ሰኔ 24 ፣ 2013

ውዝግብ የማያጣው የሀገር ውስጥ ኤጀንሲዎች አሰራር

City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮች

ላየን ሴኪዩሪቲ የተባለ ሰራተኞቸን የሚያስቅጥር ኤጀንሲ ላይ ተቀጣሪዎች ቅሬታ አቅርበዋል።

Avatar: Haymanot Girmay
Haymanot Girmay

ውዝግብ የማያጣው የሀገር ውስጥ ኤጀንሲዎች አሰራር

ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገችዉ ባለታሪካችን ሰራ ለመቀጠር እየፈለገች ባለበት ወቅት ከጓደኛዋ ባገኘችው ጥቆማ መሰረት ላየን ሴኪዩሪቲ ወደተባለ ሰራተኞቸን የሚያስቅጥር ኤጀንሲ ትሄዳለች። "የ10ኛ ክፍል ውጤት እና ዋስ ካመጣሽ ስራ መጀመር ትችያለሽ" በሚል ለቀጣዩ ቀን ቀጠሮ ይሰጧታል። በቀጠሮዋ ቀን የተጠየቀችውን አሟልታ ቡና ባንክ አየርጤና ቅርንጫፍ በተላላኪነት እንደምትሰራ ተነግሯት ወደ ተጠቀሰው ቦታ አመራች። 

“በቦታው ስደርስ ግን ስራው ገለፃ ሲደረግልኝ እንደተነገረኝ ተላላኪነት ሳይሆን ፅዳት መሆኑን አወቅኩ" የምትለው ባለታሪካችን 'ስራ መፈለጊያ ይሆናል' በሚል በስራው ለመቀጠል መወሰኗን ትናገራለች። ከስራው በፍቃደኝነት ለመልቀቅም ሆነ አሰሪው ለማባረር ሲፈልግ የስራ መፈለጊያ የ1 ወር ጊዜ እንደማይሰጥም ነው የገለጸችው።

በተመሳሳይ የፅዳት ስራ ስትሰራ የነበረችው ባልደረባዋ ምንም እንኳን ወደ ኤጀንሲው ስታመራ የስራውን አይነት ያወቀች ቢሆንም ለተወሰኑ ወራት ብቻ በስራው መቆየቷን ትናገራለች። ስራውን ያለመቀጠሏ አንዱ ምክንያት የደሞዝ አከፋፈል ሂደቱ ላይ ቅሬታ ስላደረባት መሆኑን ትገልፃለች። 

"የገንዘብ መጠኑ ወር ከወር የመቶዎች ብር ልዩነት ነበረው" ያለች ሲሆን ይህም ከ1,600 እስከ 1,800 ብር ውስጥ ነበር። ለቅጥር የወጣው የክፍያ መጠን 2ሺ እንደነበር የምታስታውስ ሲሆን ከነበረው ልዩነት በተጨማሪ ከድርጅቱ የደሞዝ እርከን ግማሹ ብቻ ክፍያ ተፈፅሞ የተቀረው ግማሽ ለኤጀንሲው መሆኑን በዙሪያዋ ካሉ ሰዎች መስማቷን ተናግራለች።

ከ“ቤተልሄም የጽዳት አገልግሎት” ጋር ውል ካለው አንደኛው ድርጀት ውስጥ በጽዳት ስራ የሚተዳደሩ አንዲት እናት በበኩላቸው ከስራቸው ለመልቀቅ እንኳን ቢያስቡ በተቀጠሩበት ድርጅት ያለ ክፍያ ለ15 ቀናት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው ነግረውናል።  ኤጀንሲው በእነዚህ 15 ቀናት ከአሰሪው ተቋም የሚያገኘውን ክፍያ ሙሉ ለሙሉ ለራሱ ብቻ ያውለዋል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅጥር ከመፈጸሙ አስቀድሞ ''የስራ ማስታወቂያ ያለበትን ቦታ ለመጠቆም ብቻ ታይም ኤጀንሲ 600 ብር አስከፍሎኛል'' የምትለው ትእግስት የኔነው ናት። በተማረችበት የሙያ ዘርፍ አፕላይድ ኬምስትሪ ማስታወቂያ ያለበት እንዲሁም በማንኛውም የስራ ዘርፍ ስራ ይገኛል በማለታቸው መክፈሏን ትናገራለች።    

