መስከረም 25 ፣ 2013

“የምትጭነው ሰው ቫይረሱን ለመከላከል ትክክለኛውን ጥንቃቄ እንደሚያደርግና እንደማያደርግ የምታረጋግጥበት መንገድ የለም።” መሳይ ሸምሱ - ትራንስፖርት መሐንዲስ

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

የአዲስ አበባ ከተማን የትራፊክ ፍሰት ችግር ለመቅረፍ ኮድ ሁለትና ሶስት መኪናዎች በስራ መውጫና መግቢያ ሰዓታት ለከተማይቱ ነዋሪዎች የትራንፖርት አገልግሎት…

“የምትጭነው ሰው ቫይረሱን ለመከላከል ትክክለኛውን ጥንቃቄ እንደሚያደርግና እንደማያደርግ የምታረጋግጥበት መንገድ የለም።” መሳይ ሸምሱ - ትራንስፖርት መሐንዲስ
የአዲስ አበባ ከተማን የትራፊክ ፍሰት ችግር ለመቅረፍ ኮድ ሁለትና ሶስት መኪናዎች በስራ መውጫና መግቢያ ሰዓታት ለከተማይቱ ነዋሪዎች የትራንፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የምክረ ሀሳብ መቅረቡን ፋና ብሮካስቲንግ ኮርፖሬት የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ጅሬኛ ሄርጳን አጣቅሶ መዘገቡ የሚታወስ ነው። ታድያ አዲስ ዘይቤ ይህ በአይነቱ ለየት ያለ የመፍትሄ ሀሳብ ከወቅታዊ የከተማዋ ገፅታዎች አንፃር እንዴት እንደሚታይ ከትራንስፖርት መሐንዲሱ መሳይ ሸምሱ ጋር ባደረገችው ቆይታ የተለያዩ ነጥቦችን አንስታለች።የመጀመርያው የመነሻ ሀሳብ የሚሆነው የመፍትሄ ሀሳቡ አስፈላጊነት ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ የከተማዋን የትራፖርት ችግር ማጤን ይጠይቃል። በአዲስ አበባ ከተማ በተለይም በስራ መግቢያ (ማለትም ከ1ሰዓት እስከ 3 ሰዓት) እና በስራ መውጫ (ማለትም ከ11 ሰዓት እስከ 1 ሰዓት) ሰዓታት ረዘም ያሉ ሰልፎችን መመልከት የተለመደ ነው። የትራንስፖርት መሀንዲሱ መሳይ ሸምሱ የትራንስፖርት ችግር እንደከተማዋ ዋነኛ ችግሮች ያነሳዋል። “የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ችግር ግልፅ ነው። ጥናት ሳታደርግ ፊት ለፊት የምታየው ነገር ነው።” የሚለው መሳይ እንደሀሳብ እየተጤነ በሚገኘው የኤጀንሲው ሀሳብ ይስማማል። “ዋነኛ የመኪናዎች ችግር የሚወስዱት የመንገድ መጠንና የሚያገለግሉት ሰው ብዛት አለመጣጣም ወይም Per Capita Occupancy ነው። ይህም አንድ አምስት ሰው መያዝ የሚችል መኪና አንድ ወይም ሁለት ሰዎችን ሲይዝ የሚመጣ ችግር ነው።” በማለት ሀሳቡን ለአዲስ ዘይቤ ያካፈለው የትራንስፖርት መሀንዲሱ በአንፃሩ ግን የመፍትሄ ሀሳቡ ተግባራዊነት ላይ ግን ጥያቄ ያነሳል። “ይህ የመፍትሄ ሀሳብ በተለያዩ አገራት ተተግብሮ ውጤት ቢያመጣም በአገራችን ስኬትን ያገኛል ብዬ አላምንም።” በማለት ለኢትዮጵያውያን መኪና ምን ማለት እንደሆነ ማሰብ ያሻል የሚለው መሳይ የመፍትሄ ሀሳቡን በተግባር ለማዋል እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ ያምናል። ለመሳይ መኪና መንዳት በተለይም በአገራችን ሁኔታ አስፈላጊ ከሆነባቸው ምክንያቶች አንደኛው ግላዊነት (privacy) ነው። “ሰዎች በህዝብ ትራንስፖርት ከመጠቀም ይልቅ የግል መኪናዎችን የሚነዱበት ምክንያት የራሳቸውን የግል ቦታ ከመፈለግ የተነሳ ነው። ይህ ደግሞ አመክኖአዊ አስተሳሰብ ነው።” የሚለው መሳይ በኤጀንሲው የቀረበው የምፍትሄ ሀሳብ በመጀመርያ የሚጋረጥበት ችግር ይህ እንደሆነ ይገምታል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ሌላኛው መሳይ የሚያነሳው ጥያቄ ነው። ከወራት በፊት ወረርሺኙ በተከሰተበት ወቅት ሁሉም መኪናዎች ከመጫን አቅማቸው በግማሽ እንዲጭኑ የተሰጠውን ውሳኔ የሚያስታውሰው መሳይ ቫይረሱ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ ባለበት ወቅት ይህን ውሳኔ መወሰን የተለያዩ ችግሮችን ሊፈጥር ይችላል ይላል። “የምትጭነው ሰው ቫይረሱን ለመከላከል ትክክለኛውን ጥንቃቄ እንደሚያደርግና እንደማያደርግ የምታረጋግጥበት መንገድ የለም።” ያለው መሳይ ከቫይረሱ ህቡዕ ባህርይ የተነሳ አሽከርካሪዎች ለቫይረሱ ያላቸውን ተጋላጭነት ሊጨምር እንደሚችል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል። አክሎም የቫይረሱ መሰራጨት በመፍትሄ ሀሳቡ ተግባራዊነት ላይ ከፍተኛ ችግር ሊፈጥር ይችላል ያለው መሳይ በከተማዋ የሚታየውን የፀጥታ ችግር እንደሌላ ችግር ያነሳል። “በከተማችን ከተሰራጨው የመኪና ዘረፋ አኳያ አንድ አሽከርካሪ የማያውቃቸውን ግለሰቦች በሚጭንበት ወቅት የግለሰቦቹን ሰለማዊነት ማረጋገጥ የሚችልበት መንገድ የለም” ያለው መሳይ በተጨማሪም በከተማይቱ እየጨመረ ከመጣው የስርቆትና ፖለቲካ ነክ ወንጀሎች አንፃር የሚወጣውን ህግ ማስፈፀም ሊከብድ ይቻል ሲል ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል። በተጨማሪም የትራንስፖርት ኢንጅነር መሳይ እንዳለው ከሆነ “ከአፈፃፀም ችግሮች በተጨማሪም አሽከርካሪዎች ተገቢው የህግ ማዕቀፍ በሌለበት ሁኔታ ይህንን እንዲያደርጉ ማስገደድ ተገቢ አይደለም።”እንደዘገባዎቹ ከሆነ በሀሳብ ደረጃ ብቻ እንደቀረበ የተነገረለት የመፍትሄ ሀሳብ በቀጣይ በተገቢዎቹ የመንግስት አካላት ውይይት ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተሩ ጅሬኛ ሄርጳ እንደገለፁት ከሆነ የመፍትሄ ሀሳቡ በተለይም ከስምንት ወራት በኋላ ወደትምህርት ገበታቸው በሚመለሱበት ወቅት ለሚጠበቀው ከፍተኛ የመንገድ መጨናነቅና የትራንስፖርት እጥረት አንፃር ትልቅ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

አስተያየት