You can paste your entire post in here, and yes it can get really really long.
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከ1974 ዓ.ም ጀምሮ የሚከበረው የአለም የሰላም ቀን በዛሬው እለት “ሰላምን በጋራ መገንባት” በሚል መሪ ቃል በመከበር ላይ ይገኛል። የሰላም ቀን ዛሬ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ታስቦ የሚውል ሲሆን ከመርሀ ግብሮቹ መካከል ከ700 በላይ የሚሆኑ የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች ከተለያዩ በሰላም ላይ ከሚሰሩ የድርጅቱ ሰራተኞች ጋር የሚያደርጉት ውይይት አንዱ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶንዮ ጉቲሬዝ የአለም የሰላም ቀንን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ሰላም ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አትኩሮ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ያስታወሱ ሲሆን ሰላምን ማስፈን ጦርነትን ከማጥፋት በተጨማሪ ሁሉም ዜጎች መብታቸው ተከብሮ የሚኖሩበትን አለም መፍጠር እንደሆነ ተናግረዋል። በተጨማሪም አለማችን ከተጋረጡባት ተግዳሮቶች መካከል አንዱ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ በጋራ መጋፈጥ የዘንድሮ የሰላም ቀን ዋነኛ አትኩሮት እንደሆነ ዋና ፀሐፊው ገልፀው የተጋረጠውን ችግር ለመፍታት ከግለሰብ ጀምሮ እስከ መንግስታት ድረስ በጋራ መስራትን እንደሚጠይቅ በመልዕክታቸው አስታውሰዋል። የአለም የሰላም ቀን ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ በየአመቱ በመስከረም 11 ቀን እንዲውል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመራሂ መንግስታት ጉባኤ እንደተወሰነ የተለያዩ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን የአለም የሰላም ቀን በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የሚገኙ ግለሰቦች እንዲሁም በተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና በመከበር ላይ ይገኛል።