በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ በ23.5 ሄክታር መሬት ላይ ሊሰራ የታቀደው የከሰል ድንጋይ ማምረቻ ፋብሪካ የጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክን ይዞታ የሚያካልል በመሆኑ ለፓርኩ ህልዉና ላይ ስጋት ይሆናል በሚል በአከባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን አዲስ ዘይቤ ተረድታለች፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የተፈጥሮ ሀብት ተሟጋች በቅርቡ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የድንጋይ ከሰል ማምረቻ የሚገነባበት ቦታ በብሄራዊ ፓርኩ ክልል ዉስጥ የሚገኝ በመሆኑ ወደ ፊት በፓርኩ ብዝሀ ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ አንደሚችልና በፓርኩ ውስጥ ለሚኖሩ የዱር አንስሳት ህልዉና ትልቅ ስጋት አንደሚሆን በመግለጽ የፋብሪካዉ ግንባታ ቦታ ከፓርኩ ክልል ዉጭ መደረግ ይገባዋል ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡
ስፍራው በደን የተሽፈነ መሆኑን የሚጠቅሱት የተፈጥሮ ሀብት ተሟጋቹ ማምረቻውን ለመገንባት የሚደረግ የደን ምንጣሮ ሊኖር እንደሚችልና ይህም አካባቢዉን በማራቆት ድርቅ እንዲፈጠርና ያንን ተከትሎም በአካባቢዉ የዉኃ እጥረት አንዲኖር ሊያደርግ ይችላል በማለት ስጋታቸዉን ይገልጻሉ፡፡ በተጨማሪም ፋብሪካው ስራ በሚጀምርበት ወቅት ከማምረቻዉ የሚወጣ ፍሳሽ ወደ ጊቤ ወንዝ የሚለቀቅ ከሆነ በወንዙ ላይ ብክለት ሊያስከትል እንደሚችል አያይዘው ይጠቁማሉ።
የፋብሪካዉ ግንባታ ሀገሪቱ ከውጪ የከሰል ድንጋይ ለማስገባት የምታወጣውን የዉጭ ምንዛሬ በማስቀረትም ይሁን ለበርካታ ዜጎች በሚፈጥረዉ የስራ ዕድል ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንድሚኖረዉ የሚገልጹት እኝሁ የተፈጥሮ ሀብት ተቆርቋሪ የማምረቻ ግንባታዉ በተፈጥሮ ላይ ጉዳት የሚስከትል ከሆነ ግን ፋይዳዉን ጎዶሎ ያደርገዋል ይላሉ፡፡
ሄኖክ ስዩም 'ተጓዡ ጋዜጠኛ' በሚለዉ መጠሪያ የሚያወቀውና ወደ ጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክን በተደጋጋሚ ለስራ በተደጋጋሚ የሄደው ጋዜጠኛ በፓርኩ ውስጥ የሚሰራው ፋብሪካ ፍሳሽ በታችኛው ተፋሰስ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚለዉን ሀሳብ ይጋራል። “ሙሉ በሙሉ ወደታች ያለው አከባቢ ሊጠፋ ይችላል'' የሚለው ሄኖክ በጊቤ ላይ ከተመሰረቱት ትላልቅ ግድቦች ጋር ግንኙነት ስላለው ግድቦቹንም አደጋ ላይ ሊጥላቸው ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው ይገልጻል።
መክብብ ተሰማ (ዶ/ር)፣ በዱር እንስሳትና በአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የረዥም ዓመታት ልምድ ያካበቱ ባለሙያ ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዓለም አቀፍ ግጭት እና ደህንነት አማካሪ ከተባለ ተቋም ጋር ይሰራሉ፡፡ በአከባቢ ላይ ሊያሳድር የሚችለው እንዲሁም በህብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ (environmental and social impact assessment) አስቀድሞ ጥናት ማድረግ እንደሚገባ በአጽኖት ይናገራሉ። ጥናቱ ሲደረግም ስራውን በሚሰራው ድርጅት ሳይሆን በገለልተኛ አካል መሆን እንደሚገባው እንዲሁም የተደረገው ጥናት ከወረቀት ባለፈ አፈጻጸሙ ላይ ትኩረት እንደሚያሻውም ያነሳሉ። ''በሀገራችን እንዲህ ያሉ ጥናቶች ብዙ ጊዜ ለይስሙላ ነው'' የሚደረጉት የሚሉት ባለሙያው በመንግስት ስር ለዚህ ስራ የተሰማሩ የአከባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ቁጥጥር በማድረግ ድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም ይጠቅሳሉ።
