ኢትዮጵያን ጨምሮ ዛምቢያ፣ ኒጀር፣ ኬንያ፣ ህንድ፣ ሜክሲኮ እና ፊሊፒንስ ሕጻናትና ታዳጊዎች ማስቲሽ የሚስቡባቸው ሐገራት እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እንደ ሜክሲኮ ያሉ ሐገራት ልምድ እንደሚያሳየው ሕጻናትና ታዳጊዎቹ በማስቲሽ የጀመሩትን ሱስ ወደ ተከለከሉት አደገኛ እጾች ያሳድጉታል፡፡
በአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ከተሞች የተለያዩ ቁሶችን ለማጣበቂያነት የሚያገለግለውን ማስቲሽ በፕላስቲክ ጠርሙስ ውስጥ የያዙ የጎዳና ሕጻናት፣ ታዳጊና ወጣቶችን መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ ለገሐር፣ ቦሌ፣ ፒያሳ አካባቢ የተዘዋወረ ሰው አያጣቸውም፡፡ አዳማ ከተማም ፖስታ ቤት፣ ፍራንኮ እና መብራት ኃይል አስፓልት አካባቢ አሉ፡፡ በሀዋሳ ፒያሳ ያማረ ሆቴል አካባቢ፣ አቶቴ፣ ትሩፋት፣ አዲሱ መናኸሪያ፣ አሮጌው ገበያ፣ 05 ቀበሌ፣ ተባረክ ነዳጅ ማደያ እና በተለምዶ ዋንዛ ሰፈር ወጣቶችና ህፃናቱ የሚያዘወትሯቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ እንደ ካራማራ፣ ሼል፣ ኮኔል፣ አሸዋ፣ ነምበርዋን፣ ደቻቱ፣ ቀፊራ፣ ፖሊስ መሬት ያሉት አካባቢዎች ደግሞ በድሬዳዋ ከተማ ማስቲሽ የሚጠቀሙ ወጣቶች በብዛት የሚገኙባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡
በአደገኝነታቸው ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁጥጥር የሚደረግባቸው አደገኛ መድኃኒቶች እና እጾች በ4 ክፍል ይመደባሉ፡፡ እነርሱም ናርኮቲክ፣ ሳይኮትሮፒክ እና ፕሪከርሰር ኬሚካሎች እንዲሁም ማኅበራዊ መድኃኒቶችና እፆች ናቸው፡፡ የኦፕም፣ የካናቢስ፣ የኮካ ተክሎችና ዝርያዎቻቸው በናርኮቲክ ውስጥ ይጠቃለላሉ፡፡ በሳይኮትሮፒክ ምድብ የሚያነቃቁ፣ የሚያስተኙ፣ የቁም ቅዠት ውስጥ የሚከቱ በሚል በሦስት የተከፈሉ ኬሚካሎች እና እጾች ይገኛሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የሚቀመጡት ፕሪንከር ኬሚካሎች በራሳቸው አደንዛዥ እጽ ያልሆኑ ነገር ግን ከሌሎች ጋር ተቀላቅለው አደንዛዥ እጽ ለማምረት የሚያገለግሉ ኬሚካሎች ናቸው፡፡ እነዚህኞቹን ማንኛውም ሰው እንደልብ በቀላሉ ሊያገኛቸው ይችላል፡፡ ቀዳሚ ተግባራቸው ለኮንስትራክሽን፣ ለጽዳትና ለሌሎች መደበኛ አገልግሎቶች ነው፡፡ በሀኪሞች ለታማሚዎች የሚታዘዙ መድኃኒቶች እዚህ ውስጥ የሚካተቱበት አጋጣሚም አለ፡፡ በአራተኛ ደረጃ የሚቀመጡት ማኅበራዊ አደገኛ መድኃኒቶችና እጾች ናቸው፡፡ ለዚህ እንደ ምሳሌ ጫትን ጨምሮ አልኮልና የአልኮል ውጤቶች፣ ትማባሆ እና የትምባሆ ውጤቶችና የሚሸተቱ ኬሚካሎች ይጠቀሳሉ፡፡
በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ህፃናት ቢሮ የህፃናት ልማት ደህንነት ዳሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ነኢማ ሸሪፍ “የጎዳና ሕጻናት በሁለት ይከፈላሉ” ይላሉ፡፡ እንደ ወ/ሮ ነኢማ ገለፃ የቀን ውሏቸውን ጎዳና ላይ አድርገው፣ ለምነው ያገኙትን በልተው ወደቤታቸው የሚመለሱት የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ ሁለተኛዎቹ ሙሉ ለሙሉ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ናቸው፡፡ እዚህ ምድብ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ጎዳና ላይ የሚኖሩናና የቤት ኑሮን ፈፅመው የማያውቁ፣ ከነ ሙሉ ቤተሰባቸው ጎዳና የወጡ ወይም የቤተሰባቸውን ቤት ትተው ጎዳናን የመረጡ ይገኙበታል፡፡
