መስከረም 26 ፣ 2013

የኢትዮጵያ የማስታወቂያ ስራ ማህበር ምስረታና ፋይዳው

ወቅታዊ ጉዳዮችንግድዜናዎች

በኢትዮጵያ የማስታወቂያ ዘርፍ የተስማሩ የተለያዩ ባለሙያዎችን ያቀፈው የኢትዮጵያ የማስታወቅያ ስራ ማህበር በሰኔ 16 2012 ተመስርቶ ወደ ስራ ከገባ…

የኢትዮጵያ የማስታወቂያ ስራ ማህበር ምስረታና ፋይዳው
በኢትዮጵያ የማስታወቂያ ዘርፍ የተስማሩ የተለያዩ ባለሙያዎችን ያቀፈው የኢትዮጵያ የማስታወቅያ ስራ ማህበር በሰኔ 16 2012 ተመስርቶ ወደ ስራ ከገባ ወራትን እሳልፏል። ማህበሩ እንደሙያ ማህበርነቱ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ያቀፈ ሲሆን በአገሪቱ የሚሰሩ የማስታወቂያ ስራዎች የአገሪቱን ባህልና እሴት የጠበቁ እንዲሆኑ እንደሚሰራ ባለፈው ሳምንት ማህበሩ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የማህበሩ ፕሬዝዳንትና አመራሮች ተናግረው እንደነበረ የሚታወስ ነው። ማህበሩ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን መብት ለማስከበር እንደተመሰረተ የሚናገረው አቶ አለባቸው ወዳይ ከዚህ ቀደም አላግባብ የሆኑ ስራዎች በመንግስት አካላትና በግለሰቦች ሲሰሩ ተደራጅቶ የባለሙያዎችን ፍትህ የሚያስከብር ማህበር ባለመኖሩ የተለያዩ ችግሮች ይስተዋሉ እንደነበር ለአዲስ ዘይቤ ይናገራል። “አቅማቸው ከፍ ያለ ማህበሮች ከመንግስት አካላት ጋር ካላቸው ወዳጅነት የተነሳ የበለጠ ጥቅም ያገኙ ነበር። ጥቅሙ እንኳን ቢቀር ኢፍትሀዊ አሰራር በእነሱ ላይ ብዙ አይስተዋልም።” ያለው አለባቸው አክሎም በተደራጀ መልኩ የባለሙያዎችን መብት ለማስጠበቅ የተቋቋመ ማህበር እንደሆነ ገልጿል። እንደምሳሌነት በመስቀል አደባባይ አካባቢ የሚገኙትን ቢልቦርዶች ያነሳው አለባቸው በስፍራው ላይ የማስታወቂያ ስራ ሲሰሩ የቆዩ ባለሙያዎች ያለምንም ማስጠንቀቅያ በመንግስት አካላት እንዲነሱ እንደተነገራቸው ያስታውሳል። “ይህ ነው የሚባል አሳማኝ ምክንያት ሳይሰጥ ቢልቦርዶች የተነሱበት ሁኔታ ነበር።” በማለት በወቅቱ የተወሰነውን ውሳኔ የሚያስታውሰው አቶ አለባቸው በተጨማሪም ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬቱ የተለያዩ መመርያዎችን በሚያወጣበት ወቅት የማማከር ተነሳሽነትም ሆነ የሚያማክረው የተደራጀ አካል ባለመኖሩ ምክንያት ብዙ ችግሮች ይስተዋሉ ነበር ብሏል። “የኢትዮጵያ የማስታወቂያ ኢንዱስትሪ በአግባቡ ቁጥጥር የሚደረግበት ዘርፍ አይደለም።” የሚለው አለባቸው ማህበሩ ይህን ችግር የመፍታት ትልቅ አቅም አለው ይላል። ይህን ክፍተት ለመሙላት ከ70 በላይ የሚሆኑ ባለሙያዎችን አቅፎ የተመሰረተው የማስታወቂያ ስራ ማህበሩ ፍትህን በተደራጀ መልኩ ማስከበር ዋነኛ ተቀዳሚ አላማው እንደሆነ የሚናገረው አለባቸው በቀጣይ የተለያዩ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ስራዎችን በመለየት ላይ እንደሚገኝ ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል። “በመጀመርያ ለመስራት ካሰብናቸው ስራዎች መካከል አንዱ ለረጅም አመታት በስራው ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ከመንግስት ጋር በመሆን ኦዲት ማድረግ ነው።” ያለው የማህበሩ ፕሬዝዳንት ከማህበሩ መመስረት በፊት ይስተዋል የነበረውን ግብር ያለመክፈል ችግር ለመፍታት እንደሚሰሩ ተናግሯል።