የዘርፉ ተመራማሪ እንደሚናገሩት የትኛዉም ፕሮጀክት ሲሰራ ይዞት የሚመጣዉ የራሱ ጉዳት አንዳለ እሙን ነዉ፡፡ሆኖም ግን ጉዳቱ ከጥቅሙ አንጻር የከፋ አንዳይሆን ጥንቃቄ ያሻል ይላሉ፡፡በተለይም ቦታዉ በርካታ የዱር አንስሳትና የእዕዋት ሀብቶች የሚገኙበት ሲሆን ደግሞ በተፈጥሮ ሀብቱ ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ አንደሚችል አያጠያይቅም፡፡ አሁን ግንባታዉ ይካሄድበታል የተባለዉ የጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ በብዝሀ ህይወት ሀብት የበለጸገ ለበርካታ የዱር አንስሳትና አዕዋፋት መጠለያ ስፍራ አንደመሆኑ መጠን በግንባታ ምክኒያት ተፈጥሯዊ ይዘቱን አንዳያጣ ትኩረት ሊሰጠዉ አንደሚገባ ነው የተናገሩት።
ከዚህ ቀደም በመንግስት ኢኮኖሚያዊ ልማትን ብቻ በማሰብ የተሰሩ ፕሮጀክቶች በአካባቢ ላይ ጉዳት ሲያስከትሉ መታየታቸዉን የሚናገሩት ባለሙያው ለዚህም እንደምሳሌ በኦሞ ወንዝ አከባቢ የተገነባው የስኳር ማምረቻ ፋብሪካ (ኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ) ጠቅሰዉ በወንዙ አከባቢ ባለው ማጎ ብሄራዊ ፓርክ የሚገኙ የተለያዩ እንስሳቶች ዝሆንን ጨምሮ በፋብሪካው ይዞታ ሳቢያ መተላለፊያ እንደተዘጋባቸው፣ የዱር አራዊቱ በተቆፈሩ ቦታዎች እየገቡ መሞታቸውን እና በአከባቢው ወራሪ (አዳዲስ) የእጽዋት ዝርያዎች መብቀላቸውን ያነሳሉ።
''የዱር እንስሳት ቦታ ለዱር እንስሳት መተው አለበት'' የሚሉት ዶ/ር መክብብ በፓርኮች የሚሰሩ ስራዎች ከእንስሳቱ ባለፈ ምንም እንኳን አዳዲስ የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ቢታሰብም የአከባቢው ነዋሪ የሚሰራውን ስራ እንደሚያሳጣ ይናገራሉ። በተጨማሪም ፓርኮቹ ከፍተኛ የደን መጠን የያዙ በመሆናቸው የቦታው መጠበቅ ለአየር ንብረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ይገልጻሉ።
በመጨረሻ ፓርክ ላይ በሚደረጉ ስራዎች በባለሙያዎች የሚሰጡት አስተያየቶች ልማትን ለማደናቀፍ የሚደረጉ አለመሆናቸውና እንደውም ልማቱ ዘላቂ እንዲሆን ካለው ፍላጎት የመነጨ መሆኑን ባለሙያው አንስተዋል።
በ2003 ዓ.ም የተቋቋመዉ የጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ አቅጣጫ በ178 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን 360 ስኩየር ኪሎሜትርን ይሸፍናል፡፡ የጊቤ ወንዝና በርካታ ሀገር በቀል እጽዋትን የያዘዉ ይህ ፓርክ በዉስጡ ጉማሬን ጨምሮ 17 አጥቢ አንስሳትን አንዲሁም ከ200 በላይ የአዕዋፍት ዝርያዎችን የያዘ ነዉ፡፡
ወ/ሮ ፍሬሕይወት ዱባለ ፖርኩን የሚያስተዳድረው የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊ ናቸው። ግንባታው ፈቃድ የሰጠው የዞኑ አስተዳደር ሲሆን ስለ ጉዳዮ ቢሮው እውቅና እንደሌለው ይናገራሉ። "በፖርኩ ውስጥ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ ነው ስለግንባታው የሰማነው።" በአጠቃላይ ሂደቱ ህጋዊ አሰራር ያልተከተለና ለአካባቢና የተፈጥሮ ሀብቶች ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑ እየታወቀ ግንባታው እንከናወን መፈቀዱ "የዞኑ አስተዳደር ለፓርኮች ልማትና ጥበቃ ተገቢውን ትኩረት የሚሰጥ አለመሆኑን ያሳያል።" ከሰል ድንጋይ ማምረቻው የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ተሰርቶለት ፈቃድ ስለመሰጠቱም ጥያቄ እንደሚያስነሳም ያነሳሉ።
ወ/ሮ ፍሬህይወት ፓርኩ በክልሉ ዉስጥ ካሉ ፓርኮች ዉስጥ የከፋ ተደራራቢ ችግሮች ያሉበትና አደጋ ላይ ያለ መሆኑን ጠቅሰዉ ከዚህ ቀደም በፓርኩ ዉስጥ አቅራቢያ የአበባ ልማትን ጨምሮ ሌሎች ግንባታዎችን ያለ ቢሮ እውቅና ተገንብተው ይገኛል።
ህገወጥ ሰፈራ የደን መጨፍጨፍ፤ ከሰል ማክሰልና የመሳሰሉት ተግባራት አንደሚከናወኑበት ያነሱት ምክትል የቢሮ ሀላፊዋ የዞኑ አስተዳደር ለፓርኩ የሚሰጠዉ ትክረት አነስተኛ መሆኑ እንዳሳሰባቸዉም ተናግረዋል፡፡
አሁን ያጋጠመዉ ችግር በአንድ ቢሮ ብቻ የሚፈታ አይሆንም ከክልሉ ከፍተኛ ሀላፊዎች ጋር በመነጋገር ፋብሪካዉ ከፓርኩ ክልል ዉጭ በፓርኩ ላይ ጉዳት በማያደርስበት መልኩ አንዲገነባ ቢሮዉ ግፊት ያደርጋል፡፡