ሰኔ 28 ፣ 2013

ተናጋሪ የፊልም ማስታወቂያዎች

የጥበብ ዐውድፊልም

ለፊልሞች ማስተዋወቂያ የሚሰሩት የምስል ማስታወቂያዎች (ፖስተሮች) ሰዎች ፊልሞቹን እንዲመለከቱ የሚጋብዙና እነማን እንደተወኑበት የሚያሳውቁ ከመሆን ባለፈ ከፊልሞቹ ታሪኮች ጋር ያላቸውን ተዛምዶዎች እጅግ የሚያጣጥሙ መሆን አለባቸው።

Avatar: Dawit Araya
ዳዊት አርአያ

Dawit has been the Amharic assignment editor at Addis Zeybe. He has worked in printing, electronics, and online news platforms such as Fitih, Taza, and Ye Erik Ma'ed for the past five years.

ተናጋሪ የፊልም ማስታወቂያዎች

የኢትዮጵያ ፊልም ኢንደስትሪ በብዙ አከራካሪ ጉዳዮች የተሞላ ነው። በአንድ ወገን አድጓል በሌላው አላደገም፤ በሌላ አቅጣጫ ኢንዱስትሪ ነው በሌላው ለዚያ ደረጃ አልበቃም፣ በአንዱ ጎራ ባህል በርዟል በሌላው አሳድጓል... የሚሉ ክርክሮች ከተለያዩ ጎራዎች ይደመጣል። አዲስ ዘይቤም የኢትዮጵያ ፊልም ለማስተዋወቅ የሚወጡ ፖስተሮችን /የስዕል ማስታወቂያዎች/ ይዘትና አቀራረብ ላይ መጠነኛ ዳሰሳ አድርጋለች። 

ለፊልሞች ማስተዋወቂያ የሚሰሩት ፖስተሮች ጥበባዊ አሻራቸውን እንደያዙ- ሰዎች ፊልሞቹን እንዲመለከቱ የሚጋብዙ፣ እነማን እንደተወኑበት የሚያሳውቁ እንዲሁም ከሰዎች ጭንቅላት በቀላሉ የማይጠፉ መሆን እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ የተሰሩት የምስል /የፎቶ/ ማስታወቂያዎች ከፊልሞቹ ታሪኮች ጋር ያላቸው ተዛምዶዎች መጣጣም እንዳለባቸው ብዙዎችን የሚያስማማ ጉዳይ ነው። 

በተጨማሪም በፊልሙ ውስጥ ምንያክል የትወና ሚና የነበራቸው ገጸ-ባህሪዎች ናቸው በፖስተር ማስታወቂያ ላይ መካተት ያለባቸው የሚለው ከፊልም የማስታወቂያ ሽፋን ዝግጅቶች ወቅት በደምብ ሊታሰብባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች ወስጥ ይካተታል። በዚህ ዘገባም አዲስ ዘይቤ የተወሰኑ የፊልም ማስታወቂያ የምስል ሽፋኖችን እንደምሳሌ ወስዳ ዳስሳለች።  

የመጨረሻዋ ቀሚስ፡-

በአንድ የህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ እያደጉ ስለሚገኙ እና ከHIV ቫይረስ ጋር ስለሚኖሩ ወጣቶች የሚተርክ ፊልም ነው፡፡  ፊልሙ በዕይታ ላይ በነበረበት ወቅት የተለያዩ ሽልማቶችን ለማግኘት በቅቷል፡፡

 

በምስል ማስታወቂያው ላይ ሦስት አስፋልት የሚሻገሩ እንስቶች ይታያሉ፡፡ እንስቶቹ ከአንድ የመንገድ ምእራፍ ወደ ሌላ ምእራፍ ህጉን ጠብቀው በመሻገር ላይ እንዳሉ ምስሉ ያሳያል፡፡ ዜብራው ከለመድነው የመሻገሪያ ዜብራ ጋር የተዛመደ ዕይታ ይኑረው እንጂ ልዩነትም አለው፡፡ ቁጥሮች አሉት 16፣ 17፣ 18፣ እያሉ የሚያድጉ ግን 21 ላይ የሚቆሙ፡፡ ሰልፍ በሚመስል ተራ ከቆሙት ሴቶች መሐል አንዷ 21 ላይ ቆማለች፡፡ ከፊትለፊት አንድ መነጋገሪያ አለ፡፡ የዘፋኝ የመሰለ ማይክራፎን፡፡ ድባቡ ጨለም ያለ ነው፡፡ የበራ፣ የፈካ፣ የደመቀ ነገር አይታይበትም፡፡ በምስል ማስታወቂያ /ፖስተሩ/ ላይ ያለው አጠቃላይ ትእይንት ይህ ነው፡፡

