ሰኔ 11 ፣ 2013

ጩኸት ያፈናት ከተማ

ኹነቶች

የድምጽ ብክለት መጨመር የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ለምሬት ከመዳረጉም ባሻገር የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን በመረበሽ ጭንቀትን፣ አለመረጋጋትን፣ እርስ በእርስ አለመደማመጥን ብሎም ሰላምን በማደፍረስ ትልቁን ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

ጩኸት ያፈናት ከተማ

የድምጽ ብክለት መጨመር የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ለምሬት እየዳረገ ይገኛል፡፡ ከመጠን ያለፉት ረባሽ ድምጾች፡- ከንግድ ትርኢቶች፣ ከሐይማኖት ተቋማት፣ ከምጽዋት ጠያቂዎች፣ ከጎዳና ላይ ንግድ፣ ከምግብና መጠጥ ቤቶች፣ ጋራዥ፣ እንጨት ቤት እና ብረት ቤትን ከመሰሉ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ከፊልምና ሙዚቃ መሸጫዎች፣ ከተሽከርካሪዎች እና ከመሳሰሉት ይመነጫሉ፡፡

ለመሆኑ የድምጽ ብክለት ማለት ምን ማለት ነው? ምን ጉዳት ያስከትላል? እንዴት መቆጣጠር ይቻላል? የሚለውን ጥያቄ አንስተናል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የባለሙያዎች አስተያየት እና የተጎጂዎች ሐሳብ ተካቷል፡፡

"የድምፅ ብክለት መደበኛውን የሕይወታችንን እንቅስቃሴ ይጎዳል፣ ያስተጓጉላል፣ እንቅልፍ ይነሳል፤ ውይይቶቻችንንና መደማመጣችንን ይቀንሣል፣ በአጠቃላይ የአኗኗራችን ሁኔታ የተረበሸ እንዲሆን ያደርጋል።” የሚሉት የቀድሞ የኢትዮጵያ ህክምና ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገመቺስ ማሞ ናቸው፡፡

ዶ/ር ገመቺስ ሐሳባቸውን ሲቀጥሉ “የድምፅ ብክለት በጤና ላይ በቀጥታ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ የምርታማነት መቀነስ፣ የትራፊክ አደጋ መበራከት፣ የማኅበራዊ ሕይወት መደፍረስ፣ የቤተሰብ መመሳቀል፣ የልጆች አዕምሮ መድከም፣ በውጤቱም የትውልድ ጉዳት ይከተላል።” በማለት ከዘረዘሩ በኋላ ይህ መረበሽና መስተጓጎል ከሚያደርሳቸው የበረቱ የጤና ችግሮች መካከል ከጭንቀት፣ የደም ግፊት፣ የአንደበት መተሳሰር (መንተባተብ)፣ የመስማት ችሎታን መቀነስ ግፋ ሲልም ማጣት፣ የልብና የደም ዝውውር ሥርአት መስተጓጎል፣” እንደሚገኙበት ዘርዝረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአካባቢ ደህንነት መብትን በሰብአዊ መብት ደረጃ በሕገ መግሥታቸው ከደነነጉ ጥቂት ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናት፡፡ የድምጽ ቁጥጥር ሕጉ ከንግድ አካባቢዎችና ከኢንዱስትሪ ዞኖች መውጣት የሚገባው የድምጽ መጠን በድምጽ መለኪያ አስቀጧል፡፡ በዚህም መሰረት ሰዎች በሚንቀሳቀሱበት የቀኑ ክፍለ ጊዜ በከባቢ አየሩ የሚረጨው ድምጽ 55፣ 65 እና 75 ዲሲቢል መብለጥ እንደማይገባው፤ ለሌሊት ደግሞ 45፣ 57 እና 70 ዲሲቢል መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡

በመሆኑም አንድ ግለሰብ የድምጽ ብክለት ገደቡን ተላልፎ ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ በገንዘብ ከብር ከ1,000 እስከ 5,000 በሚደርስ መቀጮ ወይም በእስራት ከ1 ዓመት ባላነሰ ከ10 ዓመት ባልበለጠ እስራት እንደሚቀጣ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡ ጥፋተኛው የሕግ ሰውነት የተሰጠው (ተቋም) ከሆነ ደግሞ ከብር 5,000 እስከ 25,000 በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይጣልበታል፡፡ የድርጅቱ ኃላፊም ከ5 እስከ 10 ዓመት እስራት ወይም ከብር 5,000 እስከ 10,000 በሚደርስ እስራት ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ ደንግጓል፡፡

ሕጉ ይህንን ቢልም ተፈጻሚነቱ ላይ ግን ችግሮች ያሉ ይመስላል፡፡ አንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ላይ ቅኝት ያደረገችው አዲስ ዘይቤ የድምጽ ብክለት ችግርን ለመቅረፍ የወጡ ሕግጋትን ከማስፈጸም አኳያ ሰፊ ጉድለት እንዳለ ተመልክታለች፡፡

ሐሳባቸውን የሰጡን የከተማዋ ነዋሪዎች የድምጽ ብክለቱ ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ “ከየአቅጣጫው የሚለቀቀው ረባሽ ድምጽ ተረጋግተን ሥራችንን እንዳንሰራ፣ ቤት ገብተንም በቂ እረፍት እንዳናገኝ፣ ልጆቻችን የተረጋጋ እረፍትና ጥናት እንዳይኖራቸው፣ አድርጓቸዋል” ሲሉ ያማርራሉ፡፡

እነዚህንና መሰል አቤቱታዎችን በመከተል የድምፅ ብክለት ችግርን ለመቅረፍ የወጡ ሕጎችን ማስፈጸም ስላልተቻለበት ምክንያት የጠየቅናቸው የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ወይሳ ፈይሳ

“አካባቢን በድምጽ የሚበክሉ ድርጅቶች እና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ የክትትል እና ቁጥጥር ተግባራት ተከናውነዋል፡፡እርምጃ የተወሰደባቸውም አሉ፡፡ የሕግ አስከባሪዎች የድምፅ መጠን የሚለኩ መሳሪያዎችን ይዘው እንደሚቀሳቀሱና ሕጉን ተላልፈው የተገኙ አካላት ላይ እርምጃ ሲወስድ መቆየቱንም ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም በቁጥጥር ሥራ ላይ የተሰማሩ አንዳንድ ባለሙያዎች ለሙስና የተጋለጡ በመሆናቸው ምክንያት የሚፈለገው ውጤት አለመምጣቱን አልሸሸጉም፡፡    

ከሃይማኖት ተቋማት የሚለቀቁ ድምጾችን በተመለከተ የአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን ዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ላይ እንደሆነ ኮሚሽነሩ አስታውሰው ችግሩ ያለበትን ደረጃ የመረዳት እና በቀጣይም ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመነጋገር እና የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ የማስተካከል እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ እና ደህንነት ባለሙያና የጥናቱ ተሳታፊ የሆኑትን አቶ ጉሌድ አብዲም "የጥናቱ ዓላማ የእምነት ተቋማት የሚገኙበትን አካባቢ የሚያማክል መጠነኛ ድምፅ ገዳቢ መመሪያዎችን መከለስ፣ ኅብረተሱቡንም ሆነ ባለድርሻ አካላትን ያማከለ ምክክር ማድረግ እና በሚቻለው መጠን ነዋሪው ጤናማ መስተጋብር እንዲኖረው የሚረዳ ነው" ሲሉ አብራርተዋል።

የድምፅ ብክለት የተባባሰባት አዲስ አበባ ያልተፈለገ ድምፅ፤ በጉዞ፣ በእንቅልፍ፣ በሥራና ትምህርት፣ በንግግር እና በመሰል የሰው ልጅ የተለመዱ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር እና ጤናማ ከባቢን በመበከል በሥነ ልቦናዊ እና አካላዊ ጤንነት ላይ ይህ ነው የማይባል ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት እና ክትትል እንደሚያሻው አዲስ ዘይቤ ታስገነዝባለች።

አስተያየት