ሰኔ 25 ፣ 2013

“ስለ ቲያትር” በቲያትር ባለሙያዎች

City: Addis Ababaወቅታዊ ጉዳዮችየጥበብ ዐውድ

“ስለ ቲያትር” በሚል እንቅስቃሴ በትላንትናው ዕለት “ቲያትራችን ሕግጋት፣ ደንቦች እና መመሪያዎች” በሚል ርዕስ ውይይት ተካሂዷል፡፡

Avatar: Dawit Araya
ዳዊት አርአያ

Dawit has been the Amharic assignment editor at Addis Zeybe. He has worked in printing, electronics, and online news platforms such as Fitih, Taza, and Ye Erik Ma'ed for the past five years.

“ስለ ቲያትር” በቲያትር ባለሙያዎች

በትላንትናው ዕለት “ቲያትራችን ሕግጋት፣ ደንቦች እና መመሪያዎች” በሚል ርዕስ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር በተካሄደው የውይይት መርሃ-ግብር ላይ የቲያትር ባለሙያዎች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡ ማለዳ 3 ሰዓት ጀምሮ በግማሽ ቀን የተጠናቀቀው ውይይት ሲካሄድ ይህ ለ5ኛ ጊዜ ነው፡፡ የአሁኑን ጨምሮ ከዚህ በቀደሙት 4 ፕሮግራሞች ላይ ቲያትር እና ቲያትር ነክ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተው ባለሙያዎች ሐሳቦቻቸውን ሰጥተውባቸዋል፡፡

ከጉዳዩ ጠንሳሾች መካከል አንዷ የሆነችው ደራሲና ዳይሬክተር መአዛ “እንቅስቃሴውን የጀመሩት ጥቂት ባለሙያዎች ናቸው” ትላለች፡፡ ደራሲዋ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራት የስልክ ቆይታ እንዳብራራችው ቲያትር የተማሩ፣ ቲያትር የሚያስተምሩ፣ ቲያትር የሚሰሩ እና ‘ፕሮድዩሰሮች’ “ስለ ቲያትር” በሚል እንቅስቃሴ የጀመሩት የሙያውን መዳከም በመመልከት ነው፡፡

ደራሲና ዳይሬክተር መአዛ “‘ስለ ቲያትር’ የተሰኘው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ቲያትር ያሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ እንዲችል የተነሳሳ የወዳጆች ወግ ነበር” ብላናለች፡፡ መአዛ ማብራሪያዋን ስትቀጥል፡

“ስለ ቲያትር ሲነሳ ወይም በሌሎች ሐገራት ያለውን የቲያትር እንቅስቃሴ ስንመለከት፣ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ፌስቲቫሎች ላይ ስንጋበዝ ይቆጨን ነበር፡፡ “ይህ ለምን አልሆነም?” “ያ ለምን ሆነ?” እንል ነበር፡፡ በዚህ ንቅናቄ አማካኝነት ለመፍጠር የቻልነው አዲስ ነገር ባለሙያው በጋራ እንዲቆጭ ብቻ ሳይሆን መፍትሔ የሚለውንም እንዲያዋጣ መጋበዝ ነው፡፡ ሁሉም ባለሙያ በጋራ ቁጭቱን፣ መፍትሔ እና ችግር ናቸው የሚላቸውን ጉዳዮች እያነሳ ሲመክር አሁን 5ኛ ላይ ደርሷል”

ቲያትርን እንደማሰቢያ መንገድ የሚጠቀሙ፣ ትምህርታቸው፣ መተዳደሪያቸው፣ ፍቅራቸውና፣ ቁጭታቸው ቲያትር የሆነ የሙያው ባለቤቶች የቀሰቀሱት ስብስብ ከፍ ወዳለ ውይይት እንዲያድግ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በአግባቡ ተጠቅሟል፡፡ ቲያትርን ነገሬ ብለው የሚወያዩና ሐሳብ የሚያዋጡ፣ ነባር እና አዳዲስ ትዝታዎችን የሚያነሱ፣ በሙያው ውስጥ ያሉ እና የሌሉ ከ11 ሺህ በላይ ተከታዮችን በፌስቡክ እና በቴሌግራም ማፍራት ችሏል፡፡

የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመግታት የተጣሉ ገደቦች ሲነሱና ሁሉም ነገር ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ የገባ ሲመስል የቲያትር ቤቶች ጉዳይ መረሳቱ የተነሳው ሐሳብ ብዙዎች እንዲጋሩት ያደረገ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይስማማሉ፡፡ እንደ ታክሲ እና አውቶብስ ያሉ በርካታ ሰዎች የሚንቀሳቀሱባቸው መገልገያዎች ከኮቪድ በፊት ወደነበረ እንቅስቃሴያቸው ሲመለሱ፣ ስብሰባዎች እና ሰልፎች ሲካሄዱ ቲያትር ቤት ግን ዛሬም በገደብ ውስጥ ነው፡፡ ቲያትር እንጀራቸው የሆነ ሰዎች መኖራቸውን እስከመርሳት የደረሰ የሚመስለውን ውሳኔ ለመታገል አንድ መሆን እንዳስፈለጋቸውም በማኅበራዊ ገጾቻቸው ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቲያትር ባለሙያዎች ማኅበር አባላት የሆኑት የሐሳቡ ጠንሳሾች ሞያቸውን የማዳን ሐሳባቸው ተቋማዊ ቅርጽ እንዲይዝ ጉዳዩን ወደ ማኅበራቸው ወስደውታል፡፡ የያዝነው ዓመት አውሮፓዊ ቅርፅ ያለው የኢትዮጵያ ቲያትር 100ኛ ዓመቱን የሚያከብርበት መሆኑ የጀመሩትን መነሳሳት እንዲገፉበት ያደረጋቸው ባለሙያዎቹ ትላንትን ጨምሮ ባካሄዷቸው ውይይቶች ዶክመንት ለማዘጋጀት የሚሆን ግብአት ሰብስበዋል፡፡

የነበሩት ውይይቶች “የቲያትር ወቅታዊ ሁኔታ”፣ “ቲያትር እና ቤተ ተውኔቶች”፣ “የግል ቲያትር አምራቾች”፣ “የቲያትር ትምህርት”፣ “የትያትር ሕጎችና ፖሊሲዎች” በሚል ርዕስ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በውይይቶቹ ላይ ርዕሰ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች እና ሌሎችም ተጋባዦች እየተገኙ ሐሳባቸውን አዋጥተዋል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን ብርሃኑ ከውይይቱ አደራጆች መካከል አንዱ ነው፡፡ “ለ5 ሳምንታት በልዩ ልዩ ቲያትር ነክ ጉዳዮች ላይ የተካሄደው ውይይት መጨረሻው?” ምንድነው ለሚለው ጥያቄ “አንድ ሰፋ ያለ ዶክመንት እናዘጋጃለን” ሲል መልሷል “ሁሉም ሰው ተመሳሳይ እውቀት እንዲኖረው የሚያስችል ዶክመንት ይኖረናል፡፡ ውይይቶቹ አሁን ያለው የቲያትር ነባራዊ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ያሳያሉ፡፡ ስለቲያትር፣ ስለቲያትር ባለሙያዎች፣ ስለቲያትር ትምህርት፣ ስለቲያትር ቤቶች፣ ስለ ቲያትር ነክ ሕግና መመሪያዎች ተወያይተናል፡፡ ችግሮችም መፍትሔዎችም ተቀምጠዋል፡፡ ዶክመንቱ ሁላችንም አንድ ዓይነት እውቀት እንዲኖረን ያስችላል” ሲል መልሷል፡፡

“ቀጣይ 6ኛ ውይይት ይኖረናል” ያለችን ደራሲና ዳይሬክተር መአዛ ደግሞ በቀጣይ የሚካሄደው 6ኛው መድረክ እንደ ከዚህ በፊቶቹ አዳዲስ ርዕሶች ተመርጠው ሐሳብ የሚንሸራሸርበት እንደማይሆን አንስታለች፡፡ “የቀደሙት 5 ውይይቶች ላይ የተነሱት ሐሳቦች ወደ ጽሑፍ ተቀይረዋል፡፡ ለዋናው ዶክመንት ግብአት መሆን በሚችሉበት መንገድ ተሰናድተዋል፡፡ የዚያ ዝግጅት ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ለ6ኛ ውይይት እንቀመጣለን፡፡ በመድረኩ ከዚህ በፊት ሐሳብ የሰጡት ባለሙያዎች የጋራ ሰነዳቸውን ይገመግማሉ፡፡ ቀረው የሚሉትን ይጨምሩበታል” ብላናለች፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን ብርሃኑም “ሰነዱ ባህል እና ኪነ-ጥበብ እንዲሁም ቲያትር የሚመለከታቸው ተቋማት እንዲደርሳቸው ይደረጋል፡፡ ተቋማቱ ትምህርት ቤቶች ቢሆኑ በቲያትር ትምህርት አሰጣጣቸው ላይ ያለውን ክፍተት ሰነዱ አካቷል፡፡ ቲያትር ቤቶች፣ የግል ቲያትር አምራቾች ቢሆኑም ችግራቸው ከነ መፍትሔው ሰነዱ ላይ አለላቸው” ብለውናል፡፡

ከዚህ ሁሉ በኋላስ ለሚለው የአዲስ ዘይቤ ጥያቄ ደራሲና ዳይሬክተር መአዛ “ለችግሮቹ ቅደም ተከተል እናወጣለን፡፡ አንገብጋቢ የምንለውን ለይተን ያንን ለመቅረፍ ደግሞ እንጥራለን፡፡ ቲያትር መኖሪያችን እስከሆነ ድረስ በሰነድ ዝግጅት ብቻ አንቆምም” የሚል ምላሽ ሰጥታናለች፡፡

የሰነዱ ዝግጅት ከተጠናቀቀ በኋላ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ ቲያትር ባለሙያዎች ማኅበር እንደሚሆም ሰምተናል፡፡

አስተያየት