ፊልሙን ከመመልከቱ በፊት ይህንን ፖስተር የተመለከተ ታዳሚ ጭንቅላት ወስጥ የተለያዩ ጥያቄዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። የምስል ማስታወቂያውን ለተመለከተ ሰው ዜብራው ምንድነው? ወዴት እየተሻገሩ ነው? አልፈዋቸው የመጡት ቁጥሮች ለምን 21 ላይ ቆሙ? ማይክራፎኑ ምንድነው? ርዕሱ የመጨረሻዋ ቀሚስ ለምን ሆነ? የሚሉት ጥያቄዎች ይጭራል።

ፊልሙ ካልታየ በስተቀር ለነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኝት አስቸጋሪ ነው፡ የዚህ ፊልም ፖስተር ከፖስተርነት አልፎ ጠንካራ መልዕክት እና የታሪኩ ስእላዊ መግለጫ መሆኑን የምንረዳው ከፊልሙ ዕይታ በኋላ ነው፡፡

ዜብራው፡- ዜብራው በማሳደጊያ ውስጥ ያሉት ወጣቶች እድሜን ያሳያል፡፡ የኤች አይ ቪ ኤድስ መድሃኒቶች እንደልብ ባልነበሩበት ወቅትና አሁን  የቴክኖሎጂ ምርምር ባልደረሰበት ወቅት ከቫይረሱ ጋር አብረው የተወለዱ ሰዎች 21 ዓመትን በህይወት መሻገር እንደማይችሉ ለማሳየት የተሞከረ ነው። ከዚያም ባለፈ  22 ብለው ለመቁጠር ያልታደሉት ለጋ ወጣቶች እድሜ… እዚያች እድሜ ላይ ያለውንም ሽግግር ይሳያል፡፡ ከአንድ ምእራፍ ወደ ሌላ ምእራፍ፡፡ ከመኖር ወደ አለመኖር፡፡ ህግ ጠብቀው፣ ስርአት አክብረው እየተሻገሩ ነው፡፡ ግን ይሞታሉ፡፡ መሞት ሕግ በማፍረሳቸው፣ ስህተት በመፈጸማቸው ምክንያት የመጣባቸው ስላልሆነ በተፈቀደ ክልል ሲሻገሩ እናያለን፡፡ በውልደት አገኙት አንጂ በሌላ አላመጡትምና።

ማይክራፎኑ፡- ከዚህ በፊት በእውኑ አለም የምናውቃቸው ድምጻዊያን ዘፈኖች ለፊልሙ በሚሆን መልኩ ተካተዋል፡፡ በአንዲት ዘፋኝ ገጸባህሪ አማካኝነት፤ ማይክራፎኑ ያንን ለማሳየት የገባ ነው፡፡

ርዕሱ፡- ለመጨረሻ ጊዜ የሚከበረው የልደት ቀን ላይ የመጨረሻዋ ሟች የምትለብሰውን ቀሚስ ለማመልከት እና በፊልሙ ውስጥ አንድ አንድ እያሉ ከህይወት መዝገብ የሚቀጠፉትን እንስቶች ለማመልከት የተሰየመ ሳቢ ርዕስ ነው፡፡

የድባቡ መጨፍገግ፡- በፊልሙ ውስጥ አስቂኝ ትዕይንት አለመኖሩን ለማሳየት ታልሞ የገባ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በሌላ አካል ስህተት በመጣባቸው መከራ ተስፋቸውን እንዳነገቡ፣ ለመኖር እንደጓጉ ህይወታቸውን ስለሚያጡ ወጣቶች የሚያሳይ ፊልም መሆኑን ለማሳየት የተደረገ እንደሆነ ያስረዳል። ፡

የሴቶቹ አመጣጥ ወደፊትለፊት ነው፤ ወደተመልካቹ፡፡ ባለሙያው ወደተመልካች እንዲመጡ ያደረገበት ምክንያት ክስተቱ በማንም ህይወት ወስጥ ሊፈጠር እንደሚችል ሊያስረግጥ እንዳሰበ መረዳት ይቻላል። 

ከምስሉ መረዳት የሚቻለው በፊልሙ ውስጥ ያሉ ክስተቶች ከሞላ ጎደል ተዳሰዋል። ሁሉም ነገሮች ፍቺ፣ ሰበብ እና በፊልሙ ታሪክ ውስጥ ድርሻ አላቸው፡፡ ቀድመን እንድንጠይቅ እንጂ ቀድመን እንድናውቅ የሚፈቅድልን አንዳች ነገር የለበትም፡፡ ፖስተሩ የፊልሙ አጭር መግለጫ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡

የባህር በር፡- 

“ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል!” ብሎ የተነሳን ተመራማሪ ታሪክ የሚተርክ ፊልም ነው፡፡ አለቶችን በድማሚት በማፍረስ ሰው ሰራሽ ወደብ መስራት ይቻላል ብሎ የሚተጋን ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የሥራ እና የምርምር እንዲሁም የቤተሰብ ታሪክ ያስቃኛል፡፡ 

 

 

ጥቁር የለበሱ ሁለት ሰዎች በፖስተሩ ላይ ይታያሉ፡፡ ፊት ተነሳስተው፣ ጀርባ ተሰጣጥተው፣ ሳቅ ርቋቸው፣… ባህር ዳርቻ ላይ የቆሙ ወንድ እና ሴት፡፡ መላቀቅ ቢፈልጉ እንኳን የማይችሉ፡፡ በወርቃማ ገመድ የተሳሰሩ ሰዎች፡፡ ከጀርባቸው መርከብ ይታያል፡፡ መርከቡ ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ይውለበለባል፡፡

አመራማሪ ክስተቶችን የያዘ ፖስተር ነው፡፡ ሁለቱም ለምን ጥቁር ለበሱ? ለምንስ በወርቃማ ገመድ ታሰሩ? ከገመዱ ጋር የተያያዘችው ቁልፍ መሰል ነገር ምንድናት? የሚሉትን ጥያቄዎችን ያጭራል።

ፊልሙን ማየት ስንጀምር በፖስተሩ ላይ የምናያቸው ገጸ-ባህሪዎች ባል እና ሚስት መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ በትዳር የኖሩ፣ ወልደው የሳሙ፣ ነገር ግን ሚስጥር የሚደባበቁ... ባል አንገቱ ላይ በወርቅ አሰርቶ ስላንጠለጠላት ጌጥ መሰል ነገር ለልጁ እናት እንኳን የማይናገር ድብቅ ሰው ነው፡፡ ሀገሩ የባህር በሯን ስለምታገኝበት መንገድ የተመራመረበትን ሰነድ የት እንደሚያስቀምጥ ለማንም ትንፍሽ የማይል ኃይለኛ ምስጢረኛ ግለሰብ ነው፡፡

ፊልሙን ስናጋምስ ሚስትም ከባሏ የሸሸገቻቸው በርካታ የሚስጥር ቋጠሮዎች እንዳሉ እንረዳለን፡፡ ይሁን እንጂ ተራቸውን ጠብቀው ምስጢሮቻቸውን ይዘረገፉልናል፡፡ የተመራማሪው ሚስት ባልዋ የሚያጠናውን ጥናት ለመዝረፍ ካሴሩ የውጪ ኃይሎች ጋር ግንኙነት አላት፡፡ ባልዋን እየሰለለች መረጃ ታቀብላለች፡፡ ሚስቱም ወዳው ሳይሆን ለዚሁ ጣጠኛ ምስጢር ብላ ያገባችውን ባሏን እየሰለለች ለሌላ ሀገር አሳልፋ ትሰጠዋለች፤ ጀርባ የተሰጣጡበት ምክንያትም ይገለጣል፡፡

እዚህ ጋር የፖስተሩ ምስጢር ይፈታል ለባሏ ጀርባዋን የሰጠች ሚስት፡፡ ለሚስቱ ሚስጥሩን የማያካፍል ባል… በቀለም ሳይንስ ጥቁር ድብቅ ቀለም ነው፡፡ ሁሉም ቀለማት በውስጡ ሸሽጓል፡፡ የብርሃን እርዳታ ካልታከለ በቀር በጨለማ መተያየት አዳጋች ነው፡፡ ለነዚህ ለማይተያዩ ጥንዶች፤ በሚስጥር ትብትብ ለታሰሩ ጥንዶች፤ ከጥቁር ውጪ ገላጭ ቀለም ከየት ይመጣ ይሆን? የወርቃማ ቀለም ትርጓሜ ደግሞ ሚስጥር ነው፡፡ ተፈላጊ ሚስጥር፡፡ 

በፖስተሩ ላይ የምናያት ቁልፍ ሚስጥርም በስተመጨረሻ ይፈታል፡፡ ተመራማሪው  የምርምር ውጤቱን እናቴ የሰጠችኝ የአደራ እቃ ነው እያለ ያወራለት በነበረውና ዘወትር ከአንገቱ በማይለየው ጌጥ መሰል የወርቅ ጋን ላይ በሚሞሪ ካርድ እንደሚያስቀምጠው ከፊልሙ ማብቂያ ላይ ይገለጥልናል።

