በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ካለው የቤት ውስጥ የኃይል ፍጆታ ወደ 90% አካባቢ የሚመነጨው አላቂ ከሆኑት የማገዶ እንጨት፣ ከሠል፣ ከእንስሳት ፅዳጅ (ኩበት) ነው፡፡ ከባህር ዳር በተወሰነ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኝው ሜጫ ወረዳ እና አካባቢው ሰፊ ቦታ የሚሸፍነውን እና ምርታማውን ዓባይ ጨምሮ የተለያዩ ወንዞች እና ምንጮች ይፈሱበታል፡፡ አካባቢው በለምነቱ እና በምርታማነቱ ብቻ ሳይሆን በትርፍ አምራችነቱም ታዋቂ ነው፡፡ ከራሱ አልፎ የቀረውን የኢትዮጵያ ክፍል ይቀልባል፡፡ አሁን አሁን ግን ይህ የተፈጥሮ ጸጋን የታደለ አካባቢ በባህር ዛፍ እና ቶሎ በሚደርሱ የሳስፓንያ ዛፎች እየተካ ይገኛል፡፡
የምግብ ሰብሎች ምግብ ነክ ባልሆኑ ቋሚ ዋነኛ የኃይል ምንጭ በሆኑት የማገዶ እና የከሰል ተክሎች የመሸፈኑ ምስጢር የቤት ውስጥ የኃይል ፍላጎቶች ከምግብ ነክ የተክል እና የሰብል አቅቦት ዋጋ ጋር ለአርሶ አደሩ ከሚሰጡት ጥቅም አንፃር ብልጫ እያገኙባቸው መምጣታቸው መሆኑን የመርዓዊ ከተማ ኗሪው ወጣት መንግስቱ አለበል ይናገራል፡፡ ይህንን ሃሳብ የሚያጠናክሩት የባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ የቀድሞው አርሶ አደር የአሁኑ ከሰል አክሳይ አቶ ደስታ ፈጠነ ናቸው፡፡ አቶ ደስታ የምግብ ምርቶችን የማምረት ሥራቸውን የቤት ውስጥ የኃይል ፍላጎትን በማሟላት የተኩበት ምክንያት ትርጉም ያለው የገቢ ልዩነት በማስተዋላቸው ምክንያት ነው፡፡
ግርማው አሸብር በ2011 እና 2012 ዓ.ም. በአማራ ክልል ከፍተኛ የወጣቶች ጥያቄ የነበረው ደን እየጨፈጨፋ ከሰል የሚያከስሉ ባለሀብቶች ላይ ለምን እርምጃ አይወሰድም የሚል እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በከሰል ማምረቱ እና ሽያጭ ሰንሰለቱ ውስጥ ለባላሃብቶች እስከ ሱዳን ድረስ የሽያጭ ሰንስለት እንዳላቸው ይጠቁማል፡፡
በመርዓዊ እና አካባቢው ባህላዊ የከሰል ማክሰል ስርዓት የሚከተሉ አርሶ አደሮች የአካበቢውን አየር እጅግ በጎላ ሁኔታ በጭስ እንዲበከል ምክንያት ሁነዋል፡፡ የከባቢውን አየር ያፈነው የጭስ ሽታና ጉም ለብሶ የሚስተዋለው ዕይታ የተቃጠለ ከተማ ያህል እንግዳ ለሆነው ሰው አስደንጋጭ ነው፡፡
ታዲያ የአየሩ መታፈን በአካባቢው ባለ ትምህርት ቤት እና ታዳጊዎች ላይ የሚኖረው የጤና ሁኔታ ተፅኖውን ለማየት ህፃን ምንተስኖትን ዳምጤን ጠይቀነው የሰጠን ምላሽ፣ "የመተንፈሻ ችግርስ ሚሆን የብር ማጣት ነው” የሚል ነበር፡፡
የሽያጭ ሰንሰለቱ ሱዳን ድረስ የተዘረጋው ሕገ-ወጥ የከሰል ንግድ ብዙ አሻሚ የሕግ እና የማኅበረሰብ ግንዛቤ ችግሮች አሉበት፡፡ ስሙ ሕገ-ወጥ ይባል እንጂ የአካባቢው ግብርና ተቋማት እና የገቢዎች መስሪያ ቤት በተዘዋዋሪ ግብር ከአርሶ አደሩ ፈቃድ ይሰጣሉ፡፡ ከሰል አክሳይ አርሶ አደር መርጌታ ይልቃል አበጀ ከሰሉን ለመንግስት በኩንታል ዘጠኝ ብር ቀረጥ ከፍለው እንደሚሸጡና በመግለፅ ሕጋዊነቱን ያስረግጣሉ፡፡
በአንድ ጊዜም አንድ አርሶ አደር በዓመት 1,200 ኩንታል ከሰል በማክሰል ለገበያ እንደሚያቀርብ መርጌታ ይልቃል ይናገራሉ፡፡ አብዛኛዎቹ አክሳዮች ሕጋዊ ካለመሆናቸው የተነሳ እርግጠኛ ቁጥራቸውን ማወቅ አስቸጋሪ ነው የሚለው የግብርና ባለሙያው ይበልጣል ተላከ “በአሁኑ ወቅት የአርሶ አደሮች የትርፍ ጊዜ ስራ ከመሆን አልፎ የሙሉ ጊዜ የምርት እና ብቸኛ የገቢ ምንጭ ወደመሆን ተሸጋግሯል” ይላል፡፡