ማህበሩ በሚመሰረትበት ወቅት ያጋጠማቹ ችግር አለ ወይ በማለት አዲስ ዘይቤ ለአቶ አለባቸው ላቀረበችው ጥያቄ አቶ አለባቸው ሲመልሱ “በተገቢው የህግ ስርዓት በመሄድ ከብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እውቅናን ካገኘን በኋላ አንዳንድ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት እኔ ነኝ መምራት ያለብኝ የሚል ጥያቄ አቅርበው ነበር። ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ ይህንን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።” ያሉ ሲሆን ከላይ የተጠቀሱት አካላት በህጋዊ አግባብ የተመሰረተው ማህበር ውስጥ በአባልነት መቀጠል እንደሚችሉ ኮርፖሬቱ እንደወሰነ ተናግረዋል።በተጨማሪም የአገሪቱን ባህልና እሴት ያላማከሉ ማስታወቂያዎችን መቆጣጠር ሌላኛው የማህበሩ ተቀዳሚ ስራ እንደሚሆን የተናገረው አለባቸው የቢራ ፋብሪካዎች የሚሰሯቸውን ማስታወቂያዎች እንደማሳያነት ያነሳል። “በግልፅ የተቀመጠ ህግና ደንብ በሌለበት ሁኔታ እነዚህ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው ፋብሪካዎች እንዴት ምርቶቻቸውን ማስተዋወቅ እንዳለባቸው የተጠና አቅጣጫ ከፋብሪካዎቹ ጋር በመወያየትና ከመንግስት ጋር በመተባበር ለመስራት እቅድ አለን” ያለው አለባቸው አያይዞ ማስታወቅያዎች የአገሪቱን ባህል፣ ቋንቋ፣ ጭፈራና የተለያዩ እሴቶች የሚያሳዩና ለተቀረው አለም የሚያስተዋውቁ እንዲሆኑ ማድረግ ማህበሩ በተጓዳኝ እንደሚሰራ ለአዲስ ዘይቤ ተናግርዋል። ከዚህ ባሻገር አለባቸው የአዲስ አበባ ከተማን ውበት ከሚያደበዝዙ የኤሌትሪክና ስልክ እንጨቶችና ግድግዳዎች ላይ ከተለጠፉ ማስታወቅያዎች አንፃር ምን ለመስራት እንደታሰበ ለተጠየቀው ጥያቄ “በቀጣይ ከበጎ ፍቃደኛ የከተማዋ ወጣቶች ጋር በመተባበር የተጠቀሱትን በኤሌክትሪክና ስልክ እንጨቶችና በግድግዳዎች ላይ ተለጥፈው የሚታዩትን ማስታወቂያዎች ለማንሳት በዝግጅት ላይ እንገኛለን።” ያለው አለባቸው አክሎም ማህበራቸው ገና ከመመስረቱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የ250,000 ብርና የአምሳ በግ ስጦታ ያበረከተበትን አጋጣሚ በማስታወስ ማህበራቸውማስታወቂያዎች ያልተጋነኑና የመንግስትና የጥቂት ግለሰቦችን ፍላጎት ከሟሟላት ይልቅ ብዙሀኑን ህብረተሰብ ያማከለ መረጃ እንዲሰጡ ማድረግ ሌላኛው የማህበሩ አላማ እንደሆነ ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል። በመጨረሻም ማህበሩ ለተለያዩ መፅሀፍታቸውን ለማሳተም ተገቢው የገንዘብ አቅም ላጠራቸው ደራስያን መፅሀፋቸውን አሳትመው ለአንባቢ የሚያደርሱበትን አጋጣሚ ለማመቻቸት በስራ ላይ እንገኛለን በማለት አለባቸው ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።ማህበሩ በካሳንቺዝ አካባቢ ቢሮ ከፍቶ ስራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ለአዲስ ዘይቤ የተናገረው አቶ አለባቸው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመዘጋጀት ላይ የሚገኘውና በቅርቡ ይፋ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውን የማህበሩን የአባልነት መስፈርት እስካሟላ ድረስ ማህበሩን መቀላቀል እንደሚችል አክሎ ተናግሯል። በመጨረሻም በእነዚህና በተለያዩ ጉዳዩች ላይ በቅርቡ መግለጫ ይሰጣል ተብሏል። 

አስተያየት