ይህ በሃገራዊ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚያውጠነጥነው ፊልም ፖስተሩ በከባድ ሚስጥር የተሳሰሩትን ሰዎች ታሪክ የሚያሳይ ታሪክ መያዙን አመላካች ፖስተር ነው፡፡

የወንዶች ጉዳይ ቁጥር 1፡- 

እንጨት ስራ ሙያ ያላቸው እና አንድ ግለሰብ ቤት ተቀጥረው ስለሚሰሩ ወጣት ጓደኛሞች የፍቅር ታሪክ ላይ የሚያውጠነጥን አስቂኝ ይዘት ያለው ነው፡፡

 

እስካሁን ከዳሰስናቸው የፊልም ፖስተሮች በተለየ መልኩ በዚህ ፖስተር ላይ በፊልሙ ውስጥ ያሉት ሁሉም ተዋንያን ሊባል በሚችል ሁኔታ ፖስተሩ ላይ ተካተዋል ነው፡፡ የስራ ቱታ የለበሱት ወጣቶቹ አንድን ሰው በእጃቸው  ተሸክመውታል፡፡ የፖስተሩ የጀርባ ቀለም /Background/ ነጭ ነው፡፡ ነጭ የሳቅና የደስታ መገለጫ በመሆኑ ከኮመዲነቱ ጋር ሰምሯል፡፡ ጫማው አካባቢ ያለው ገጸባህሪም አፍንጫውን በመያዝ የኮመዲነቱን ነገር ያጎላዋል፡፡ ውስጥ ያሉትን ትረባዎች ቀድሞ ያመላክታል፡፡ ቀብረር ያለች የምትመስለው የቆመችውም እንስት በጓደኞቹ ድጋፍ ሊይዛት የሚንጠራራውን ሰው ጀርባዋን ብትሰጠውም ዞር ብላ ታየዋለች፡፡ ፊልሙን ስናይም ይህንኑ እንረዳለን ብትሄድም አትጨክንበትም፡፡ የቱታው፣ የሸክሙ የሌላውም ትርጉም በተገቢው መንገድ የተቀመጠ ጥሩ ፖስተር ነው፡፡

የወንዶች ጉዳይ ቁጥር 2፡

በዚህኛው ክፍል ዋናው የታሪኩ አጠንጣኝ ማን እንደሆነ እና ከመጀመሪያው ታሪክ በኋላ የተከሰተውን አዲስ ነገር ማለትም እርግዝናን አካቶ ያቀረባል።

 

አልደወለም፡ 

ተሳስቶ በተደወለ ስልክ የተዋወቁትን ወንድ “ደወለ” “አልደወለም” እያሉ በሚጠባበቁ ወጣት ሴት ጓደኛሞች ላይ የሚያጠነጥን የፍቅር ፊልም ነው።

 

 

 

 

እነዚህን ለናሙና ያህል አነሳን እንጂ የፊልሞቹን ብዛት ያህል ባይሆንም ሌሎች ያላነሳናቸው ጥሩ ጥሩ ፖስተሮችም አሉ፡፡ ይሁን እንጂ የፊልም ፖስተሮችን ዲዛይን ያደረገው ማን እደሆነ የሚገልጽ ጽሑፍ በስራዎቹ ላይ የለም፡፡ 

በዚህ ዘገባ በጥሩ መልኩ የተዘጋጁ የፊልም ሽፋኖችን ብናነሳም ከዚሁ ባልተናነሰ መልኩ ቁጥራቸው ትንሽ የማይባሉ የፊልም የምስል ሽፋኖች በቂ ዝግጅት ያልተደረገባቸውና የፊልሙን ይዘት በሚገባ የማያሳዩ እንደሆኑ ታዝበናል። በፊልሙ ውስጥ ከ2 ደቂቃ ያልበለጠ ሚና ያልነበራቸው ተዋንያንን በፖስተር ላይ ደርድረው የፎቶ ኢንዴክስ ያስመሰሉትን፤ ከሃሳቡ ጋር ምንም የማይገናኝ ፎቶ የሚጠቀሙ፤ የ5 ደቂቃውን ትዕይንት የሙሉ ፊልሙ ሙሉ ሃሳብ አስመስለው የሚያቀርቡ፣ ከፊልሙ ዋና ጭብጥ ጋር የተቃረኑ ቀለማት የተጠቀሙ የፊልም ፖስተሮች በቁጥር ቀላል አይደሉም።

አስተያየት