በአካባቢውም ከከሰል ምርት ብቻ በዓመት ከ50 ሚልዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚገኝ የወረዳው አካባቢ ጥበቃ ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡ “ከሠል ማክሠል በአስገዳጅ እና አጓጊ ኃይሎች መሃል የተወጠረ ክስተት ነው” ሲል የሚገልፀው የማኀበራዊ ጥናት መድረክ ባንድ በኩል ወቅትን ጠብቆ የሚከሰት የገበሬ ቤተሰብ ምግብ እጥረት አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ገበሬው ከሠል እንዲያከሥል በነጋዴዎችና በደላሎች የሚቀርብለት በርካታ ማትጊያዎች አሉ ሲል የሁኔታውን አባባሽ ምክንያቶች ያስረዳል፡፡
ከሰል ቸርቻሪዋ ወ/ሮ ጎጃሜ አያል በበኩላቸው በአካባቢው የሚቸረችሩት ከሰል ከሌላው የንግድ ዓይነት የበለጠ ገቢ እንደሚያስገኝላቸው ያብራራሉ፡፡ “ከሰል የምግብ ያህል የቤት ማዕድን እናሟላበታለን” የሚሉት ወ/ሮ ጎጃሜ የዋጋውም ከፍተኛነት “ከጋዝ እና ከኤለክትሪክ ኃይል በላይ እየሆነ ነው” ሲሉ ያነፃፅሩታል፡፡
ከአማራ ክልል ውሃ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በየጊዜው እየተራቆተ የመጣውን የደን ሀብት ጠብቆ በአግባቡ በቁጠባ መጠቀም እንዲሁም በአየር ንብረት መዛባት ላይ የሚያስከትውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከል አማራጭ የኢነርጂ ምንጮችን መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም በክልችን አማራጭና ታዲሽ የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎች በስፋት እየተሰራጩ ሲሆን መብራት ከምንጠቀምባቸው አማራጭ የኢነርጂ ቴክኖልጂዎች ባሻገር ብዙ ኃይል የሚጠይቁ የምግብ ማብሰያ ምድጃዎችን በተሻሻለ ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎች በመተካት በአማራ ክልል ያለውን የተሻሻለ የኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን ስርጭት ሽፊን በ2013 ዓ.ም. መጀመሪያ ከተደረሰበት 54.39% ወደ 58.29% ማሳደግ ተችሏል፡፡ በዚህም መሰረት ባለፈው አንድ ዓመት 140,148 የሶላር ቴክኖሎጂዎችን በማሰራጭት 0.952 ሜጋ ዋት ኃይል ማቅረብ ችሏል ያሉ ሲሆን በዚህም 140,351 ከኤሌክትሪክ ዋና መስመር ርቀው የሚገኙ የክልሉን የገጠር አባወራና እማውራዎችን ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በተለይ ከሠል በማክሰል ስራ ላይ የተሠማሩ ሠዎች በአብዛኛው የስራ አማራጭ በማጣት ብቻ በዚህ የስራ መስክ ለመተዳደር የተገደዱ ሰዎች አለመሆናቸው ደግሞ የችግሩን ስፋት በአካባቢው የሚሰጠውን የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች ልል አፈፃፀም የግንዛቤ ችግር ያሳያሉ፡፡
ባሕላዊው የአከሳሰል ዘዴ እንጨቱን መሬት ላይ አደራርቦ በመከመር በሳርና ቅጠላቅጠል ከሸፈኑ በኋላ አየር እንደልብ እንዳይገባ በአፈር ሸፍኖ በሁለትና ሦስት ቀዳዳዎች በኩል ክምሩን በመለኮስ የሚካሄድ ነው፡፡
