መስከረም 29 ፣ 2013

የአለም የፖስታ ቀን ኢትዮጵያን ጨምሮ በ192 አገራት እየተከበረ ይገኛል

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎችኹነቶች

በየአመቱ በመስከረም 29 ቀን በአለም የፖስታ ማህበር (Universal Postal Union) የሚከበረው የአለም የፖስታ ቀን በዛሬው እለት በማህበሩ 192…

የአለም የፖስታ ቀን ኢትዮጵያን ጨምሮ በ192 አገራት እየተከበረ ይገኛል

በየአመቱ በመስከረም 29 ቀን በአለም የፖስታ ማህበር (Universal Postal Union) የሚከበረው የአለም የፖስታ ቀን በዛሬው እለት በማህበሩ 192 አባል አገራት በተለያዩ መርሀግብሮች ይከበራል። ማህበሩ እነደገለፀው ከሆነ ዘንድሮ የአለም የፖስታ ቀን አከባበር የተለየ ርዕስ ያልተሰጠው ቢሆንም የማህበሩ ሶስት መርሆዎች የሆኑትን ፈጠራ፣ ውህደትና አካታችነት ቀኑ ተከብሮ በሚውልበት ወቅት ታስበው ይውላሉ። በተጨማሪም የአለም የፖስታ ቀን በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ የተነሳ ለመጀመርያ ጊዜ በኢንተርኔት የተደገፈ ስብሰባ እንደሚያደርግ ገልጿል። 

በቀኑ አከባበር ዙርያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶንዮ ጉቲሬዝ ባስተላለፉት መልዕክት  “የፊት መከለያ ማስኮችን ለተለያዩ ግለሰቦች ከማዳረስ አንስቶ ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን የትምህርት መፃህፍትና መሳርያዎች እንዲያገኙ እስከማስቻል ድረስ ፖስታና የፖስታ ቤት ሰራተኞች ትልቅ ሚና ተጫውተዋል”  በማለት በተለያዩ አገራት ውስጥ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ የሚገኙ የፖስታ ቤት ሰራተኞችን አመስግነው በተለይም በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ወቅት አገልግሎቱን በመስጠት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የፖስታ አገልግሎትን ከሚሰጡ ድርጅቶች አንዱ በሆነው ዲ.ኤች.ኤል (DHL) ውስጥ የደንበኛ አገልግሎትን የሚሰጠው ፊሊሞን አወጣኸኝ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገረው ከሆነ ምንም እንኳን በቴክኖሎጂ ዘመን እንደቀድሞ ባይዘወተርም አሁንም ዘርፉ በኢትዪጵያ አስፈላጊ የሚባሉ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል። “ደንበኞች አንዳንድ በኢሜይል ሊላኩ የማይችሉ በአይነታቸው ሚስጥራዊ የሆኑ ዶክመንቶችን ለመላክ አሁንም ቢሆን የፖስታ አገልግሎትን ይመርጣሉ።” ያለው ፊሊሞን በተለይም በኢንተርኔት ሊከሰቱ ከሚችሉ ጥቃቶች የተነሳ ዘርፉ አሁንም ተመራጭ ነው ሲል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

ከኮሮና ቫይረስ አንፃርም ዘርፉ አያሌ ሚናን ተጫውቷል የሚለው ፊሊሞን በተለይም ቫይረሱ በተከሰተበት ወቅት ዲ.ኤች.ኤል በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን የማስክና የተለያዩ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ምርቶች እጥረትን ለመግታት ትልቅ ሚና ተጫውቷል ይላል። “ምንም እንኳን አንድ እቃ ወይም ዶክመንት ከተላከበት ጊዜ አንስቶ ለደንበንኛ እስከሚደርስበት የሚወስደው ጊዜ በበረራዎች እጥረት ምክንያት ቢረዝምም ድርጅታችን አገልግሎቱን ሲሰጥ ቆይቷል።” ያለው ፊሊሞን ድርጅቱና ዘርፉ ትልቅ ሚናን ተጫውተዋል ይላል።

በመጨረሻ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ምን ይመስላሉ ለሚለው ጥያቄ ፊሊሞን ምላሹን ሲሰጥ በመንግስት መስሪያቤቶች በተለይም በገቢዎችና ጉምሩክ ድርጅቶች ዘንድ የሚታየው የቢሮክራሲ ችግር የተላኩ እቃዎች በወቅቱ ለደንበኞች እንዳይደርሱ ትልቅ ሳንቃ ነው ሲል ተናግሯል። አክሎም “የዘርፉን አስፈላጊነት ስለምረዳ በዚህ የስራ ዘርፍ - በተለይም በኮሮና ቫይረስ ወቅት - በመሰማራቴ ደስተኛ ነኝ።” ያለው ፊሊሞን የአለም የፖስታ ቀን ተከብሮ ሲውል መንግስት አስፈላጊውን የአሰራር ለውጥ ማድረግ እለበት ብሎ እንደሚያምን ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

የአለም የፖስታ ቀን በ1962 በቶክዮ ጃፓን በተደረገው የአለም የፖስታ ኮንግረስ ወቅት በመስከረም 29 ቀን እንዲከበር ከተወሰነበት ወቅት ጀምሮ የሚከበር ሲሆን በማህበሩ አባል አገራት በተለያዩ መርሀ ግብሮች ሲከበር ቆይቷል። የአለም የፖስታ ማህበር የተመሰረተው በ1867 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ሲሆን ኢትዮጵያ በ1901 ዓ.ም ማህበሩን ከተቀላቀለች ጀምሮ የማህበሩ አካል እንደሆነች በማህበሩ ድህረ ገፅ የሰፈሩ መረጃዎች ያሳያሉ። ማህበሩ በአለም ዙርያ ከ650,000 በላይ ቢሮዎችን ያቀፈ መረብ ሲሆን ከ5 ሚልዮን በላይ ሰራተኞች አሉት።

 

 

 

አስተያየት