ሐምሌ 6 ፣ 2010

ዘመን ተሻጋሪ ዘፈኖቻችን በተራ ቪዲዮ?

ኑሮሙዚቃየጥበብ ዐውድ

«ጀንበር ሳለች እሩጥ እናት ሳለች አጊጥ»ጋሽ ጥላሁን ገሠሠን እምባ ቦይ ሆኖ ጉንጭ ሲሰነጥቀው ከሚያሳየው የአገር ዜማ ባሻገር “ኢትዮጵያ”ን እናስባለን፤…

«ጀንበር ሳለች እሩጥ እናት ሳለች አጊጥ»ጋሽ ጥላሁን ገሠሠን እምባ ቦይ ሆኖ ጉንጭ ሲሰነጥቀው ከሚያሳየው የአገር ዜማ ባሻገር “ኢትዮጵያ”ን እናስባለን፤ ፀጋዬ እሸቱን አንስተን በሀልዮ ካልሆነ በቀር በነቢብ/በቃል ለመግለፅ ስለሚከብደን የአገር ምልክት የዘፈነውን “ሰንደቃችን ኑሪ”ን እንጠቅሳለን፤ ንዋይ ደበበ ውልብ ሲልብን ሰምና ወርቅ ስለሆነችው ውድ አገር የቀመረውን “የዜማ የቅኔ”ን ውብ ገለፃ እናስታውሳለን። የዘመን አቻቸው የሆነውን ድምጻዊ ፀሐዬ ዮሐንስን ካነሳን ደግሞ ያለ ቅፅበት ማመንታት ከልብ ከአዕምሮአችን ፈልቆ ከፊታችን ድቅን የሚለው ሌላው የአገር ዜማ “ማን እንደ እናት” ነው። የእነዚህን ዘፈኖች ጉልበትና ሃያልነት ለመግለፅ የረቂቅ ዜማ ሀልዮት አያሻም ወይ ደግሞ ስለ ግጥም የሰላ ሀያሲ መስካሪ መሆንም አያሻም፣ ዘመንን ተሸክሞ የሚያሻግረው የትውልድ ልቦና ከመለኪያዎች ኹሉ የሚበልጥ ነውና። በየትውልዱ የሚነሳ የፖለቲካ የማንነትና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች የአገር ትርጉምን ሊያምታቱ በሚሞክሩበት የተገላቢጦሽ ጊዜ በምስል ያልታገዙት እነዚህ ዜማዎች ከአልፎ ሂያጁ ትውልድ ልብ ጋር ያለከላካይ ተንሰላስለው የብሔራዊ መዝሙር ያህል ተቆራኝተው ቆይተዋል።የኢትዮጵያ ሙዚቃ ፈርጦች ብዬ ከምጠራችው ውድ የኢትዮጵያ ልጆች መካከል ግንባር ቀደሙ ፀሐዬ ዮሐንስ ነው። ፀሐዬ በአስራ ዘጠኝ ሰባዎቹና ሰማኒያዎቹ መጀመሪያ ገነው ከወጡት ከእነ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ነዋይ ደበበና ፀሃዬ እሸቱ ጋር ያንጸባረቀ ዜመኛ፣ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ኮከብ ነው።የሙዚቃው ለዛና ተወዳጅ ግጥሞቹ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ በክብር አስቀምጠውታል። ፀሐዬ ሀገር ወዳድና ለስራው ክብር ያለው ሙዚቀኛ እንደሆነ የሚጠራጠር ያለ አይመስለኝም። ልጅነታችንን ካፈኩልንና አብረን እያንጎራጎርን እንባ እንባ እያለን በስሜት ያበድነበትና ሀገርና እናትን አዛምደን አንድነታቸውንና ትክ ለትክ መሆናቸውን ያወቅንበት ‘ማን እንደናት’ የተሰኘው ሙዚቃው የምንጊዜም የኢትዮጵያ ምርጥ ዜማ ነው።