በ2013 ዓ.ም. በተደረገ ጥናት በአሸብር ዲንጎቶ እና ደስታ ቃልሳ እንዳብራሩት በኢትዮጵያ ከጠቅላላ የኃይል ፍጆታችን ውስጥ ኤሌትሪክ 48.27 ከመቶ ዜጎች አቅርቦት አላቸው፤ ነዳጅ (ማለትም ቤንዚል፤ ናፍጣና፤ ቡታጋዝ) 7 ከመቶ፤ እንጨትና የመሳሰሉት 92 ከመቶውን ይሸፍናሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ባካሄደው ጥናት ኢትዮጵያ ከዓለም በከፍተኛ የከሠል ምርት ከሚታወቁ ሦስት ሀገሮች አንጇ ስትሆን ቀዳሚዎቹ ሁለቱ ብራዚልና ናይጄሪያ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ከሚመረተው የእንጨት ከሠል ምርት የ8 በመቶ ድርሻ ስትይዝ፤ ብራዚል 11 ከመቶ ናይጄሪያ ደግሞ 8 ከመቶ ያመርታሉ፡፡ በዚሁ መረጃ መሠረት ከ1998-2010 ባሉት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ከ40 ሚሊዮን ቶን በላይ ከሠል እንደተመረተ ተመልክቷል፡፡ ይህም በዓመት 3.8 ሚሊዮን ቶን በላይ መሆኑ የ2011 የዓለም ባንክ ሪፖርት ያሳያል፡፡
የሀገሪቱ ዓመታዊ የከሠል ፍጆታ መጠን ስንመለከት (3.8 ሚሊዮን ቶን) ብዙ ቤተሠቦች ከሠልን በማምረት እንደሚተዳደሩ ወይም የኑሮዋቸው መደጎሚያ እንደሚያደርጉትና በሚሊዮን የሚገመቱ ደግሞ በዋና የኃይል ምንጭነት እንደሚጠቀሙበት ያሳያል፡፡ ከዚህም በላይ ከሠል ከኢትዮጵያ በሕገ-ወጥ መንገድ ከሶማሌ፣ ከአፋርና ከአማራ ክልሎች ወደ ጎረቤት አገሮች እንደሚላክ ብዙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በኢትዮጵያ ትልቁ የከሠል ፍጆታ ያለው በዋና ከተማዋ በአዲስ አበባ ሲሆን የማኅበራዊ ጥናት መድረክ ይፋ ባደረገው የፖሊሲ ምክረ ሃሳብ ውስጥ እንደተጠቀሰው በአዲስ አበባ ለ24 ሰዓታት ለአራት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው ቆጠራ በየቀኑ በአማካይ 50 ኪሎ ግራም የሚመዝን 42‚045 ኬሻ ከሠል ወደ ከተማዋ እንደሚገባ ተመዝግቧል፡፡
የከሰል ምርት የአፈር መሸርሸርን፤ የዱር እንሰሳት መመናመንን፤ የአፈር መከላትን፤ የተደጋጋሚ ድርቅ መከሰትን፤ ብሎም ድህነትን እንደሚያስከትል ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ አርብቶ-አደሩ እና አርሶ አደሩ ቋሚ መተዳደሪያው እየሆነ ነው፡፡ በዚህ በከሠል ኢኮኖሚያዊ ጥቅም (ምርትና ንግድ) ትስስር ውስጥ አምስት ወገኖች እየተሳተፉበት ነው፡፡ እነዚህም ዛፍ አብቃይ (አምራች)፣ ከሠል አምራች፣ አጓጓዥ፣ አከፋፋይ/ቸርቻሪና ተጠቃሚ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ከሠል በተፈጥሮ ከበቀለ የደን ዛፍ በነጻ የሚገኝ በመሆኑ ቆራጭ እንጂ አብቃይ የለውም፡፡ ይህ አካሄድ በደን ሀብቱና በገበያው ላይ ከፍተኛ ተዕእኖ እያሳደረ ነው፡፡
በቂ የአየር ዝውውር በሌለበትና በተዘጋ ቤት ውስጥ ከሠልን በመጠቀም በሚፈጠረውና አድብቶ ገዳይ (silent killer) ተብሎ በሚታወቀው ካርቦን ሞኖ ኦክሳይድ መርዛማ ጋዝ ሳቢያ አያሌ ሰዎች ለተለያዩ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችና (respiratory diseases) ብሎም ለሞት ይዳረጋሉ። ይህ መርዛማ ጋዝ ደም ውስጥ በመግባት የኦክስጅንን ቦታ በመሻማትና የኦክስጅን እጥረት በመፍጠር ለሞት ይዳርጋል።
ይሁንና እ.ኤ.አ በ1965 ዓ.ም. ከወጡት የመጀመሪያዎቹ የደን ሕጎች ጀምሮ በ1980፣ በ1994፣ በ2007 እና በ2018 በወጡት ሕጎች ውስጥ የከሠል አመራረቱንም ሆነ ገበያውን አቅጣጫ ለማስያዝ የተቀረፀ ሕግ የለም፡፡