በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ አካባቢዎች የታየው የጸጥታ ችግር የምግብ እና ሌሎች ሸቀጦች ዋጋ እንዲንር ምክንያት ሆኗል፡፡ በተጨማሪም ካሳለፍነው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ በሐገራችን በስፋት መታየት የጀመረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሸቀጦችን ዋጋ ያናረ ክስተት እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ በሰሜኑ የሐገራችን ክፍል የተፈጠረው የሰላም እጦት እና አለመረጋጋትም ዋጋን በማናር ከሚጠቀሱ ምክንያቶች ውስጥ ይካተታል፡፡
ጅግጅጋ ከተማ የሚገኘው የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር የከተማዋን መደብሮች ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡ ከሁሉም የጅግጅጋ ከተማ ክፍለ ከተሞች የመጡ ገበያተኞች የሚገበያዩበት ጅግጅጋ 01 ቀበሌ ወይም ሀቫና ገበያ ባካሄደው ቅኝት ያነጋገራቸው ገበያተኞች የሸቀጦች ዋጋ መናር እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል 01 ገበያ አዝርዕት፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመም እና ሌሎች ለምግብነት የሚውሉ ሸቀጦች ለግብይት የሚቀርቡበት ገበያ ነው፡፡
በገበያው ጤፍ በኪሎ ከብር 39 ጀምሮ እንዲሁም በርበሬ በኪሎ ከ150 እስከ 190 ብር፣ እየተሸጠ እንደሚገኝ በጤፍ ንግድ ላይ የተሰማሩት ወ/ሮ አበራሽ ሞላ ይናገራሉ፡፡ ወ/ሮ አበራሽ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የነበረው ዋጋ ከወቅታዊው የሽያጭ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል ይላሉ፡፡ ሁኔታው አሁን ባለበት የጭማሪ ፍጥነት ከቀጠለ የገዢውን የመግዛት አቅም በእጅጉ ከመፈተኑም በላይ በርካታ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን ጾም ወደማደር ሊገፋ እንደሚችል ስጋታቸውን ይናገራሉ፡፡
“በኪሎ 150 ብር የነበረው ኮረሪማ 190 ብር ገብቷል፡፡ ጥቁር አዝሙድ በኪሎ እስከ 160 ብር ይሸጥ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ እስከ 280 በኪሎ እየተሸጠ ነው፡፡ ከዋጋ ንረቱ በተጨማሪ እጥረትም አለ፡፡ ለምሳሌ ጥቁር አዝሙድ የለም፤ በውድም ቢሆን እየተገኘ አይደለም” ብለዋል፡፡
ከሳምንት በፊት ለጤፍ ሸመታ እዚሁ ገበያ የመጡት እናት ወ/ሮ ማንያዩሻል ሰፈፈ ደግሞ በኪሎ ከ35 ብር በታች የሸመቱት ጤፍ ከ45 ብር በላይ ሆኖ ጠብቋቸዋል፡፡
“የዋጋ ጭማሪው እንደ በፊት ሳምንታት እና ወራት አይታገስም፤ እየጨመረ ያለው በቀናት ልዩነት ነው” የሚሉት ወይዘሮዋ አንዳንድ የዋጋ ጭማሪዎች ይህ ነው የሚባል ምክንያት እንኳን ሊሰጥላቸው እንደማይችል ያነሳሉ፡፡ “ነጋዴው ለህዝቡ ማሰብ አለበት፡፡ ትርፉን ብቻ ካሰበ ነገ የሚገዛው ላይኖር ይችላል፡፡ ገዢው ከሞተ በኋላ ብቻውን እህል ታቅፎ ቢቀመጥ ምን ይሰራለታል?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የሸቀጦች ዋጋ ከአካባቢ አካባቢም ልዩነት አለው፡፡ ጎዴ አካባቢ በኪሎ ብር 120 የሚሸጠው በርበሬ ዘነበ ወርቅ ብር 150 ይሸጣል፡፡ ሌሎች ቦታዎች ላይም ብር 175 እየተሸጠ ነው፡፡ ይህ ዋጋ በአምናው ተመሳሳይ ወቅት በኪሎ ብር 80 ይሸጥ ከነበረው ዋጋ የእጥፍ ጭማሪ እንዳሳየ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በደጋህቡር አንድ ኪሎ ሽንብራ ብር 26፣ ባቄላ ከብር 25 እስከ 27 እየተሸጠ ሲሆን፣ አተር ክክና ድፍን አተር ከ40 እስከ 42 ብር እየተሸጡ መሆኑን በደጋህቡር ከተማ የእህል ነጋዴ አቶ ኡሰማን አብዱላሂ ለአዲሰ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡
ጥራጥሬ ቀድሞ ይሸጥበት በነበረው ዋጋ እንደቀጠለ እንደሚገኝ የገለጹልን ሸማች ወይዘሮ ሙና አህመድኑር ሸማቾች ምናልባት በተለያዩ ክልሎች የበረሃ አንበጣ በመከሰቱ ምክንያት ዋጋ ጭማሪ ሊኖር ይችላል ብለው መሥጋታቸውን ሆኖም ከሰኔ በኋላ አዲስ እህል ሲገባ ይበልጥ ቅናሽ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ነጋዴዎችም ይህንኑ ሐሳብ ተጋርተዋል፡፡
ከሰሞኑ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ግጭት በተነሳ ቁጥር የንግድ ሰንሰለቱ ላይ የዋጋ ንረት መታዘብ ከጀመርን ሰንበትበት ያለ ቢሆንም መንግሥት በትግራይ ክልል ላይ በጀመረው ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ ምክንያት የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ ሶማሌ ክልል ላይ መታየቱን አዲሰ ዘይቤ በተዘዋወረችባቸው የገበያ ማዕከላት ታዝባለች፡፡
የጅጅጋው ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው በእህል ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ደግሞ የዋጋ ንረቱ ምክንያት የግብይት ሰንሰለቱ ነው የሚል ሐሳብ አላቸው፡፡ እንደ ነጋዴዎቹ አባባል ከገበሬው ማሳ አንስቶ ነጋዴ እጅ እስኪገባ ባለው የግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ተዋንያን የችግሩ ባለቤት እና ፈጣሪ ናቸው፡፡ ችግሩ መፍትሔ ተበጅቶለት ዕልባት ካገኘ ነጋዴዎችም ሆኑ ተጠቃሚው ማኅበረሰብ አቅርቦቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
የእህል ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ የሚንርበት ዋነኛ ምክንያት በአገሪቱ በሚከሰቱ ግጭቶች እንደሆነ፣ አቅራቢውም ይህንን ተገን በማድረግ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ ነው የሚል ሐሳባቸውን ያጋሩን ሃሊማ ሁሴን የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ሃሊማ የእህል ዘሮች የመሸጫ ዋጋ ተመጣጣኝ የሚባል እንደነበርና በአሁኑ ወቅት ግን ተገላቢጦሽ መሆኑ ትልቅ ችግር እንደፈጠረባቸው ነግረውናል፡፡
ለችግሩ አፋጣኝ እልባት ካልተበጀለት አቅራቢዎችም ለነጋዴው በተመጣጣኝ ዋጋ ማስረከብ ካልቻሉና የዋጋ ንረቱ እየተባባሰ ከሄደ ከፍ ያለ የኑሮ ቀውስ ሊያጋጥም እንደሚችል የነጋዴዎቹም የሸማቾችም ስጋት ነው፡፡
የሶማሌ ክልል ንግድና እንዱስትሪ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አህመድ ሀቢብ አግባብነት የሌለው የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡ አቶ አህመድ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ “በአሁኑ ወቅት ከ1ሺህ 7መቶ በላይ የንግድ ተቋማት በመዘዋወር ክትትል ተደርጎባቸዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 1ሺህ የሚሆኑ የንግድ ተቋማት ሕጋዊ ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸውም ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ምርት የደበቁ፣ አላግባብ ያከማቹ እንዲሁም ፈቃድ የሌላቸው 77 መጋዘኖች ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል” ብለዋል፡፡
የምርት አቅርቦቱ አናሳ እንዳይሆን ከክልልና ከሶማሌ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር በቅንጅነት በመሥራት አገልግሎቱን እያቀረቡ መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ተቋሙ በየክፍለ ከተማው የሚገኙ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕግ የሚያቀርብ ኮሚቴ አዋቅሯል ያሉ ሲሆን ወደፊት ተመሳሳይ ተግባር እንደማይስፋፋ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን በመከታተልና በመለየት ያለውን ችግር መፍታት እንደሚቻልም አስታውሰዋል፡፡