው?" ስትል የኮሚሽኑን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታን ጠየቀች፤ "በአዲስ አበባ በጫኝና አውራጅ ስራ የተሰማሩ እና በህጋዊ መንገድ የተደራጁ ወጣቶች አሉ። ይሁን እንጂ ከህጋዊዎቹ ጋር ተቀላቅለውና ህዝቡን የሚያማርሩ ቡድኖች መበራከታቸውንም በዚያው ልክ ብዙ መሆናቸውን ደርሰንበታል" ይላሉ ኮማንደሩ።

አክለውም "ለምሳሌ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በህጋዊ ሽፋን ህገወጦቹም አንፀባራቂ ልብስ እየለበሱ እቃውን ለማውረድ እና ለመጫን እቃው ከሚያወጣው ዋጋ በላይ እየጠየቁ ህዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያማርሩ ሞገደኛ ቡድኖች እንዳሉ ጥቆማ ደርሶናል። ኮሚሽኑም ይህን ጥቆማ ተገንዝቦ በሁሉም ቦታዎች ስምሪት እንዲኖር ተደርጎ ጠንካራ ክትትል እየተደረገ ነው። አሁንም ይህ ክትትል ይቀጥላል።" ብለዋል።

የገላን ኮንዶሚኒየም የነዋሪዎች ኮሚቴ ዋና ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዋቆ ቦጃ በበኩላቸው በፖሊስ በኩል ክፍተት እንዳለ ያነሳሉ "ሰራተኞቹ በህጋዊ መንገድ የተደራጁ ስለሆኑ ተደራደሩ ከማለት ውጪ ፖሊስ ምንም መፍትሔ አይሰጥም" ይላሉ።

አክለውም "ፖሊሶች ጋር ደውለን ሲመጡ ስራቸው ነው ስለዚህ አትስሩ ማለት ስለማንችል በመግባባት ተደራደሩ ነው የሚሉን። በዚሁ ጉዳይ ጥል ሁሉ ተፈጥሮ ሲመጡ በህግ ተደራጅተው ነው እና ስሩ የተባሉት እነሱም ይስሩ እናንተም ተነጋገራችሁ ተግባቡ በማለት ትተው ይሄዳሉ በማለት ተናግረዋል።

ከዚህ ቅሬታ ጋር በተያያዘ ማብራሪያ የጠየቅናቸው ኮማንደር ፋሲካ "ከሙያዊ ስነምግባር ያፈነገጡ እና መጥፎ ባህሪ የተላበሱ ፖሊሶች ስለሚኖሩ እንደዚህ አይነት አጋጣሚ አልፎ አልፎ ሊፈጠር ይችላል። ሆኖም ግን ፖሊሶች በዚህ ጉዳይ ተባባሪ ሆነው ሲያይ ህብረተሰቡ ማለፍ የለበትም ወደ ጣቢያ በመሄድ በየደረጃው ላሉ የፖሊስ አካላት ሪፖርት በማድረግ ችግሩን እንድንቆጣጠር ሊያግዙን ይገባል" ብለዋል

በህጋዊ መንገድ ተደራጅተው በየቦታው የሚሰሩ ጫኝና አውራጆችም ቢሆኑ ከባለንብረቱ ፍቃድ ውጪ የማንንም ንብረት የመንካት መብት እንደሌላቸው ኮማንደሩ አስረግጠው የተናገሩ ሲሆኑ "ማንኛውም ሰው በህግ የተሰጠው ንብረቱ ላይ የማዘዝ መብት ስላለው እንዲህ አይነቱን አጋጣሚ በቸልታ ሊያየው አይገባም ሊከስ ይገባል" ሲሉም አሳስበዋል።

ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባገኘነው መረጃ መሰረት እስካሁን 86 ጫኝና አውራጆች በወንጀሉ ተከሰው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ሲሆን ከህጋዊ ጫኝና አውራጆች ጋር ተቀላቅለው ህገወጥ ስራ የሚሰሩ 214 ግለሰቦችም በህጋዊ መንገድ ተመዝግበውበት ከነበረው ስራ እንዲወጡ ተደርገዋል። በተጨማሪም በቤታቸው ቁጭ ብለው የሚያዙና የህገወጥ ድርጊቱ መሪ የሆኑት ግለሰቦችም እየተለዩ ወደ ህግ እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው።

አስተያየት