ሐምሌ 3 ፣ 2010

ከ65 ዓመታት በኋላ ታሪክ ራሱን ደገመ? ዶ/ር ዐቢይ በአየር ተሳፍረው አሥመራ፤ ቀኃሥ መረብን ተሻግረው ኤርትራ!

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

ዛሬ ዛሬ በየሰዓቱ የምናየውና የምንኖረው ለውጥ ነገ ከነገ ወዲያ ውጤቱና አቅጣጫው ምንም ይሁን ምን በተለይ ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. የሆነው ነገር…

ከ65 ዓመታት በኋላ ታሪክ ራሱን  ደገመ?  ዶ/ር ዐቢይ በአየር ተሳፍረው አሥመራ፤ ቀኃሥ መረብን ተሻግረው ኤርትራ!
ዛሬ ዛሬ በየሰዓቱ የምናየውና የምንኖረው ለውጥ ነገ ከነገ ወዲያ ውጤቱና አቅጣጫው ምንም ይሁን ምን በተለይ ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. የሆነው ነገር በመላው የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሥፍራ እንደሚይዝ አያጠያይቅም፡፡ የአሥመራና የአካባቢው የኤርትራ ሕዝብ ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቀባባል ያደረገው በቃላት ሊገለጽ በማይችል የደስታ፤ የፍቅርና የተስፋ ስሜት ተውጦ እንደነበር በኤርትራ ቴሌቪዥን ተመልክተናል፡፡ በዓይናችን እንዳየነው፤ በጆሮአችን እንደሰማነው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተደረገው አስደናቂ አቀባባል ኤርትራውያንን የጎረቤት አገር ሕዝብ ከማለት ይልቅ ቤተሰብ ማለት የሚያስመርጥ  ነበር፡፡በአሥመራ ጎዳናዎች የሰማነው “ዐቢይ ዐቢይ” የሚል የአድናቆት ጥሪ አዲስ አበባ የተጀመረው የለውጥ ሀሳብ ድንበር እንደተሻገረ አመላካች ነበር፡፡ በራት ግብዣው ላይ አዲሱ የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ መሪ ዐቢይ አሕመድ በትግርኛና በአማርኛ ያደረጓቸው ንግግሮች፤ በምላሹም በቀጣናው ውስብስብ ታሪክ ውስጥ በፖለቲካዊና በወታደራዊ ልምድ አንጻር ለረዥም ዓመታት  የዘለቁት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የተናገሩት ነገር አስገራሚ ነበር፡፡ በተለይ ‘ወዲ አፎም’ በንግግራቸው የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር የወሰዱት እርምጃ ከባድ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ይህን ያሉት የቀጣናውን ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሁኔታ ለዓመታት ከማወቃቸው የተነሳ ነው፡፡  እርምጃው ከባድም ሆነ ቀላል፤ ለዐቢይ በአሥመራ የተደረገው አቀባበል በዓይነቱ ልዩ ነበር፡፡ ሙዚቃውና ዳንሱ፤ ከምንም በላይ ደግሞ በሳቅ የታጀበውና ቀን ከአውሮፕላን ጣቢያ ማታ እስከ እራት ግብዣ የቀጠለው የመሪዎቹ ልፊያ አስደማሚ ነበር፡፡  ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በመራራ ሽምቅ ውጊያና በቀውስ በተሞላ ቀጠና ውስጥ ሕይወታቸውን የገፉት “ወዲ አፎም” ራሳቸው ሊቆጣጠሩት ባልቻሉት ሳቅና መደመም ውስጥ ነበሩ፡፡ የሕዝቡም የተስፋ ሥሜት በግልጽ ይነበብ ነበር፡፡ኤርትራውያን ይህን የመሰለ አቀባበልና መስተንግዶ ለኢትዮጵያ መሪ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው አልነበረም፡፡ ከመስከረም 1945 ዓ.ም. ጀምሮ ለበርካታ ቀናት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ከመረብ ወንዝ አንስቶ እስከ አሥመራ ድረስ እንዲሁ በእልልታና በጭፈራ ተቀብሎ እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል፡፡ ይህ እንግዲህ የዛሬ 65 ዓመታት ገደማ መሆኑ ነው፡፡ ታዲያ ያን ጊዜ ኤርትራ ከ1882 ዓ.