በድሬደዋ ነምበርዋን መጨረሻ እና የአሸዋ መግቢያ አካባቢ ነዋሪ የሆነችውና የጤና ባለሙያ ወ/ሪት ዮዲት ዘውዴ በመኖርያ አካባቢዋ ብዛት ያላቸው ህፃናት ማስቲሽ ሲስቡ እንደምትመለከት ትናገራለች፡፡ ማስቲሽ በታዳጊዎቹ ተመራጭ የሆነበትን የሚመስላትንም ምክንያት እንዲህ ታብራራለች፡፡ “ማስቲሽ ከሌሎቹ ሱስ አስያዥ ንጥረ-ነገሮች አንጻር በቀላሉ ሊገኝ የሚችል ነው፡፡ ዋጋውም በአንጻራዊነት ርካሽ ነው፡፡ ተጠቃሚዎቹ የሚፈልጉትን ውጤት በፍጥነት ይሰጣቸዋል” ካለች በኋላ፤ በእድሜ ለጋ የሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ከማስቲሽ በተጨማሪ የተለያዩ ነዳጆች፣ ቀለም፣ የቀለም መበጥበጫ ወይም ማቅጠኛ እንደሚጠቀሙ ነግራናለች፡፡
“የሚሳቡት ኬሚካሎች አንዳንዶች ላይ ‘ለቀቅ ’ የማለት እና የኃይለኝነት ስሜት፣ ሌሎች ላይ ድካም ይፈጥራል፡፡ በተደጋጋሚ እንዲወሰዱ የሚያደርጋቸው ለተወሰነ ጊዜ የሚቆየው ‘የመንሳፈፍ ዓይነት ደስታ’ ነው። ከፍ ባለ መጠን ከተወሰደ የፍርሀት ስሜት ያመጣል፡፡ ለረዥም ጊዜ ሲወሰድ የአዕምሮ እድገትና በተለይ የማስታወስ ችሎታ ላይ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ይህ ችግር በታዳጊዎች ላይ በይበልጥ ይጎላል”። ትላለች የጤና ባለሙያዋ።
እንደ ወ/ሪት ዮዲት ገለፃ ማስቲሽን የሚጠቀሙ ህፃናት በአካልም ሆነ በስነ-ልቡና የተለያዩ ጉዳቶች ይደርሱባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ራሳቸውን መጠበቅ ስለማይችሉ ማስቲሹ በራሱ ከሚጎዳቸው በተጨማሪ የመደፈርና የመሳሰሉት ሌሎች ጥቃቶች ሊደርሱባቸው ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተጠቃሚዎቹ ማስቲሹ ስለሚያደነዝዛቸው የተለያዩ ወንጀሎች ላይ እንዲሳተፉ ሊደረግ እንዲሁም ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ሊፈፀሙባቸው ይችላል፡፡
"ማስቲሽና ቤንዚል ወደ ውስጠኛው የሰውነት ክፍል ሲገቡ የአዕምሮንና የሰውነትን አሰራር የሚቀይሩ ነገሮች ናቸው” ያሉን በድሬደዋ ድልጮራ ሪፈራል ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሔኖክ ነጋ ናቸው፡፡ ማስቲሽ የሳበ ሰው ከሌላው ጊዜ ምንም የተለየ ነገር ሳይፈጠር የደስታ ስሜቱ ጣራ ይነካል፣ ከፍርሃት ነፃ ይሆናል፣ ዕይታው ይዛባል፣ ቅዠትና ህልም ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ አሁን የሚገኙበትን እንዳያስተውሉና ከእውነታው የተለየ ነገር እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል።
እንደ ባለሙያው ገለፃ ማስቲሽ መሳብ ተጨማሪ አደገኛ ጉዳቶች አሉት፡፡ ለምሳሌ ልክ እንደ ረሀብ፣ ብርድ እና የመሳሰሉትን ነገሮች እንዲረሱ ያደርጋቸዋል፡፡ ምክንያቱም ማስቲሹ የአዕምሮ አሰራርን ስለሚቀይር ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች የሚገነዘበውን ንቁ የአዕምሮ ክፍል ሥራ አዛብቶ ስሜቶቹ እንዲረሱ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ሰውነት ፈሳሽ ማጣት (ድርቀት)፣ የምግብ እጥረት እንዲገጥመው ያደርጋል፡፡ የፈሳሽ ማጣቱና የምግብ እጥረቱ መደራረብ ድንገተኛ ህልፈት እንዲከሰት ያደርጋል፡፡