የተጋነነ የደሞዝ መጠን በመጥራት ክፍት የስራ ማስታወቂያ አለበት ወደ ተባለው ቦታ ይጠቁማሉ የምትለው ትእግስት ወደተጠቆመቻቸው ቦታዎች ስትደርስ ግን አንዳንዶቹ ማስታወቂያ የወጣበት ጊዜ ካለፈ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል፣ በቦታው ሰዎች ተቀጥረዋል የሚል ምላሽ ታገኛለች፡፡ የተነገራት የክፍያ መጠንም የተጋነነ ወይም ከእውነት የራቀ ሆኖባታል፡፡ በመጨረሻም ተስፋ በመቁረጥ ስራ ለመፈለግ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣቷ በፊት ትኖርበት ወደነበረው ደብረብርሀን ከተማ ተመልሳለች።

የሴኪዩሪቲ ላየን ኤጀንሲ የሽያጭ ባለሙያ:- ኤጀንሲው ቀጣሪ እንደመሆኑ ከተቀጣሪዎቹ ጋር የሚኖረው ስምምነት እንደአሰሪ ነው። ለተቀጣሪዎች ኤጀንሲው ይሆናል ያለውን የገንዘብ መጠን አውጥቶ ቅጥር እንደሚፈጽም እና በኤጀንሲው አማካኝነት ስራ የሚያሰራው አካል (ድርጅት) ስለሚያወጣው ገንዘብ ከኤጀንሲው ጋር የሚፈጸም ውል መሆኑን ተናግረዋል።

ኤጀንሲው ለሰራተኛው የሚያወጣው ወጪ እንዲሁም የሚከፍለው ደሞዝ በኤጀንሲው እና በአሰሪው መካከል የሚያልቅ እንጂ ከተቀጣሪው ክፍያ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ አለመኖሩን ገልጸው “ክፍያው ለስራው በቂ ነው ወይስ አይደለም?” ሚለውን ተቀጣሪዎቹ ቀድመው አስበውበት መቀጠር ይገባቸዋልም ብለዋል። 

'ከተጠቀሰው የደሞዝ መጠን በታች ክፍያ ይፈጸማል' ተብሎ ለተነሳው ቅሬታ ''ያልተጣራ ደሞዝ ከሆነ ለመንግስት ግብር ሊቆረጥ ይችላል፤ ነገር ግን ይሄን ሲቀጠሩ እናሳውቃለን፤ ከቀጣሪው ድርጀት ጋርም የተጣራ እና ያልተጣራ ክፍያ የሚባለውን በውላችን ላይ በግልጽ እናስቀምጣለን'' ብለዋል። 

ስለዚህ እንደ ባለሙያዋ ገለጻ አሰሪው ድርጀት ከሚያወጣው ገንዘብ ላይ 50 በመቶ፣ ከዛ በታች ወይም በላይ ይቆረጣል የሚለው ሀሳብ ኤጀንሲው ከሚያወጣው ወጪ አንጻር ከድርጅቱ ጋር በሚዋዋለው ውል የሚወሰን እንጂ የተቀጣሪዎችን ደሞዝ የሚነካ አሊያም የነሱን ስምምነት የሚፈልግ አይደለም።           

ከዚህ ቀደም የኤጀንሲ ስራ ላይ ተሰማርቶ ከነበረ ግለሰብ ባገኘነው መረጃ መሰረት ሰራተኞቹ ውላቸውን የሚፈጽሙት ከኤጀንሲዎች ጋር እንደመሆኑ ክፍያው የሚፈፀመው በኤጀንሲው በኩል ነው። በኤጀንሲዎች በኩል ቅጥር የሚፈፅመው ድርጅት እና አስቀጣሪው ኤጀንሲ በሚኖራቸው ውል መሰረት ተቀጣሪዎቹ የሚከፈላቸው ክፍያ እና ኤጀንሲዎቹ የሚያገኘው የገንዘብ መጠን ይወሰናል። ማለትም አንድ ድርጀት ለአንድ ተቀጣሪ ለመክፈል ካስቀመጠው የደሞዝ እርከን በተጨማሪ ለመንግስት የሚከፈል ቀረጥ፣ ለሰራተኞች የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እና ለአገልግሎት ወጪ ያደርጋል።