እናም ሰሞኑን ሀገራችን ካለችበት አስገራሚና ለማመን የሚከብድ የለውጥ ግስጋሴ ጋር ተያይዞ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት ይሄንን ዜማ ፀሃዬ እንደገና በማቀንቀን የሙዚቃ ቪዲዮ ለመስራት ሞክሯል። ይህንንም ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ  የዚህ ሙዚቃ ቪዲዮ አጠቃላይ ይዘትና ሙዚቃውን ለመወከል የተሄደበት መንገድ ግዴለሽነትና ዜማው የተሸከማቸውን ጉልበታም ሃሳቦች ወደ ምስል የመቀየር ድካም ነው። ዳግም የተሰራውን የሙዚቃ ቅንብር በተመለከተ የሙዚቃ ባለሙያዎች ሀሳብ እንዲሰጡበት እተወዋለኹ፡፡«ይራበኝም ይጥማኝ ያንድደኝ ያብስለኝ ጎኔን ይቆርቁረኝ በናት ከመጡብኝ፤የሱዋን ክፉ ለኔ በአይኔ ከሚያሳየኝ እኔን ያስቀድመኝ ሞቼ አፈር ያድርገኝ»እንደዚህ አይነት ስሜትን ገዝተው ቀልብን ሊያስቱ የሚችሉ ስንኞችን የያዘ ጠንካራና ጊዜ የማይሸረው ዜማ ነው። ሀገርና እናት እናትና ሀገር ለኢትዮጵያውያን ተተካኪ ሀሳቦች መሆናቸውን ማስረዳት ቅሽምና እንደሚሆን አልጠራጠርም፤ ሙዚቃው እናትን በሀገር ተክቶ ሀገርን በእናት ሰይሞ ቀልባችንን ይይዛል።የማንኛውም የሙዚቃ ቪዲዮ ዋነኛ አላማ የዘፈኑን ሀሳብና ይዘት ወደ ምስል በመቀየር ለታዳሚው የበለጠ በስሜት እንዲቀርብና የተለየ አተያይ ካለው ሃሳቡን ዘርዘር አድርጎ ማቅረብ ነው። አንዳንድ የሙዚቃ ቪዲዮዎች ዘፋኝን ለማስተዋወቅ ይሰራሉ፤ እንደነዚህ አይነቶቹ ቪዲዮዎች አብዛኛውን የአየር ጊዜያቸውን ዘፋኙ ላይ የሚያጠፉ ሲሆኑ ዋና አላማቸው አዲስ የሚመጣ ዘፋኝን ከአልበሙ በፊት ቀድሞ ማስተዋወቅ ነው። ሌላኛው አይነት ደግሞ የዘፈኑን ግጥም ታዳሚው ወይም ተደራሹ ጋር ለማድረስ የሚሰራ ሲሆን የጥበባዊነት ይዘቱ በጣም ዝቅ ያለ ሆኖ ግጥሙን ቃል በቃል ወደ ምስል በመለወጥ ግጥሙ ሊያስተላልፈው የፈለገውን ሃሳብ በድራማ እያዋዛ ሃሳቡን ታዳሚው ጋር ለማድረስ የሚጥር ነው። ሦስተኛውና በጥበባዊ ይዘቱ ተመራጭ የሆነው የሙዚቃ ቪዲዮ አይነት በምስል ትንተናና አቀራረብ ላቅ ያለ ሲሆን ዘፈኑን ተመልካች ካላሰበው ወይም ቀድሞ ካልተረዳው አቅጣጫ በማሳየት፣ ጥልቅ የሆነ ይዘት ያለው ሲሆን ታሪክን የሚናገርበት መንገድ በጣም የበሰለና ተደጋግሞ የሚታይ ቪዲዮን የመፍጠር አቅም ያለው ነው።የፀሐዬ ዮሐንስ ‘ማን እንደናት’ ሙዚቃ አዲስ ቪዲዮ ሦስተኛውን የሙዚቃ ቪዲዮ የሚሰራበትን ዓላማ እንደያዘ መገመት ይቻላል።ይህ አሁን በማኀበራዊ ሚዲያ ተለቆ ያየሁት ቪዲዮ የሙዚቃውን ሐሳብ በተገቢ ያስቀመጠ ወይም የተረከ ሳይሆን ጥበባዊ ይዘቱ በጣም የወረደና እያዩት እንኩዋን የሚሰለች ተራ የሆነ አቀራረብ የታየበት ነው። አንድ የቪዲዮ ዝግጅት ወሳኝና የግጥሙን ወይም የሙዚቃውን ሀሳብ ማድረሻ ቆንጆ አተራረክ ይፈልጋል። የፕሮዳክሽን ጥራትን ቀጥሎ የሚመጣ ጉዳይ ሲሆን ግጥምን በምስል መግለጽ የመጨረሻ ግቡ ለሆነ የጥበብ ስራ ደካማ ምስልና ገላጭነት የሌለው ተራ ቪዲዮ ጠንካራውን ሙዚቃ ይዞት ገደል እንደሚገባ ጥርጥር የለውም።