ማስቲሽ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችንም ክፉኛ ይጐዳል፡፡ ለምሳሌ ኃይለኛ ሳል ለጉሮሮ (የመተንፈሻ አካላት) ቁስለት ይዳርጋል፡፡ ምክንያቱም ቤንዚል በውስጡ “ቡቴን” እና “ሙቴን” የሚባሉ ንጥረ-ነገሮችን የሚይዝ ሲሆን እነዚህም ለሰንባ ነቀርሳ፣ ለሳንባ ካንሰር እንዲሁም ለሳንባ ምች ያጋልጣል፡፡ ከዚህም ሌላ ጡንቻ በማሸማቀቅ፣ መራመድን ይገታል ይላሉ ዶ/ር ሔኖክ፡፡
ይህንን ማስቲሽ መጠቀም ከጀመሩ ብዙም ያልቆዩ ከሆኑ እና ሱሳቸው ስር ካልሰደደ ከሆነ የንግግር ህክምና (Psychotherapy) በመስጠት ከሱሱ እንዲላቀቁ መርዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ልናስተውለው የሚገባው የንግግር ህክምና ማለት ሰዎች ከሀሳባቸው ትንሽ ወደኃላ ብለው ሀሳባቸውን በራሳቸው መመርመርና መለወጥ እንዲችሉ ማገዝ እንጂ ብዙዎች እንደሚመስላቸው ሰዎችን መምከር አይደለም ሲሉ በእነንደዚህ አይነት ሱስ ውስጥ ያሉ ሰዎችን መርዳት የምንችልበትንም መንገድ ዶ/ክ ሔኖክ ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ሔኖክ እነዚህ ህፃናት ከሱስ ተላቀው ወደ መደበኛ ህይወት እንዲመለሱ ሁሉም ሰው እንዲረባረብና መኖሪያ ቤት እንዲሁም የትምህርትና የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ማድረግን ጨምሮ፣ ማስቲሽ ለወጣቶቹ እንዳይሸጥ ከገበያ ማገድ ወይም ቁጥጥር ማድረግ፣ ማስቲሽ ለህፃናት የሚሸጡ ሰዎችን እየያዙ ለሕግ ማቅረብ፣ ማስቲሽ መሳብ የሚያስከትለውን አደጋ በተመለከተ በሬዲዮና በቴሌቪዥን አንዲሁም በማኅበራዊ ድረ-ገፅ መረጃ ማሰራጨት፣ በት/ቤቶችም ማስተማር፣ ከዚህም በተጨማሪም የጐዳና ህፃናትን ቁጥር መቀነስም ያስፈልጋል ሲል የመፍትሄ ሀሳብ ነው ያለውን ገልጿል፡፡
በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ህፃናት ቢሮ የህፃናት ልማት ደህንነት ዳሬክተር ወ/ሮ ነኢማ በ2013 ዓ.ም. 315 ህፃናትን ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከጎዳና ላይ የማንሳት ስራ መሰራቱን ገልፀው እነዚህ ህፃናት ልክ እንደ ማስቲሽ ያሉ ሱሶች የነበሩባቸው ሲሆን ማገገሚያ በማስገባት ከሱሳቸው ለማላቀቅ የተለያዩ የስነ-ልቦናና የተለያዩ እርዳታዎች በማድረግ ቤተሰብ ያላቸውን ወደ ቤተሰባቸው እንዲመለሱ የማድረግ፣ አሳዳጊ የሌላቸውን ደግሞ የተለያዩ ሙያዎችን በማሰልጠን ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑን ጠቅሰው ፓድ እና ሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ ለዚህ ስራቸው እንደረዷቸው ጠቅሰዋል፡፡
ፓድ የተባለው የውጪ ግብረሰናይ ድርጅት ሲሆን የሁለት ዓመት ፕሮጀክት በመንደፍ 315ቱን ህፃናት በየተለያየ ሙያ እያሰለጠነ ይገኛል፡፡ የድሬዳዋ ከተማ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ በበኩሉ ከልዩ ልዩ መሥሪያ ቤቶች ከሚሰሩ ከደሞዝተኞች ላይ 0.25% ተቀንሶ በሚሰበሰብ ሕጻናቱን ለመታደግ መታቀዱንና በዚህ አጋጣሚ ነዋሪው እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