ሰኔ 27 ፣ 2013

‘ማል መሊሳ’ - ከፍቅር እስከ ትግል

ሙዚቃ

በአዲሱ የሃጫሉ አልበም ላይ የተደረገ የወፍ በረር ቅኝት

Avatar: Naol Getachew
ናኦል ጌታቸው

Naol is a journalist and fact-checker at Addis Zeybe for HaqCheck. He is a professional working in the fields of fact-checking, journalism, online storytelling, and translation.

‘ማል መሊሳ’ - ከፍቅር እስከ ትግል

በብዙሃን ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትና ዝናን ያተረፈው ሙዚቀኛና የሰብአዊ መብት ታጋይ ሃጫሉ ሁንዴሳ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለበትን አንደኛ  አመት ተከትሎ ከዚህ በፊት በህይወት እያለ የሰራቸውን 14 የኦሮምኛ ሙዚቃዎች ያካተተ ‹‹ማል መሊሳ›› የተሰኘ አልበም ከሰሞኑ ለአድማጮቹና ለአድናቂዎቹ ገበያ ላይ ውሏል፡፡

ማል መሊሳ - 14 ትራኮችን የያዘ ሰንዱቅ ነው፡፡ ከ14ቱ ሙዚቃዎች የ13ቱ ግጥም እና የ12 ዜማዎች የተሰሩት በራሱ ሃጫሉ ሁንዴሳ ነው፡፡ Haadha Wabbi በዮሳን ጌታሁን ግጥምና ዜማው ሲሰራ የKuullee koo ግጥም ደግሞ ሃጫሉ፣ ላሊሳ ኢድሪስ እና ስንሻው ሙለታ በጋራ ተሳትፈውበታል፡፡ አቀናባሪ ዳዊት ታደሰ ዘጠኝ ፣ ዲንቂሳ ደበሌ ሶስት ፣ አብርሃም ኪዳኔና ካሙዙ ካሳ እያንዳንዳቸው አንድ ሙዚቃዎችን በማቀናበር በአልበሙ ስራ ላይ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡ ስመጥሩ የሙዚቃ ባለሙያ አበጋዙ ሺዮታ ያላለቁ ስራዎችን ጭምር ሚክሲንጉንና ማስተሪንጉን በመስራት አልበሙ የሰመረ እንዲሆን አንዲሁ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

ማል መሊሳ ከሃገር ውስጥ የሸዋ ኦሮሞ ፣ የወሎ ፣ ባሌ ከውጪ የሬጌ ፣ ፖፕ እና ሌሎች የሙዚቃ ስልቶችን በውስጡ ይዟል፡፡

 

የት ነው ያለሽው?

ሃጫሉ ከትግል ዘፈኞቹ ባሻገር ብዙ ድንቅ የፍቅር ዘፈኖች ያቀነቀነ ድንቅ አርቲስት ነው፡፡ እንደውም የሙያ አጋሩና ጓደኛው ጃምቦ ጆቴ ‹‹ከፖለቲካ ሙዚቃዎቹ ይልቅ የፍቅር ዘፈኖቹ ይበዛሉ›› ይላል፡፡ በዚህኛው ‹‹ማል መሊሳ›› በተሰኘ አልበሙም በርከት ያሉ የፍቅር ዘፈኖችን አካትቷል፡፡ እነ Sagalee keetan Hawwe ፣ Kuullee Koo ፣  Eessa jirta በሰፌድ አልበሙ ውስጥ ያሉ ውብ የፍቅር ሰበዞች ናቸው፡፡ 

‘Eessa jirta’ በአማርኛ ሲተረጎም የትነው ያለሽው የሚል መልእት ያለው ሙዚቃ  በአልበሙ ላይ በመጀመሪያው ላይ የተቀመጠው ሙዚቃ ነው፡፡ በፍቅሯ ልቡ የጠፋበት ጉብል የጠፋችበትን እንስት እያሰሰ የሚከተለውን ስንኝ ይቃኛል...