ኤጀንሲውም ከድርጅቱ የሚቀበለውን ገንዘብ ከሰራተኞቹ ጋር ባለው ውል መሰረት ክፍያ የሚፈጽመው እንዲሁም አንድ ቀጣሪ ሊያደግው የሚገባውን ለመንግስት የሚከፈለውን ግብር ጨምሮ ሙሉ ሂደቱ በኤጀንሲዎቹ ይሆናል።  አንድ ኤጀንሲ ከአንድ ድርጀት ጋር ለመዋዋል ለአንድ ተቀጣሪ ይሄን ያህል ገንዘብ ድርጅቱ ቢያወጣ ተብሎ ኤጀንሲው በሚያስገባው የገንዘብ መጠን ተወዳድሮ (በጨረታ) አሸናፊ የሆነው ማለትም ድርጀቱ አነስተኛ የገንዘብ መጠን ለጠየቀው ኤጀንሲ ስራውን ይሰጣል። ከዚያም ለተቀጣሪዎች የሚከፈለው መጠን እና ሌሎች ወጪዎች ታሳቢ ተደርገው ከሰራተኞቹ ጋር ውል ይፈጸማል።

በተመሳሳይ አሰሪው ድርጀት ተቀጣሪውን ከስራ ማሰናበት ቢፈልግ በአሰሪ እና ሰራተኛ አዋጅ ላይ እንደተደነገገው የስራ መፈለጊያ ጊዜ ከአሰሪው ጋር የሚፈፀም አይሆንም። ድርጅቱ ያለማስጠንቀቂያ በፈለገበት ጊዜ ቢያሰናብት ለተቀጣሪው ቀጣይ እጣፈንታ ወይም ተቀያሪ ስራ መፈለግ የሚገባው ኤጀንሲው ይሆናል።

በአዲስ አበባ ሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ የሀገር ውስጥ የቅጥር አገልግሎት ተጠሪ አቶ በላይ ተሰማ እንደሚገልጹት የደሞዝ አከፋፈል ስርአቱ የሚወሰነው በኤጀንሲው እና በቀጣሪው ስምምነት ሲሆን ኤጀንሲው የሚያገኘው ገንዘብ ከተቀጣሪው ክፍያ ላይ መሆን አይችልም። ''ከሰራተኛው ላይ 5 ሳንቲም መቀነስ የለበትም'' የሚሉት አቶ በላይ 20 በ 80 በሚባለው አሰራር በሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ በወጣ አዋጅ  መሰረት መሆኑንም ገልጸዋል። ይህም አሰሪው ለሰራተኛው ከሚያውለው ገንዘብ ላይ 20በመቶ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚከፈል እና 80በመቶ ለተቀጣሪው ክፍያ የሚውል ይሆናል። 

314 ኤጀንሲዎች ከሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ ንግድ ቢሮ እና ፌደራል ፖሊስ ፍቃድ ወስደው እንደሚገኙ ኃላፊው ገልጸው ከዚህ ውስጥ 158 ላይ ዳሰሳ የተደረገ መሆኑን እና በአሰራራቸው ችግር ሳቢያ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው እንዲሁም መሰናበት ያለባቸው ኤጀንሲዎች መኖራቸውን ይናገራሉ። እንዲሁም 78 ብቻ ፍቃዳችውን አድሰው በስራ ላይ እንደሚገኙ አክለው ያለ ፍቃድ ኤጀንሲዎች እየሰሩ ካሉ ንግድ ቢሮ የሚከታተለው ይሆናል ብለዋል።

በጥቃቅን እና አነስተኛ እንዲሁም ኅብረት ስራ አመራር በመደራጀት በአሰሪ እና ሰራተኛ ዘርፍ የተሰማሩ መኖራቸውን ጠቅሰው ልክ አለመሆኑን ገልጸዋል። ቢሮው አየርመንገድ አከባቢ 12 የሚሆኑ ኤጀንሲዎች እየሰሩ መሆኑን መረጃ ስለደረሰው ወደ መስመር ለማስገባት እየሰራ ይገኛል ብለዋል ኃላፊው። የሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ አሰራር ተላልፎ የሚገኝ አካል በአዋጅ 618 መሰረት ከ5 ዓመት ባላነሰ ከ10 ዓመት ባልበለጠ እና 100ሺ ብር መቀጮ ይቀጣል በማለት ተናግረዋል።

 ''ከሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ የብቃት ማረጋገጫ ከሌላቸው ኤጀንሲዎች ጋር ውል የሚፈጽም አሰሪ በጉዳዩ ኃላፊነት ይወስዳል'' የሚሉት ሀላፊው በስራ ሂደት ለሚያጋጥም ችግር ተቀጣሪዎች ለቢሮው ቅሬታ እንዲያቀርቡ እና መፍትሄ እንዲያገኙ ጠቁመዋል።

አስተያየት