ሰኔ 23 ፣ 2013

የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን ዳግም መመለስና ቀጣይ ዕጣ ፈንታ

City: Addis Ababaማህበራዊ ጉዳዮች

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የልጆች የቴሌቪዥን ጣቢያ በመሆን የተለያዩ አስተማሪና አዝናኝ ፕሮግራሞችን ያቀርብ የነበረው በገንዘብ ቀዉስ ምክኒያት ኝ ከአየር ወርዶ የነበረዉ የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን ዳግም ወደ ስርጭት ሊመለስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን ዳግም መመለስና ቀጣይ ዕጣ ፈንታ

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የልጆች የቴሌቪዥን ጣቢያ በመሆን የተለያዩ አስተማሪና አዝናኝ ፕሮግራሞችን ከመስከረም 20፤ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለወራት ያህል ሲያሰራጭ ቆይቶ በተፈጠረበት የገንዘብ ቀዉስ ምክንያት ከአየር ወርዶ የነበረዉ የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን ዳግም ወደ ስርጭት ሊመለስ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ጣቢያዉ በየቀኑ ለ24 ሰዓታት የሚተላለፍ የልጆች ቴሌቪዥን ጣቢያ ሆኖ ለመቀጠል አቅዶ ሲንቀሳቀስ የነበረ ቢሆንም በልጆች ፕሮግራም ላይ ማስታወቂያ እንዳይተላለፍ በሚከለክለው ሕግ ምክንያት እና ከመንግስት ተገቢውን ድጋፍ በማጣቱ የተነሳ ከአየር ለመውረድ አንደተገደደ የቴሊቭዥኑ ዋና መስራች የሆኑት የማስታወቂያ ባለሙያ እና ጋዜጠኛ ቢኒያም ከበደ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡

ጣቢያው የተነሳበት ዋና አላማ በልጆች ማንነት ውስጥ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ማተም ነዉ የሚሉት ቢኒያም ይህንን ግብ የመምታት ትግል ግን ቀላል እንዳልነበረና ከዘጠኝ ዓመት በፊት ጣቢያዉን ለማቋቋም በተነሱበት ወቅት ገና ከጅምሩ ለቴሌቪዥን ጣቢያው "የኢትዮጵያ ልጆች" የሚለውን ስያሜ ሲመርጡ ፈቀድ በሚሰጠዉ የመንግስት አካል ስያሜአችሁን ቀይሩ አንደተባሉም ይናገራሉ፡፡

አክለውም "ይህን አላማ ለማሳካት ነው የብሮድካስት ፈቃድ ሲከለክሉን እጃችንን አጣጥፈን ሳንቀመጥ ለዘጠኝ ዓመታት ሙሉ ለኢትዮጵያ ልጆች ስንቅ የሚሆን የተለያዩ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት በማህደራችን ስናጭቅ ቆይተን ነው ሲፈቀድልን አየር ላይ የዋልነው።" ብለዋል።

ስለተቋረጠበት ምክንያትም ሲያስረዱ "በዋነኛነት የገጠመን ችግር የገንዘብ ነው። በዚህም ምክንያት ከአየር ወረድን። የፕሮግራም እጥረት ሳይኖርብን ለወራት ፕሮግራማቸንን ማሰራጨት አቁመን ነበር አሁንም ዳግም ያለንን አቅም ሁሉ ተጠቅመን። ከልጆቻችን ጋር ዳግመኛ ለመገናኘት ተነስተናል ይሁን እንጂ አሁንም የተመለስነዉ የህብረተሰቡን ድጋፍ ይዘን ስለሆነ መንግስት ሊያግዘን ይገባል" ብለዋል።

የቴሌቭዥኑ ዋና ፕሮግራም አዘጋጅ የሆኑት አርቲስት ህብስት አሰፋ በበኩላቸው "ይህ ቴሌቭዥን ጣቢያ የሚሰራው የመንግስትን ስራ ጭምር ነውና በመንግስት መታገዝ ነበረበት።  የሴቶችና የሕፃናት ሚኒስቴር፤ ባሕል ሚኒስቴር እና የሠላም ሚኒስቴር በወጣቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሲሰሩ እንደዚህ አይነት ታዳጊዎች ላይ የሚሰራን ተቋም መመልከት እና ማገዝ አለበት'' ብለዋል። አያይዘውም “አሁንም ትንፋሽ ሰብስበን፣ አቅማችንን ጠንከር አድርገን ወደ አየር ስንመለስ እንደገና በገንዘብ ችግር መውረድ አንፈልግም። ማኅበረሰቡም መንግስትም ያግዘን። የምንሰራው ሀገር እስከሆነ ድረስ መንግስት እኛን የማገዝ የውዴታ ግዴታ አለበት ብለን እናምናለን። ለዚህም የሁሉም ዜጋ ድምፅ ያስፈልገናል" ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በሌላ በኩል አዲስ ዘይቤ በከተማችን ተዟዙራ ካነጋገረቻቸው ወላጆች መካከል አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ደሴት አበበ “የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን በገንዘብ  እጥረት ምክንያት መቋረጡ ያሳፍራል። ይህ ቴሌቭዥን ዳግም እንዳይቋረጥ በመንግስት አካላት እና የሀገሪቱ ባለሀብቶች ሊመለከቱት ይገባል። ሌሎቻችን ደግሞ ቢያንስ ከ10 ብር ጀምሮ እንኳን ብንደግፍ ብዙ ነው ።ሁላችንም ለተግባር እንዘጋጅ ልጆቻችን አጀንዳችን ይሁኑ” ሲሉ አስተያየታቸውን አቅርበዋል።

“ይህ ጣቢያ በልጆች ንቃት ላይ ያሳረፈው ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፤ ለትምህርታቸዉ ጭምር አጋዥ ነው የሆነው። ዳግም እንዳይቆም የሚመለከተው አካል ሁሉ ሊያስብበት ይገባል።” ያሉት ደሞ በአዲስ አበባ ከሚገኙት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በአንዱ መዋእለ ህፃናት ውስጥ መምህርት የሆኑት ፍቅርተ ታደሰ ናቸው።

ልጆች ከሚማሩባቸውና ዕውቀት ከሚገበዩባቸው የጣቢያው ዝግጅቶች መካከል ቢጢቆ፣ አለቃ ገብረሃና የተረት አባት እና የተረት ጊዜ፣ ሲሆኑ ከህፃናትም አልፎ በወላጆች ጭምር እጅግ የሚወደዱ ተናፋቂ ፕሮግራሞች ናቸው።

የጣቢያው ባለድርሻ አካላት “ለትውልድ ትልቅ መሠረት እየጣለ የሚገኘው የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥንን ሁሉም ያግዝ። አግዙን ስንል፣ ልታግዙን የምትችሉባቸውን መንገዶች በቅርብ ቀናት ውስጥ የምናሳውቃችሁ መሆኑን እየገለፅን ከጎናችን ስለሆናችሁ፤ ከጎናችን ስለምትሆኑም አስቀድመን እናመሰግናለን!” ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

አስተያየት