Halkan guyyaa ijarraa nan baddu

Ciisee ka’uus waanuma keen yaada

Takkitikoo kan dur dabarsine

Odo Keenya Yadadhetan gadda

Eessa jirta Maloo kotuu

(ቀንና ሌት ካይኔ አትጠፊም

ስላንቺ ነው የማስበው ተኝቼ ስነሳም

አንድያዬ ድሮን አብረን ያሳለፍን

ጓሯችን ትዝ ሲለኝ አዝናለሁ

የት ነው ያለሽው)

ይላታል፡፡  ይቀጥልና፡-

Hanga lubbuun jirru addunyaa tanarra

Furtuun gafachuu koo suma harka jira

Isa nan jette san akkam goote adaraa

Afuura ken dhabe barbacha ken joora

Essa jirta maloo kootuu

(በሕይወት እስካለን በዚህች አለም

የጥያቄዎቼ ቁልፍ በእጅሽ ነው ያለው

እንዴት አደረግሽው - አደራ ያን ያልሽኝን

በፍለጋሽ ተንከራተትሁ አጣሁት ትንፋሽሽን

የት ነው ያለሽው - እባክሽ ነይ)

 

‘Sagalee keetan hawwe’ የሚለው ሌላኛው ትራክ በባሌ ዘዬ የተሰራው ሌላኛው የፍቅር ዘፈኑ ነው፡፡ ድምፅሽን ነው የተመኘሁት እንደማለት ነው፡፡ ጥቂት ስንኞቹም፡-

Sagalee keetan hawwe taliila kee qabana

Garaan na rasa ana aka baro shekana

Fudheen si lixa fudhen sii

(የተመኘሁት የሚያረጋጋኝን ያን ድምፅሽ

ሆዴ ይናጣል እንደ ባሮ ሼከና

ይዤሽ እበርራለሁ ይዤሽ)

 

Ilma Nama (የሰው ልጅ)

ማል መሊሳ አልበም ከያዛቸው ስራዎች አንዱ Ilma Namaa (የሰው ልጅ) የተሰኝው ሙዚቃ  ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን የመንከባከብን ኃለፊነትን ለወገን በማስታወስ አልሞ የተሰራ ሙዚቃ ነው። በዚህ ሙዚቃ ሃጫሉ ዘፈንን ለማህበራዊ ፋይዳ አውሎታል፡፡ ኢልመ ነማ እንዲህ ይላል፡-

Carraa ilma namaa

Jalqabaaf dhumaa

Tilmaamuun hin ulfaataa

Waan hunduma keessaa

Ilmi nana daggalaa

Tuuree buleet dabalaa

(የሰው ልጅ ዕጣው

መነሻ መድረሻው

መገመት ይከብዳል

ከሁሉም ከሁልም

ጫካ ነው የሰው ዘር

የሚጨምር ውሎ ሲያድር)

በዚህ ሙዚቃው አርቲስት ሃጫሉ የሰው ዘርን በጫካ ይመስለዋል አያይዞም ልክ እንደ ጫካ የሰውን  መነሻ መድረሻውን ለመገመት እንደማይቻል በሙዚቃው ውስጥ ይገልፃል፡፡ የልጆችንም መነሻ ከማን እንደሚወለዱ ፤ ወላጆችም መድረሻቸው መቼ እና የት እንደሆነ መገመት አንችልም ይለናል ሃጫሉ በዘፈኑ፡፡ ስለሆነም፡- 

Silaa akkuma keenyaatti

Dhalaa namaati isaanis

Har’aaf caarraan gantee

Haadhaaf abbaa dhabanii

Haadhaaf abbaa dhabuun isaani qooda rabbiiti

Da’iimman kana gargaaruun qooda lammiiti

(እነሱም እንደኛው የሰው ልጆች ናቸው

ዛሬ ዕድል ጠምማ ወላጆቻቸውን ቢያጡ

እናት አባት ማጣታቸው የእግዜር ፈንታ ነው

ልጆቹን መርዳት ደግሞ የዜጎች ድርሻ ነው)

የፈጣሪን ሰራ ለእርሱ ትተን የኛ (የሰዎች) ድርሻ የሆነውን ሃላፊነት ራሳችን እንወጣ የሚል ሰብዓዊነትን የሚያቀነቅን ድንቅ ስራ ነው - ኢልመ ነማ፡፡

 

ያልተቋጨው የሐጫሉ ትግል

አርቲስቱ ባነሳው የመብት ትግል የተነሳ በአፍላ ዕድሜው ለአመታት እስር ተዳርጎ እንደነበር በሰፊው ይነገራል፡፡ ከእስር ከተፈታም ወዲህ በሚሰራቸው ሙዚቃዎች የኔ ለሚለው ማህበረሰብ ሲታገል ቆይቷል፡፡ በዚህኛው አልበሙም ይኸው ትግሉ የቀጠለ ይመስላል፡፡ Goota koo በሚለው ሙዚቃው ውስጥ ቄሮን አወድሷል፡፡ የተለያዩ አካባቢዎችን ስም እየጠራ ‹‹ያ ጎተኮ›› (ያ ጀግናዬ) እያለ ያሞግሳል፡፡ 