«ጀምበር ካለች እሩጥ እናት ሳለች አጊጥ፥ በናት አትበለጥ በሀገርህ ተደሰት፤ያለ እናት የበሉት ያላጋር የጠጡት፥ አይሆንም ሰውነት ጠብ አይልም ካንጀት»እነዚህን የመሰሉ ስንኞችን ሜዳ ላይ የሙዚቃ ባንድ ደርድሮ በመዝፈን ብቻ ለመግለፅ መሞከር በጣም ደካማና ለጥበቡ ክብር አለመስጠትን ያሳያል። እንደዚህ አይነት የሀገር ሀብት የሆኑ ትላልቅ ዘፈኖችን ወደ ቪዲዮ ለመቀየር ሲታሰብ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ካልሆነ ባይነኩና ቪዲዮ ባይሰራላቸው የተሻለ ነው።ሙዚቃውን ስታከብረው ሀገርህን ስታከብርና ስትወድ እንደዚህ አይነት የሀገር ስራዎች እንደ ብሔራዊ መዝሙር የሚደጋገሙ ግጥሞችን እንደተራ ዘፈን አንስተህ ሰው ሰብስበህና ኪቦርድና ጊታር አስጨብጠህ ለመስራት አትሞክርም። እዚህ የፀሐዬ ቪዲዮ ውስጥ አንዲት ባንዲራ ጥለት ያለው ቀሚስ ያደረጉ እናት ሜዳ መሀል ተቀምጠው አልፎ አልፎም እየተወዛወዙ ይታያል። ይሄ በጣም የተለመደና ቀጥተኛ የሆነ ትርጉዋሜ ያለው የሚመስል በደካማ ምስል የታጀበ ኩነት ለዚህ ሙዚቃ በፍፁም የሚመጥን አይደለም።አሁን አሁን በአለም ዐቀፍ ደረጃም የምስል ጥበብ ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል፣ በጣም ውድና ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ካሜራዎች ኢንደስትሪውን ከመቀላቀላችው አልፎ እኛም ሀገር ለስራ እየዋሉ ይገኛሉ። ከዚህ በመነሳት «ትዝ ትዝ አለኝ እምባዋን አፍስሳ የወላድ መካን ነኝ ብላ ስትጣራ» የሚል ግጥምን በምስል ለመወከል ወገብን መወጠር ያለህን ጊዜ እና ዕውቀት መስዋዕት ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ስራው ዘመን ተሻጋሪና ትውልድ ለምስክርነት ሲፈልገው እንደ መዛግብት(archive) ሆኖ ሊያገለግል የሚችል መሆን ይገባዋል፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ የይድረስ የይድረስ ይህንን አደረኩኝ ለማለት መስራት ተገቢ አይደለም። የእውነት ሀገርህን ስትወድ የሚገባትን ትሰጣታለህ፣ ሀገርህን መሸከም የሚችል ሀሳብ ለማፍለቅ ትታትራለህ፣ ትቆዝማለህ፣ ታስባለህ፣ ገና ለገና እድሉን አገኘሁ ብለህ ዘው ብለህ አትገባም፤ ሰከን ብለህ ታስባለህ፣ ስራው ላይ ስምህ ታትሞ ይኖራል ልጆችህ እና የልጅ ልጆችህ ያዩታል ይነጋገሩበታል።