ተዳፋታማ አቀማመጥ ያላት አዳማ ከተማ እንደ አብዛኛዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ የዝናብ መጠን የምታገኘው በሰኔና መስከረም መካከል ባሉት ወራት ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያሻቅበው የህዝብ ቁጥሯ ምክንያት ከከተማዋ መስፋፋት እንዲሁም በዋናነት ከመሰረተ-ልማት ግንባታ ችግሮችና አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የጎርፍ እና የውሃ መጥለቅለቅ ችግር የየክረምቱ የኗሪዎች ሮሮ እየሆነ ቀጥሏል፡፡
በከተማዋ ከጎርፍና ከፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር ጋር በተያያዘ የሚነሱት ቅሬታዎች የተለያዩ መልክ አላቸው፡፡ በቂ የሆነ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ መሰረተ ልማት አለመኖር፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎቹ መጥበብ፣ ለአፈሳሰሱ ስልጠት የሚረዳው ግድለት (slope) አለመኖር ወይም በቂ አለመሆን፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎቹ ጠጣር ነገሮችን የሚያስቀርላቸው ወንፊት አለመኖር ወይም ወንፊቱ የሚጠበቅበትን አገልግሎት አለመስጠቱና፣ የፍሻሽ ማስወገጃ ቱቦዎቹ ክዳን ጥራቱን የጠበቀና ጠንካራ አለመሆን በዋና ዋና የችግር መንስኤነት ተጠቅሰዋል፡፡
የተዘረዘሩት ችግሮች በፍሳሽ ማስወገጃዎች ላይ ደረቅ ቆሻሻዎች እንዲጠራቀሙና፣ ፍሻሹ ከማስተላለፊያ ቱቦዎቹ አልፎ የእግረኛና የተሽከርካሪ መንገዶች ላይ ፈሶ እንቅስቃሴን እንዲያውክ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ የፍሳሽ ማስወገጃዎቹ የታቀደውን ጥቅም ከመስጠት ይልቅ ተጨማሪ በከተማዋ መንገዶችን ነዋሪዎች ላይ ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ ክስተቱም ነዋሪዎቹ በአካሉ፣ በህይወቱ እና በንብረቱ ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡
በጋራ ሉጎ ቀበሌ ጥቁር ዓባይ አካባቢ በአትክልት ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ደጉ ተስፋዬ እርሳቸው የሚሰሩበት አካባቢ በክረምት ወቅት ከፍተኛ የጎርፍ ችግር የሚስተዋበት እንደመሆኑ በስራቸው ላይ ከፍተኛ ችግር የፈጠረባቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በጎርፍ ወቅት ከገበያ መራቅ አንስቶ የጎርፍ ውሃው ለተለያዩ ትንኞች መራቢያ በመሆኑ ለሽያጭ ሚያቀርቡት አትክልት ምርት ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ለጎርፉ መፈጠር ዋነኛ ምክንያት አንዱ የጎርፍ ማተላለፊያዎቹ በቆሻሻ መደፈናቸው ነው፡፡ ስለጉዳዩ ሲያብራሩም “ኅብረተሰቡ በቆሻሻ አወጋገድ ጉዳይ ላይ ማኅበራዊ አንቂ ያስፈልገዋል” ይላሉ፡፡ እርሳቸው በቆሻሻ አወጋገድ ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ የሚናገሩት አቶ ደጉ በአካባቢያቸው ከፍተኛ የቆሻሻ አወጋገድ ችግር መታዘባቸውን ለአዲስ ዘይቤ አጋርተዋል። ይህንንም ለማስተካከል መንግሥት ከማስተማሩ ባለፈ ጠንከር ያለ ቅጣት ቢወሰድ የተሻለ ይሆናል የሚል ሀሳብም አንስተዋል፡፡