ም ጀምሮ በጣሊያን ቅኝ ግዛት፤ ከ1933 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ  በእንግሊዝ የሞግዚት አስተዳደር ሥር በባዕዳን ሥትደዳር ቆይታ ነበር፡፡ በወቅቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ኤርትራ ያቀኑት በትግራይ አድርገው ነበርና የሁለቱን አገራት በለያየው  መረብ ወንዝ አድርገው ድንበሩን ሲሻገሩ የተናገሩትን ንግግር ዘውዴ ረታ  በዝነኛ መጽሀፋቸው ዘግበውታል፡፡ “…ለብዙ ዓመታት የሁለቱን ወንድማማች ሕዝቦች የለየውን የመከራ ምዕራፍ በዛሬው ቀን ለዘለዓለሙ እንዘጋለን……”(የኤርትራ ጉዳይ፤ 1992፤370)ጃንሆይ እንደተናገሩት የመከራው ምዕራፍ ለዘለዓለሙ ይቅርና ለሀያ ዓመታት እንኳን መዝለቅ አልቻለም፡፡ የፌዴሬሽን ጋብቻው በሁለቱም ባለትዳሮች እንዲሁም በጎረቤቶች የተወደደ አልነበረምና ብዙም ሳይዘልቅ ፈረሰ፡፡ አሰቃቂው የምስራቅ አፍሪካ ጦርነትም ለሰላሳ ዓመታት ተካሄደ፡፡ ጦርነት ለሰሚ ተመላካች ዜና ነው፡፡ በውስጡ ላሉት ግን ገሀነም! “የርስበርሱ” ወይም “የነጻነት” ጦርነት የመቶ ሺዎችን ሕይወት ቀጠፈ፤ አካል አጎደለ፤ ኑሮ አመሳቀለ፤ አጎሳቆለ፡፡ መሆን ያልነበረበት መዓት በምስራቅ አፍሪካ ሰማይ ላይ ወረደ፡፡በ1983 ዓ.ም. ኤርትራ ነጻ አገረ-መንግስት መስርታ የሁለቱ አገራት ወንድማማች/እህትማማች ሕዝቦች ጥቂት የሰላም ፋታ ለሁለተኛ ጊዜ አግኝተው ነበር፡፡ “የሰላም እንቅልፍ አትተኙ” ተብለው የተረገሙ ይመስል እነዚህ ሕዝቦች ከጥቂት ዓመታት በኋላ በድንበር ግዛት ይገባኛል ሰበብ ሌላ ዙር ጦርነት ውስጥ ገብተው አስር ሺዎች አልቀዋል፤ አካላቸው ጎድሏል፤ እንዲሁም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ጥላቻው በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ጦር ሠራዊት በድንበር ላይ እንዲከማች ምክንያት ሆኗል፡፡ከዓመታት መራራቅና መነፋፈቅ በኋላ የታየው የአሥመራ መስተንግዶ በታሪኩ አቻ እንደሌለው ታሪካችንን እምብዛም  የማያውቁት፤ ለማወቅም ፍላጎት የሌላቸው አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች ባላዋቂ ድፍረት ቢዘግቡም ከላይ ለመጠቆም እንደሞከርነው የዛሬ 65 ዓመት እንዲሁ ጃንሆይ የኤርትራን ምድር መረብ ወንዝን ተሻግረው ከረገጡበት ከመስከረም 1945 ዓ.ም. አንሥቶ አስመራን ጨምሮ በሌሎች አውራጃዎች ባደረጉት የ25 ቀናት ጉብኝት የታየ ነበር፡፡ በርግጥ ካርል ማርክስ እንደሚለው ታሪክ ራሱን ደገመ?ታሪክ ራሱን ደገመም አልደገመም የሁለቱ ወንድማማች/እህትማማች ሕዝቦች ለሶስተኛ ጊዜ ወደ ጦርነት ድግስ እንዳይገቡ ከቀደሙት  ሁለት የመቀራረብና የሰላም ፋታዎች ትምህርት መወሰድ እንደሚኖርበት ብዙዎች ይጠቁማሉ፡፡ የስልክና የትራንስፖርት እንዲሁም የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች እንደገና መጀመራቸው የሚያስደስት ታሪካዊ ሂደቶች ቢሆኑም የሁለቱ አገራት መሪዎችና ወንድማማች/እህትማማች ሕዝቦች ቀሪ የቤት ሥራዎች አሏቸው፡፡ በሥሜት የተናደው ግንብ እና በዚያው ሥሜት የተገነባው ድልድይ፤ በሃሳብና በተቋማት መሰረት ላይ ማረፍ እንደሚጠበቅበት አሌ አይባልም፡፡ ሥሜት ጊዜያዊ ነው፤ ውሎ ሲያድር ይቀዘቅዛል፤ ይረሳል፤ እንደጤዛም ይረግፋል፤ ይተናልም፡፡ ሀሳብና ተቋማት ግን ይዘልቃሉ፡፡ ያንን ሁሉ መከራ ያዩት ሁለቱ ሕዝቦች ዘላቂ ፍቅርና ሰላም ያገኙ ይሆን?

አስተያየት