Galatoomaa ደግሞ በትግል ውስጥ የተሰውትን ያመሰግናል፤ ይዘክራል፡፡ ርዕሱ እንደሚጠቁመው ‹‹እናመሰግናለን›› ይላቸዋል፡፡

Siniin nuuf milkaa’e tole qabsoon Keenya

Sintu lubbuun darbeef alaa galuun Keenya

(በናንተ ነው የሰመረው - ትግሉ የተቃናልን

ተሰውታችሁ ነው - መጥተን መግባታችን)

ብሎ በትግል ውስጥ መስዋዕትነት የከፈሉትን ያመሰግናል፡፡ ዝቅ ብሎም

Kufee hinkufu kan dhugaaf dhabbatu

Haaqasaf falmatu

Galatooma

(ወድቆ አይወድቅም ለእውነት የቆመ

ለሃቁ የሚታገል

እናመሰግናለን (ተመስገኑ) )

 ይላቸዋል፡፡ ታጋዮች ብትወድቁም አልወደቃችሁም ለሃቅ ነውና የቆማችሁት የሚል ይዘት ያለው ስንኝ ነው፡፡

 

በ Xiqqaat guuddaa Caale (ትንሹ ትልቁን በለጠ) በሚለው ሙዚቃው ውስጥ ደግሞ ሐጫሉ ትካዜውን ብስጭቱን ያጋራናል፡፡ ያስተከዘውንም በስንኙ እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፡

Qaaqee ciinaachi koo yemuu nafa gahu anarrafu see’a

Narrafes hinrrafne hinrrafne jechuufis cisakooran jirra

(ጎኔ ሲያርፍ የተኛሁ ብመስልም

ተኝቻለሁ እንዳልል አልተኛሁ ፤ አልተኛሁ እንዳልል መኝታ ላይ ነኝ)

ካለ በኃላ ምክንያቱን ሲገልፅ

Gaaffii deebii dhabdetu na keessaa marmartii

(መልስ ያጣ ጥያቄ ውስጤ ይመላለሳል)፡፡

“ መልስ በሌለው ጥያቄ እረፍት አጥቻለሁ” የሚለው ከያኒው ‹‹ትንሹ ትልቁን በለጠ ፤ ትልቁ አነሰ ለዚያ ነው ትካዜዬ›› ይለናል፡፡ ‹‹ማነው ከማን የሚያንስ? ያነው የሚያበሳጨኝ “ ይለናል - በሶውል ሙዚቃው፡፡

ሌላኛው ሃጫሉ የኔ በሚለው ማህበረሰብ ላይ በደል እየደረሰ ነው ብሎ በማመኑ ትግሉን መቀጠሉን የአልበሙ መጠሪያ በሆነው ‹‹ማል መሊሳ›› ይናገራል፡፡ 

ሙዚቃው ሲጀምር:-

Haadha biyyaa (የሃገር እናት)

Abbaa biyyaa (የሀገር አባት)

Barataakoo (ተማሪዋ)

Qarattukoo (ተማሪው)

Qotee bulaa (አርሶ አደሩ)

በሚል መግቢያ የገባው ሙዚቃው በውስጡ ‹‹እስካሁን እየሞትን ነውና ምን ይሻላል?›› የሚል መጠይቅ ተሸክሟል፡፡

Hayyuuf goota meeqa arjoofne kunoo har’a geenyee

Anooleef calanqoo irrataran bishoftutti raajii taane

ስንት ሊቅ ጀግና ሰውተን ዛሬ ብንደርስም ከአኖሌና ጨለንቆ ወዲያም “ቢሾፍቱ ላይ ሞትን” እያለ በ2009 ቢሾፍቱ ላይ ይከበር በነበረው የኢሬቻ በዓል ላይ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎችና በክብረ በኣሉ ታዳሚዎች መካከል በተነሳው ግጭት ምክንያት የሞቱትን ዜጎች አስታውሷል፡፡ በዚህ ዘፈን ላይ ሙዚቀኛው የመቶ አመቱን የሕዝብ ሞት እያስታወሰ ዛሬም ሰው እየሞተ መሆኑን ያነሳና ‹‹መፍትሔው ታዲያ ምንድነው?›› ሲል ያጠይቃል፡፡

Kaara bayyee qabna yoom nu dhibe karan irra demnu

Silaa hinuma deemna hinuma deemna maalif galma hingeenyu?

(መንገድ ብዙ አለን - አልቸገረን መሄጃው

ብንሄድ ብንሄድ - ለምን ይሆን እስካሁን - ከግብ የማንደርሰው?)

መሄጃ አልቸገረንም ይላል ሐጫሉ፡፡ በርግጥም መጓዝም አላቆምንም ይኸው እንሄዳለን - ለምን ይሆን የማንደርሰው?

 

አስተያየት