«ያለ እናት የበሉት ያላጋር የጠጡት አይሆንም ሰውነት ጠብ አይልም ካንጀት» ለሚል ደማም ስንኝ አንጀት ላይ ጠብ የሚል ቪዲዮ መስራት ያልቻለ ባለሙያ ሀገርንስ መውደዱ በምን ይገለጻል? ሀገርን በሚገባት መጠን ማገልገል ያልተቻለበት ባለሙያነት ለራሱ አለ ብለን መናገር እንችል ይሆን?ሃሳቤን ሳጠቃልል ድምጻዊው ፀሐዬ ዮሐንስ የሙዚቃ ቪዲዮ እውቀት ላይኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን ጥሩ የሙዚቃ ቪዲዮ አያውቅም ብየ አላስብም:: ስለዚህ ለሀዝብ ከመዋሉ በፊት ተመልክቶ ይህ ስራ ዐቢይ የሙዚቃውን መልዕክት አይወክልም ማለት ይገባው ነበር፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም በስማቸው ህዝብ ዘንድ የሚደርስን ስራ የሚገመግሙ አድማጭ ተመልካችን የሚያከብሩ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በሀገራችን በመኖራቸው ይህንን አለማድረግ ለማስተባበል የማይመች ነው፡፡ ይሄንን ቪዲዮ ፕሮዳክሽንም የሰራ ድርጅት ሀገር መውደድ ለሀገር ውለታ መዋል ምን ማለት እንደሆነ ማወቁን እጠራጠራለኹ፡፡ ልጅነታችንን መዝሙራችንን እንደነጠቀንና በራሱ ተራና ያልተብላላ ምናብ ውስጥ ሊከተን መሞከሩ ደስ የማይል ድርጊት ነው።ይህ የሙዚቃ ቪዲዮ እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡ በዚህ ስራ የተሳተፉ ሰዎችም ለምን እንደዚህ እንደሆነ አንድ ሺህ ሰበቦችን ሊደረድሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህን ምክንያቶች መስማት ብዙም የሚያጓጓ አይደለም፡፡ ነገር ግን የመከተል አባዜ በክፉ የሚያጠቃው የኪነጥበብ ዘርፋችን ከዚህ ጎድሎ ከቀረበው ቪዲዮ ሊወስደው የሚገባው ትልቅ ቁም ነገር አለ። አንደኛ የማፍረስ ባህል ነው። ሙዚቃው በራሱ ሙሉ ሆኖ ሳለ በየሰው ልብ ያለውን እሳቤ መሻገር ወይም መስተካከል ሲጎድለውና ወርዶ ሲተረጎምለት ሰጥቶት የነበረውን ዋጋ ይቀንሰዋል። ሁለተኛው መገደብ ነው። ሙዚቃው ትውልድን እንዳይሻገር እንቅፋት የተጋረጠበት ይመስላል፡፡ የወቅቱን የፖለቲካ ትኩሳት ለመከተል ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ለመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ያነሱትን ንግግር እንደምሳሌ እንድጠቅስ ይፈቀድልኝ። ሰራዊቱ ሃይለማርያም ሄዶ አብይ ሲመጣ ካልተቀበለ ወይም አብይ ሄዶ ሌላ ሲመጣ መቀበል ካልቻለ “የአገር” ሰራዊት አይደለም እንዳሉት በተመሳሳይ እንዲህ ላለው ዜማ የሚሰራው ቪዲዮ ሁሉንም የአገር ሰው ከትውልድ ትውልድ ሲመለከተው እንዲነዝረው ተደርጎ ካልተሰራ በዘፈኑ ላይ እድሜ ይፍታ እስር እንደተፈረደበት ይቆጠራል።

አስተያየት