በኦዳ ቀበሌ ዋርካ አካባቢ የምትሰራው ብስራት ተመስገን “አካባቢው የታክሲ መጫኛ እና ማውረጃ እንደመሆኑ ዝናብ የሚያመጣው ጎርፍ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ እክል ይፈጥራል ስትል የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች ትገልፃለች፡፡ ታክሲዎችም ሆኑ ተሳፋሪ መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ የጎርፍ መፍሰሻ መስመሩ በአግባቡ ባለመከደኑ ጎርፍ በሚሞላ ወቅት መንገድ እየመሰላቸው አካቢውን የማያውቁ እግረኞች፣ መኪኖች እየገቡበት ከፍተኛ የአካል እና የንብረት ጉዳት መድረሱ የተለመደ ነው” ብለች፡፡ ከዚህ ሌላ በበጋ ወቅት በመፍሰሻ ውስጥ የቀረው ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ ከፍተኛ ሽታ እንደሚፈጠር በአካባቢው መስራትም ሆነ ማለፍ እንደሚያዳግት፣ ጎርፍ ያመጣው ደለል ሲደርቅ አቧራ እንደሚያስከትል ትናገራለች፡፡ በአካባቢው ያሉ የንግድ ቤቶችም ለጎርፍ መፍሰሻው መደፈን እና በቆሻሻ መሞላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ትናገራለች፡፡ እንደ ብርሃን ገለጻ ተቋማቱ የሚገኙበትን አካባቢ በጽዳት የመያዝ፣ የማሳመርና የማስዋብ ግዴታ ቢኖርባቸውም ከጫት ገራባ እና ከፕላስቲክ ጠርሙስ ጀምሮ ተረፈ ምርታቸውን የሚጥሉት በአቅራቢያቸው በሚገኝ የፍሳሽ ማስወገጃ ነው፡፡
የጎርፍ እና የውሃ መጥለቅለቅ ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው የቀድሞ አውቶብስ ተራ አካባቢ የሚገኝው የናሽናል ፎቅ አካባቢ ነው፡፡ በአካባቢው ያነጋገርነው በግንባታ እቃዎች ሽያጭ ላይ የተሰማራው ወጣት አብድልቃድር መሀመድ "አጎቴ ከዚህ ሱቅ ሲወጣ አካባቢው በውሃ በመጥለቅለቁ የውሃ መውረጃው ቦይ ስለማይታይ የመንገድ መስሎት ውስጡ ገብቶ ህይወቱ አልፏል" ሲል በቤተሰብ አባሉ ላይ ያጋጠመውን አደጋ ለአዲስ ዘይቤ አጋርቷል፡፡
በአካባቢው በዝናብ ወቅት ከፍተኛ የውሃ መጥለቅለቅ ስለሚኖር በትንሹ ለአንድ ሰዓት እንቅስቃሴ ይቋረጣል፡፡ አንዳንድ እንደኑር ገበያ ባሉ የንግድ ማዕከላት ደግሞ ጎርፉ እየገባ የንብረት ጉዳት እንደሚደርስ የሚናገረው ወጣት አብዱልቃድር ችግሮቹ የጎርፍ እና ፍሳሽ አወጋገድ ችግሮች ምክንያት እንደሆነ ያምናል፡፡ “በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው የቆሻሻ አወጋገድ ባህል እጅግ ዝቅተኛ መሆኑም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የከተማዋን ንጽህና በተመለከተ የባለቤትነት ስሜት አንስቶ ቆሻሻዎችን በፈርጅ በፍርጅ ለይቶ አለማስወገድ ከፍተኛ ለውጥ የሚፈልጉ ችግሮች ናቸው፡፡” ሲል ሐሳቡን ደምድሟል፡፡
ለስብሰባ፣ ለመዝናናት፣ ለህክምና እና የተለያዩ ጉዳዮች የሚቆጠሩ እንግዶችን በየእለቱ ተቀብላ ምትሸኘው አዳማ በአውራ ጎዳናዎቿም ሆነ በውስጥ ለውስጥ መንገዶቿ እና መንደሮቿ ይህ ነው የሚባል ቆሻሻን ማስወገጃ ሁነኛ ዘዴ እንደሌላት ታዛቢዎች ይናገራሉ። ተደራጅተው ቆሻሻ በማስወገድ ላይ የተሰማሩ ማኅበራትም ቢሆን ከአገልግሎት ጥራት አንጻር ይተቻሉ፡፡ በእያንዳንዱ የዝናብ ቀን ጎርፍ አስፋልት ላይ መተኛቱ፣ ቱቦዎች ሞልተው እንቅስቃሴ መግታታቸው የዘወትር ጉዳይ ከሆነ ሰንበት ብሏል የሚል ምሬታቸውን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡
በኤምዋይ የምህንድስና አማካሪ ቢሮ ውስጥ በአርክቴክት የምትሰራው ገነት ዘበናይ ስለጎርፍ እና የውሃ መጥለቅለቅ ችግር መንስኤ የግንባታ ብቻ ሳይሆን የአጠቃቀም መሆኑን ትናገራለች፡፡
“ነዋሪዎች የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻዎቻቸውን በአግባቡ አለመጣላቸው ግንባታዎቹ ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጓል፡፡ የፕላስቲክ ጠርሙሶች፣ የጫት ገራባዎች፣ ፌስታሎች እና ሌሎችም ከመኖርያ ቤትና ከንግድ ተቋማት የሚወገዱት ቆሻሻዎች አግባብነት ያለው የአወጋገድ ስርአት ሊገነባላቸው ይገባል” ትላለች አርክቴክት ገነት አይልም “ይህ ሲባል ግን ግንባታው ችግር የለበትም ማለት አይደለም፣ ነገሩን ማየት የሚገባን ከግንባታ ጥናት እሰከ ድህረ-ግንባታ የጥገና እና ክትትል ሂደት ድረስ ያለውን ነው፡፡”
እንደ ባለሙያዋ ገለፃ በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ ኮንትራክተሮች የችግሩ ፈጣሪዎች ናቸው፡፡ አርክቴክቷ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራት ቆይታ እንደ መፍትሔ የምትለውን ሐሳብም እጋርታለች፡፡ “የመጀመሪያው መፍትሔ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው” ትላለች “ኅብረተሰቡ የአስተሳሰብ ለውጥ ሲያመጣ ችግሩ ሳይደርስ በፊት ቀድሞ የማሰብ ክህሎት ያዳብራል፡፡ ችግሩ ሳይደርስ ማለት ክረምት ሳይመጣ፣ የሰዎች ቤት በጎርፍ ሳይወሰድ፣ ንብረት ሳይወድም፣ ሰዎች ሳይሞቱ ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሁለት አካላትን እናስቀምጥ፡፡ አንደኛው ተጠቃሚው ነው ሁለተኛው ደግሞ ገንቢው አካል ነው፡፡ በመንገድ አጠቃም ላይ ሁለቱም ኃላፊነት አለበት፡፡ ተጠቃሚው በአግባቡ መጠቀም፣ ገንቢው በአግባቡ መገንባት አለበት” ስትል የመፍትሄ ሃሳቦችን አስቀምጣለች።
ተነግብተው በመጠናቀቅ ላይ ስላሉት መንገዶችን ባለሙያዋ ስትናገር “በቅድሚያ ይህ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች መለየት ነው፡፡ በልየታው ወቅት የችግሩ መኖር ብቻ ሳይሆን የችግሩ መንስኤ እና መፍትሔ መቀመጥ አለበት፡፡ ቀጣዩ የማስተካከያ እቅድ ማውጣት ነው አንዳንዱ ቱቦ ውሃ ከሚያሾልክበት በጣም በብዙ ሜትሮች ርቀት በሚገኝ ችግር ምክንያት ሊሆን ይችላል የተበላሸው ስለዚህ እሱን በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ቀጣዩ ተግባር ማጽዳት፣ ጥገና ማድረግ፣ እንደ ክዳን (ማን ሆል) ያሉ የተጓደሉ ነገሮችን ማሟላት፣ ለአጠቃቀም ክፍት ማድረግ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ተጠግኗል ብሎ መተው ሳይሆን ተከታታይነት ያለው ክትትል ይፈልጋል፡፡ ክትትል እና አግባብነት ባለው ሁኔታ መጠቀም ሁሌም መታለፍ የሌለባቸው ናቸው” ብላለች፡፡
ያነሳነውን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ ሐሳብ እንዲሰጡን የአዳማ ከተማ አስተዳደር የጽዳትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የጽዳት ሴክተር ኃላፊን በስልክ እና በአካል አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